ዲያሊስስ፡- የሕክምናው ሳይንስ፤
ዲያሊስስ – ከባእድ ቋንቋ ተላምዶ ቤተኛ የሆነ የተውሶ ስም ነው፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች ኩላሊት ችግር ሲያጋጥመው ማስወገድ ያልቻላቸውን ቆሻሻዎችና ትርፍ ፈሳሾች ከደም ውስጥ በእጥበት የሚወገድበት የሕክምና ዘዴ የኩላሊት እጥበት (ዲያሊስስ (Dialysis) በመባል ይታወቃል፡፡ እጥበቱ የሚከናወነው ዲያሊሴት በተባለ የተለየ የፈሳሽ ውህድ አማካይነት ሲሆን፤ ፈሳሹ ከንጹሕ ውሃና ከኬሚካሎች ጋር ተቀላቅሎ ለዚሁ ዓላማ የሚዘጋጅ ነው፡፡ ጥንቃቄ በታከለበት የሕክምና ትግበራ ሰውነታችን የሚፈልጋቸውን ንጥረ ነገሮች ለይቶ በማስቀረት ቆሻሻውን ከደማችን ውስጥ ገፍቶ በማውጣትም ተግባሩን ያከናውናል፡፡
የዘርፉ ሕክምና እንዳረጋገጠው ዲያሊስስ የዕድሜ ልክ ክትትል የሚያስፈልገው ሕክምና ነው፡፡ ኩላሊት አንድ ጊዜ ሥራውን ካቆመ በሕይወት ለመሰንበት ቢያንስ በሣምንት ሦስት ያህል ጊዜያት የዲያሊስስ ሕክምናን መውሰድ ግድ ይላል፡፡ ያውም ለእድሜ ልክ። በአሁኑ ውቅት በአገራችን በከፍተኛ ደረጃ እየተስፋፉ ካሉ የጤና ችግሮች መካከል አንዱ ከኩላሊት ጋር የተያያዘ ሕመም መሆኑን የጤና ተቋማት በየጊዜው እየገለጹ ይገኛሉ፡፡
ችግሩ ሥር ሰዶ ኩላሊት ፈጽሞ መሥራት ካቃተውና ታማሚው ከለጋሾች ተመሳሳይ የሆነ ኩላሊት ካገኘም በንቅለ ተከላ የረቀቀ ሳይንሳዊ የሕክምና ጥበብ የተጎዳው ኩላሊት ወጥቶ አዲሱ ሊተካለት ይችላል፡፡ ለኩላሊት ሕመም ላለመጋለጥ ዋነኛው መከላከያ ዘዴ ጤናማ የአመጋገብና የአኗኗር ዘይቤን መከተሉ አማራጭ የሌለው የቅድመ መከላከያ መፍትሔ መሆኑንም ባለሙያዎች አስረግጠው ይመክራሉ፡፡
ዘረኝነት፡- የከፋው የማንነት ቀውስ በሽታ፤
ዘረኝነት አንድን ሕዝብ፣ ብሔርን፣ ጎሳን፣ ቡድንን ወይንም ግለሰብን በቀለሙ፣ በዘሩ፣ በቋንቋው፣ በባህሉ፣ በአቋሙ፣ ወይንም በአጠቃላይ ማንነቱ በመፈረጅ “እኔ ወይንም የእኔ የሆነው ሁሉ ከሌሎች የሚበልጥበትና የሚለይበት ባህርይ አለው” ብሎ የሚያምን የተንሸዋረረ አመለካከት ነው፡፡ መገለጫውም ንቀት፣ ማጥላላት፣ ማራቅ፣ ማግለል፣ ማፈናቀል፣ ዘረፋ፣ አካላዊ ጥቃት ሲከፋም እስከ ግድያና የቁስ ውድመት ሊያስከትል የሚችል ክፉ የማንነት ቀውስ ውጤት ነው፡፡
ከዘረኝነት ክፉ ደዌ የነጻ አገር ስለመኖሩ እርግጠኛ ለመሆን ያዳግታል፡፡ መገለጫው ይለያይ እንጂ በዚህ ክፉ በሽታ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ያልተመረዘ አገር ይኖራል ብሎ ለማመን ይከብዳል፡፡ የዘረኝነቱ በሽታ የጸናባቸው በርካታ አገራት ምን ያህል የከፋ ታሪክ እንዳስተናገዱ ተደጋግሞ ስለተገለጸ ዝርዝሩን ማቅረቡ እጅግም ላያስፈልግ ይችል ይሆናል፡፡ ከቅርብ ዓመታት ዘግናኝ ታሪኮች አንዱን ብቻ አስታውሰን ወደ ኋላ ብናፈገፍግ በዋነኛነት ወደ አእምሯችን የሚመጣው በሁቱና በቱትሲ ብሔረሰቦች መካከል ዘረኝነት ሰበብ ሆኖ ሩዋንዳ ያለፈችበት ዘግናኝ እልቂት የሚዘነጋ አይሆንም፡፡
