አብዛኛው ሕዝቧ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ኑሮው በግብርናው ዘርፍ ላይ የተመሰረተባት ኢትዮጵያ ከቀደመው ጊዜ ጀምሮ የግብርናውን ዘርፍ ምርታማነት ለማሳደግ የሚያስችሉ በርካታ ተግባራትን ስታከናውን ቆይታለች። በመንግሥትና በዓለም አቀፍ ድርጅቶች የተደገፉ ተከታታይነት ያላቸው የግብርና ልማት እንቅስቃሴዎች ተግባራዊ ተደርገዋል። ከእነዚህ እንቅስቃሴዎች መካከል በቀደሙት የመንግሥት ስርዓቶች የተተገበሩት የባለ ብዙ ዘርፍ የግብርና ልማት ማዕቀፍ ፕሮግራም (Comprehensive Agricultural Package Program) እና የግብርና ልማት ኤክስቴንሽን ትግበራ (Extension Program Implementation Department (EPID) እንዲሁም የቅርብ ጊዜዎቹ የኢትዮጵያ የልማት ፕላን መመሪያ ማዕቀፍ፣ የግብርና መር ኢንዱስትሪ ፖሊሲ (Agricultural Development Led Industrialization (ADLI)፣ የዘላቂ ልማትና ድህነት ቅነሳ ፕሮግራም፣ የመጀመሪያው እና ሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዶች (GTP I እና GTP 2) ተጠቃሽ ናቸው።
በእነዚህ የግብርና ዘርፍ ማሻሻያ መርሃ ግብሮችም የአገሪቱን ምጣኔ ሀብት ያሳደጉና የሕዝቡን፣ በተለይም የአርሶ አደሩን፣ ሕይወት ያሻሻሉ ውጤቶች ተመዝግበዋል። ከግብርና የሚገኘው ምርት በየዓመቱ ጭማሬ አሳይቷል፤ ቁጥሩ ቀላል የማይባል የህብረተሰብ ክፍልም ከድህነት መላቀቁን መረጃዎች ያመለክታሉ። የግብርናና ገጠር ልማትን ለማሻሻል የተወሰዱ እርምጃዎች ብዙ ባለሀብት አርሶ አደሮችን መፍጠር ችለዋል።
ይሁን እንጂ እነዚህ ተግባራት ኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ ካላት አቅም አንፃር ሲመዘኑ ለአገሪቱ የምግብ ዋስትና፣ የሥራ እድል ፈጠራና የምጣኔ ሀብት እድገትም ሆነ ለዘርፉ ችግሮች አስተማማኝ መፍትሄ የሰጡ አይደሉም። አሁንም ግብርናው በዘላቂነት ከኋላ ቀር አስተራረስና ከዝናብ ጥገኝነት አልተላቀቀም፤ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በብዛት ከመጠቀም የራቀ ሆኖ ይታያል። ሚሊዮኖች ከድህነት ወለል በታች እየኖሩ ነው። በአጠቃላይ የምጣኔ ሀብት መዋቅራዊ ለውጥን እውን ማድረግ አልተቻለም።
የግብርናውን ዘርፍ በማሳደግ አገሪቱ የግብርና አቅሟን በመጠቀም ከድህነት እንድትላቀቅ ለማድረግ ከሚቀርቡ ምክር ሃሳቦች መካከል አንዱ ግብርናውን በቴክኖሎጂ ማዘመን ነው። የግብርናውን ዘርፍ መረጃዎች በዲጂታል አሰራር ማደራጀትና ማሰራጨት ደግሞ ግብርናውን በቴክኖሎጂ ለማዘመን የሚደረግ እንቅስቃሴ አካል ነው።
በአሁኑ ወቅት በርካታ የዓለም አገራት የግብርና ዘርፋቸውን በዲጂታል አሰራር እንዲታገዝ በማድረግ የዘርፉ ምርታማነት እንዲጨምርና ዘርፉ በአገራዊ ምጣኔ ሀብታቸው ላይ የተሻለ አስተዋፅኦ እንዲኖረው እያደረጉ ይገኛሉ። የዓለም ባንክም የግብርና ዘርፋቸውን በዲጂታል አሰራር እያዘመኑ ለሚገኙ አገራት ድጋፍ እያደረገላቸው ነው።
