የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱት ጥያቄዎች የሰጡትን ማብራሪያና ምላሽ ክፍል ሁለት ትናንት ማቅረባችን ይታወሳል። በዛሬው በክፍል ሶስት እትማችን ከሰላምና ድርድር፣ ከጸጥታ ተቋማት ዝግጅት፣ ከመፈናቀል፣ ህግ ከማስከበር፣ በመብት ተሞጋቾችና በማህበራዊ ሚዲያ ዙሪያ ለተነሱ ጥያቄዎች ጠቅላይ የሰጡትን ምላሽና ማብራሪያ ይዘን ቀርበናል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ምላሽ፦
በመጀመሪያ ግጭቱን፣ ጦርነቱንና የሰላም ሂደቱን በሚመለከት ለተነሳው ጉዳይ የተከበረው ምክር ቤት እንደሚያስታውሰውና እንደሚገነዘበው ከጅምሩ ጀምሮ የእኛ መሻትና ፍላጎት ግጭት የሚባል በአገር ውስጥም በአካባቢው አገራትም እንዳይኖር ማድረግ ነው:: ለምሳሌ ከኤርትራ ጋር የነበረውን ግጭት በሰላም እንፍታ ብለን ኤርትራ ድረስ የሄድንበት ዋነኛው ዓላማ በኤርትራና በኢትዮጵያ መካከል ሰላም ቢኖር የሁለቱም አገራት ህዝቦች ይጠቀማሉ ከሚል መነሻ ነው:: ይህ በቀጥታ ኢትዮጵያን የሚመለከት ጉዳይ ነው:: ነገር ግን ሶማሊያና ኬንያ ሲጋጩ ግጭት ተገቢ አይደለም፤ አንድ መሆን አለባችሁ ብለን የሶማሊያን መሪ ናይሮቢ ወስደን መሪዎቹን በማገናኘት ችግሩን ለመፍታት የሞከርንበት ምክንያት ቀጥታ ባይመለከተንም ግጭት ስለሚጎዳን ነው::
የደቡብ ሱዳን ምክትል ፕሬዚዳንቱ ከአገር ወጥተው ደቡብ አፍሪካ በነበሩበት ጊዜ ወደአገር እንዲመለሱና ድርድር እንዲጀምር ጥረት ያደረግነው የደቡብ ሱዳን ሰላም ለእኛ ስለሚጠቅመን ነው:: ሱዳን ከመፈንቅለ መንግስቱ በኋላ የገጠማት ችግር ሽግግሩ ሰላማዊ እንዲሆን ከፍተኛ ሚና የተጫወተችው ኢትዮጵያ ናት:: በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በአካባቢውም ሰላም እንዲኖር እንፈልጋለን:: የቀጣናው ሰላም ላይም ተሳትፎ አለን:: አሁን መግለፅ ማለት ባልፈልግም ከቀጣናችንም ባሻገር ባሉ በርካታ የሰላም ድርድሮች ውስጥም ተሳትፈናል::
ሰላም በጣም ወሳኝ ነው፤ ሰላም ያስፈልጋል:: ለሰላም የሚከፈል መስዋዕትነት ካለ ለመክፈል ዝግጁ መሆን አለብን:: ለሰላም የሚሰጥ ማንኛውም ነገር ካለ ማድረግ ተገቢ ነው:: ሰላም ሁሌም የሚደናቀፈው በግጭት ነው:: ሰላም የሚወዱ ሰዎች ግጭት እንዳይፈጠር ይጥራሉ፤ ግጭት ሲፈጠር ደግሞ እንዲያጥር ይሰራሉ:: መልሰው ሰላም እንዲሰፍን ይታትራሉ::
እኛን በሰላም መፈለግ ጉዳይ ጥያቄ መጠየቅ የሚከብድ ይመስለኛል:: ምክንያም በሰላም ጉዳይ ከቤተክርስቲያን እስከ አለምአቀፍ ደረጃ እውቅና አግኝተናል:: ሰላም ፈላጊ መሆናችንን አለም ያውቀዋል:: የዛሬ ሁለት አመት መጪው መስከረም ዘመን መለወጫ ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ላይ የትግራይ ህዝብ የጥይት ድምጽ ይበቃዋል፤ እንኳን ውጊያ የጥይት ድምጽ አያስፈልገውም ብዬ ሁለት ወር ሳይሞላው ነው ወደ ውጊያ የገባነው::
እኛ ከማንም ጋር ውጊያ አንፈልግም:: ትናንትም አንፈልግም፤ ዛሬም አንፈልግም፤ ነገም አንፈልግም:: እኛ የምንሳተፍበትም ብቻ ሳይሆን የማንሳተፍበትም አንፈልግም፤ የዩክሬንና የራሽያ ውጊያም አንፈልግም:: እኛ ውጊያ ሳይሆን ሰላም ነው የምንፈልገው:: ሰላም ትርፋማ ያደርጋል:: ሕወሓት ይህን ውጊያ ከመጀመሩ በፊት ስፖንሰር እያደረገ በየቦታው የሚፈጠረው መፈናቀል፣ በየቦታው ያለው ግጭት በገንዘብ ደጋፊውና አሰልጣኙ ማን እንደነበር ይታወቃል:: ልክ ግጭቱን ከፈጠሩ በኋላ በሚዲያዎቻቸው በርካታ የመጠራጠር ስሜት እንዲፈጠር ይሰሩ ነበር::
መከላከያ እየገነቡ፤ መከላከያን ከውስጥ እያፈረሱ ነበር፤ በየቦታው በሚፈጠረውን ግጭት በመከላከል ስንባዝን በመዘጋጀት ጊዜውን ለመጠቀም ሞክረዋል:: አሁን ሸኔ የሚባል ከሪፎርም በፊት አራት ሺ፣ አምስት ሺ ሀይል የሌለው፤ በየወሩ አንድ ሺ፣ ሁለት ሺ እየተማረከ እየተገደለ የሚፈለፈለው ከየት ነው? ምንጩ ከየት ነው? ትንሽ ከመንደር ንግግር ወጣ ብሎ ማየት ያስፈልጋል:: እናም የግጭቱ ዋንኛ መንስኤ ሕወሓት የፖለቲካ ሽንፈቱን እየዋለ እያደር መቀበል በመቸገሩ ነው :: እኛ መጀመ እንደምታውቁት እስክሪፕቶ እና ሀሳብ ብቻ ነው ያለን:: ጦሩም ታንኩም ብሩም በእነርሱ እጅ ነበር::
ካሸነፍን በኋላ ያንን ሽንፈት መቀበል ስላልቻለ፤ ሽንፈቴን በጉልበት ላሳካው እችላለሁ:: አንድም እያበጣበጥኳቸው ካልሆነ መጥቼ ነው ያሉት:: ይሄን መንግስት በአጭር ጊዜ እናፈርሰዋለን ብለው ሲናገሩ ነበር:: መንግስት እጥላለሁ፤ አገር አፈርሳለሁ፤ ህዝብ አናክሳለሁ፤ ይህ እንዲሳካ ሲኦልም እገባለሁ አሉ:: ተው አያዋጣም እያልን ነበር:: እየተዋጋን እንኳን ሁለት ሶስት ቀን ይሄ አያዋጣምና እጃችሁ ስጡ፤ ይቅር እያልን ነበር::
