ወባ ከዓለማችን ገዳይ በሽታዎች አንዱ ነው። ከምዕራባዊቱ አሜሪካ ጀምሮ ምዕራብ ፓስፊክ አካባቢ፤ ምሥራቅ ሜዲትራኒያዊ፤ ደቡብ ምስራቅ ኢሲያ በአጠቃላይ ከምድር ወገብ በታች ያሉ አገራት ለበሽታው ተጋላጭ መሆናቸው ይነገራል። በተለይ በአፍሪካ ተስፋፍቶ ይስተዋላል። ለአብነትም ከሳሐራ በታች ያሉ የአፍሪካ ሃገራት በከፍተኛ ተጋላጭነታቸው እንደሚጠቀሱ የዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት መረጃ ያሳያል። በበሽታው ከሚሞቱት ሰዎች መካከል ከ80 በመቶ በላይ የሚሆኑት ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆነ ህፃናት መሆናቸው በእጅጉ ያሳስባል።
የሚያጠቡና ነፍሰጡር እናቶች አብዝተው በሞት የሚጠቁበት ሁኔታም መኖሩን መረጃው ያመለክታል። እንደ መረጃው እ.ኤ.አ በ2017 በ87 የዓለም አገራት 219 ሚሊዮን ሰዎች በወባ ተይዘዋል። በዚሁ ዓመት ከተያዙት ውስጥ በትንሹ 435 ሺ ሰዎች እንደሞቱም ይገመታል። በፈረንጆቹ 2017 በወባ የተጠቁ ሰዎችን የተመለከተ መረጃ እንደሚያሳየው ግማሽ ያህሉን ካስመዘገቡት አምስት አገራት አራቱ አፍሪካውያን ሲሆኑ እነሱም ናይጀሪያ፤ ኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ፤ ሞዛምቢክና ዩጋንዳ ነበሩ።
የወባ በሽታን ከገፀ – ምድሯ ለማጥፋት የተለያዩ መርሐ ግብሮች ዘርግታ በመንቀሳቀሱ ረገድ ከአምስት አሥርት ዓመታት በላይ ባስቆጠረችው ኢትዮጵያም ወባ የሚያደርሰው ጉዳት ከፍተኛ መሆኑን በጤና ሚኒስቴር የበሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር ዳይሬክተር ወይዘሮ ሕይወት ሰለሞን ይናገራሉ። የወባ በሽታን እ.አ.አ በ2030 ከኢትዮጵያ ጨርሶ ለማጥፋት የሚያስችል ስትራቴጂክ ዕቅድ ተነድፎ ወደተግባር መገባቱን ያወሱት ዳይሬክተሯ 75 በመቶ የሚሆነው የኢትዮጵያ መልካ ምድር ለወባ በሽታ ስርጭት ምቹ መሆኑ ደግሞ በበሽታው የሚደርሰውን ጉዳት አስፍቶታል።
በዚህ አካባቢ ከሚኖረው ሕዝብ በአጠቃላይም ከኢትዮጵያ ሕዝብ 52 በመቶ ያህሉ ለወባ በሽታ ተጋላጭ የሆነውም ለዚህ ነው ብለዋል። በኢትዮጵያ በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች የወባ ስርጭት የሚከሰተው የዝናብ ወራቱን ተከትሎ እንደሆነ ያስታወሱት ዳይሬክተሯ ከመስከረም እስከ ታኅሣሥ ድረስ ባሉት ወራት ውስጥ እንደሚከሰትም ያስረዳሉ። የበልግ ዝናብን ተከትሎም በሚያዚያ እና በግንቦት ወራት በተወሰነ መልኩ ስርጭቱ የሚባባስበት ሁኔታ እንደሚከሰትም ያወሳሉ። በረጅም የዝናብ ወቅት እና ጎርፍ በበዛበት ጊዜያትም የስርጭቱ ምጣኔ ከፍ የሚልበት ሁኔታ መኖሩንም ያነሳሉ።
የበሽታው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖ የጎላ ነው ያሉት ዳይሬክተሯ በምርት መሰብሰቢያ ወቅትና የክረምቱን ዝናብ ተከትሎ ከመከሰቱ በፊት መከላከል ካልተቻለ ጉዳቱ የከፋ እንደሚሆንም አስምረውበታል። በተጨማሪም አርሶ አደሩ የግብርና ሥራውን በአግባቡ እንዳያከናውን፤ ተማሪዎችም ትምህርታቸውን በተገቢ መልኩ እንዳይከታተሉ የልማት ጣቢያ ሰራተኞችም ውጤታማ ሥራ እንዳይሰሩ ያደርጋል።
