ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብፅ እኤአ 1957 የተጀመረውን የአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታ የጠነሰሱና የጀመሩ አገራት በመሆናቸው ታሪክ ይዘክራቸዋል። እኤአ 1956 የኢትዮጵያ የግብፅና የሱዳን ባለሥልጣናት ከደቡብ አፍሪካ ተወካይ ጋር በመሆን የአፍሪካ አህጉራዊ ውድድርን ለመመስረት በፖርቹጋል በነበረው የፊፋ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ተገኙ። የመጀመሪያው የአፍሪካ ዋንጫም እኤአ 1957 በሱዳን መዲና ካርቱም እውን ሲሆን የደቡብ አፍሪካ ፌዴሬሽን ከተለያዩ ዘሮች የተውጣጣ ቡድን ለመላክ ፈቃደኛ ባለመሆኑ ከውድድሩ ተገለለ።
ሶስቱ አገራት ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ እየተፈራረቁ ሶስቱን የመጀመሪያ የአፍሪካ ዋንጫዎች በማንሳትም የአህጉሪቱ ሃያል ተፎካካሪ ሆኑ። ይሁን እንጂ የሶስቱ አገራት ሃያልነትና ብርቱ ተፎካካሪነት ዘመናትን የሚሻገር አልሆነም። ሁለቱ ምስራቅ አፍሪካውያን ጎረቤታሞች እንደ ታሪካቸው መራመድ ተስኗቸው ከሰሜን አፍሪካዋ አገር በብዙ ወደ ኋላ ቀሩ። ይህም የእግር ኳስ ደረጃ ልዩነት ዘመናትን ተሻገረ፡፡
ሌላው ቀርቶ ሶስቱ የአፍሪካ ዋንጫ ጠንሳሾች በአንድ የአፍሪካ ዋንጫ መድረክ ላይ ለመሳተፍ ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ ፈጀባቸው። ይህም ከ52 ዓመታት በኋላ ሦስቱ አገራት ለመጀመሪያ ጊዜ በአንድ አፍሪካ ዋንጫ መሳተፍ የቻሉበት ያለፈው የካሜሩን አፍሪካ ዋንጫን ታሪካዊ አደረገው።
በአፍሪካ ዋንጫ ቀዳሚ ስፍራ ያላቸው ሦስቱ አገራት ከፍተኛ ግምት የሚሰጠውን ዋንጫ አሸናፊ ቢሆኑም ግብፅ ሰባት ጊዜ በማሸነፍ ከየትኛውም አገር በላይ ክብረወሰንን ጨብጣለች። ሁለቱ የምስራቅ አፍሪካ አገራት ግን ዳግም ለዋንጫ ክብር መድረስ ቀርቶ ከሰሜን አፍሪካዋ አቻቸው ጋር ያላቸውን የእግር ኳስ ደረጃ ሰፊ ልዩነት ማጥበብ ሳይችሉ ዘመናት ነጉደዋል።
እግር ኳስ በምሥራቅ አፍሪካ አገራቱ ኢትዮጵያና ሱዳን ከፍተኛ ተወዳጅነት ያለውና ጥሩ ተሰጥኦ ያላቸው ተጫዋቾች መፍለቂያ እንደሆኑ ቢታመንም ከነበራቸው ከ1960ዎቹና 70ዎቹ ታላቅነት በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ኋላ ቀርተዋል። ከምሥራቅ አፍሪካ አገራት በብቸኝነት ዋንጫውን ያነሱት ኢትዮጵያና ሱዳን ተመሳሳይ የእግር ኳስ ታሪክን መጋራታቸው ለዚህ ልዩነት ምክንያት ይሆን?።
ሁለቱ አገራት በአፍሪካ ዋንጫ ቀደምት ስፍራ ቢኖራቸውም ሁለቱም ብቸኛ ድሎቻቸውን ያሳኩት እራሳቸው አዘጋጅ በነበሩበት ውድድር ነበር። ኢትዮጵያ ለ31 ዓመታት ያህል ለአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያው ማለፍ አቅቷት እኤአ 2013 ነበር ወደ ውድድሩ መመለስ የቻለችው፤ በተመሳሳይ ሱዳንም ለ32 ዓመታት ያህል ከውድድሩ ርቃ እኤአ 2008 ነበር ተሳታፊ የሆነችው።