መጀመሪያ ለምን ተዋጋችሁ የሚል ሰው ካለ፤ እኛ ተከላከልን እንጂ አልተዋጋንም:: ታንካችንን ጀነራላችንን፣ ወታደራችን በተኛበት በገዛ ቤተሰቡ ታፍኖ በሺ የሚቆጠር ሰው እንዲሁም ንብረት ስለተያዘብን ልንከላከል ነው የተንቀሳቀስነው፤ ያንን የተያዘብንን ሰውና ሀብታችንን አስመለስን:: እንዳንወጣ ደግሞ ህዝቡ ተቸገርኩ አለ:: ከዚያ በፊት ታስታውሱ ከሆነ መውጣት እናስብ ነበር:: ሌላ የምንሰጋባቸው አካባቢዎች ስለነበሩ:: አትወጡም የተባልነው በሕወሓት ነው:: ሰው እያስተኙ አትወጡም አሉን:: በሌላ በኩል እንዳንወጣ ደግሞ ውሀ፣ መብራት፣ መንገድ እንዲሁም የጤና ችግር አለ ስንባል ህዝባችን ነው በሚሊዮን በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ መድበን ስንሰራ ነበር:: እኛ ልማቱን ስንሰራ እነርሱ ዝግጅት ያደርጉ ነበር::
የዓለም ሚዲያ ደግሞ ዘመቻ ጎን ለጎን ይከፍትብናል፤ ስለዚህም የእኛ መኖር ካልተመቻቸው ሲፈልጉን እንገናኛለን በሚል እሳቤ ለመውጣት ስንሞክር ደግሞ ጊዜው አሁን ነው ብለው በሰልፍ የምታውቁትን አይነት ጦርነት አካሄዱ:: ያኔም ተከላክለን ወደክልል ከመለስናቸው በኋላ ከዚህ በኋላ አንቀጥልም፤ ብንቀጥል ረሀብ፣ ስደት እንዲሁም መፈናቀል ይመጣና ተጨማሪ ጣጣ ነው ብለን ተውነው:: በሂደት ውስጥ እኛ የተከተልነው መንገድ ኢትዮጵያ አንድም ቀን ቢሆን ሰላም እንድታገኝ ነው::
ይሄ ብቻ አይደለም፤ ሪፎርም ከመጣ በኋላ ኤርትራ ያሉ ግንቦት 7፣ ኦነግ፣ ኢህአፓና ሌሎች ስማቸው ብዙ የሆኑ ፓርቲዎችን ኑ ግቡ በጋራ አገር እናልማ አላልንም እንዴ? በምርጫ ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ የኢትዮጵያ ህዝብ ተሰልፎ ከመረጠን በኋላ ግዴለም ብቻችንማ አንመራም፤ በፌዴራልም በክልልም የሚፎካከሩ ፓርቲዎች ምርጫ ከተወዳደሩ ይግቡ ብለን ፓርቲዎች የካቢኔ አባላት ሆነዋል:: ሶስት የካቢኔ አባላት የሚፎካከሩ ፓርቲዎች ናቸው:: በዓለም ላይ አሸንፎ መቀመጫ የሚጋራ አንድም ፓርቲ አታገኙም:: ከተሸነፈ ይጋራል:: ካልተሸነፈ ግን አይጋራም:: ይቅር፤ ባህል ይቀየር፤ አብረን እንስራ ነው አላማው::
ይህ በመረታታትና መጠናከር አለበት:: አንዳንዶቹ ግጭት በገጠመን ወቅት እዚህ ፓርላማ ያሉ አባላት ጭምር ከብልፅግና አባል ባልተለየ ሁኔታ ኢትዮጵያን ሊከላከሉ ተሰልፈዋል:: ስለዚህ ፓርቲ የሚለው ጉዳይ ሁልጊዜ የማይሰራ አንዳንዴ በትብብር ልንሰራ የምንችልባቸው ጉዳዮች መኖራቸውን የሚያመላክት ነው። ለዚህም ስልጣን ብንጋራ ችግር የለውም:: አብረን አገር ብናቀና፤ ብናለማ ችግር የለውም:: ምንድነው የነበረው ችግር ያላችሁኝ እደሆን ጽንፈኝነትና ጥላቻ ነው:: ብሄር መጥላት፣ ሰው መጥላት ነው:: ጥላቻ መርዝ ነው::
ይሄውላችሁ ባለፉት ሀምሳ አመታት ዩናትድ አረብ ኢምሬትስ በተለምዶ ዱባይ፣ አቡዳቢ የሚባለው አገር ሼህ ዛይድ ጀምረውት አሁን ሼህ መሃመድ የሚመሩት አገር በሃምሳ ዓመት ውስጥ ዱባይን ከአፈር ወደ ወርቅነት ቀየሯት:: ከድንኳን ታይቶ ወደማይጠገቡ ህንጻዎች ቀየሩ:: በልቶ መጥገብ ሳይሆን እንደኛ አይነቱን መቶ ሚሊዮን ቁጥር ያለውን ህዝብም የሚያበላ ሃብት ፈጠሩ፤ ይህ የሆነው በ50 ዓመት ውስጥ ነው:: ከምንም ተነስተው እጅግ አስደማሚ ውብ በዓለም ተመራጭ አገር ፈጠሩ:: የሚያደምጥ፣ የሚከተል፣ የሚያግዝ፣ ልማት የማያደናቅፍ ህዝብና የሚሰሩ አመራሮች ተባብረው አገራቸውን ቀየሩ::
ይሄን ቁጥር እኛ ጋር አምጡት ሕወሓት ሲቀነስ ሲደመር 48፣ 47፣ 49 ዓመት ታግሏል:: ቢያንስ ትግራይን ከ81 ጀምሮ እስካሁን እያስተዳደረ ነው:: 30 ምናምን ዓመት ነው:: ባለፉት 50 ዓመታት ወይም 48 ዓመታት የሕወሓት ትግል የትግራይ ህዝብ ምን አተረፈ? ካላችሁ ጥላቻ፣ ጦርነት እና ልመና ነው:: የዛሬ 50 ዓመትም ችግር አሁንም ችግር፤ የዛሬ 50 ዓመት መሰረተ ልማት የለም፤ አሁንም የለም:: የዛሬ 50 ዓመትም ስደት አለ፤ አሁንም ስደት አለ:: አንዳንዶች በ50 ዓመት የሌለ አገር ያደርጋሉ:: እነዚህ በቁጥርም በስፋትም ከትግራይ የሚያንሱ ናቸው::
አንዳንዶች ደግሞ እነሱ ለ50 ዓመት ኮብራ ይቀያይራሉ፤ ሰው እዛው ነው:: በሕወሓት አጠቃላይ ትግል አንድ ሺ፣ ሁለት ሺ፣ አምስት ሺ፣ አስር ሺ የዛ አካባቢ ሰዎች ኮብራ ነድተው ሊሆን ይችላል፤ የትግራይ ህዝብ ግን ምንም አላገኘም:: ይህን እንኳን ቆሞ ለማሰብና የኛ መፈጠር ምንድን ነው? ሕወሓት ከናካቴው ባይፈጠር የትግራይ ህዝብ ምን ያጣ ነበር? ብሎ እንኳን ለማሰብ ዝግጁ አይደለም:: አንዳንዶች አሁን ፓርቲ ስንሆን በእኛ መፈጠር በህዝባችን ላይ ምን የተሻለ ነገር እንጨምራለን የሚለውን አብረን ካላየን በስተቀረ መፈጠርና ዕድሜ መቁጠር ብቻ ዋጋ የለውም::
ጦርነቱ የእኛ አይደለም፤ እየለመንን ነው አትችሉም አይችሉም ተብለን የገባንበት። ብዙዎች ልካችንን ስለማያውቁ በልካቸው እያሰቡ የሞኩራት ጉዳይ ነው፤ ያኔም ዛሬም ያለው:: የእኛ መሻት በውጊያ የተገኘውን ድል በሰላም መድገም ነው:: በውጊያ አትፈርስም ብለን አገር አስቀጥለናል:: ኢትዮጵያ በልማት ጎዳና ላይ ነው ያለችው ጥያቄ የለውም:: ብዙ ፈተናዎች መቋቋም የሚችል ተቋም እየገነባች ነው ጥያቄ የለውም፤ አይታችሁታል::
ለልጆቻችን ቁርሾ አንተው፤ ጥላቻ አንተው:: እኛ ዋጥ አድርገን ስሜታችንን ወደሰላም እንሂድ:: የምንፈልገው ይህንን ነው:: ከሕወሓትም ከማንም ሰው ሰላም ፈላጊ ከሆነ ሰው ሁሉ ጋር ሰላም ነው የምንፈልገው:: ለምን ከተባለ ከእያንዳንዷ የሰላም ቀን ትርፍ ስለምናገኝ ነው:: ጥይት ይተኮሳል፤ ዶላር ነው፤ ሰው ይሞታል፤ ወጣት ነው:: ሽማግሌ አይደለም የሚሞተው፤ ወጣት ነው፤ ሊሰራ የሚችል ሰው ነው የሚሞተው:: በዛም ሞተ በዚህም ሞተ ያው ነው:: ማስቀረት የሚቻል ከሆነ ለሰላም መቆም ችግር የለውም::
ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ናይጄሪያ ተገናኙ፤ ሶማሊያ ተገናኙ፤ አውስትራሊያ ተገናኙ፤ ሶሪያ ተገናኙ፤ የሚባል ተረት ግን ተረት ነው:: አጋጣሚ ናይጄሪያ በነበርኩበት ጊዜ እኔ ከናይጄሪያ መንግስት ጋር በነበረን ንግግር በጣም በርካታ ጉዳይ ነበረን:: እንዳጋጣሚ ሆኖ ለአንዲት ሰከንድ ሕወሓት የሚል ቃል አልተነሳም፤ እነሱም ትኩረታቸው አልነበረም:: እንደውም አልፎ አልፎ እንደምንጠየቀው የሰሜን ጉዳይ ምን ሆነ አላሉንም፤ ሌሎች ጉዳዮች ላይ ነው ጊዜ ያባከነው:: ግን ናይጄሪያ፣ ሶሪያ ሶማሊያ እየተባለ ይነገራል፤ እሱ ስህተት ነው::
ክቡር ዶክተር ጫኔ ላነሱት ጉዳይ ፓርላማው ብቻም ሳይሆን የኢትዮጵያ ህዝብም ንግግር ሰላም የሚፈልግ ቢሆንም የማውቀው መብት አለው:: እና ብልጽግና ተሰብስቦ ከእንግዲህ በኋላ ያለውን ጉዟችንን እንዴት ነው የምንፈታው ብሎ አሁን ወጥተው የሚያሙትም ጭምር ባሉበት ስብሰባ ላይ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አቋቁሟል:: ይህ ኮሚቴ ክቡር አቶ ደመቀ መኮንን የሚመሩት ኮሚቴ ነው:: ሰላምን በሚመለከት ኢትዮጵያ ምን ምን ትፈልጋለች? ዝም ብሎ ድርድር አይካሄድም ብዙ ስራ አለ:: ምን ሲሳካ ነው የምንነጋገረው እንዴት ነው የምንነጋገረው የሚለውን ጉዳይ የሚያጠና ኮሚቴ ተቋቁሞ፤ ኮሚቴው ሲያጠና ቆይቷል::
እስካሁን ለስራ አስፈጻሚ ሪፖርት አላቀረበም፤ ምናልባት በሚቀጥሉት አስር አስራ አምስት ቀናት እንጠብቃለን:: ኮሚቴው ሪፖርት ይዞ ሲቀርብ አንድ፣ ሁለት፣ ሶስት፣ አራት ሲሟሉልኝ ንግግር ማድረግ እችላለሁ፤ በዚህ በኩል ይሄ ይሄ እንዲሟላ እፈልጋለሁ፤ እኔ ደግሞ ይሄን አደርጋለሁ፤ ለሰላም ስል ይሄን ዋጋ እከፍላለሁ የሚል ሃሳብ ሲመጣ ለህዝባችን በግልጽ እናውጃለን:: የሚደራደረውም ኮሚቴ ይሄው ኮሚቴ ነው፤ እኔ ናይጄሪያ ሄጄ ሶማሊያ ሄጄ የምገናኝበት ምንም ምክንያት የለም:: አጥንቶ አውቆ የሚሰራ ኮሚቴ ተመድቧል::
ብዙ ጊዜ እኛ ስለ ስንዴ ስንናገር ሰው አያምንም፤ ሰው የሚያምነው ዶክተር ሲናገሩ አኪና ዲሲና ሲናገሩ ነው:: ኢትዮጵያዊ እንደዚህ ነው፤ ምን እናደርጋለን:: በትዊተር ሲነገር ነው እንጂ የሚታመነው እኛ ስንል አይታመንም:: የ‹‹ኢንትሪክ፣ የኮንስፓይረንሲ›› ፖለቲካ ልምምድ ስላለን ሁሉም በዛ ይታያል:: እኛ ውጊያ አልደበቅንም፤ ውጊያ ተነስቷል፤ አገር ተደፍሯል፤ በቃ እንዋጋለን ብለን ለህዝባችን ነግረን ውጊያ የገባን ሰዎች ነን:: ታድያ አሁን ሰላም ለማምጣት ምን አስደበቀን:: ሰላም የሚደበቅ ነገር አይደለም:: ምክንያቱም ውጊያውንም አልደበቅንም:: እናም ዝም ብሎ መሰቃየት አያስፈልግም:: ጊዜው ሲደርስ እና ንግግር ሲጀመር እንናገራለን::
አሉባልታው፣ ስሞታው፣ ሽኩቻው ብዙ ነው:: ያ እንደተጠበቀ ሆኖ ግን አማራ ሳያውቅ የተባለው ስህተት ነው:: ሕወሓት የአማራ ጠላት ሳይሆን የኢትዮጵያ ጠላት ነው:: የተዋጋውም ኢትዮጵያ ነው፤ የሞተውም ኢትዮጵያ ነው:: ይሄ ነገር ሰንጥቆ ለራስ መውሰድ ትክክል አይደለም:: አማራ የሚደራደር ከሆነ፤ አማራ ብቻ እዛ ይዋጋ:: እዛ እየሞተ ያለው ኢትዮጵያዊ ነው፤ የሚደራደረውም ኢትዮጵያዊ ነው:: ጠላቱም የኢትዮጵያ ነው፤ ሕወሓት በአማራ ብቻ የሚቆም አይደለም:: አማራን ቆርጥሞ፣ ኦሮሞን ቆርጥሞ የሚቆም አይደለም:: ከጨረሰን ወደ ሌላ ጎረቤት አገር ይቀጥላል:: ለብቻ የተሰራ ስራ የለም፤ በጋራ እንሰራዋለን::
አጋጣሚ ሆኖ ኮሚቴውን የሚመሩት አቶ ደመቀ ናቸው:: ሌላ አማራ ፈልገን ካላመጣን በስተቀረ የአማራን ጥቅምና ሁኔታ ይገነዘባሉ:: አማራ ተወላጅ የሆኑም የአፋር ተወላጆችም ሶማሌዎችም በኮሚቴው ውስጥ ስላሉበት በጋራ እየሰሩ ነው:: እኛ የምናስበው የኢትዮጵያን ችግር፣ የኢትዮጵያ እዳ፣ የኢትዮጵያ ፍዳ ነው፤ ኢትዮጵያዊያን በጋራ እንቋቋመዋለን ብለን ነው የምናስበው:: እና ነገሩን ዝም ብሎ ወደታች ማውረድ ጥሩ አይደለም:: በነገራችን ላይ ስለፖለቲካ ስንናገር እዛ ሰራዊቱ ጋር የሚያመጣውን ችግር ማሰብም ጥሩ ነው:: እየሞተ ያለውን፣ በጸሃይ እየተቃጠለ ያለውን ሰው ምንም አያገባህም ካልነው አደገኛ ነው:: በኋላ ችግር ያስከትላልና በዛ አይን ማየት ጠቃሚ ይሆናል::
የኢትዮጵያ መንግስትም ሆነ የኢትዮጵያ ህዝብ ፍላጎት ግን አንድም ጥይት ኢትዮጵያ ውስጥ እንዳይተኮስ ነው:: ለጥይት የሚወጣው ዶላር ለመድሃኒት፣ ለግንባታ እንዲውል ማድረግ ነው:: ይህ የእኛም የህዝባችንም ፍላጎት ነው:: ማነው ጦርነትን ያለ ልክ የሚያስጮኸው? መዋጋት የማይችለው ነው:: ስንዋጋ የለም ስንመለስ ተዋጉ ይሉናል:: በየአገሩ ተቀምጦ ውጊያ ሰፈር ሳይደርስ ውጊያ ውጊያ የሚል አለ፤ ውጊያ እኛ አንወድም:: በጣም ነው የምንጠላው:: እኔ በ14ዓመቴ ነው ክላሽ የተሸከምኩትና አውቀዋለሁ፤ ስለዚህ አልፈልገውም:: ማየት አልፈልግም፤ ብዙ ሲበላ አይቻለሁ፤ ውጊያ ጓደኛ የሚበላ፣ ወንድም የሚበላ አደገኛ በሽታ ነው::
