<<ሱፉን ግጥም አርጎ ተከርክሞ ፀጉሩ
መልዓክ መስሎ ታየኝ አይ ያለው ማማሩ>>
ስትል አስቴር አወቀ ያዜመችለት ጉብል ትውስ አለኝና በእዝነ ህሊናዬ ተመለከትኩት፡፡ ይህ ዜማ በሰማነው ቁጥር አንድ ያማረበት ወጣት ዘንጦ ከፊታችን ድቅን ብሎ ይታየናል፡፡ የሆነ ዘመናይና ሽክ ያለ ከራስ ፀጉር እስከ እግሩ ዘንጦ ውበትን ደርቦ የሚጎማለል፡፡ ስትመለከተው ከፍ ያለ ውበት ተላበሰባትና አስቴርም በውበቱ ምክንያት መልዓክነት አለበሰችው፡፡ እዚህ ዜማ ላይ የተጠቀሰው ዘናጭ ከሱፉ ባሻገር ዝነጣ በፀጉር ቁርጡ (ክርከማ) ከፍ አድርጎታልና ለወንዶች ልዩ ውበትን የሚላብሰው የፀጉር ቁርጥ በዛሬው የፋሽን አምዳችን ልንመለከተው ወደድን።
ወንዶች በየዘመናቱ የተለያዩ አይነት የፀጉር አሰራርና አቆራረጥ ስልቶችን (ስታይል) ሲከተሉ ቆይተዋል፡፡ ዛሬም በተለያዩ አካባቢዎች ዘመን ባፈራቸው መሳሪያዎች ፀጉራቸውን የሚቆረጡበትና የሚንከባከቡበት ጊዜ ላይ ከመደረሱ በፊት የፀጉር አሰራርና እንክብካቤ ጅማሮ የነበረው ቤተመንግስት ውስጥ በንጉሶችና በልዑሎች ዘንድ እንደነበር የታሪክ መዛግብት ያመላክታሉ፡፡
በተለይ የጥንት የሮማውያን ንጉሶች በፀጉር አያያዝና እንክብካቤ እንዲሁም ልዩ የሆነ አሰራር ከሌላው ተራው ህዝብ በተለየ ይታዩ እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ቀስ በቀስም በንጉሳውያኑ የተለመደው የፀጉር አሰራር በተራው ህዝብ ዘንድ ተለመደ፡፡ በዘመኑ ወንዶች ፀጉራቸውን በማስረዘም በተለያየ መልኩ በማስያዝ ይዋቡ ነበር፡፡
በተለይም በ16 ክፍለ ዘመን የወንዶች ፀጉር ማስረዘም እንደ ነውር ይቆጠር ነበር፡፡ ይህ ፀጉርን የማስረዘም ነውርነትና አለመወደድ በ17 ክፍለ ዘመን መልሶ እንደ አዲስ ተለምዶ ፋሽን ሆነ፡፡ ከዚያ በፊት ወንዶች የተለያየ የፀጉር አሰራር ይከተሉም ነበር፡፡ በተለይም ከ19ኛ ክፍለ ዘመን ጅማሮ አንስቶ ደግሞ አዲስ የአቆራረጥ ስልት ይተገበር ጀመር፡፡
የእግር ኳስ ተጫዋቾችና የመርከብ ሰራተኞች በተለያየ የፀጉር አቆራረጥ ስልታቸው ይታወቁ ነበር፡፡ እነዚህ የእግር ኳስ ተጫዋቾችና ከአንዱ አገር ወደሌላው የሚጓጓዙት የመርከብ ሰራተኞች ሌላው ህዝብ እነሱን እየተመለከተ የሚሰሩትን የፀጉር ቁርጥና አሰራር እየተከተለ በራሱ መንገድ ይተገብረው ጀመር፡፡
