
• በመዲናዋ ከ292 ሺ በላይ ደንብ ተላላፊዎች ላይ እርምጃ መወሰዱን ባለስልጣኑ አስታወቀ
አዲስ አበባ፡- ከሐምሌ 2013 ዓ.ም ጀምሮ ባሉት አሥራ አንድ ወራት ወረራ ተፈጽሞበት የነበረ አንድ ሚሊዮን 662 ሺ 349 ካሬ ሜትር መሬትን ከወረራ ማጽዳት መቻሉን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ደንብ ማስከበር ባለስልጣን አስታወቀ።
የባለስልጣኑ ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ደሳለኝ ፉፋ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ ወረራ የተፈጸመበት ከአንድ ሚሊዮን ካሬ ሜትር በላይ መሬት ከወረራ በማጽዳት የመንግሥትን ሀብት እንዲድን ተደርጓል።
የመሬት ወረራን ለመከላከል በተሠራው ሥራ 19 ሺ 649 ቦታዎች ወይም አንድ ሚሊዮን 980 ሺ 654 ካሬ ሜትር መሬት ላይ ወረራ እንደተፈጸመ መለየቱን አስታውሰው፤ ከዚህ ውስጥ 19 ሺ 522 ቦታዎች ወይም አንድ ሚሊዮን 662 ሺ 349 ካሬ ሜትር መሬት ላይ እርምጃ በመውሰድ የመንግሥትን ሀብት ማዳን መቻሉን አመልክተዋል።
ባለስልጣኑ በከተማዋ የሚስተዋሉ ሕገወጥ ድርጊቶችን ለመከላከልና ለማስወገድ በርካታ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝና ከሐምሌ 2013 ዓ.ም ጀምሮ ባሉት አሥራ አንድ ወራት ውስጥም የመሬት ወረራ፣ ሕገወጥ ግንባታን መከላከል፣ ሕገወጥ የጎዳና ላይ ንግድን መከላከል፣ አዋኪ ድርጊቶችን ማስወገድን ጨምሮ በሌሎችም ሕገወጥ ተግባራት የተሳተፉ የመለየት ሥራ መሰራቱን አስታውቀዋል።
በትግበራውም 294 ሺ 839 ደንብ ተላላፊዎችን መለየት መቻሉን እና ከተለዩት ውስጥም በአሥራ አንድ ወራት ውስጥ 292 ሺ 828 ደንብ ተላላፊዎች ላይ እርምጃ እንደተወሰደ አቶ ደሳለኝ ገልጸዋል።
ከሕገወጥ ግንባታ ጋር በተያያዘ 8 ሺ 633 ቦታዎች ተለይተው 8 ሺ 465 ቦታዎች ላይ እርምጃ ተወስዷል ያሉት ምክትል ሥራ አስኪያጁ፤ በተጨማሪም 58 ሺ 385 ሕገወጥ የጎዳና ላይ ነጋዴዎችን በመለየት እስካሁን ድረስ 57 ሺ 327 ሕገወጥ ነጋዴዎች ላይ ሕጋዊ እርምጃ መወሰዱን ጠቁመዋል። በተወሰደው እርምጃም የገንዘብ ቅጣት እና ንብረታቸው እንዲወረስ መደረጉን አመልክተዋል።
ሺሻ ማስጨስና ጫት ማስቃምን የመሳሰሉ አዋኪ ድርጊቶችን ለመከላከል በተደረገው እንቅስቃሴ ሁለት ሺ 858 ቦታዎች ተለይተው 28 ሺህ 377 ቦታዎች ላይ የማስተካከያ እርምጃ መወሰዱን ገልጸው፤ አግባብነት የሌለው የደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ፣ ሕገወጥ የእንስሳት ዝውውርና ሕገወጥ ማስታወቂያዎችን ለመከላከልም ሰፋፊ ሥራ መሠራቱን ምክትል ሥራ አስኪያጁ አስታውቀዋል።
ባለስልጣኑ እርምጃ ከመውሰድ ባለፈም ሕገወጥ ተግባራትን በተመለከተ ሰፋፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን ሠርቷል፣ ለተገኘው አበረታች ውጤትም የሕዝቡ ተሳትፎ የማይተካ ሚና ተጫውቷል፣ በቀጣይነትም ሕዝቡ የሚያስተውለውን ማንኛውንም አይነት ሕገወጥ ተግባር በባለስልጣኑ ነጻ የስልክ መስመር 9995 በመደወል ማሳወቅ እንደሚቻል አስረድተዋል።
ፋንታነሽ ክንዴ
አዲስ ዘመን ሰኔ 13 /2014