ውጊያ ሳይሆን የምፈልገው ልማት ነው:: ማነው ውጊያን የሚወደው ? ውጊያን የማያውቅ ብቻ ነው:: ሰላም እንፈልጋለን ማለታችን የተደበቀ ድርድር እናደርጋለን ማለታችን አይደለም:: የተደበቀ ድርድርም ፍሬ የለውም:: አሁን ተደራድረን ለምሳሌ መብራት ይገባላችኋል ብሎ መንግስት ቢወስን ሰሞኑን እንደሚወራው፤ መብራት ሲገባ አይታይም እንዴ? መብራት እኔ አላስገባ፤ መደበቅ እኮ አይቻልም:: ደብቆ ድርድር፣ ደብቆ ምናምን የሚባል ነገር ብዙ ቦታ የለውም:: ግን ለሰላም እስከሆነ ድረስ እናንተ በርቱ አይዟቹ ሞክሩ አቅማችሁ እስከቻለ ድረስ ሰላም አምጡ በርቱ ነው ማለት ያለባችሁ:: የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም አቅጣጫ መሆን ያለበት ወደ ሰላም ሂዱ፤ ኢኮኖሚ የለንም፤ ብዙ ደሃ አለን፤ የዋጋ ግሽበት አለ፤ የሚል ምክር ቢሆን ይበልጥ ጠቃሚ ይመስለኛል::
ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ የጸጥታ ተቋማት ዝግጅታቸው ምን ይመስላል የሚለው ተነስቷል፤ የኛ የጸጥታ ተቋም ለሕወሓት አይደለም የሚዘጋጀው:: የእኛ የጸጥታ ተቋም ሕወሓት የሚልከውም የሚያስበውም የሚመኘውም የኢትዮጵያን ህልውና እገዳደራለሁ ካለ ኢትዮጵያ የተባለች ድንቅና ታሪካዊ አገር አጽንቶ ለማስቀጠል ነው የሚዘጋጀው:: የሰፈር ዝግጅት ብቻ አናደርግም:: ይህማ ሞኛ ሞኝ ሃሳብ ነው፤ ጦር አዘጋጅተን ከሕወሓት ጋር በሰላም ቢያልቅ እናፈርሰዋለን ማለት ነው? ሕወሓትን የላከው አካል ሌላ ተላላኪ ይፈልጋል:: እና ዝግጅቱ ኢትዮጵያን ለማስቀጠል ነው::
እንዳያችሁት ደግሞ ጅማሮው ጥሩ ነው፤ ብዙ ስራ ይጠበቅብናል:: ምንም ጥያቄ የለውም፤ ገና ነው:: ቢያንስ ቢያንስ ግን አሁን ያለው ጦር ሕወሓት ካለበት ሁለት ሶስት እጥፍ በቁጥርም በቴክኖሎጂም በአቅምም ይሻላል:: ይሄ ጥርጣሬ የለውም፤ ይሄ በቂ ነው አይደለም ከተባለ በየቀኑ የሚወለድ እውቀትና ብቃት ስላለ አብረን ማደግ አለብን፤ መማር አለብን:: ኢትዮጵያ ትልቅ አገር ናት፣ ሃብታም አገር ናት፤ ታላቅ አገር ናት፤ ስመጥር አገር ናት :: ልጆቿ ስላልገባቸው ቢያረክሷትም በአፍሪካ ቁንጮ የሆነች አገር ናት፤ መቀጠል አለባት:: እሷን የሚያስቀጥል ተቋም ይገነባል:: ተቋም ሲባል ግን ዶክተር እንዳነሱት የፊዚካል (አካላዊ) ውጊያን የሚከላከል ብቻ አይደለም:: የቨርቹዋል ውጊያው ከፊዚካል ውጊያው እየበለጠ ነው::
ለምሳሌ ዘንድሮ በሳይበር ጥቃት በዓለም አቀፍ ደረጃ የደረሰው ጉዳት ከምንገምተው በላይ ነው:: 16 ቢሊዮን ዶላር በቀን በሳይበር ውጊያ /ዎርፌር/ ጥቃት ጉዳት ይደርስበታል:: በዓለም ላይ በአንድ ሰዓት ውስጥ 685 ሚሊዮን ዶላር ጥቃት ይደርሳል:: በዓለም ላይ በአንድ ደቂቃ 11 ሚሊዮን እንዲሁም በአንድ ሰኮንድ 190 ሺ ዶላር የሚያክል ጉዳት ይደርሳል:: ይህ ቀላል ነገር አይደለም:: እኛ ከተዋጋንበት ውጊያ ሀብት በብዙ እጥፍ ይበልጣል:: ኢትዮጵያ ላይ ባለፉት 9 ወራት ብቻ 5 ሺ 860 ገደማ የቨርቹዋል ጥቃት ተካሂዷል:: ስድስት ሺ ጥቃት ደርሶብናል ማለት ይቻላል:: በሚሊዮን ብር ያጣንበት አለ፤ በቢሊዮን ያዳንንበት አለ:: እርሳቸው እንዳነሱት፤ በዋናነት ፋይናንሻል ሴክተር፣ አይ.ሲ.ቲ፣ ኢንፍራስትራክቸር እና ሬኢንፎርስመንት ኤጀንሲስ፣ መንግስት ተቋማት እና ፕሮጀክቶቻችን በብዙ መንገድ ይሞከራሉ::
ፕሮፋይሊንግ ላይ የሚሰራ ስራ አለ:: ሳይበር ኤክስፕሎይት ለማድረግ የሚሰራ ስራ አለ፤ ሳይበር ወርፌር አለ:: ለምሳሌ ኮሮና መጣ፤ እኛ ዘንድ እንኳን ብዙ ችግር የለውም፤ አፍሪካ ግን በየሜዳው ሬሳ ይታያል፤ በሚሊየኖች ይሞታሉ ተባለ:: እኛ ደጋጎች ነን፤ ከዚህ ሲሆን አንሰማም፤ ከውጭ ሲሆን እንሰማለን:: ሁሉም ሙያተኛ እንዲባል አፍሪካ በየመንገዱ ይሞታል እያለ ሪፖርት ጽሁፍ ያወጣ ነበር:: ሞትን እንዴ? ፈጣሪ እኮ ደግ ነው፤ አልሞትንም:: አሁን ደግሞ ችግር አለ አለም ላይ አለ:: ችግሩን ወደ አፍሪካ ሲያመጡት አፍሪካ በረሀብ ምክንያት ይሰደዳል እያሉ ነው::
እነሱ የማይራቡ የማይቸገሩ ነው የሚመስላቸው:: ግን አይደለም:: እንደዚህ አይነት አጀንዳ ኤክስፖርት አድርገው ሞኛ ሞኞች እያጫወቱ ኑሯቸውን ለመግፋት የመጣር ፍላጎት እዚህም እዚያም አለ:: ተሰብስበው ኮንፍረንስ ምናምን ብለው ተቀምጠው ሳያፍሩ አፍሪካ በረሀብ ትሰደዳለች ይላሉ:: አፍሪካ ኤክስፖርት ብታደርግስ? እንደዚህ አይነት ጨዋታዎች አሁን ለምሳሌ ድርድር እንደሚባለው ድርድር በጣም ይገርመኛል፤ ድርድር የሚጭበረበርበት መንገድ፤ ለሰላም መነጋገር የከፋ ይመስል ሆን ብሎ፣ ቁጭ ብሎ የሚሰራ ሰው አለ:: ለምን? በውስጣችን መጠራጠር በውስጣችን መባላት እንዲፈጠር የሚደረግ ሙከራ ነው:: እና ሰላምን በሚመለከት በቨርቹዋልም በፊዚካልም የሚደረግ ማንኛውም ጥቃት አቅም በፈቀደ መጠን ለመከላከል እና ኢትዮጵያን እንደ አገር ለማስቀጠል ይሰራል እየተሰራም ነው:: ይሄ እንደተጠበቀ ሆኖ በሰላም የሚገኝ ማንኛውም ድል ካለ ደግሞ ቢበዛ ሰላም ለማምጣት እንሰራለን::