ከጥንት ጀምሮ ማህበረሰባችን የራሱ የሆነ የፀጉር አሰራር ልምዶች ነበሩት፡፡ ኢትዮጵያዊያን በፀጉር አሰራር ስልታቸው እራሳቸው በራስ ጥበብ ማሳመራቸው የዘመናት ልምዳቸው ነው፡፡ በየዘመኑ የራሳቸው የሆነ የፋሽን ጥበብ ተከትለው ወቅቱ ያቀረበላቸው መሳሪያና የውበት ማድመቂያ ተጠቅመው ፀጉራቸውን በልዩነት ይሰራሉ፡፡
ጥንት በተለያዩ አካባቢዎች የነበረው ፍሪዝና አፍሮ በተለይም በ1950ዎቹ በተለያየ ዓለም አገራት ወንዶች የሚዋቡበት ፋሽን ነበር፡፡ ከዚያ በፊት በተለይም በ1920ዎቹ አብዛኛው ወንዶች ፀጉራቸውን በመላጨትና ኮፍያ በማድረግ ይዋቡ ነበር፡፡ በተለይም በወቅቱ ይወጡ የነበሩ የተለያዩ ፊልሞችና ሲኒማ ላይ የሚታዩ ገፀ ባህሪያት ላይ የሚስተዋሉ የፀጉር ማስረዘም እንዲሁም መልከ ብዙ የፀጉር ቁርጦች በብዙዎች ዘንድ እየተለመደ መጥቷል፡፡
20ኛው ክፍለ ዘመን የወንዶች ፀጉር አሰራርና ፍሸን ልዩ የሆነ የእድገትና የመሻሻል ዘመኑ ሆነ፡፡ ወንዶች ለበዓላትና ለአዘቦት ቀን በተለያየ ወቅትና ቦታ ሁኔታው የሚፈቅደውና በዚያ ቦታ የተለመደ የተለያየ መልክና ቀለም ያለው የፀጉር አቆራረጥ በአዲስ መልክ ይከሰት ጀመር፡፡
በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የወታደሮች የፀጉር አቆራረጥ ስልትም በብዙዎች ተተግብሯል፡፡ ይህም ፀጉር እጅግ በጣም አሳጥሮ እኩል በሆነ መልኩ የሚቆረጥበት ስልት ነበር፡፡ በተለይም በ1950ዎቹ የፊልም ሰሪዎች የፀጉር አቆራረጥ ስልት በስፋት እንደ ፋሽን ተቆጥሮ በብዙዎች ተመርጦ ተተገብሯል፡፡ በተለይም በስፖርት በሙዚቃና በፊልም ኢንዱስትሪ ውስጥ በሚታወቁ ታዋቂና ዝነኛ ሰዎች ምክንያት በስፋት አዳዲስ ፋሽን ይተዋወቅና ይተገበር ነበር፡፡
በአሁኑ ዘመን እጅግ ሰፍቶና አድጎ በየቦታው ቴክኖሎጂ ያበረከታቸው የውበት መጠቀሚያዎች ከመፈጠራቸውም በፊት የእኛ አባቶችና ወጣት እያሉ የራሳቸው የሆነ ልዩ ፀጉር መዋበያ ፈጥረዋል፡፡ አባቶች፣ ወጣቶችና ልጆች በየዘመናቱ በተለያዩ መልኩ በፀጉር አያያዝና በየዘመኑ ፋሽን አምረው ታይተዋል፤ በዘመናቸው በምርጫቸው የውበት አክሊልን ደፍተዋል፡፡
