ቀደም ሲል ምክር በቤተሰብ ብሎም በጎረቤትና በመምህራን የሚሰጥ ነበር። በጣም ከበድ ካለ ደግሞ በአገር ሽማግሌዎች አማካኝነት ይከወናል። እንደዛሬው ሆስፒታል ተሄዶ አለያም ሐኪም በግል ቀጥሮ የሚተገበር አልነበረም። እንደውም እስከ ቅርብ ዓመታት ድረስ እኔ አማካሪ የሚያስፈልገኝ እብድ አይደለሁ ይባልም ነበር። ምክንያቱም የጥቅሙን ምንነትና ማንነት ብዙ ሰው ስላልተረዳው። ትንሽ ተረዳሁም የሚለው የማህበረሰቡ ክፍልም የለመደውን መኖር ስለሚፈልግ ከዚህ የተለየ ተግባር ይከውናል ለማለት ያስቸግራል። ስለዚህም ምልከታው አልሰፋምና በይሉኝታ ሊተገብረውም ፈቃደኛ አይደለም። በዚህም አማካሪ ፍለጋ የሚወጣውን ሰው ቁጥር ጥቂት እንዲሆን አድርጎታል።
አሁን አሁን ግን ይህ ጉዳይ በብዙ መልኩ ተቀይሯል። አንዱ በሕግ መደገፉ ሲሆን፤ ተቋማዊ አደረጃጀት ጭምር ያለው ሆኖ እንዲሰራ ተደርጓል። የአገልግሎት አሰጣጡም እንዲሁ በዘርፍና በቁጥር በዝቷል። ይህ ሲባልም እንደቀደመው በስነልቦና ብቻ የተንጠለጠለ ብቻ ሳይሆን በሙያም ጭምር ተዋቅሯል። እኛ ግን ለዛሬ ጉዳያችን ያደረግነው የቀደመውንና በስነልቦና ላይ ትኩረቱን የሚያደርገውን የማማከር ተግባር ነው፤ ትኩረታችንን ደግሞ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ላይ አድርገናል።
ለዚህ መነሻ የሆነን በወሩ መጨረሻ አካባቢ በትምህርት ሚኒስቴርና የአሜሪካ ኤምባሲ አማካኝነት የተሰጠው ስልጠና ሲሆን፤ እንደ አገር በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሚማሩ ተማሪዎችን ያግዛሉ ተብለው የተመደቡ የስነልቦና አማካሪዎች ተሳትፈውበታል። እናም ስልጠናው ለተማሪዎች ያለውን ጥቅም እንዳስሳለን። በዘርፉ ያሉ ችግሮችን ከነመፍትሄያቸው ከሚመለከታቸው አካላት በመጠየቅ ይዘን እንድንቀርብ ሆነናልም።
የስነልቦና አማካሪዎች መኖር ሙያተኛው የሥራ እድል እንዲያገኝ፤ ለተማሪዎች ደግሞ በሁሉም ጉዳይ ላይ ችግር እንዳይገጥማቸው ያግዛል። ይሁንና ከትምህርት ቤት ብዛትና ከተማሪው ቁጥር እንዲሁም ከአማካሪዎች እጥረት አኳያ ሁሉም ትምህርት ቤት ይህንን እድል ያገኛሉ ለማለት ያስቸግራል።
የስልጠናው ዋና አላማ የስነልቦና አማካሪ ያለባቸው ትምህርት ቤቶች በቀደመ ልምዳቸው መጓዝ የለባቸውም፤ ዘመኑን ዋጅተው መጓዝ ይገባቸዋል የሚል ነው። እውቀታቸውን የሚያሳድጉ ስልጠናዎች ያስፈልጓቸዋል። ስለሆነም ሁለቱ ተቋማት በጋራ ሆነው ስልጠናውን እንዲሰጡ ተደርጓል። ስልጠናውን የወሰዱት አማካሪዎች ከተለያዩ ክልሎች የመጡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አማካሪዎች ሲሆኑ፤ በየዓመቱ ይህንን አይነት ስልጠና እንደሚሰጥም ነግረውናል።