ሪፖርቱ ለስራ አስፈጻሚ ሲቀርብ ወዲያው ለህዝባችን እናሳውቃለን:: በእነዚ በእነዚህ ነጥቦች ለመነጋገር ዝግጁ ነን ብለን:: ለመነጋገር የምንፈልግበት ምክንያት እኮ በጣም ብዙ ነው:: አለም በሙሉ ነው የሚያናግረን፤ እናንተን የሚያክል አገር አንዴት ይህን ችግር አይፈታም እያለ ያናግረናል:: አይ ግዴለም እኛ እንዋጋለን አይባልም:: የምንኖረው ከአለም ጋር ነውና:: በዚህ በኩል እየለመንክ፤ በዚህ በኩል እየፎከርክ እንዴት ይሆናል:: የግል ክብር ብቻ ሳይሆን የአገር ጥቅም ይጎዳል:: ይሄን ታሳቢ ያደረገ አካሄድ መሄድ ጥሩ ነው::
ሰላም ከመጣ አንደኛው ተጠቃሚ የትግራይ ህዝብ ነው:: መፈናቀል ብላለች እህቴ፤ አንደኛው የሚጠቀመው የትግራይ ህዝብ ነው:: ከፍተኛ ችግር ላይ ስለሆነ፤ ይሄ ፓርላማም ለእዚያ ህዝብ መቆርቆር አለበት:: ከሆነ አይቀር ድንበር ላይ ብቻ ሳይሆን፤ ትግራይ ላይ ስደት፣ ረሃብ፣ ችግር እየበዛ ነው:: ሰዎቹ ግድ የላቸውም:: ሰዎቹ ጄነሬተራቸው ነዳጅ ካገኘ እነሱ የኤሌክትሪክ ሃይል ጉዳይ አያስጨንቃቸውም:: እነሱ ውሃ ካገኙ የሌላው ሕዝብ ማጣት ጉዳያቸው አይደለም፤ መሃል ላይ ህዝቡ ይጎዳል ብሎ ማሰብ ከሁላችን የሚጠበቅ ነው:: በዚህ አግባብ ማየት አለብን:: በሰላሙ ትግራይ ከተጠቀመ በኋላ አፋርም አማራም፣ ኦሮሚያም፣ ደቡብም ሁሉም ይጠቀማል::
ሰላም ከመጣ ኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን ጎረቤትም ይጠቀማል:: በዚህ ጦርነት እኮ ቀጠናው ላይ በብዙ የሚነግድ ሰው አለ:: የሚያቀባብል አለ፤ ለዚያ ሁሉ መፍትሄ ይሆናል:: እንግዲህ እኛ ሰላም ፈለግን ማለት፤ እኛ ለሰላም ተጋን ማለት በዚያው ልክ ግብረ መልስ እናገኛለን ማለት ላይሆን ይችላል:: እኛ ግን ሁልጊዜ የምናውጀው ሰላምን ነው:: የምንለምነው ለሰላም ነው:: ሰላምን አልፈልግም ኢትዮጵያን አፈርሳለሁ ብሎ ከመጣ ‹‹እኔን ካፈረስከኝ በኋላ ነው፤ አትችልም::›› ብለን እንከላከላለን::
ይሄን ያደረግነው እና የምናደርገውም ጉዳይ ነው:: ስለዚህ ሰላምን ጥያቄ ውስጥ ማስገባት ተገቢ አይደለም:: በዚህ አይነት ማየት ጥሩ ነው:: አሉባልታውን ወሬውን እንተወው:: እርሱ ከመከፋፈል ውጪ ጥቅም የለውም:: ሲደርስ እና ሲያስፈልግ በግልጽ የምናየው እና የምንሰማው ይሆናል::
ከህግ ማስከበር ጋር ተያይዞ ለተነሳው ጥያቄ በመጀመሪያ የህግ ማስከበሩ ስራ የተጀመረው የብልጽግና አባላት ሆናችሁ ጉባኤ የተሳተፋችሁ ሰዎች ታስታውሱታላችሁ:: ጉባኤው ላይ አንዱ አጀንዳ ህዝባችን እናድምጥ፤ የህዝባችን ስሜት እንረዳ ብለን ነው፤ ጉባኤውን በጨረሰን ማግስት ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ አካሄድን:: ስብሰባው ላይ በመጀመሪያ የተወያየንበት ጉዳይ ህዝባችን ጋር ሄደን እንወያይ፤ ህዝባችንን እናነጋግር ተባባልን::
ከዚህ ጉባኤ ህዝቡ ብዙ ነገር ይጠብቃል፤ ምን እንደሚለን እንስማ አልን:: በአገር ደረጃ ሁሉም ሰው ተሰማርቶ ውይይት ተካሄደ:: ብዙ ጉዳይ ተነስቷል፤ ከነዚህ ውስጥ ሶስት አንኳር ጉዳዮችን ልጥቀስ:: አንደኛው ሰላም ሰላም ሰላም የሚል ከሰላም ጋር የሚያያዝ ጉዳይ በሁሉ አካባቢ ተነስቷል:: ሁለተኛ የዋጋ ግሽበት፤ ኑሮ ተቸገርን፤ እኛ መርጠናችኋል እንድትሰሩልን እንፈልጋለን፤ መርጠናችኋል ግን ባካችሁ መፍትሄ አምጡ የሚል ከፍተኛ ጥያቄ ነበር::
ሶስተኛው ስለመልካም አስተዳደር ነው:: በኑሮ ውድነት ላይ ሌቦች አስቸገሩን፤ የማይሰሩ ሰዎች አስቸገሩን፤ ይሄን ነገር መንግስት አንድ ይበለን የሚል ጥያቄ ነበር:: ብዙ ጉዳይ ነበር:: ነገር ግን ዋና ዋናው ሶስቱ ጉዳዮች እነዚህ ነበሩ:: ይሄንን ማዕከላዊ ኮሚቴው ከተመለሰ እና ከተወያየን በኋላ በአገር ደረጃ ጥናት እንዲጠና አደረግን:: ጥናቱን በጋራ ስናይ ኦሮሚያ፤ አማራ፤ ቤኒሻንጉል ሶስቱ ላይ በጣም ሰፋ ያለ ከሰላም ጋር የሚያያዝ ችግር አለ:: አዲስ አበባ ላይ ደግሞ ቀማኞች፤ በሞተር ሳይክል እየሄዱ ቦርሳ እና ሞባይል የሚቀሙ እንዲሁም የጠላት ወኪል የሆኑ ሰዎች በስፋት አሉ::
በሌላ በኩል ሶማሌ ላይ ኮንትሮባንድ እና አልሸባብ አለ:: መንግስት ትኩረቱ ሰሜን ስለሆነ የኮንትሮባንድ ትስስሩ (ኔትወርክ) እንዲሁም አልሸባብ እያስፋፋ ነው:: እነዚህ ከላይ የጠቀስኳቸው ጉዳዮች ላይ ትኩረት እናድርግ አልን:: ሌሎቹ ደግሞ ሥራቸውን ይሥሩ የሚል ስምምነት አደረግን:: ይሄ በጥቅሉ አንድ ወር ተኩል፤ ሁለት ወር ሊሆን ይችላል::በዚህ ሁለት ወር ተኩል ኦሮሚያ ክልል መሠረታዊ ዘመቻ ተካሄደ:: ኦሮሚያ ክልል ከ1ሺ በላይ የሸኔ አባላት ተገድለዋል:: በብዙ ሺ ተማርከዋል::
አንዱ በጣም መሠረታዊ የሚባል ውጤታማ ስራ የተሰራው ኦሮሚያ ነው:: ሁለተኛው አማራ ክልል ነው:: አዲስ አበባ እና ቤኒሻንጉል ላይም ሰፊ ስራ ተሰርቷል:: አልሻባብ እና ኮንትሮባንድን በሚመለከትም ተሰርቷል:: በድምሩ የገመገምነው በባለፈው ከህዝብ ውይይት በኋላ ሰላምን የማረጋገጥ፣ ህግ የማስከበር ስራችን ውጤት እያመጣ ነው:: ብለን ገምግመን ህዝቡን ደግሞ እናወያየው አልን:: ህዝቡን ደግሞ አወያይተን በቅርቡ ከነበረው ሪፖርት ከጫፍ ጫፍ የሰማሁት ህዝቡ ደስተኛ ነው የሚል ነው:: አማራ ክልል ብቻ ሳይሆን በሰላም ማስከበሩ ምእራብ ጎጃም በጣም ደስተኛ ነው:: ይህን ከተቻለ አቶ ክርስቲያን ሄደው ቢያወያዩ ጥሩ ነው:: ሰሞኑን ጠፍተዋል የሚሉ ሀሜቶች ሰምቼ ነው፤ ቢያወያዩ እውነቴን ነው ደስታውን ይሰሙታል::
