የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን(ዋልያዎቹ) የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ የምድብ የመጀመሪያ ሁለት ጨዋታዎችን አድርገው በማላዊ ቢሸነፉም ግብፅን አሸንፈው ያልተጠበቀ ውጤት አስመዝግበዋል። ይህም በቀጣይ የአፍሪካ ዋንጫ ለመሳተፍ ያላቸውን ተነሳሽነትና ተስፋ አሳድጎታል። ይሁን እንጂ ዋልያዎቹ ሕዝብን ያስደሰተ ውጤት አስመዝግበው በጥሩ መነቃቃት ላይ ባሉበት በዚህ ወቅት ከመጪው መስከረም ጀምሮ በሚያደርጓቸው የማጣሪያ ጨዋታዎች ሁለት እንቅፋቶች ሊፈትኗቸው እንደሚችሉ ከማላዊው ጉዞ በኋላ ፌዴሬሽኑ ባለፈው ሰኞ ከሰጠው መግለጫ ለመረዳት ተችሏል።
አስተዳደራዊ ጉዳዮችን በተመለከተ የፌዴሬሽኑ የጽሕፈት ቤት ሀላፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን በመግለጫው በሰጡት ማብራሪያ፣ ዋልያዎቹ በገለልተኛ አገር ጨዋታዎችን ለማካሄድ ከመገደዳቸው ጋር ተያይዞ ፌዴሬሽኑ ከፍተኛ የውጪ ምንዛሬ የሚያወጣ በመሆኑ ከገንዘብ እጥረት ጋር በተያያዘ ያለው ስጋት አሁንም እንዳልተቀረፈ አስረድተዋል።
ፌዴሬሽኑ በማላዊ ባደረጋቸው ሁለት ጨዋታዎች ለስቴድየም ኪራይና ለሌሎች ወጪዎች ከ50 ሺ ዶላር በላይ ወጪ ማድረጉ ኪሱን በእጅጉ ቢጎዳውም በጨዋታዎቹ ወቅት ከማስታወቂያና ከትኬት ሽያጭ ካወጣው የበለጠ ያላሰበው ገቢ ማግኘቱ ይታወቃል። ያም ሆኖ ያለበት የገንዘብ እጥረት ወደ ፊት ብዙ የሚያራምደው እንዳልሆነ ተጠቁሟል።
‹‹አሁን ላይ በተለያዩ የገበያ አማራጮች አስፍተን ገንዘብ መስራት ችለናል። መንግስትም ደግሞ አሁን የተመዘገበውን ድል በመመልከት የሆነ ነገር ያደርግልናል ብለን እንጠብቃለን። አስቀድመንም ጥያቄያችንን አቅርበናል። ይሄ ነገር ይሆናል የሚል እምነት አለን። ከገንዘብ እጥረት ጋር በተያያዘ የተጋረጠብንን አደጋ ለጊዜውም ቢሆን ቀንሷል፣ ግን አሁንም በዚሁ መልኩ የሚቀጥል ከሆነ ፌዴሬሽኑ አቅሙ እየተሟጠጠ ነው የሚመጣው››በማለት አቶ ባህሩ ያለውን ስጋት ገልጸዋል። በቀጣይ ጨዋታዎች ተመሳሳይ ገቢ ማግኘት ላይቻል እንደሚችል የጠቆሙት አቶ ባህሩ፣ ፌዴሬሽኑ የተረጋጋ የፋይናንስ ጉዞ ላይ ነው ብሎ መናገር እንደሚከብድ አብራርተዋል።
ዋልያዎቹ ቀሪዎቹን ሁለት ጨዋታዎች በሜዳቸው የማካሄድ ጉዳይን በተመለከተ ዋና ጸሐፊው ከጋዜጠኞች ለተነሳላቸው ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ “ከስታዲየም ጋር ተያይዞ እኛ ከባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ጋር ነው እየተነጋገርን ያለነው። በተጨማሪም በአንድ መድረክ ከጠቅላይ ሚኒስትር ማኅበራዊ ዘርፍ አንድ ተወካይ መጥተው ጥያቄያችንን አቅርበናል። ገና ድልድሉ ሳይታወቅ እንደ ኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አቋማችንን አሳውቀን ነበር። እንግዲህ ለሚመለከተው አካል ጥያቄው ቀርቧል ወይስ አልቀረበም የሚለውን ማጣራት ያስፈልጋል። ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ጉዳዩን በደንብ ያውቀዋል። የጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮም እንደዛው፣ ግን ጥያቄው ለሚመለከተው አካል ቀርቧል የሚለው መታየት አለበት። እኛ አሁንም መግፋታችንን እንቀጥላለን” በማለት ተናግረዋል።