በሽታው በወረርሽኝ መልክ ሲከሰት ደግሞ የሚያስከትለው ተፅዕኖ እጅግ ከፍተኛ ይሆናል። በጥቂት ጊዜ ውስጥ ብዙ ሰዎችን ለህመምና ለሞት የሚዳርግበት ጊዜ አለ። በዚህ ምክንያትም እንደ አገር ከፍተኛ ማህበራዊና ኢኮኖሚዊ ቀውስ ይከሰታል። የንግድና የቱሪዝም እንቅስቃሴንም በማስተጓጎል በአገር ኢኮኖሚ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳድራል።
የዓለም የጤና ድርጅት ሪፖርትን ዋቢ አድርገው ዳሬክተሯ እንደተናገሩት በሽታው በዓለም አቀፍ ደረጃ እ.ኤ.አ በ2020 በአንድ ዓመት ብቻ በ14 ሚሊዮን መጨመሩን አሳይቷል። ከዚህ ቁጥር መካከል 95 በመቶ የሚሆነው ድርሻ የአህጉረ አፍሪካ እንደሆነም ነው የተናገሩት።
እንደሳቸው በዓለማችን ፕላስሞድየም ፋልሲፓረም፣ ፕላስሞድየም ማላሪዬ፣ ፕላስሞድየም ኦቫሌ እና ፕላስሞድየም ቫይቫክስ የተሰኙ የወባ ፓራሳይቶች ይገኛሉ። ፕላስሞዲየም ፋልሲፓረም እና ፕላስሞዲየም ቫይቫክስ የሚባሉት ሁለት ዓይነት የወባ ፓራሳይቶች ደግሞ በኢትዮጵያ ውስጥ ነው የሚገኙት። ሰዎች በነዚህ ፓራሳይቶቹ በተያዙ ወባ አስተላላፊ እንስት ቢምቢዎች ከተነከሱ በወባ በሽታ ይያያዛሉ ።
በኢትዮጵያ ላለፉት 50ና በላይ ዓመታት ወባ በሽታን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ጥረት ሲደረግ የቆየ መሆኑን የሚያስታውሱት ዳይሬክተሯ በሁሉም ክልሎች ወባን የመከላከል ስራው በጤና ሚኒስቴር በኩል በሰፊው እንደሚሰራም ያብራራሉ። የወባ በሽታ ስርጭት በሌሎች የኢትዮጵያ ክልሎች የዝናብ ወቅትን ተከትሎ የመጨመር እና የመቀነስ ሁኔታ ያለው በመሆኑ ጎን ለጎንም ይሄንኑ መሰረት ያደረገም የመከላከል ሥራ በስፋት እየተሰራ እንደሚገኝም አክለዋል።
‹‹የተግባሩ ውጤታማነት በዓለም ጤና ድርጅት ተቀባይነት አግኝቷል›› ያሉት ዳይሬክተሯ ባሳለፍነው በ2013 ዓ.ም ከስምንት ሚሊዮን በላይ አጎበር መሠራጨቱንም ነው የሚናገሩት። ዘንድሮም 20 ነጥብ 6 ሚሊዮን አጎበር ለማሠራጨትና 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ቤቶችን ኬሚካል ለመርጨት እየተሠራ እንደሚገኝም አውስተዋል። በ2014 ዓ.ም በጀት ዓመት በ10 ወራት ውስጥ በወባ በሽታ ለተጠረጠሩ 5 ሚሊዮን 909 ሺህ 196 ህሙማን ምርመራ ማድረግ ተችሏል። በ 1 ሚሊዮን 302 ሺህ 360 ወይም 22 በመቶ ወባ ለተገኘባቸው ህሙማን ሕክምና ተሰጥቷል። ይሄ ክንውን ከአምናው 2013 ዓ.ም ጋር ሲነፃፀር በ16 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል ።