ህዝቡ ለምን ደስተኛ ሆነ? ያላችሁኝ እንደሆነ፤ አማራ ክልል እናቶች መተኛት አይችሉም ነበር:: ማታ ማታ ጥይት ይንጣጣ ነበር:: በየከተማው ልክ እየተንጣጣ ሲያድር የምናመርት ይመስላል:: በዶላር የማይመጣ ይመስል:: ጠላት ጎኑ ተቀምጦ ተከብቤያለሁ እያለ ነገር ግን ዝም ብሎ ሲተኩስ ያድራል:: ሰው ይጨነቃል፤ የወጣ ልጅ ካለ ይጨነቃል፤ ይሄን ደግሞ እናንተ በደንብ ታወቁታላችሁ:: ሥርዓት ወደ ማስያዝ ሳንገባ ከተቻለ በሰላማዊ መንገድ ትጥቅ ይፈታ ሞክሩ አልን::
ክቡር አቶ ክርስቲያን እኔ ባለኝ መረጃ ከአማራ ክልል ፕሬዚዳንት ጋር እርስዎ ራስዎ በሰላም አስገባለሁ ብለው ውይይት ለማድረግ መሞከርዎን አውቃለሁ:: አሁን ሳይሆን ቀደም ብሎ ባለው ሁኔታ ተነግሮኝ፤ በሰላም ከተቻለ ሳንያያዝ ይሞክሩ ብዬ እርስዎ እንኳ እንደሞከሩ አውቃለሁ:: በሰላም የሚመጣ ነገር ካለ ደስ ይለናል:: እኛ ውጊያ ምን ያደርግልናል? የሚወጣው ገንዘብ እኮ ነው:: ከህይወት ብቻ ሳይሆን ከትንሿ ነገር ጀምሮ ኪሳራ ነው፤ አስፈላጊ አይደለም::
ግሽበት ላይ የጓሮ አትክልት ብለን ከቤተመንግስት ጓሮ የጀመርነው፤ ቅድም እንዳነሳሁት ድጎማ ያደረግነው ለዛ ነው:: መልካም አስተዳደር ላይ ከ5ሺ በላይ የብልጽግና አባላት በሁሉም ክልል አስረናል፤ አባርረናል፤ ከደረጃ ዝቅ አድርገናል:: በዚህች ሁለት ወር ውስጥ ይህን ሰርተናል:: ተቃዋሚ ጋር ብቻ ሳይሆን በውስጣችን ያሉ ሌቦችንም ለማጥራት ሙከራ አድርገናል:: በቂ ነው ወይ? ከተባለ አይደለም ገና ብዙ ስራ ይጠበቅብናል:: እርስዎ እንዳሉት በሰላም ከሞከርን በኋላ አልሳካ ሲል፤ ብቸኛ ሀይል የመጠቀም ስልጣን ያለው መንግስት ነው:: ለእዚያ ደግሞ አቅም አለው:: አቅም እንደሌለው ሆኖ የታየበት ዋና ምክንያት ዴሞክራሲውን ብንለማመድ የሚል ፍላጎት ስላለ ነው:: ያም ሆኖ የፌደራል ሥርዓት ስሪታችንንም በደንብ መገንዘብ ጥሩ ነው::
በአማራ ክልል የተካሄደው እያንዳንዱ ሕግ ማስከበር መቶ በመቶ የተካሔደው በአማራ ልዩ ሀይል ነው:: አንድም የፌደራል ጦር የለበትም:: አንድም የሚመራው ፕሬዚዳንት ነው፤ የሚሳተፈው የአማራ ልዩ ሀይል ነው:: እኛ ያደረግነው በሴኩሪቲ ካውንስል ጥናቱ ሲቀርብ ጉዳዩን ካየን በኋላ፤ ክልሎች ይምሩት ብለናል:: የሴኩሪቲ ካውንስል አባላት ግን በየክልሉ ቴክኒካል ድጋፍ ይስጡ ብለን የመደብናቸው ሰዎች አሉ:: መረጃ እና ድጋፍ እንዲያገኙ ተደርጓል:: በዋነኝነት እነሱን የሚመራው ግን ፕሬዚዳንቱ ነው::
አማራም፣ ደቡብም፣ ኦሮሚያም ሁሉም ቦታ ከተሳካም ከተበላሸም የሚመራው ያው ፕሬዚዳንቱ ነው:: አንዳንዴ ፌዴራል ሰው ታፍኗል ሲባል፤ ክልሎች ህጋዊ የማሰር ስልጣን ያላቸው፤ ህግ አስፈጻሚም፤ የህግ ተርጓሚ አባላት በየክልሉ እንዳሉ ሰው አይገነዘብም:: በየክልሉ ህግ አውጪ፤ ህግ ተርጓሚ፤ ህግ አስፈጻሚ አለ:: የማሰር የመጠየቅ መብት ያለው አለ:: በዚህ ምክንያት አማራ ክልል የተደረገው ህግ ማስከበር (ኦፕሬሽን) የአማራ ክልል ምክር ቤት ሪፖርት ሲቀርብ ተወካዮች ህዝብ አነጋግረው ሪፖርት ማቅረብ አለባቸው:: እኔ ባልመራሁት ዘመቻ በዝርዝር ይሄ ነው፤ ያ ነው ማለት አልችልም::
ዝርዝር እቅድ ሰምቻለሁ፤ ሁኔታውን አውቃለሁ:: ነገር ግን ልክ የፌደራል መንግስት እንደሚመራው አይነት ተደርጎ የቀረበው ስህተት ነው:: የአማራውን ዘመቻ አማራ ይመራዋል፤ የኦሮሚያውን ኦሮሚያ ይመራዋል፤ የቤኒሻንጉልን ቤኒሻንጉል፣ የሶማሌውን ሶማሌ ይመራዋል:: ሁሉም ጋር ግን ቴክኒካል ድጋፍ ይደረጋል:: እናም አንደኛ ኦፕሬሽኑ ከውስጥ መሆኑን ማወቅ ጠቃሚ ነው:: ሁለተኛ በህዝብ ጥያቄ የተጀመረ መሆኑን ማወቅ ጥሩ ነው::
በተጨማሪ ከተጀመረም በኋላ ህዝብ ደስተኛ መሆኑንና ሰላም እያገኘ መሆኑን ማወቅ ጥሩ ነው:: ይሄ እንደተጠበቀ ሆኖ በስንዴ ማሳ ስንዴ ብቻ ሳይሆን እንክርዳድ፤ በብልጽግና እሳቤ ውስጥ አበልጻጊ ብቻ ሳይሆን ሌቦች እንዳሉት ሁሉ በሚያኮራ ስም እና ሁላችንም ልንመካበት በሚገባ ስም ሌሎች መጠቀም ፈልገዋል::
ፋኖ ለአማራም ለኢትዮጵያም ኩራት ነው፤ ምንም ጥያቄ የለውም:: በጀግንነት ተዋግቷል፤ ወደፊትም በጀግንነት ይዋጋል:: እሱ የአብይን ውዳሴ፣ ሙገሳ ጠብቆ የሚዋጋ ሳይሆን አገሩን ወዶ የሚዋጋ ነው:: ከተነካችበት ወደፊትም አይቆምም:: አድርጓል፤ ያደርጋል፤ እያደረገም ነው:: ይሄ ጥያቄ የለውም መወደስ አለበት፣ መመስገን አለበት፤ መከበር አለበት:: ይሄንን ስም ግን መጠቀሚያ ማድረግ ጥሩ አይደለም::
በከተማ ተኩስ ብቻ ሳይሆን፤ መዝረፍ፣ ሴቶች መድፈር፣ ሕጻን መጥለፍ፣ ነጋዴ መዝረፍ፣ ግብር መሰብሰብ፣ ሃሰተኛ (ፎርጅድ) ብር ማምረት፤ ይሄ የፋኖ ሥራ ሊሆን አይችልም:: ፋኖ ሃሰተኛ (ፎርጅድ) ብር አይሰራም:: ሴት አይደፍርም፣ ሕጻን አይጠልፍም:: ሲባጎ ለጥፎ ግብር አይሰበስብም:: አማራ ክልል የነበረው ይሄ ነው፤ የአማራ ክልል ተወካዮች ታውቃላችሁ:: እማታውቁ ከሆነ ሕዝባችሁን ሂዱና ጠይቁ::