ከከፋ ዞን ጠሎ ወረዳ ጠሎ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ስልጠናውን ለመሳተፍ የመጡት አማካሪ አቶ ኬሮ ኢሚቶ እንደሚሉት፤ እንደነዚህ አይነት ስልጠናዎች እጅግ አስፈላጊና ተደጋግመው ሊሰጡ የሚገባቸው ናቸው። የአማካሪውን እውቀት ከመገንባትም በላይ አማካሪው አዳዲስ ነገሮችን አውቆ ተማሪው ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ እንዲያመጣ ያግዛል። ከተማሪውም እኩል እንዲራመድ እድል ይሰጠዋል። በተለይም በገጠሪቱ ኢትዮጵያ የሚኖሩ አማካሪዎች ለአዲስ ነገሮች ቅርብ ስላልሆኑ አዳዲስ ነገሮችን እንዲለምዱና ወደተግባር እንዲቀይሩ ከማድረግ አንጻር የማይተካ ሚና ይኖረዋል። ወቅታዊ ሁኔታውን ማዕከል አድርገውም እንዲሰሩ ብርታት ይሰጣቸዋል።
ከቴክኖሎጂው ጋር እኩል የሚራመዱበት ሁኔታ ስለሌለ ዘመኑን ያማከለ ሥራ ሊሰሩ አይችሉም። ስለሆነም ስልጠናው የነቁና የበቁ እንዲሆኑም ያስችላቸዋል የሚሉት አቶ ኬሮ፤ እንደአገር ሁሉም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች አማካሪ ላያገኙ ይችላሉ። በዚህም በአንዳንድ መምህራን አጋዥነት ነገሮች እንዲስተካከሉ ይደረጋል። ይህ አካሂድ ግን መልካም ጎን እንዳለው ሁሉ አሉታዊም ተጽዕኖም ይኖረዋል።
በዘልማድ የሚሰጥ የማማከር አገልግሎት ተማሪዎችን የባሰ ችግር ውስጥ ሊከት ይችላል የሚሉት አቶ ኬሮ እናም ይህንን አይነት አገልግሎት የሚሰጡ መምህራን ከተማረው እኩል የሚሆኑበትን መጠነኛ የአሰራር እውቀት እንዲጨብጡ፤ በፕሮግራም የተመራ የተማሪዎች እገዛ እንዲያደርጉ በእንደዚህ አይነት ስልጠና ሊታገዙ እንደሚገባ ይመክራሉ።
የማማከር ሥራ እንደ አገር የሚታየው የትርፍ ጊዜ ተግባር ተደርጎ እንደሆነ የሚያነሱት አማካሪው፤ በብዙዎቹ ትምህርት ቤቶች ዝርዝር ተግባር ተሰጥቶበት አይሰራም። በትምህርት ስርዓት ውስጥም ተካተው ተገቢውን ተግባር ተሰጥቷቸው የሚከወኑም አይደሉም። ስለዚህም ውጤታማ ናቸው ለማለት ያስቸግራል ይላሉ። በምክንያትነት የሚጠቅሱትም የሥራ መዘርዝር አለመሰጠቱን ነው። ይህ አይነት አሰራር ተጠያቂነት የሰፈነበት ስላልሆነ አማካሪውን ሰነፍ ከማድረጉም በላይ ተማሪዎችን በተገቢው ሁኔታ እንዳይታገዙና እንዲጠቀሙ ያደርጋቸዋል። የተለካና ሊጠየቅበት የሚችለው የሥራ መዘርዝር ቢኖር ግን በሠራው ልክ ስለሚመዘን ጠንክሮ ተግባሩን ይከውናል። ሥራው የትርፍ ጊዜ ሥራም እንደሚሆን ያስረዳሉ።
የአማካሪነት ሚናንና ተግባርን ያልተረዳ መምህር ለራሱም ሆነ ለተማሪው ምንም የሚሰጠው ጥቅም የሚሉት አቶ ኬሮ ከራሱ ልምድ ብቻ በመነሳት ነው ሊመክር የሚችለው ይህ ደግሞ እንደተመካሪው ማንነትና ፍላጎት ይለያያልና ውጤቱ ላይ አመርቂ ላይሆን ይችላል። ስለሆነም አማካሪዎች በእውቀት የጎለበቱ ቢቻል ሙያ ውስጥ ያሉ ቢሆኑ ይመረጣልም ይላሉ። ይህ ካልሆነ ግን እንደ አገር ልንገነባው የታሰበውን ትውልድ ልንፈጥር አንችልም። እናም እንደመንግስት በስልጠናም ሆነ በቅጥር ዙሪያ ከመጀመሪያ ደረጃ ጀምሮ ለተማሪዎች የስነልቦና አማካሪ ሊመድብ እንደሚገባም ያነሳሉ።