ከዓለም የራቀ የፀጉር አቆራረጥ ስልትና ፋሽን ባንከተልም ኢትዮጵያዊያን በራሳቸው የፀጉር አሰራር ዘመናትን ተሻግረዋል፡፡ ሹሩባቸው ስናይ ማንነታቸውን ጎፈሬያቸውን ስንመለከት ዘመናቸውን እንለካለን፡፡ የአርበኞች ጎፈሬ የንጉሶች የፀጉር አሰራር የወጣቶች ቁንጮ የጎበዞች ሹሩባ ኢትዮጵያዊያን በየዘመኑ ጊዜና ወቅቱን መስለው ተውበው የታዩበት ፋሽን ነበር፡፡ ጎፈሬ እኛ ጋር ብርቅ አልነበረም፣ መፈረዝም የተለመደና ሌሎች ጋር ተዟዙሮ ቆይቶ በአዲስ መልክ የመጣ እንጂ እኛ ጋር ዘመናት የተሻገረ መዋቢያ እንደነበር አፋሮችን በማሳያነት መጥቀስ ይቻላል፡፡
የአፋር ወጣቶች በአካባቢያቸው ያገኙትን ዕፅዋት ተጠቅመው እኛ እዚህ ከተማ ላይ ፀጉር ከመፈረዛችን በፊት ከጥንት ጀምሮ አምረው ታይተውበታል፤ተውበው አጊጠውበታል፡፡ እዚህ ከተማ ውሎ አድሮ ከዚያ ተኮርጆ ፋሽን ሆኖ ይሄው ዛሬም ተሻግሯል፡፡ ዛሬ ኢትዮጵያዊያን ወጣቶች እና አባቶች ብሎም ልጆች የተለያየ የፀጉር ቁርጥ ፋሽንን ይከተላሉ፡፡ በዚያም ዘመናቸውን መስለው ከተለያየ አለባበስና ወቅት ጋር የሚሄድ ከራስ ቅልና ከፊታቸው ገፅታ ጋር የሚያምረውን ከፀጉር ስራ ባለሙያ ጋር ተማክረውና መርጠው ይሰራሉ፡፡ በዚያም አምረውና ደምቀው ይታያሉ።
ወንዶች የሚቆረጡት የፀጉር ቁርጥ እንደ እድሜያቸው ምርጫቸውም የተለያየ እንደሆነ የፀጉር ስራ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ በየጊዜው የሚለመዱ የፀጉር ቁርጥ ስልቶች ወይም ፋሽኖች በአብዛኛው በወጣቱ የሚተገበሩ ሲሆኑ እድሜያቸው ከፍ ያሉትና በአነስተኛ የእድሜ ደረጃ የሚገኙ ወንዶች የሚቆረጡት የፀጉር አይነት የተለመደና ብዙም ወጣ ያላለ መሆኑን ባለሙያዎቹ ያስረዳሉ፡፡
ወጣት ሰለሞን አየለ ከአምስት ዓመታት በላይ በፀጉር ስራ ቆይቷል፡፡ የወንዶች ፀጉር ስራ ላይ ዓመታትን እንዳሳለፈ ባለሙያ ደንበኞቹ ወደፀጉር ማስተካከያ ሳሎኑ ሲመጡ የሚሰሩትን የፀጉር ቁርጥ ስልት ወይም እነሱ “ስታይል”ይሉታል ያማርጣቸዋል፡፡ በእርግጥ ደንበኞቹ ከሆኑ የሚወዱትና የሚያዘወትሩት ስለሚታወቅ በዚህ እንደማይቸገርና በቀጥታ የተለመደውን ቁርጥ እንደሚሰራ ያስረዳል፡፡
እንደ ባለሙያው ሰለሞን የፀጉር አቆራረጥ ስልቶች እንደ ወቅትና ጊዜው ይለያያሉ፡፡ ክረምት ላይ አሳጥሮ መቁረጥ ይቀንሳል፡፡ ከዚህ ይልቅ ፀጉር ባለበት መንከባከብና ቅርፁን ማስተካከል ይዘወተራል፡፡ በአንፃሩ ደግሞ በጋ ላይ አሳጥሮ በተለያየ ቅርፅ መሰራት ብዙዎች ያዘወትራሉ፡፡
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን ሰኔ 13 /2014