ኢትዮጵያም አርሶ አደሩ የማምረት አቅሙን በማሳደግ የአገሪቱን የግብርና ምርት በእጥፍ ለመጨመር ያግዛል የተባለውን ‹‹የኢትዮጵያ ዲጂታል የግብርና ኤክስቴንሽን እና የምክር አገልግሎት ፍኖተ-ካርታ 2030›› (Ethiopian Digital Agricultural Extension and Advisory Services)ን አዘጋጅታለች። በዚሁ ፍኖተ ካርታ ላይ ሰሞኑን ውይይት ተካሂዷል። ይህ የዲጂታል ግብርና ኤክስቴንሽንና የምክር አገልግሎት ፍኖተ ካርታ አርሶ አደሮች ጥራት ያለውና ወቅታዊ የሆነ የዲጂታል ግብርና ኤክስቴንሽንና የምክር አገልግሎት እንዲያገኙ እንዲሁም በዘርፉ ላይ የሚሰሩ ሁሉም ተቋማት እርስ በርስ እንዲደጋገፉና በቅንጅት እንዲሰሩ የማድረግ ዓላማ አለው።
የፍኖተ ካርታውን ዝግጅትና ትግበራ የሚያስተባ ብረው የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ማንደፍሮ ንጉሤ እንደገለፁት፤ ፍኖተ ካርታው ሦስት ዋና ዋና ምሰሶዎች አሉት። የመጀመሪያው ምሰሶ መረጃ ማግኘት ወይም መሰብሰብ ነው። በዚህም አሁን ያለውን የመረጃ ማዕከልና መሰረተ ልማት በመጠቀም የተለያዩ አካላት የሚያመጡትን መረጃና እውቀት እንዲሰባሰብ ይደረጋል። ሁለተኛው ምሰሶ የተሰበሰበውን መረጃ ለተጠቃሚዎች በሚሆን መልኩ ማደራጀት ሲሆን የተሰበሰበውንና የተደራጀውን መረጃ ለመረጃ ፈላጊዎችና ለተጠቃሚዎች ማሰራጨት ደግሞ ሦስተኛው ምሰሶ ነው። እነዚህ ሂደቶች ትክክለኛ መረጃዎችን ለአርሶ አደሩ ለማድረስ ያስችላሉ።
‹‹ዲጂታል አገልግሎት ቋሚ አቅምን ይገነባል›› ያሉት ዶክተር ማንደፍሮ፣ ‹‹ለግብርና ትራንስፎርሜሽን እውን መሆን የዲጂታል አገልግሎት ወሳኝ ነው። በግብርናው ዘርፍ የሚተገበረው የዲጂታል አሰራር አርሶ አደሩ የበለጠ ምርታማና ተወዳዳሪ እንዲሆን ያደርጋል። በዚህም የአርሶ አደሩ ሕይወት እንዲሻሻል፣ የግብርናው ዘርፍ ለኢኮኖሚው የሚያበረክተው አስተዋፅኦ የተሻለ ጥራት እንዲኖረውና አገራዊ ኢኮኖሚው እድገት እንዲያስመዘግብ ጉልህ ሚና ይኖረዋል›› ብለዋል።
ከዓለም አቀፍና አገር አቀፍ የትምህርት ተቋማት የተሰበሰቡ መረጃዎች የሚከማቹበት የመረጃ ቋት (Data Center) እንዲደራጅ እንደሚደረግም ዶክተር ማንደፍሮ አስረድተዋል። ‹‹የፍኖተ ካርታው ትግበራ የግብርና ግብዓቶችና መሳሪያዎች የት እንደሚገኙ ለአርሶ አደሮች መረጃ ለማቅረብ ያስችላል። መረጃን ተንትኖ የሚያቀርብ ቡድን አለ። የተሰበሰበው መረጃ አስፈላጊው ግምገማና ማጣራት ይደረግበታል›› ብለዋል። የኢንስቲትዩቱ ሚና የፍኖተ ካርታውን ዝግጅትና ትግበራ ማስተባበር እንደሆነና ኢንስቲትዩቱ ሁሉም አካላት ተቀናጅተው ለግብርናው መሻሻል የሚያደርጉትን ጥረት ማስተባበሩን እንደሚቀጥልም አመልክተዋል።
የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ዑመር ሑሴን እስካሁን ያለውን የአገሪቱን የግብርና ዘርፍ አፈፃፀም ምን እንደሚመስል በማስታወስ አሰራሩን ማሻሻል እንደሚገባ ሲያስረዱ ‹‹በግብርና ኤክስቴንሽን ሥራ ኢትዮጵያ ከብዙ የአፍሪካ አገራት የተሻለ አፈፃፀም አላት። በተለይ በሦስተኛው ዙር የኤክስቴንሽን መርሃ ግብር የልማት ጣቢያ ሠራተኞች በአካል ተገኝተው አርሶ አደሩን እንዲደግፉ በመደረጉ በግብርናው ዘርፍ በርካታ ለውጦችን ማስመዝገብ ተችሏል። ይሁን እንጂ እስካሁን የተከናወኑት ተግባራት በቴክኖሎጂ የታገዙ አይደሉም። ይህም ከታችኞቹ የአስተዳደር መዋቅሮች በሚገባ የተደራጁ መረጃዎችን ወደ ፌዴራል ተቋማት በፍጥነት ማቅረብ አስቸጋሪ እንዲሆን አድርጎታል። ይህ ደግሞ የፖሊሲ አውጭዎችን በማሳሳትና ምርታማነትን በመቀነስ አገርን አደጋ ውስጥ ሊጥል ይችላል። ምርትን የሚጨምሩ ምክረ ሃሳቦችን ለአርሶ አደሩ በበቂ ሁኔታና በፍጥነት ማቅረብ ምርታማነትን ለማሳደግ ከሚያስችሉ ቁልፍ ግብዓቶች መካከል አንዱ ነው። ይህን ለማሳካትም የግብርና ምክረ ሃሳቦች የሚቀርቡበት አማራጭ ዘመናዊ፣ ወጪ ቆጣቢና ፈጣን ሊሆን ይገባል። ስለሆነም ወቅቱን የሚመጥንና የግብርናውን ዘርፍ በማዘመን ከዘርፉ የሚገኘውን ውጤት ለማሳደግ የሚያስችል የመረጃ አያያዝና አቀራረብ ስርዓት መዘርጋት አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል›› ይላሉ።
እርሳቸው እንደሚሉት ዲጂታል የግብርና ኤክስቴንሽን እና የምክር አገልግሎት ፍኖተ-ካርታው ለግብርናው ዘርፍ እድገት የራሱን አስተዋፅኦ ያበረክታል። ፍኖተ ካርታው የመረጃ አያያዝ ስርዓቱን ያዘምናል። በተበታተነ ሁኔታ የሚሰሩ የቴክኖሎጂ ባለድርሻ አካላትን እንዲሰባሰቡና በጋራ እንዲሰሩ ለማድረግ ያስችላል። ከዚህ በተጨማሪም ከግብርናው ዘርፍ አጋሮችና ተቋማት የሚደረጉ ድጋፎች ግልፅና የተቀናጁ እንዲሆኑም ያደርጋል። የግብርና ግብዓቶችንና ምርቶችን የዝውውር ሰንሰለት የተሳለጠ ያደርገዋል። በአጠቃላይ ፍኖተ ካርታው የግብርና ዘርፍ ምርታማነትን ያሳድጋል።
የፍኖተ ካርታውን ትግበራ ውጤታማ በማድረግ ሂደት የሁሉም ባለድርሻ አካላት ተሳትፎና ትብብር ወሳኝ እንደሆነ አያጠያይቅም። መሰረተ ልማቶችን በመገንባትና ወደ ተጠቃሚው የኅብረተሰብ ክፍል በማድረስ ረገድ ትልቅ ኃላፊነት ያለበት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ደግሞ ከባለድርሻዎቹ መካከል አንዱ ነው። ይህም ሚኒስቴሩ የዲጂታል ግብርና ኤክስቴንሽንና የምክር አገልግሎት ፍኖተ ካርታ ጥቅም ላይ እንዲውል ትልቅ ሚና እንዲኖረው ያደርጋል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሁሪያ አሊ የግብርናው ዘርፍ በአገራዊ ጠቅላላ ምርት እና በሥራ እድል ፈጠራ ከፍተኛ ድርሻ ያለው ዘርፍ በመሆኑ በዲጂታል አሠራር ቅድሚያ የተሰጠው ዘርፍ እንደሆነ ተናግረዋል። ግብርና በኢትዮጵያ ከፍተኛ የሰው ሃይል የተሸከመና የውጭ ምንዛሬ ማግኛ እንደመሆኑ መጠን የዲጂታል አሰራር ዝርጋታ ላይ ልዩ ትኩረት ያስፈልገዋል ብለዋል። ለዘርፉ ችግሮች በቴክኖሎጂ የታገዘ መፍትሄ በመስጠት በዲጂታል አሰራር እንዲታገዝ ከተደረገ ምርታማነት እንደሚጨምር ጠቁመው፤ ፍኖተ ካርታው ውጤታማ እንዲሆን የሁሉም አካላት ትብብር አስፈላጊ እንደሆነም ገልፀዋል።