አሁን ያለው ተማሪ በብዙ መልኩ እገዛን የሚሻ ነው የሚሉት አቶ ኬሮ በተለይም በስነልቦናና በስነምግባር መኮትኮት ላይ ብዙ ሥራ ሊሰራበት ይገባል። አገር ተረካቢና አሻገሪ እንዲሁም የወደፊቱን ቀያሽ መሆኑ ታውቆ ተገቢውን ትኩረት ይፈልጋል። ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ ባለሙያ የሆኑ አማካሪዎችን መመደብ ካልተቻለ ደግሞ በስልጠና የጎለበቱና ሥርዓቱን የተረዱ መምህራንን መቅጠር የውዴታ ግዴታ መሆን እንዳለበትም ያስገነዝባሉ።
ሌላው ያነሱት ጉዳይ አማካሪዎች ተጨማሪ ሥራ ሊሠጣቸው አይገባም የሚል ሲሆን፤ በእነርሱ አካባቢም ባይሆን ከተሞክሮዎች ሲናገሩ ሥራ ስለማይበዛባቸው በሚል ክፍል ገብተው ትምህርት እንዲያስተምሩ ይታዘዛሉ፤ ይህ ደግሞ ተማሪዎችን ማገዝ ባለባቸው ልክ እንዳይደግፏቸው ስለሚያደርግ አማካሪዎችን መረዳትና ሥራቸውን አውቆ ተግባራቸውን ብቻ እንዲያከናውኑና በተማሪዎች ለውጥ ላይ ብቻ ትኩረታቸውን እንዲያደርጉ መፍቀድ አስፈላጊ እንደሆነም ይጠቁማሉ።
በአንድ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ ቢያንስ ከ1ሺ በላይ ተማሪ ይኖራል። ሁሉም ደግሞ እገዛን ይፈልጋሉ የሚሉት አቶ ኬሮ፤ ለእነርሱ ደህንነትና ውጤት ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ ከሁሉም አማካሪ ይጠበቃል። በዚያው ልክ ሌላውም መምህር ሆነ ኃላፊ የአማካሪዎቹ ሥራ የእነሱንም ተግባር እንደሚያገዝ ማመን ይኖርባቸዋል። ይህ መተጋገዝ ካለም ብቻ ነው ነጻና ውጤታማ የሆነ ትውልድን መፍጠር የሚቻለው። ይህ ሲሆንም ብቻ ነው ትኩረቱን ትምህርት ላይ ያደረገ ተማሪ ልንፈጥር የምንችለው። ስለሆነም ይህንን እያዩ መስራትም እንደሚገባ ያነሳሉ።
እንደ አቶ ኬሮ ገለጻ፤ ተማሪዎች ለነገ የሚበጃቸውን አስቀድመው ለመለየት መንገዱን የሚያሳያቸው ሰው በማንኛውም መስክ ይፈልጋሉ። በተለይም መምህራን የሚሏቸውን የሚሰሙበት ሁኔታ እጅግ የላቀ ነው። ስለሆነም ከእውቀት ማስጨበጡ ባሻገር የምክር አገልግሎት መስጠት ላይ ትኩረት በማድረግ ውጤታማና ጥሩ ተስፋ ሰናቂ እንዲሆኑ ማድረግ ይቻላል።
ተማሪዎች ቀደም ባሉት ጊዜያት ወደፊት መማር እና መሆን የሚፈልጉትን ነገር ደፍሮ ለመናገር ይፈሩ ነበር ያሉት አቶ ኬሮ ቅንጦት እስኪመስል ድረስም ተማሪዎች ይሸማቀቁ ነበር፤ ስለዚህም በቤተሰብ ተጽዕኖ ውስጥ በመሆን የእነርሱን ፍላጎት ትተው የቤተሰባቸውን ፍላጎት እንዲያሟሉ ይሆናሉ። አሁን ግን ይህ ተቀይሯል። በተለይም አማካሪዎች በየትምህርት ቤቱ መመደባቸው ችግሩን በስፋት ከቀነሰው መካከል ነው። ስለሆነም ይህንን ማጠናከር ያስፈልጋል። ከስነ ምግባር ወጣ ያሉ ተማሪዎች የሚያሳዩትን ጸባይ ለማረም እና ነጋቸውን በስኬት እንዲደመድሙት ለማድረግም የማይተካ ሚና እንዳለው ይታመናልና በስልጠና ጭምር አማካሪዎችን በማብዛት ሚናውን ማስፋት እንደሚገባም ገልጸዋል።
