‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› ንቅናቄ የአገር ውስጥ ችግሮችና ዓለም አቀፍ ጫናዎች የሚቋቋም ኢንዱስትሪ እስከ መፍጠር እንደሚዘልቅ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር መግለጹ ይታወቃል። ንቅናቄው የአንድ ወቅት የዘመቻ ሥራ ሆኖ እንዳይቀር ሊሠራባቸው የሚገቡ ነጥቦች መኖራቸውን ደግሞ በዘርፉ ያሉ ባለሙያ ይናገራሉ።
በኢትዮጵያ ታምርት መርህ ላይ አዲስ ዘመን ያነጋገራቸው፤ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በዲቨሎፕመንት ኢኮኖሚክስ ሶስተኛ ዲግሪያችውን በማጠናቀቅ ላይ የሚገኙና በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የልማት ምጣኔ ትምህርት ክፍል መምህር፣ ተመራማሪና እድገት በልማት ኢኮኖሚ ዙሪያ አማካሪ እጩ ዶክተር ዘካሪያስ ሚኖታ እንደሚናገሩት፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ ማምረት በዋናነት ሶስት ዘርፎች አሉት። እነዚህም ማምረት፣ መሸመትና ማሰራጭት ናቸው።
ምርት ለሁሉም ነገር መነሻ ነው። ምርት ሳይኖር ስለፍጆታ ማውራት አይቻልም። እንዲሁም ማምረትና መሸመት ሳይኖር ስለስርጭት ማውራት አይቻልም። እነዚህ ሶስቱ ነገሮች በውስጣቸው በዋናነት አራት ነገሮችን ይይዛሉ። እነዚህም ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ ተቋማዊና አካባቢያዊ ነገሮች ናቸው። በመሆኑም ኢትዮጵያ ታምርት የሚለው መርህ በአሉታም ሆነ በአዎንታ ጎኑ ሁሉንም ነገር በዚህ መልኩ የሚነካ ነው፡፡
ወደ ማምረት ሲመጣ መሰረት የሚያደርገው አራት ነገርን ነው። ይኸውም የሰው ኃይል፣ መሬት፣ ካፒታልና ቴከኖሎጂ እንዲሁም እውቀት የሚባሉት ናቸው። በእነዚህ አራቱ ነገሮች የተሻለ ምርት ማግኘት እንደሚቻል የሚናገሩት እጩ ዶክተሩ፣ በተቃራኒው ሊሆን የሚችልበትም አጋጣሚ ይኖራል ይላሉ። ጥሩውንም መጥፎውንም ማድረግ የሚችለው ግን ራሱ የሰው ልጅ እንደሆነ ይገልጻሉ።
ለምሳሌ የሰው ሀብት የሚባለው ምርታማነት እንዲኖር ትልቁን ድርሻ የሚወጣ ነው። ይህ ለሁሉም ማለትም ለቴክኖሎጂው፣ ለካፒታሉም ሆነ ለመሬቱም መነሻ ነው። ስለዚህም የሰው ዝግጁነት የአንበሳውን ድርሻ የሚይዝ ነው። ምክንያቱ ደግሞ የሰው ልጅ ሁሉንም የሚያቀናጅ በመሆኑ ነው። ካፒታሉም መሬቱም ሆነ ቴክኖሎጂውን የሚያቀናጀው ራሱ የሰው ሀብት የሚባለው ነው፡፡