“እኛ ስለ አዲስ አበባ ስታዲየም ብቻ አይደለም የምናወራው” ያሉት አቶ ባህሩ፣የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር በባለቤትነት ከሚያስተዳድራቸው ስታዲየሞች መካከል የአዲስ አበባ ስታዲየም ላይ የማሻሻያ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ጠቁመዋል። ቶሎ ለማድረስም ሙከራ ላይ መሆናቸውን ገልጸው ፌዴሬሽኑም የተመለከታቸው ነገሮች እንዳሉ አብራርተዋል። የፌዴሬሽኑ ፍላጎት የትኛውም ስታዲየም ቶሎ እንዲደርስና ዋልያዎቹ ጨዋታቸውን በአገራቸው እንዲያደርጉ መሆኑን አያይዘው ገልጸዋል።
“የባህር ዳር ስታዲየም ጥቃቅን ስራ ብቻ አይደለም የሚቀረው። ይሄንን ሁሉም ሰው ሊያውቀው ይገባል። በጣም ብዙ ነገር ነው የሚቀረው። ስታዲየሙ ትልቅ ነው ግን የጎደሉት ነገሮች ጥቃቅን ናቸው ብለን የምንተዋቸው አይደሉም፣መመርመር አለብን። ቢያንስ አንድ ቦታ ላይ የስትራክቸር ችግር እንዳለበት (የሚዲያ እና የቪ አይ ፒ) ተነስቷል። ይሄንን ለማስተካከል ምን ያህል ወጪ ይጠይቃል። ሌሎችን የተዘረዘሩትን ነገሮችንም መመልከት ያስፈልጋል። አሁን እኩል ትኩረት ተሰጥቶ ስታዲየም እንዲደርስልን እንፈልጋለን። ግን በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚደርስ ስታዲየም ካለ እሰይ የሚያሰኝ ስለሆነ እዛ ላይ ትኩረት ይደረግልን ነው እያልን ያለነው” በማለት ዋና ጸሐፊው ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ዋልያዎቹ በመጪው መስከረም የሚያደርጉት ጨዋታ ከመድረሱ በፊት በተቻለ መጠን የአዲስ አበባ ስታዲየምን ለውድድር ለማድረስ እንደሚሰራ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ለፌዴሬሽኑ መናገሩን የጠቆሙት አቶ ባህሩ፣ ጨዋታዎቹን በገለልተኛ አገር መጫወት የፌዴሬሽኑ አስተዳደራዊ የሆኑ ወጪዎች ላይ ከፍተኛ የሆነ ጫና እንደፈጠረ ተናግረዋል። እነዚህን አስተዳደራዊ ወጪዎች ፌዴሬሽኑ በተለያዩ መንገዶች ለመሸፈን ሞክሯል።
ዋልያዎቹ ቀጣዮቹን ጨዋታዎች በሜዳቸው ማድረግ ካልቻሉ ፌዴሬሽኑ ምን አይነት አማራጭ እቅድ እንዳስቀመጠ ለተነሳው ጥያቄ “ስለቀጣይ ለማውራት ከባድ ነው ግን ማላዊ ያለው ነገር በጣም ጥሩ ነው። ግን ይሄንን የሚወስነው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ነው። ስለዚህ አንዱ አገር ላይ ውሳኔው ይተላለፋል። እኛ ግን አሁንም ይሄኛው የሚያልቅልን ከሆነ ስቃያችን ይቀንሳል ብለን ነው የምናስበው። ያለበለዚያ ግን ከፍተኛ ችግር ውስጥ ነው እየገባን የምንሄደው” በማለት አቶ ባህሩ ምላሽ ሰጥተዋል።
ኢትዮጵያ በከፍተኛ ወጪ እያስገነባችው የሚገኘውን የአደይ አበባ ብሔራዊ ስቴድየምን በተመለከተ ካፍ ግንባታውን ከአመት በፊት አህመድ ሀራስ በሚባል የክለብ ላይሰንሲንግ ባለሙያ አማካኝነት መመልከቱን ያስታወሱት አቶ ባህሩ፣ ባለሙያው ስታዲየሙ አስፈላጊ መስፈርቶችን ባሟላ መልኩ እየተገነባ እንደሚገኝ አስተያየት መስጠታቸውን ገልጸዋል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ሰኔ 9/2014