የስነልቦና አማካሪዎች ዋና ተግባራቸው ተማሪዎችን እንደ ጓደኛ መቅረብ፣ ጥሩ አድማጭ መሆን ፣ ጽናት እና ችግራቸውን ማየትና መለየት ከዚያም መፍታት እንደሆነ የተናገሩት አቶ ኬሮ ተማሪዎች ይህ ሲሆንላቸው ደግሞ በአስተማማኝ፣ ደጋፊ እና አካባቢ ውስጥ እንዲካተቱ ይሆናሉ። ከአስተማሪዎች፣ ከአስተዳደር እና ከተማሪ ጋር በእጅጉ እንዲገናኙም እድል ይፈጥርላቸዋል። በተጨማሪም ስለ ችግሮቻቸው ማውራት እንዲጀምሩም ያደርጋቸዋል። እናም አገልግሎቶቹን የሚመሩት የስነልቦና አማካሪዎችን እንከባከባቸውም ሲሉ ይመክራሉ።
የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ፋንታ ማንደፍሮ በበኩላቸው፤ ለአማካሪዎች የሚሰ ጠው ስልጠና እጅግ አስፈላጊ ነው። በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን ትስስር ከማጠናከሩም በላይ ለአማካሪው የሚሰጠው ፋይዳ ላቀ ያለ ነው። በመማር ማስተማሩ ሂደት ውስጥም ትልቅ ሚና ይኖረዋል። በተለይ የትምህርት ጥራትን ከማምጣት አኳያ የማይተካ ሚናን ይጫወታል። በተጨማሪም በትምህርት ቤቶች ላይ የሚሠሩ የማማከር አገልግሎቶችን ያጎለብታል።
የሰለጠኑ ጠንካራ እና ቁርጠኛ የሆኑ የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አማካሪዎች መኖር ለተማሪዎች ቀጣይ ሕይወት መንገድ እንደሚከፍት የሚያነሱት ዶክተር ፋንታ፤ ከዚህ ቀደም ኤምባሲው የአቅም ግንባታ ስልጠና መስጠቱን አስታውሰው በትምህርት ዘርፍ እያደረገ ላለው ድጋፍ ከፍተኛ ምስጋና ያቀርባሉ። እንዲህ አይነቱ ድጋፍ ቀጣይነት እንደሚኖረውም እምነት አላቸው።
በአሜሪካ ኤምባሲ የአሜሪካ ትምህርት አማካሪው አቶ ተክለሚካኤል ተፈራ እንደሚናገሩት፤ ኤምባሲው በገንዘብ እና ቴክኒክ ድጋፍ በማድረግ እንዲህ አይነት ስልጠናዎችን ሲያደርግ ከሁለቱም አኳያ ነው። በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የማማከር ሥራ የሚሠሩ፣ ተማሪዎችን ለኮሌጅ እና ለዩኒቨርሲቲ የሚያዘጋጁ መምህራን እና ሠራተኞችን ማሰልጠንም ነው። በዚህ ደግሞ ተማሪዎችን በምን ጉዳይ ላይና እንዴት ማማከር እንዳለባቸው ግንዛቤ እንዲይዙ ተደርጓል። በተለይም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አጠናቀው ወደ ዩኒቨርሲቲ ለመግባት የሚዘጋጁ ተማሪዎችን እንዴት ማገዝ እንዳለባቸው የተረዱበት ነው።