በነገራችን ላይ የተከበሩ አቶ ክርስቲያን፤ በአማራ ክልል ሕግ ማስከበር ከተያዙ ሰዎች በጣም የሚገርማችሁ 3 ሺህ 500 ሰው የተያዘው የከዳ ሠራዊት ነው:: ከዚህ ውስጥ ከሁለት ሺህ በላይ የአማራ ልዩ ኃይል ነው:: ከአማራ ልዩ ኃይል ታጥቆ ሠልጥኖ የከዳ፤ የከዳ ብሎ ፋኖ ከየት የመጣ ነው? አማራማ ባለ በሌለ አቅሙ አሰልጥኖ አስታጥቆ ጠብቀኝ አለው:: ጠብቀኝ ካለው ቦታ ጠፍቶ፣ የሰፈር አለቃ ሆኖ፣ ክላሽ እየተኮሰ ሕዝብ የሚያምስ ሰው ሲያዝ ለምን ሕግ ተከበረ? ማለት ጥሩ አይደለም::
ምክንያቱም እርስዎ እንዳሉት አርሶ አደር የሚያርሰው ሰላም ካገኘ ነው:: አገር የሚለማው ሰላም ካገኘ ነው:: መባል ያለበት ችግር የለውም ጠላት ይረብሻል፤ በገዛ ልጆቻችን ግን መታመስ የለብንም ማለት ይገባል:: ከድቶ በሰፈር አለቃነት ሰው ማስቸገር ጥሩ አይደለም:: ለጊዜው ከፖለቲካ አንፃር እናንተም ደግፋችሁት ይሆናል፤ ግን ድንገት በሚቀጥለው ምርጫ ብታሸንፉና ክልሉን ብትመሩ ይሄን ዓይነት ልምምድ ጥሩ አይደለም:: ሁሉም ነገር ሕግ የተከተለ መሆን አለበት::
በነገራችን ላይ በአማርኛ ሚዲያ ሕወሓት አንዲት እናት አምስት ልጆቿን ሰጠች፣ ሦስት ልጆቿን ሰጠች እያለ ይናገራል:: በአማርኛ የሚናገረው ለማነው? ለእኛ እኮ ነው:: ለእሷማ የሚያወራት በትግርኛ ነው:: እየነገረን ያለው ለእኛ ነው:: በአማርኛ አምስት ልጆች ሰጠች እያለ፤ እኛ አምስት አያስፈልግም ብለን አንዳንድ የወሰድነው እንኳን ምሽጉን ጥሎ ሰፈር ከገባ ማን ይጠብቅሃል? የገባው በግዴታ አይደለም ወዶ ነው:: ወዶ ገብቶ ክላሽ ሰርቆ ሸጦ ባጃጅ የሚገዛ፣ ክላሽ ሰርቆ ሸጦ ሰፈር ሄዶ የሚዘርፍና የሚሸፍት ሰው መፍጠር ትክክል አይደለም::
የተሠራውን ሥራ በጥቅሉ ብቻ ሳይሆን በውጤት ደግሞ እንመልከተው፤ 3 ሺህ 500 የከዳ ሠራዊት፣ ብዙ ኩንታል ሀሽሽ ተያዟል፤ ፋኖ ሀሺሽ ምን ያደርግለታል? በኦሮሚያም በአማራም ብዙ ኩንታል ሀሺሽ ተይዟል:: ከፍተኛ ቁጥር ያለው የውጭ ምንዛሬ፣ ሀሰተኛ (ፎርጂድ) ገንዘብ፣ የሰበሰብነው ይሄን ነው:: ቦምብ፣ የሚቀጣጠል ፈንጂ፣ ስናይፐር ይዘናል::
በነገራችን ላይ የተከበረው ምክር ቤት እንዲገነዘበው የምፈልገው፣ ከዚህ ውጊያ በኋላ የገዛነው ለየት ያለ ክላሽ አለ:: ኢትዮጵያ ውስጥ ድሮ አልነበረም፤ ከዚህ ግጭት በኋላ ያስገባነው መከላከለያ ብቻ ያለው ክላሽ አለ:: በቀለሙ ብቻ የሚለይ ክላሽ ነው:: ይህንን ክላሽ አገር እንከላከል፣ አገር አትፈርስም ብለው የቆሰሉ ኦሮሞዎችን፣ አማራዎችን፣ ወላይታዎችን ገድሎ መሳሪያ የወሰደ ሁሉ ፋኖ ነኝ ብሏል:: ሊከላከለው የሄደውን ወንድሙን ገድሎ፤ መከላከያ ያንን ክላሽ ሲያይ ያመዋል:: ያ ክላሽ ማንም ጋ የለም፤ ክልል የለም፤ ፖሊስ ጋር የለም:: ሳያፍር አንጠልጥሎ ይሄዳል፤ ይሄ ትክክል አይደለም፤ ይጎዳናል::
ነፃነትና ብልጽግና ሥርዓት ሲኖር ነው:: ሥርዓት ያስፈልጋል፤ ሁሉ ነገር በስርዓት መሆን አለበት:: የጀገነ አንድም የአገር መከላከያ ሚኒስቴር አባል ይሆናል:: የአማራ ልዩ ሃይል ይሆናል፤ ሚሊሻ ይሆናል፤ አልያም ‹‹ስትፈልጉኝ ጥሩኝ›› ብሎ ቤቱ ይቀመጣል፤ ያርሳል:: አሥርና ሃያ ሰላሳ ሆኖ እንደመከላከያ መሆን እና ሃይል መጠቀም ለአማራም ጥሩ አይደለም::
ለምክር ቤት ለመናገር አይመቸኝም፤ ግን አማራ ገጠመኝ የሚለው ጦር ሕወሓት ከሆነ፣ ሕወሓት እኮ አንድ ቋንቋ የሚያወራ፤ የሚደማመጥ፣ ችግር እንኳን ቢኖር ደብቆ የሚያወራ እንጂ በየሚዲያው የሚሰዳደብ አይደለም:: አማራን ጠንካራ የሚያደርገው፤ አንድ ግንኙነት ሲኖር እንጂ አስር ቦታ ከተከፋፈለ እዚያ ሚሊሻ፣ እዚያ ልዩ ሃይል፣ እዚያ ሌላ ሲሆን መከላከልም አይችልም፣ ለአማራም ለኢትዮጵያም አይበጅም::
አንድ መሆን መሰብሰብ ያስፈልጋል:: ይሄ መሳሪያ የያዘ ኃይል፣ ወጣት ኃይል፣ ብር የለመደ ሃይል፣ መኪና የሚቀማ ሃይል አርሶ አደር በሬ ሸጦ ሲመለስ የሚቀማ ሃይል እሳት ነው:: በአማራ ባህል ውስጥ እሳት ዝም ብሎ አይለቀቅም:: እናቶች ዝም ብለው እሳት አይለቁም:: እንጀራ የሚጋግሩ ከሆነ እሳቱ እንዳይረጭ ሰብሰብ የሚያደርገው በእበት የሚሰራ አንከርት የሚባል አለ:: እሳት ከተረጨ ቤት ያቃጥላል:: ወጥ የሚሰሩ ከሆነ ሰብሰብ አድርጎ እሳቱን የሚይዝ ጋቻ የሚባል ነገር አለ:: ይሄ እሳት ሰብሰብ ተደርጎ ካልተያዘ ወደፊትም ልንዋጋ አንችልም:: ወደኋላም አስቸጋሪ ይሆናል:: በዚያ መነጽር ማየት ጥሩ ነው::
የመብት ተሟጋቾች እንደዚህ ብለዋል ለተባለው፤ እነዚህ ተሟጋቾች የሚሟገቱት ለሰው ከሆነ ለሚጠለፈው፣ ለሚዘረፈው እና ለሚደፈረው ሕዝብ አይናገሩም እንዴ? በኢትዮጵያ ውስጥ ታዋቂ ያልሆኑ ሰዎች በሕይወት የመኖር መብት፤ ታዋቂ ከሆኑ ሰዎች ከመናገር መብት ጋር እንዴት አቻ ሆኖ ይታያል? ሰዎች በሕይወት ለመኖር እየተቸገሩ፣ እንደተባለውም እየተፈናቀሉ፣ እየተቸገሩ ኢትዮጵያዊ ሆነው በአገራቸው ውስጥ እንደሁለተኛ ዜጋ ሆነው እየኖሩ፣ እርሱን ለማስከበር የሚሰራ ጥረት እንዴት ከመናገር መብት ጋር እኩል ይታያል? ከመናገር ሰው ማኖር አይበልጥም? ይሄን ማየት ጥሩ ነው::