በ10 ዓመቱ የልማት እቅድ እና በአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሃ ግብር ዋነኛ ምሰሶ ከተባሉ ተቋማትና ዘርፎች መካከል አንዱ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ መሆኑን ያስታወሱት ወይዘሮ ሁሪያ፤ ተቋማት የየዘርፋቸውን የዲጂታል ስትራቴጂ ሲነድፉ ከኢትዮጵያ ዲጂታል ስትራቴጂ 2025 ጋር በተጣጣመ መልኩ መሆን እንደሚገባውም አሳስበዋል።
የፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች የውጤታማነት ደረጃ ለትግበራቸው በተሰጠው ትኩረት የሚወሰን ነው። የዲጂታል ግብርና ኤክስቴንሽንና የምክር አገልግሎት ፍኖተ ካርታ ውጤታማ የሚሆነው ባለድርሻ አካላቱ በሚኖራቸው የቁርጠኝነት ልክ ነው። ስለሆነም የፍኖተ ካርታው ትግበራ ትኩረትና ትጋት እንደሚፈልግ አቶ ኡመር በአፅንዖት ተናግረዋል።
‹‹ዋናውና ጠቃሚው ነገር ፍኖተ ካርታውን ወደ አርሶ አደሩ በመውሰድ መተግበሩ ነው። የዶክመንት ዝግጅት ሥራ በቂ አይደለም። በፍኖተ ካርታው ዝግጅት ሂደት ድጋፍ ያደረጉ ተቋማትን ጨምሮ ሁሉም የግብርና ዘርፍ ባለድርሻ አካላት ሥራቸውን ዳር ማድረስ ይጠበቅባቸዋል። የሥራቸውን ውጤት መመልከትና በአርሶ አደሩ ሕይወት ላይ አዎንታዊ ለውጥ መፍጠር የሚችሉበትን ተግባር ማከናወን ይኖርባቸዋል። ከዚህ በኋላ ወደ አርሶ አደሩ ዘንድ መድረስ የምንችለው በተበታተነ መልኩ ሳይሆን በፍኖተ ካርታው አማካኝነት ነው›› በማለት ቴክኖሎጂውን ለመተግበር ከወቅቱ ጋር የሚጣጣም ቁመና ላይ መገኘት እንደሚገባ አሳስበዋል።
በኢትዮጵያ መሠረታዊ የሆነ መዋቅራዊ የምጣኔ ሀብት ለውጥ ለማምጣት ዘርፉን በቴክኖሎጂ ማገዝ ወሳኝ እርምጃ ነው። በግብርና ልማት ኋላ ቀር መሆን በምግብ ራስን ለመቻል በሚደረገው ጥረት ላይ የሚኖረውን ቀጥተኛ ተፅዕኖ በመገንዘብ የበለጸጉ አገራት የተገበሯቸውን የዳበሩ የቴክኖሎጂ ውጤቶች መጠቀም ያለውን ጠቀሜታ መገንዘብ እጅግ አስፈላጊ ነው። የችግሩ አስከፊነትና ግዝፈት በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚና በአካባቢያዊ ሁኔታዎች በገሀድ የሚታይ በመሆኑ በተቀናጀና በተናበበ መንገድ ፈጣን፣ ግልፅና ወሳኝ የሆኑ የመፍትሄ እርምጃዎችን መውሰድ ያስፈልጋል።
አገር በቀል የሆኑ እውቀቶች ላይ ቴክኖሎጂን በማከል የግብርናውን ዘርፍ በከፍተኛ ሁኔታ ውጤታማ ማድረግ እንደሚቻልም ሊዘነጋ አይገባም። የግብርናው ዘርፍ ያለውን አቅምና ያሉበትን ችግሮች ተረድቶ ለወቅቱ በሚመጥን አሰራር ማገዝ ከተቻለ ኢትዮጵያ ዜጎቿን መግባ ለሌላ የሚተርፍ ምርት ማስገኘት የሚችል እምቅ ሀብት ያላት አገር መሆኗን በተግባር ማሳየት ይቻላል። ለዘመናት ባልተቀየረ የማረሻ መሳሪያና የአስተራረስ ስልት በማደግ ላይ ያለውን የአገሪቱን ሕዝብ ቁጥር የመመገብ ግዴታውን በመወጣት ላይ የተጠመደው የግብርናው ዘርፍ ባለበት ይዘትና ቅርጽ እንዲቀጥል መፈቀድ የለበትም።
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ሰኔ 13 /2014