እርሳቸው በተጨማሪነት ሌላ አንድ ጽንሰ ሐሳብ ሲጠቅሱ እንዳሉት፤ ምርት ሲኖር በአካባቢው የራሱ የሆነ ጫና ይፈጥራል። የኢኮኖሚ እንቅስቃሴና አካባቢ አንዱ ሌላውን ይቃረናል። ለምሳሌ ተፈጥሮ በሆኑ ነገሮች ላይ መሰረት ያደረጉ አገሮች ከአካባቢያቸው ጋር እየተጣሉ ነው ማለት ነው። በአካባቢው ላይ የሚያመጣው ተጽዕኖ በጣም ከባድ ነው። ይህም ተጽዕኖ የአየር ጸባይ መዛባት፣ ዝናብ በወቅቱ አለመዝነብ፣ ሙቀትና መሰል ነገር ሲሆን፣ ይህ ነገር ከሰው ልጅ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ጋር ተያይዞ የሚመጣ ነው፡፡
በዓለም ላይ የሚስተዋለው 99 በመቶ የአየር ቀውስ እየተፈጠረ ያለው በሰው ልጆች እንቅስቃሴ ነው። ይህም የማምረት፣ የመሸመትና የማሰራጨት እንቅስቃሴ የሚባለው ነው። በተፈጥሮ በኩል የሚመጣው ተጽዕኖ ግን አንድ በመቶ ብቻ ነው። ለምሳሌ የእሳተ ጎመራ ሂደት ለውጡን ማየት የሚቻለው በሺዎች በሚቆጠሩ ዓመታት ውስጥ ነው። ይህም በጣም ዘገምተኛ የሆነና ብዙ ጊዜ የሚቆይ ሲሆን፣ በተፈጥሮ በኩል ይመጣሉ የሚባሉት ነገሮች የሚያመጡት ተጽዕኖ አንድ በመቶ ብቻ ነው ማለት ነው። ስለዚህም በዓለም ላይ የሚፈጠረው የአየር ቀውስ ምክንያት የሰው ልጅ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ነው ማለት ነው።
ስለዚህ ምርት ስናመርት እነዚህን ነገሮች ታሳቢ ማድረግ የግድ የሚል እንደሆነ ነው እጩ ዶክተር ዘካሪያስ የጠቀሱት። ከዚህ ቀደም ብዙ ትኩረት ባንሰጥም እንኳ የተፈጥሮ ሀብቱ፣ ደኑ፣ ውሃው በጣም ብዙ ስለሆነ ከስርጭት አኳያ ስላልተጎዳ የመቋቋም ጉልበት ነበረው። አሁን የሰው ልጅ ቁጥር እየጨመረና መሬቱም ከህዝብ ቁጥር አንጻር እየቀነሰ ስለመጣ ለአየር ቀውስ የመጋለጥ እድሉ እየሰፋ መጥቷል። በአብዛኛው ታዳጊ አገሮች ላይ ለአገልግሎት የሚውለው ከተፈጥሮ የሚገኘው ሀብት ነው። ለምሳሌ ልብስ፣ እቃም ሆነ ሌሎችም ግብዓቶች የሚገኙት ከአካባቢያችን ካሉ ተፈጥሮዎች እንደሆነ ይገልጻሉ።
ስለዚህ ኢትዮጵያ ታምርት ሲባል በአካባቢው ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ተገቢ ጥንቃቄ የታከለበት ሊሆን ይገባል። እንዲሁም የተቋማት ዝግጁነትን ታሳቢ ያደረገ ብሎም የአካባቢዎችን አግሮኢኮሎጂ መሰረት ያደረገ መሆንም ይጠበቅበታል። ለምሳሌ አንድ ቦታ ላይ ስንዴ የሚመረት ከሆነ ሁሉም ቦታ ላይ ስንዴ ይመረታል ማለት አይደለም። ሌላ ቦታ የሚመረተው ሩዝ ወይም በቆሎ ወይም ደግሞ አትክልትና ፍራፍሬ ሊሆን ይችላል። መቃኘት ያለበት እንደየአግሮኢኮሎጂው ነው።
ወደ ኢንዱስትሪውም ሲኬድ ደግሞ ለምሳሌ አንድ ቦታ ላይ ለሲሚንቶ ምርት የሚሆን ግብዓት በብዛት ያለበት አካባቢ ከሆነ ማምረት የሚገባው ራሱ ሲሚንቶን ነው። ሌሎች ፋብሪካዎችን ከመገንባት ይልቅ የሲሚንቶ ፋብሪካዎችን ማስፋፋቱ ተመራጭ ይሆናል።