ይሄ ማለት ግን ይሔን የሚያክል ሕግ የማስከበር ሥራ ሲሰራ በስህተት የተያዘ ሰው የለም፤ ጥፋት አይጠፋም፤ የእኛ መንግስት እንከን አልባ ነው ማለት አይደለም:: መገምገም አለበት:: በስህተት የተያዘ ሰው ካለ፣ የተጎዳ ሰው ካለ፤ አላግባብ ሃይል የተጠቀመ ካለ መጠየቅ አለበት:: ምክንያቱም አንደኛውን ጥፋት ለማከም ሌላ ጥፋት ማጥፋት ትክክል አይደለም::
ይሄን ደግሞ የተከበረው ምክር ቤት፤ በዋነኛነት የክልል ምክር ቤት ሥራ ቢሆንም የተከበረው ምክር ቤት ያለውን ነገር ኮሚቴ አቋቁሞ ማጥናት መጠየቅ ይችላል:: ችግር ካለ ማረም አለበት:: የአማራ ክልል ባለኝ ሪፖርት በሺህ የሚቆጠር ሰው አጣርቶ ፈቷል:: የቀረም ካለ ተጣርቶ መለቀቅ አለበት:: የተጎዳም ካለ ካሳ መከፈል አለበት:: እኛ የምንፈልገው ሰላማዊ ክልል እንድንሆን ነው እንጂ ዜጎች እንዲበደሉ አይደለም:: ግን ሦስት ሺህ 500 የከዳ ሰራዊት የት እንደገባ አይታወቅም? ለሚለው የከዳ ሰራዊት የሚጠየቅበት አለው:: እና ይሄን ማየት ጥሩ ነው:: እርስዎም ከሌሎች የፓርላማ አባላት ጋር ሄደው አይተው ጥሩ ጎኑን ማጠናከር፣ ችግር ካለ ደግሞ የሚታረምበትን መንገድ መፍጠር አስፈላጊ ነው::
‹‹መንግሥት እያሸበረ ነው›› የሚለው የሶሻል ሚዲያ ንግግር ጥሩ አይደለም:: ቢያምኑም ባያምኑም አማራ ክልል ባሉ ከተሞች የጥይት ድምጽ ስለቀነሰ፤ እናቶች ተኝተው እያደሩ ያሉት አሁን ነው:: ጎንደር መተኛት እኮ አይቻልም:: ቅማንት ነው ምናምን እየተባለ የሚያድረው ሲተኮስ ነው:: ሰዎች ለመውጣት ለመግባት ይፈራሉ:: ባህርዳር ከተማ ውስጥ ተመሳሳይ ነው:: ይሄን ደግሞ በደንብ የምትገነዘቡት ይመስለኛል::
ሕግ ይከበር፣ ሰላም እናስጠብቅ፤ ስህተት ካለ ግን ያንን እየቀነስን ትክክለኛውን መስመር የምንከተልበትን፤ እኛ በሕግ የምንታረምበትን መንገድ መከተል ጠቃሚ ይሆናል:: ያ ካልሆነ ጥሩ አይሆንም:: በሁሉም ክልሎች የሕግ ማስከበር ዘመቻው ተጠናክሮ ይቀጥላል:: መፍትሔው ሕግ ማክበር ነው:: እንትና ነኝ፣ አርሶ አደር ነኝ፣ ባለባንዲራ ነኝ፣ ባለከዘራ ነኝ ማለት አይሰራም:: ሕግ ያላከበረ ይጠየቃል:: እኛ የምንሰቃየው በስንቱ ነው? ዋስትናው ህግ ማክበር ብቻ ነው:: ከዚህ በመለስ ሀሳብ መግለጽ፣ መነጋገር ችግር የለውም::
እዚያው ላይ ማህበራዊ ሚዲያን በሚመለከት፤ እንግዲህ በመጪው አምስት አሥርት ዓመታት የዓለም የኑሮ ሥርዓት ይቀየራል:: የገንዘብ ሥርዓት፣ የጤና ሥርዓት፣ የትምህርት ሥርዓት፣ የፖለቲካ ሥርዓት፣ ብዙ ነገር ይቀየራል:: ማህበራዊ ሚያው ብዙ ነገር እየነካካ ነው:: አሁን እኛ ጋ ልምምዶች ናቸው::
ብዙ ዕድሎችም ፈተናዎችንም ይዞ ይመጣል:: ፈተናውን እንዴት አድርገን እንቋቋመዋለን፣ ዕድሉን ደግሞ እንዴት እንጠቀመዋለን? የሚለውን ማሰብ ያስፈልጋል:: የቴክኖሎጂ ባለቤቶች ዋና ሥራቸው ዜጎች በእነርሱ ፍላጎት (አፕሊኬሽን) ላይ ተጥደው እንዲውሉ ማድረግ ነው:: አሊጎሪዝሞች የሚጻፉት በዚሁ ስሜት ነው:: ለምሳሌ እዚሁ ፓርላማ ያላችሁ ሰዎች እዚያ ጫፍ ያሉት ሰውዬና እዚያ ጫፍ ያሉት ሴትዮ ሁለታችሁም ወጥታችሁ ዩ ትዩብ ብትከፍቱ ሁለታችሁ ገጽ ላይ አንድ ዓይነት አይመጣም::
እርስዎ የሚፈልጉትን፣ እርሳቸውም የሚፈልጉትን ዩትዩብ ያውቃል፤ ያጠናችኋል:: የሚሰጣችሁ የምትፈልጉንት ተቃራኒ ሃይል ነው:: ዩትዩብ ላይ በአጀንዳ ሴቲንግ የሚሰሩ በርካታ የውሸት ዜናዎች የብዙ ሰው ጭንቅላት ያምሳሉ:: ሲሰራ ውሎ እስኪ ዜና ልስማ ብሎ የውሸት ዜና ሰምቶ ሲታመም የሚያድርና ነገ ሥራ የሚበላሽበት በየአገሩ ስንት ሰው አለ?
እነዚህ አልጎሪዝሞች አላማቸው በውሸት፣ በጥላቻ፣ በስድብ ብዙ ተከታይ ያፈራሉ:: ለምን? ብዙ ተከታይ ያለው ሰው ብዙ ብር ያገኛሉ:: ኢትዮጵያ ውስጥ በዩ ትዩብ የሚከፈል ገንዘብ፤ ታክስ የሚከፍል የለም:: ዩ ትዩቡን ላይክ ሼር እያደረግን የምናባዛው እኛ ነን:: የእሱ አካውንት ያለው ግን የሆነ ቦታ ነው::
ይሄን የመገናኛ ብዙሃን ባለስልጣኑም፤ የመረጃ እና ደህንነቱም ማጥናት አለበት:: ማንኛውም ዜጋ ከሚያገኘው ገቢ ታክስ መክፈል አለበት:: የሚያገኘው በዶላር እኮ ነው:: በዚህ ምክንያት ሥራው ማጋባት፣ ማፋታት ማጣላት ነው:: ሰው በባህሪው ተቃራኒ ሃይል ስለሚስበው፤ ሰው እንዲያይ ሁል ጊዜ መርዶ ያቀርባሉ::
ሌላው ችግር አክቲቪስት፣ ጋዜጠኛ እና ፖለቲከኛ ተቀላቅሏል:: አንድ ሰው ጠዋት አክቲቪስት ነው፤ ከሰዓት ፖለቲከኛ ነው፤ ከዚያ ደግሞ ጋዜጠኛ ይሆናል:: ሲያባላ አክቲቪስት ነው፤ ሲጠየቅ ደግሞ ጋዜጠኛ ነው:: ይሄ ትክክል አይደለም፤ ወገኖቼ ይሄ አገር በቋፍ ነው፤ መጠናከር አለበት፤ ዝም ብሎ ማንም መከላከያን የሚያፈርስ ሥራ ሲሰራ አትደግፉ::
እነዚህን እናንተ የምትናገሩላቸው አክቲቪስቶች በኢሜል የአማራ ጀኔራል አትዋጋ፤ የኦሮሞ ጀኔራል አትዋጋ እያሉ መከላከያን የሚያፈርሱ ናቸው:: መከላከያ ከፈረሰ በማንኛውም ቅፅበት አገር ትፈርሳለች:: ተቋም የሚያፈርሱ ሰዎችን ጋዜጠኛ አክቲቪስት እያልን ስም አንስጣቸው:: የመናገር እና ሃሳብን የመግለፅን መብትን እየነካችሁ እያፈናችሁ ትላላችሁ? ኢትዮጵያ ውስጥ እንደ ዐቢይ የተሰደበ መሪ አለ? በስድብ እስክስታ እየተወረደ ነው:: በቀን ሶስት ሰዓት እና አራት ሰዓት እየተኛሁ፤ በለፋሁለት ህዝብ እንድዋረድ የሚለፈልፍ አለ::
( ይቀጥላል)
አዲስ ዘመን ሰኔ 11/2014