
አዲስ አበባ፡- ጥቃት በደረሰባቸው አካባቢዎች ሰላም እና ደህንነትን መመለስ አሁንም ቅድሚያ የምንሰጠው ተግባራችን ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አስታወቁ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት “በንጹሓን ዜጎች ላይ በሕገወጥ እና በኢ-መደበኛ ኃይሎች የሚደርስ ጥቃት እና መተዳደሪያን ማውደም ተቀባይነት የለውም” ብለዋል።
“ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በቤኒንሻንጉል እና ኦሮሚያ ክልሎች፣ ዋና ዓላማቸው ኅብረተሰቡን ማሸበር ከሆነ አካላት የተፈጸመው የሰው ልጆችን ሕይወት የሚቀጥፍ ዘግናኝ ድርጊት የምንታገሰው አይደለም” ብለዋል።
በተያያዘ ዜና የኢፌዲሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት እንደገለጹት፤ በፀጥታ አስከባሪ አካላትና በሕዝቡ የተባበረ እርምጃ በደረሰበት ሽንፈትና ኪሳራ አሸባሪውና ፅንፈኛው ቡድን የቀቢፀ ተስፋ እርምጃዎችን እየወሰደ ይገኛል፡፡
በቅርብ ጊዜ በጋምቤላ አካባቢ ያደረገው ሙከራ ሲከሽፍበት በምዕራብ ወለጋ በጊምቢ አካባቢ ደግሞ በንፁሓን ዜጎች ላይ በተለይም በሕጻናትና በሴቶች ላይ ያካሄደው ጭፍጨፋ እጅግ አሳዛኝ እና ኢ-ሰብዓዊ ነው ብለዋል፡፡
አቶ ደመቀ በተለያዩ አካባቢዎች ቡድኑ በወሰደው እኩይ የጥፋት እርምጃ ምክንያት በንፁሓን ወገኖቻችን ላይ ለደረሰው ጉዳት የተሰማኝን ጥልቅ ኀዘን እየገለጽኩ፤ በመንግሥት በኩል ሕግ የማስከበር እርምጃው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ላረጋግጥ እወዳለሁ ብለዋል።
በቀጣይ ተጎጂ ቤተሰቦችን የማረጋጋት፣ የመደገፍ እና መልሶ የማቋቋም ሥራ በትኩረት የሚሠራ ሲሆን፤ አሸባሪዎችን እና ጽንፈኞችን ለሕግ የማቅረቡ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል።
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ ወለጋ ዞን ግምቢ ወረዳ ቶሌ ቀበሌ አሸባሪው ሸኔ በንጹሐን ወገኖች ላይ በፈጸመው ግድያ የተሰማቸውን ኀዘን ገልጸው፤የጉዳቱ ሰለባ ለሆኑ ቤተሰቦቻቸውም መጽናናትን እመኛለሁ” ብለዋል።
“ድርጊቱ ሀገራችንን ከአሸባሪዎች ለማጽዳት የጀመርነውን ዘመቻ አጠናክረን ከመቀጠል ውጪ ሌላ አማራጭ እንደሌለን ማሳያ ነው” ሲሉም ርዕሰ መስተዳድሩ አስታውቀዋል።