በዋናነት የምርት ዋጋም ሆነ ስርጭት የሚወሰነው ያንን በማምረት የሚወጣ ወጪ ከግምት ውስጥ ሲገባ ነው። የሚወጣው ወጪ ከፍተኛ ከሆነ የምርት አቅርቦትም ሆነ ስርጭት ሊሳለጥ አይችልም። አሊያም ውድ ይሆናል። የቱንም ያህል የመግዛት አቅም ቢኖር እንኳ ትክክለኛ ዋጋ ካልሆነ በስተቀር ውድ ከሆነ ሰው አይፈልገውም። ስለሆነም ምርት ሲመረት በዋናነት ግብዓትንም ቴክኖሎጂንም መሰረት ያደረገና በተመጣጣኝ ዋጋ መሆን አለበት። በዝቅተኛ ዋጋ ማምረትና አገልግሎት መስጠት የሚቻልበት ሁኔታ መፈጠር አለበት። ስለሆነም ኢትዮጵያ ታምርት ሲባል አንደኛ በዝቅተኛ ወጪ መሆን አለበት ይላሉ ቴክኖሎጂው በሁሉም ቦታ መድረስ ያለበት ዝቅተኛ በሆነ ዋጋ ነውና እዚህ ላይ በአግባቡ ማሰብ ይጠይቃል፡፡
ሌላው እነዚህን ሁሉ ሊያስተባብር የሚችል ተቋማዊ አደረጃጀትና ተቋማዊ ስርዓት ሊኖር ይገባል። እንዲህም ሲባል ልማቱን ለማሳለጥ የሚወጡ ፖሊሲዎች፣ ስትራቴጂዎች፣ መመሪያዎች፣ ደንቦች፣ አሰራሮችና ፕሮጀክቶች ሲሆኑ፣ እነዚህ ሁሉ ምርትን ለማሳደግም ሆነ ምርትን ለማቀጨጭ ምክንያት ሊሆኑ የሚችሉ ናቸው። ስለሆነም የሚወጡ አሰራሮች ምን ያህል ሊያሰሩ እንደሚችሉ መታወቅ አለበት። ለምሳሌ ኢትዮጵያ ታምርት ሲባል አካባቢውን ታሳቢ ያደረገ መሆን አለበት።
ከኢትዮጵያ የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ጋር ቅንጅት በመፍጠር ሊሰራ ይገባል። ይህ ደግሞ በአንድ ሰሞን ዘመቻ ሳይሆን መደበኛ በሆነ መልኩ ታሳቢ ተደርጎ በእቅድ መሰራት አለበት። አካባቢ ሳይበከል ምርት ማምረት የሚያስችልን መንገድ መጠቀም ተገቢ ነውና ተቋማዊ አደረጃጀት ወሳኝ ነው።
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱት ጥያቄዎች ማብራሪያና ምላሽ በሰጡበት ወቅት ኢንዱስትሪን አስመልክተው እንደተናገሩት፤ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› የሚባል በጣም ጥሩ ጅማሮ ጀምሯል። ዋና አላማው አጠቃላይ ያሉ ኢንዱስትሪዎች ቢያንስ 50 ከመቶ ማምረት እንዲችሉ ነው። ይህ ጅማሮ ጥሩ ውጤትም እያመጣ ነውና፤ ተጠናክሮ ይቀጥላል።
ይህ ብቻ ሳይሆን ከለውጥ በፊት ኢትዮጵያ ሶስት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ነበሯት ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ እነሱም ሃዋሳ፣ ኮምቦልቻና መቀሌ መሆናቸውን አስታውሰዋል። ኢትዮጵያ ከለውጡ በኋላ አስራ ሁለት የገነባች ሲሆን፣ ሶስት የአግሮ እና ዘጠኝ የኢንዱስትሪ ፓርኮች እንደሆኑም ተናግረዋል፡፡