ዳይሬክተሯ የወባ ህሙማን ቁጥር መጨመር አስመልክቶም ምክንያት ያሏቸውን ዘርዝረዋል። እንደ ሙቀትና እርጥበት መሰል ለወባ መራባት ምቹ የሆነ የአየር ሁኔታ መኖር በምክንያትነት ይጠቀሳል። ከአየር ንብረቱ ጋር ተያይዞ ድርቅ የነበረባቸው አንዳንድ አካባቢዎች ዝናብ መዝነቡ በዚህ ምክንያትም ለወባ ትንኝ መራባት ምቹ ሁኔታ መፍጠራቸውም ለወባ ህሙማን ቁጥር መጨመር ሌላው ምክንያት ነው። በተጨማሪም የፀጥታ ችግር ባለባቸው አካባቢዎች የተሳለጠ መርሐ ግብር አተገባበር ክፍተት መኖሩ እንዲሁም የማህበረሰቡና በግለሰብ ደረጃ የሚካሄዱ የወባ መከላከል ሥራዎች መሥራት ላይ ክፍተት መኖሩም የህሙማን ቁጥር ለመጨመሩ በምክንያትነት የሚነሳ ነው።
በተለይ ደግሞ የአጎበር አጠቃቀምና የአካባቢ ቁጥጥር ሥራዎች ላይ ክፍተትና መዘናጋቶች መኖራቸው ለቁጥሩ መጨመር እንደ ችግር ተወስዷል። በግብርና ልማት ሥራዎች መስፋፋት ምክንያት ለወባ ትንኝ መራባት ምቹ የሆኑ ቦታዎች መኖራቸውም እንደ አንድ ችግር የሚነሳ ነው። በሽታውን የመከላከል ተግባሩ እነዚህን ሁሉ ችግሮች መሰረት አድርጎ የሚከናወን ነው።
እንደ ዳይሬክተሯ በተለይ ዘንድሮ በዘጠኝ ወራት ውስጥ በወባ በሽታ መከላከል ዙርያ በርካታ ሥራዎች እየተሰሩ ያለበት ሁኔታ አለ። በ229 ወረዳዎችና በ 4ሺህ 400 ቀበሌዎች ላይ ሰፊ የማኅበረሰብ ንቅናቄ በመፍጠር ከ25 ሚሊዮን ለሚበልጥ ሕዝብ በሽታውን በመከላከሉ ዙሪያ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ መሰራቱን ለአብነት ወስዶ ማየት ይቻላል ።
በተጨማሪም የመከላከል ሥራውን በፈጣን ቴክኖሎጂ የተደገፈ ለማድረግም የተሰሩ ሥራዎች አሉ። 5 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሕሙማን ለመመርመር የሚያስችል ፈጣን የወባ መመርመሪያ ኪት ግዢ የሥራዎቹ ማሳያ ይሆናል። የመመርመሪያ ኪት ግዢውን ተከትሎ 565 ወረዳዎች ወደ ማኅበረሰብ አቀፍ የምርመራና ምላሽ ትግበራ እንዲገቡም ተደርጓል። ዳይሬክተሯ 4 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሕሙማን ማከም የሚያስችል የፀረ ወባ መድሃኒት ግዢና ስርጭትም የተካሄደበት ሂደት አለ።
‹‹በተለይ ወባማ አካባቢዎች ሕብረተሰቡ ሳያሰልስ የአልጋ አጎበር በመጠቀም በሽታውን መከላከል ይችላል›› የሚሉት ዳይሬክተሯ ለዚህ ሲባልም የበሽታውን ስርጭት ለመግታት የሚያስችል የአልጋ አጎበር በስፋት መሰራጨቱንም አንስተዋል። በመጀመሪያ ዙር 2 ነጥብ 9 ሚሊዮን አጎበር ተገዝቶ እየተሰራጨ መሆኑን በማሳያነት ጠቅሰዋል። የአጎበር ስርጭቱ ሂደት በታቀደለት ጊዜ መሰረት ይከናወናልም ብለዋል። ከዚህ በተጨማሪም 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ቤቶችን ለመርጨት የሚያስችል የፀረ ወባ ትንኝ ኬሚካል ተገዝቷል። ወደ ወረዳዎች ለማሰራጨትም ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል።
አሁን ላይ ኢትዮጵያ ወባ በሽታን ለዘለቄታው በመከላከሉ ብሎም በማስወገዱ ረገድ በዚህ መልኩ እየሰራች ትገኛለች። በተለይም ከቅርብ ዓመታት ጀምሮ ሪፖርት የተደረገችውን የወባ አስተላላፊ ትንኝ ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችል የድርጊት መርሐ ግብር ተዘጋጅቷል። መርሐ ግብሩ ወደ ትግበራ የገባበት ሁኔታ አለ። በተጨማሪም ወባን ለማስወገድ የሚረዱ ሰነዶችን የወባ ማስወገድ ፍኖተ ካርታ፣ የወባ ማስወገድ አፈጻጸም መመርያዎችና ፎርማቶች የሚመለከታቸውን የፌዴራል፣ የክልልና የአጋር ድርጅቶች ባለሙያዎች በማሳተፍ ክለሳ እንደተደረገበትም ዳይሬክተሯ ተናግረዋል።