‹‹በእግር ኳሱ ዘርፍ ሱዳንና ኢትዮጵያን ወደ ኋላ በመመለስ ረገድ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ሚና አላቸው›› የሚሉት የሚቺጋን ስቴት ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰርና ‘አፍሪካን ሶከርስኬፕስ፡ ሀው ኤ ኮንቲነንት ቼንጅድ ዘ ወርልድ’ስ ጌም’ የተሰኘ መጽሐፍ ደራሲ ፒተር አሌጊ ይናገራሉ። በሁለቱም አገራት የተራዘሙ የእርስ በርስ ጦርነቶች፣ የፖለቲካ አለመረጋጋት፣ የኢኮኖሚ ውድቀትና ተፈጥሯዊ አደጋዎች ተደማምረው በአገራቱ የእግር ኳስ እድገትና ሂደት ላይ የራሳቸውን ተጽዕኖ አሳድረዋል። የኢትዮጵያ እኤአ 1962 በተካሄደው በሦተኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ያኔ አረብ ሪፐብሊክ ትባል የነበረችውን ግብፅ 4 ለ 2 በመርታት ቻምፒዮን በመሆን ድሏን አጣጣመች።
ይህ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ወርቃማ ታሪክ ጥር 13/ 1954 ዓ.ም ሲፃፍ ግቦቹን ከመረብ ያሳረፉት ታሪካዊው ተጫዋቾች መንግሥቱ ወርቁ (ሁለት ግብ)፣ግርማ ተክሌና ኢታሎ ቫሳሎ አንዳንድ ግቦችን በስማቸው አስመዝግበዋል፡፡ ከዚያ በኋላ ግን ኢትዮጵያ ፈርኦኖቹ ላይ ሁለትና ከዚያ በላይ ግብ አስቆጥራ ለማሸነፍ ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ ቆይታለች። ይህን ታሪክ ከስልሳ ዓመት በኋላ ለመቀልበስም ባለፈው እሁድ ከፈርኦኖች ጋር ያገናኛትን የ2023 የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ ጠብቃለች፡፡ ዳዋ ሆጤሳና ሽመልስ በቀለም የስልሳ ዓመቱን የታሪክ ግንብ የናዱ ግቦችን በማስቆጠር ለምስራቅ አፍሪካ እግር ኳስ ትንሳዔ በር ሊከፍት የሚችል ታሪክ መስራት ቻሉ፡፡
ሱዳን እኤአ በ1970 እንደ አሊ ጋጋሪ፣ ጃክሳ በመባል የሚታወቀውና ናስር ኤዲንን ባካተተው ወርቃማ በሚባለው የእግር ኳስ ትውልዷ ጋናን 1 ለ 0 በመርታት ብቸኛውን ዋንጫ አሸንፋለች። ሱዳን በእግር ኳስ ታሪኳ ከኢትዮጵያ በተለየ መልኩ በተመሳሳይ ዓመት በሜክሲኮ በተካሄደው የዓለም ዋንጫ ላይ ለመሳተፍ ተቃርባም ነበር። ከሁለት ዓመት በኋላም እኤአ 1972 ሙኒክ ኦሊምፒክ ተሳትፋ በአንፃራዊነት የተሻለ የእግር ኳስ ታሪክ ጽፋለች። ነገርግን በቀጣዮቹ ዓመታት ‹‹ዘ ሴክሬታሪ በርድስ›› የተሰኘው ቡድኗ ውድቀት ገጠመው። ዛሬም ድረስ ከወደቀበት ለመነሳት ዳዴ እያለም ነው።
‹‹በወቅቱ አገሪቱ ውስጥ የነበረው መረጋጋት ለእግር ኳስ ማደግ ከፍተኛ ሚና ተጫውቶ ነበር። ነገር ግን የፖለቲካ አለመረጋጋት እና የምጣኔ ሀብት ችግሮች አገሪቱ በሌሎች ጉዳይ ላይ እንድታተኩር አድርጓታል›› በማለት የወርቃማው ትውልድ ቡድን አባል የነበረው በአሁኑ ወቅት የ77 ዓመት እድሜ አዛውንቱ ጃክሳ በቅርቡ ለቢቢሲ ተናግሯል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ሰኔ 12/2014