እንደ እርሳቸው ገለጻ፤ በየትኛውም መመዘኛና በየትኛውም ቁጥር በኢንዱስትሪ፣ በትምህርትም፣ በስኳርም፣ በቴሌም፣ በአየር መንገድም፣ እንዲሁም በመብራትና በውሃም ሊወዳደር አይችልም። አስደማሚ እምርታዎች አሉ። የሚለፉና የሚተጉ ኢትዮጵያውያን በየቦታው አሉ። ነገር ግን በዛው ልክ የሚሰርቅ፣ የሚያላግጥ ወሬ የሚተነትንና መፍትሄ የማያመጣ ስላለ ከዚያ በላይ መሄድ ሲገባ የቀነሰ ነገር ይኖራል።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጋር በነበራቸው ቆይታ በአገር ውስጥና በውጭ ጫናዎች እየተፈተነ ያለውን ኢንዱስትሪ መታደግ የሚያስፈልግበት ነባራዊ ሁኔታ መምጣቱ ተናግረዋል። በጦርነትና በተከሰተው በኮቪድ 19 ወረርሺኝ ሳቢያ በርካታ ኢንዱስትሪዎች ስራቸውን አቁመዋል፤ ቀሪዎቹም ማምረት ከሚገባቸው ከ50 በመቶ በታች እያመረቱ እንደሆነም አስረድተዋል፡፡
በተለያዩ የአለም አገራት የሚደረጉ ግጭቶች ወደ ውጭ በሚላኩና ከውጭ በሚገቡ ምርቶች ላይ ጫና በማሳደሩ ኢትዮጵያንና መሰል በማደግ ላይ ያሉ አገራት ኢኮኖሚ በከፍተኛ ሁኔታ እየጎዳው እንደሆነ እንደ ማሳያ ሊወሰድ ይችላል ብለዋል። ኢትዮጵያ በእነዚህና በሌሎች የተለያዩ ችግሮች ሳቢያ የተጎዳውን ኢንዱስትሪ በዘላቂነት ለማቋቋም ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› የሚል ንቅናቄ መጀመሯን አስታውሰዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ኢንዱስትሪ ላይ የሃይል፣ የፋይናንስ፣ ሎጀስቲክስና ቢሮክራሲ ችግር ቢፈታ እና ከ50 በመቶ በላይ ቢያድግ ምርታችን በርግጠኝነት በከፍተኛ ደረጃ ለውጥ ያመጣል ይላሉ። ኢንዱስትሪ ውስጥ ሁለት ነገር ማየት ይገባል። አንደኛ አግዋ ቀርቶ እንኳ እያለ ዘንድሮ የኤክስፖርት ንግድ አድጓል። አጎዋም ተዘግቶ ጫናም እያለ የኤክስፖርት ምርት አድጓል እንጂ አልቀነሰም ሲሉም ያክላሉ።
ይህ ብቻ ሳይሆን የገቢ ምርት መተካት ላይም ከፍተኛ ስራ መሰራቱን ተናግረዋል። ቀደም ሲል በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ የሚወጣባቸው የከሰል ድንጋይ፣ ገብስ፣ ልብስ፣ ጫማ፣ የደምብ ልብስና ሌሎችም በሀገር ውስጥ እየተመረቱ መሆኑን ነው ያመለከቱት። እጩ ዶክተር ዘካሪያ በበኩላቸው፤ እነዚህን ጉዳዮች ታሳቢ ያደረገ ስራ መስራት ተገቢነቱ እንደተጠበቀ ሆኖ ፡፡
እርሳቸው እንደሚናገሩት፤ ኢትዮጵያ ታምርት ሲባል ሌላው ነገር አግሮኢኮሎጂውን፣ ተደራሽነትንና ዝቅተኛ ዋጋን ታሳቢ ማድረግም ያስፈልጋል። በአንድ ቦታ ያለ ኢንዱስትሪ የሚያመርተውን ምርት ለሌሎች አካባቢዎች ማድረስ ካልተቻለ አቅርቦት ላይ ችግር ሊፈጠር ይችላል። ስለዚህ ትርፍ እንዲኖር አድርጎ ማምረት ደግሞ ይጠበቃል። ትርፍ ማምረት ካልተቻለ ውጤታማ ወይም ቀጣይነት ያለው እንቅስቃሴ ሊኖር አይችልም። ትርፍ ሲኖር ለነገ የሚሆን ግብዓት ማዘጋጀት ይቻላል።