ብዙዎቹ ዩኒቨርሲቲ ለመግባት እየተዘጋጁ ያሉ ተማሪዎች በአሜሪካ እና በሌሎች አገራት ሄደው መማር ይፈልጋሉ። ሆኖም በቂ የማማከር አገልግሎት ስለማያገኙ ስኬታማ አይሆኑም። ስለዚህም እንደ አሜሪካ ኤምባሲ ይህ ችግር በተደጋጋሚ በመታየቱ ስልጠናውን መስጠት አስፈልጓል የሚሉት አቶ ተክለሚካኤል፤ ኤምባሲው ብዙ የሚረዳቸው ተማሪዎች በመኖራቸው ይህ ስልጠና እንዲሰጥ ሆኗል።
ኮቪድ እያለ በ2021 ወደ 2ሺ166 ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች አሜሪካ አገር ሄደው እንዲማሩ መደረጋቸውን የጠቆሙት አማካሪው፤ ስልጠናው በኤምባሲው በኩል ብቻ ሳይገደብ ተማሪዎቹ በትምህርት ቤታቸው ሆነው በቂ መረጃ እና ምክር አግኝተው የውጭ አገር የትምህርት እድል እንዲኖራቸው ለማድረግ የሚያግዝ መሆኑንም አንስተዋል። ከዚያም ባሻገር ተማሪዎች በውጭ አገር ላሉ ዩኒቨርሲቲዎች ራሳቸውን በሚገባ ለማስተዋወቅ እንዲችሉ የሚገባውን እውቀት የሚያስጨብጡት አማካሪዎች በመሆናቸው ስልጠናው ለዚህም እንዲያ ግዛቸው ተደርጎ የተሰጠ እንደሆነም ይናገራሉ። ለዚህ ደግሞ ይህንን ሊያግዙ የሚችሉ 560 መጽሐፍትን ኤምባሲው ለትምህርት ሚኒስቴር ማስረከቡን ያስረዳሉ።
በትምህርት ቤት ውስጥ ያሉ አማካሪዎች ከትምህርት በተጨማሪም ከተማሪዎች ጸባይ በመነሳት በርካታ ሥራዎች ይሠራሉ። ‹‹እኛ በብዛት ትኩረት የምናደርገው ተማሪዎችን ለዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸው ማዘጋጀትን ነው›› ያሉት አቶ ተክለሚካኤል፤ አብዛኛውን ጊዜ ተማሪዎች ምን መማር እንደሚፈልጉ አያውቁትም። ለዚህም የወላጆች፣ የአቻ ጓደኛ ተፅዕኖና ግፊት አንዱ ሲሆን፤ ተማሪዎች እራሳቸውን አውቀው ስኬታማ እንዳይሆኑ ያደርጋቸዋል። ስለሆነም የችግሩ ሰለባ እንዳይሆኑ ለማድረግ የአማካሪዎችን አቅም ማጎልበት ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ ስልጠና ከፍተኛ ሚና እንዳለውም ተናግረዋል።
እንደ አቶ ተክለሚካኤል ገለጻ፤ የዚህ ስልጠና ግብ ስልጠና ሰጠን ለማለት ብቻ ሳይሆን ተግባሩ እንዴት ተከውኖ ውጤት ያመጣል የሚለው ነው። ለዚህ ደግሞ ስልጠናውን የወሰዱት አማካሪዎች ልምድ ያላቸው አማካሪዎቹ ከሆኑ የበለጠ ተማሪዎችን እንዲደግፉ፤ አዳዲሶቹ ደግሞ ከሚሰጠው ስልጠና እና ልምድ ተነስተው እንዲሁም ልምድ ካላቸው ተምረው የማማከር ሥራቸውን እንዲጀምሩ ማድረግ ነው። ስለሆነም ለተግባራዊነቱ ጥብቅ ክትትል ይደረጋል።
እኛም አማካሪዎች ምክራችሁን ተቀብላችሁ የማ ንም ጉትጎታን ሳትፈልጉና ቅጣት ይደርስብኛል ሳትሉ ተማሪዎቹን የነገ አገር ተረካቢና አገር አሻጋሪ አድርጓቸው በማለት ሀሳባችንን ቋጨን።
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ሰኔ 13 /2014