የመከላከሉን ግንዛቤ በሕብረተሰቡ ዘንድ ከመፍጠሩ አንፃር የተሰሩ ሥራዎች መኖራቸውን ያወሱት ዳይሬክተሯ ለምሳሌ በተከለሱ መመሪያዎችና ማንዋሎች ላይ ከአገሪቱ ክልሎች ተመልምለው በወባ ማስወገድ ላይ ለሚሰማሩ ባለሙዎች የአሰልጣኞች ስልጠና ተሰጥቷል። በስልጠናው 1 ሺህ 825 ባለሙያዎች መሳተፍ የቻሉ ሲሆን ከዚሁ ጋር የተያያዘ የበጀት ድጋፍም ተደርጓል።
በአጠቃላይ የወባ በሽታ ወቅታዊ ስርጭትን አስመልክቶ ‹‹አሁን ላይ ወባ በሽታ በየትኛውም የአገሪቱ ክፍሎች በወረርሽኝ መልክ አልተከሰተም›› የሚሉት ዳይሬክተሯ ሊከሰት ያልቻለው መከላከል ላይ ያተኮሩ ዘርፈ ብዙ ሥራዎች በመሰራታቸው እንደሆነም አበክረው ይናገራሉ። በተለይ ደግሞ የበሽታውን ወቅታዊ ስርጭትን አስመልክቶ የተወሰኑትን ዘርዝረዋቸዋል። አንዱም ለውሳኔ አሰጣጥ በሚረዳ መልኩ ለመተንተን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በጋራ በመሆን አስፈላጊው እርምጃ እየተወሰደ ይገኛል። የህሙማን ቁጥር በጨመረባቸው አካባቢዎች ባለሙያዎች ተመድበው ሙያዊ ድጋፍ እየሰጡ የሚገኙበት ሁኔታ አለ። የመረሐ ግብሩን አተገባበር ከበፊቱ የተሻለና የተሳለጠ ለማድረግ በበጀት ዓመቱ ለሁሉም ክልሎች ከ280 ሚሊዮን ብር በላይ ተልኳል ብለዋል።
በመከላከል ስራው ላይ የገጠሙ አንዳንድ ተግዳሮቶችንም ሲያነሱ መድሃኒቶችና መመርመሪያ መሣሪያዎች በበቂ ደረጃ ቢሰራጭም በአንዳንድ ጤና ተቋማት ላይ የስርጭት መቆራረጥ ፣ በሕብረተሰቡ ዘንድ የተሰራጩ አጎበሮችን በአግባቡ አለመጠቀምና ለሌላ ተግባር ማዋል እንደ ችግር አንስተዋል። የአካባቢ ቁጥጥር ሥራዎች ላይ የማህበረሰብ ተሳትፎ መቀነስ፤ በሽታውን ከማስወገድ አንፃር በሽታው ቀንሷል በሚል መዘናጋት እንዲሁም በባለድርሻዎች ዘንድ ተገቢውን ትኩረት አለመስጠትና በአንዳንድ አካባቢዎች በፀጥታ ችግር ምክንያት ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት እንቅፋት መሆን ከገጠሙ ተግዳሮቶች ይጠቀሳሉ ሲሉም አብራርተዋል።
እንደ ዳይሪክተሯ በነዚህ ተግዳሮቶች ምክንያት ዘንድሮ በከምባታ ጠንባሮ፤ በቤንች ሸካ ዞን፤ በምዕራብ አርሲና ምስራቅ ወለጋ ፤በኢሉባቦር፤ በአማራ ክልል ምዕራብና ማዕከላዊ ጎንደር ወረዳዎች የመጨመር አዝማሚያ ተስተውሏል። ሆኖም በ2013 በጀት ዓመት የወባን ስርጭት ምጣኔ በ2012 ዓ.ም ከነበረበት 1ነጥብ 7 ሚሊዮን ወደ 1ነጥብ 2 ሚሊዮን መቀነስ ተችሏል። በወባ ምክንያት የሚሞቱ ህሙማንን ምጣኔም ከ 0 ነጥብ 39 በመቶ ወደ 0 ነጥብ 28 በመቶ መቀነስ የተቻለበት ሁኔታ ተስፋ ሰጪ መሆኑን ተናግረዋል
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ሰኔ 11/2014