ለትርፋማነት ግብዓት የሚሆኑ ተቋማትን መገንባት ደግሞ ያስችላል። በተለይም በእውቀት፣ በልምድ፣ በቴክኖሎጂ ከአገር ውስጥ ገበያ ተነስቶ እስከ ዓለም አቀፍ ገበያ ድረስ ትስስሩን ማጠናከር የሚቻለው ትርፍ ማምረት ሲቻል ነው። ትርፍ ካልተመረተ ከእጅ ወደአፍ ይሆናል ይላሉ፡፡
ኢትዮጵያ ታምርት ሲባል በተመሳሳይ ቴክኖሎጂም መታሰብ አለበት። ይህ ደግሞ ለምሳሌ በግብርናው ዘርፍም ሆነ በሌላው አገር በቀል ቴክኖሎጂን በመጠቀም ሊሆን ይችላል። ቴክኖሎጂ ሲባል ማንኛውኛም ምርትን ሊያሳድግ የሚችል ከሐሳብ ጀምሮ ያለ ዘዴ ሊሆን ይችላል። ቴክኖሎጂው ምርት መሰብሰብ ላይም ሆነ ስርጭት ላይም ሊሆን ይችላል። ምክንያቱም በአሁኑ ጊዜ ከቴክኖሎጂ ተላቅቆ ምርት ማምረት አይቻልም። ይሁንና
መርሁ ግን የአንድ ወቅት የዘመቻ ስራ ሆኖ እንዳይቀር ሊሰራበት ያስፈልጋል ሲሉ ጠቅሰዋል። የአንድ ሰሞን ዘመቻ ከሆነ ግን የሚፈጠረው ብክነት ነው። ሰዎች ከዚህ በኋላ የሚመጡ መርሃ ግብሮችን አዎንታዊ በሆነ መልኩ እንዳይቀበሉ ሊያደርግ እንደሚችል ስጋታቸውን ተናግረዋል፡፡
ስለዚህ በመጀመሪያውኑ በአግባቡ ተጠንቶ እንዲሁም አደረጃጀት ተፈጥሮለት በተጨማሪም ተጠያቂነት ተፈጥሮለት ብሎም በተዋረድ ግንዛቤው እንዲፈጠር ተደርጎለት መሰራት አለበት። ሌላው ቀርቶ ኢንዱስትሪው ያለበት አካባቢ ያለ ማህበረሰብ ኢንዱስትሪው ስለሚያመርተው ምርትና ስለሁኔታው ተገቢው እውቀት ሊኖረው እንዲገባ ማድረግም የግድ ነው። ዝም ተብሎ ሄዶ የአንዱን አካባቢ መቆፈር ተገቢ ካለመሆኑም በተጨማሪ አካሄዱም አደገኛ ነው።
ህዝቡ በአካባቢው ስለሚሰራው ስራ ማወቅና ሊጠብቀው የሚችልም መሆን ይኖርበታል። ህዝብ ያላወቀው ነገር ጥፋቱ የከፋ ነው። ምክንያቱም ቀጣይነቱ ላይ ኢንዱስትሪው ፈተና ሊጋረጥበት ይችላልና ህዝቡን ማሳተፍ መልካም ነው። ያ ሲሆን፣ ህዝቡ የባለቤትነት ስሜት እንዲኖረው ያደርገዋል፤ ንብረቱንም እንደራሱ ንብረት መጠበቅ ይጀምራል። ከዚህም ባሻገር ኢንዱስትሪው ያለበት አካባቢ ያለ የህብረተሰብ ክፍል ከኢንዱስትሪው ተጠቃሚ ሊሆንም ይገባል ብለዋል፡፡
ሌላው ይላሉ እጩ ዶክተሩ፣ በኢትዮጵያ በየጊዜው የሚታየው የተቋማት መለዋወጥ በዚህ መርህ ላይ ጫና የሚያሳድር ነውና እዚህ ላይ ጥንቃቄ ማድረጉ ተገቢ ነው። ተቋማትን ማዋሃድና ማፍረስ መረጃም እንዲጠፋ ከሚያደርገው ነገር አንዱ ሲሆን፣ ሰራተኛውም ጥርጣሬ ውስጥ ይገባል፤ የተቋማት መቀያየር በኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ላይ የሚያሳድረው ጫና በቀላሉ መታየት የለበትም። ስትራቴጂ ሲቀየር ከጊዜ፣ ከገንዘብና ከጉልበት አኳያ ያለው ተጽዕኖ በጣም ከባድ ነው።
