
• በ22 መሰረታዊ ማህበራት ለተደራጁ 88 ሺ አርሶ አደሮች የገበያ ትስስር ተፈጥሯል
አዲስ አበባ፡- በይርጋለም የተቀናጀ ኢንዱስትሪ ፓርክ በአቮካዶ ምርት የተሰማሩ ሁለት ፋብሪካዎች ባለፉት 10 ወራት ብቻ ወደ ውጭ ከላኩት ምርት ሁለት ሚሊዮን 405 ሺ የአሜሪካ ዶላር ገቢ መገኘቱን የሲዳማ ኢንዱስትሪያል ፓርክ ልማት ኮርፖሬሽን አስታወቀ፡፡
ሁለቱ የአቮካዶ ፋብሪካዎች በ22 መሰረታዊ ህብረት ለተደራጁ 88 ሺ አርሶ አደሮች የገበያ ትስስር ፈጥረዋል፡፡
በሲዳማ ኢንዱስትሪያል ፓርክ ልማት ኮርፖሬሽን የቢዝነስ ልማትና ኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ጴጥሮስ ማርቆስ በተለይም ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በፓርኩ በአጠቃላይ 22 ባለሃብቶች ከኮርፖሬሽኑ ጋር ተዋውለው ምርት ለማምረት ዝግጅት ላይ ናቸው።
ከ22 ባለሃብቶች መካከል ሁለት የአቮካዶ፣ የማርና የወተት ፋብሪካዎች እንዲሁም ዘይት ማምረቻ ፋብሪካ በማምረት ላይ ይገኛሉ። ወደ ውጭ ገበያ የሚያቀርቡት ሁለቱ ፋብሪካዎች ድፍድፉን ወደ ውጭ ገበያ እያቀረቡ ነው።
እንደ አቶ ጴጥሮስ ገለጻ፤ ዋይቢኤም የተባለው የአቮካዶ ፋብሪካ ብቻ ሥራ የጀመረው በቅርብ ጊዜ ቢሆንም 168 ሺ ያላለቀለት የአቮካዶ ድፍድፍ ዘይት ወደ ውጭ በመላክ 845 ሺ የአሜሪካ ዶላር ገቢ አስገኝቷል።
ፋብሪካው ብቻውን በዚህ ዓመት 280 ሺ ሊትር የአቮካዶ ምርት ወደ ውጭ ልኮ አንድ ሚሊዮን 560 ሺ የአሜሪካ ዶላር ገቢ በአስር ወር ውስጥ አስገኝቷል። ሁለቱ የአቮካዶ ፋብሪካዎች ባለፉት 10 ወራት ብቻ ሁለት ሚሊዮን 405 ሺ የአሜሪካ ዶላር ገቢ አስገኝተዋል።
እስካሁን በ40 ዙር አቮካዶን ወደ ውጭ መላክ የተቻለ ሲሆን ፋብሪካዎቹ ሥራ ከጀመሩ ጀምሮ እስካሁን የተገኘው ገቢ 5 ሚሊዮን 518 ሺ 500 የአሜሪካ ዶላር ገቢ ተገኝቷል ብለዋል።
የአቮካዶ ፋብሪካዎቹ በአስር ወር ውስጥ 3 ሚሊዮን 590 ሺ 722 ኪሎግራም ጥሬ አቮካዶ ከአርሶ አደሮች ተረክበው ጥቅም ላይ መዋላቸውንም ገልጸዋል።
የምርት ትስስር ከመፍጠር አኳያ ሁለቱ የአቮካዶ ፋብሪካዎች ምርት ሲያገኙ የማምረት አቅማቸው ሙሉ ይሆናል። በዚህም 22 መሰረታዊ የህብረት ሥራ ማህበራት በሥራቸው ለተደራጁ 88 ሺ አርሶ አደሮች የገበያ ተስስር ፈጥረዋል፤ ለ250 ሠራተኞች ደግሞ ቋሚ የሥራ ዕድል መፍጠራቸውን አቶ ጴጥሮስ ተናግረዋል።
ለግብርና ኢንዱስትሪ ትልቁ ሀብት ግብዓት ነው። በኢንዱስትሪው ውስጥ ወደ ምርት ከገቡ ፋብሪካዎች መካከል በወተትና ማር ማቀነባበሪያ ዘርፍ የተሰማሩት በሙሉ አቅማቸው እያመረቱ አይደለም። ለዚህም የግብዓት አቅርቦት ችግር ትልቅ እንቅፋት ፈጥሯል። በተጨማሪም ሌሎች ፋብሪካዎች ወደ ሥራ እንዳይገቡ የግብዓት አቅርቦት እጥረት፣ የመንግሥት አገልግሎት ውስንነት ፋብሪካዎቹ ወደ ምርት እንዳይሸጋገሩ ማነቆ ሆኗል ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ በፓይለት ከተመረጡ አራት የኢንዱስትሪ ፓርኮች መካከል የይርጋለም የተቀናጀ የኢንዱስትሪ ፓርክ አንዱ ነው። ፓርኩ በ294 ነጥብ 5 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈም ነው።
ሞገስ ተስፋ
አዲስ ዘመን ሰኔ 13 /2014