እነዚህ የተጠቀሱት ዋና ዋና ጉዳዮች ተሟልተው የሚተገበሩ ከሆነ ኢትዮጵያ ታምርት የሚለው መርህ በአግባቡ ተግባራዊ ሊደረግ ይችላልና በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ የበኩሉን አዎንታዊ ሚና ይጫወታል። አንዱ የስራ እድል መፍጠሩ ነው። የስራ እድል ተገኘ ማለት ሰው ገቢ አገኘ ማለት ነው፤ ገቢ ሲያገኝ የመግዛት ፍላጎት ይፈጠራል። እግረ መንገዱን ይቆጥባል፤ መቆጠብ ማለት ደግሞ ሌላው ኢንቨስትመንት እንደማለት ነው። ከዚህ ጎን ለጎን አምራቹ በመሸጥ የሚያገኘው ገቢ ይኖረዋል። ለመንግስት ደግሞ ከምርት የሚገኝ ግብር ይኖራል።
የምጣኔ ሀብት ባለሙያው እንደሚናገሩት፤ ከኢኮኖሚ ጠቀሜታው በተጨማሪ ሌላ ጥቅም አለው። ከፖለቲካው በኩልም ሲታይ እንዲሁም የማህበራዊ ሁኔታው ተረጋግቶ እንዲሄድ ከማድረግ አኳያም የራሱ የሆነ በጎ ተጽዕኖ አለው ብለዋል። ከዚህ በተጨማሪ ስልጡን ህዝብ እንዲኖር ያደርጋል። ልምድና እውቀት በቀላሉ ያለምንም ወጪ ማግኘት ያስችላል። በጥቅሉ የቴክኖሎጂ ሽግግርን በቀላሉ ያስገኛልና ፋይዳው ብዙ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ንቅናቄው በ2022 ዓ.ም እንደ አገር የበለጸገች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የተያዘውን ዕቅድ ለመተግበር ሰፊ እድል እንደሚኖረው ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል። አገሪቱ ያላትን የተፈጥሮ ሀብት በመጠቀም በቀጣዮቹ አስር ዓመታት ኢንዱስትሪው አገራዊ የምርት ድርሻው ከ6 ነጥብ 9 በመቶ ወደ 17 ነጥብ 2 በመቶ ለማሳደግ ግብ መጣሉም ታውቋል።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ እንደተናገሩት፤ አገሪቱ በ2022 ዓ.ም ከአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ በዓመት ወደ ውጪ ከሚላክ ምርት አሁን ከሚገኘው 4 መቶ ሚሊዮን ዶላር ወደ 9 ቢሊዮን ዶላር ማሳደግ ዋነኛ ዓላማውም ነው። የአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ የማምረት አቅም ወደ 85 በመቶ ማሳደግ እንዲሁም ከ5 ሚሊዮን ለሚልቁ ዜጎች የስራ እድል ለመፍጠር ተወጥኗል፡፡
የኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም ለመጨመር የሀይል አቅርቦት፣ የመሬት፣ የሥልጠና፣ የብድር አቅርቦትና ተያያዥ ችግሮችን ለመፍታት ከባለድርሻ አካላት ጋር ከመቼውም ጊዜ በላይ እየተሰራ መሆኑንም ሚኒስትሩ አስረድተዋል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 14/2014