እ.ኤ.አ ከኤፕሪል 7 እስከ ጁላይ 15 ቀን 1994 በቆየው የ100 ቀናት የዘረኝነት የእርስ በእርስ የእልቂት ቆይታ ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ሩዋንዳዊያን እንደረገፉ በጥቁር የታሪካቸው ገጽ ውስጥ ተመዝግቧል፡፡ በአውሮፓ ውስጥ የነበሩ ስድስት ሚሊዮን አይሁዳዊያን ያለቁበት የሆሎኮስት እልቂትም ሌላው የሚታወስ የዘረኝነት ክፉ የጥፋት ታሪክ ነው። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ከ1941 – 1945 የናዚ ጀርመንና ተባባሪዎቻቸው የፈጇቸው እነዚህ ንጹሐን የዓለም ዜጎች ደማቸው ደመ ከልብ የሆነው በተለምዶ አይነት የግድያ ግፍ ብቻ ሳይሆን ለጆሮ የሚሰቀጥጡና ሰብአዊ ፍጡር ይፈጽማቸዋል ተብሎ በማይገመቱ በርካታ ድርጊቶች ጭምር ነበር፡፡ ዘረኝነት ክፉ ተብሎ የሚገለጽ ብቻ ሳይሆን ከሰይጣናዊ ግብር ጋር የሚስተካከል እንደሆነም ውጤቱ ያረጋግጥልናል፡፡
ራሷን የፍጹም ዲሞክራሲ መገለጫ አድርጋ የምትቆጥረውና በፕሮፓጋንዳ ሞገዶቿና ተግባሯ የዓለምን ማኅበረሰብ ለማሳመን መዘናጋትን የማታውቀው አሜሪካ ይሏት አገር ምን ያህል በዘረኝነት እየተናጠች እንዳለች ታሪኳ ብቻ ሳይሆን የዕለት ተዕለት ዜናዎችም ሳይቀሩ የዘረኝነቱን ጥግ በግላጭ እያሳዩን ነው፡፡
በተለየ ሁኔታ ለአውሮፓ አሜሪካዊያን በሚያደላውና በነጭ አንግሎ ሳክሰን አምላኪነቱ ሥር የሰደደው “ነጭ የሰው ዘሮች ከሁሉም የዓለም ዜጎች ይበልጣሉ” እምነታቸው በተለይም በጥቁር አፍሪካ አሜሪካዊያን፣ በስደት አፈሯ ላይ በሚኖሩትና በነባሮቹ ሕዝቦቿ ላይ ሁሉ ሳይቀር ሲያደርስ የኖረውና እያደረሰ ያለው ኢሰብዓዊ ድርጊቶች ምን ያህል የዘረኝነቱ በሽታ ጠልቆ እንደበቀለ የሚያረጋግጥ ነው፡፡ ታዳጊ ሕጻናት ሳይቀሩ ጠብመንጃ አንግተው “የማይሞተው የሰው ልጅ ማደጊያ ሥፍራ” እየተባለ በሚከበረው ት/ቤት ውስጥ እየገቡ ጭምር በዘረኝነት አብደው የፈጇቸውን ንጹሐን ታዳጊዎችና ወጣቶችን በተመለከተ ስንሰማ መኖራችን ብቻም ሳይሆን ድርጊቱ ዛሬም ድረስ በጠራራ ፀሐይ እየተፈጸመ እንዳለ የምናስተውለው ነው፡፡
በጥቁር ቀለማቸው ምክንያት የግፍ ዋንጫ የተጎነጩትን፣ በአደባባይ ተገድለው ያለፉትን፣ ሰላማዊ ሕይወት እየመሩ ባሉበት ሁኔታ የተዘረፉትንና ለአካላዊ ጉድለት የተዳረጉትን፣ ከመኖሪያ አካባቢያቸው የተፈናቀሉትን ወዘተ. ታሪክ እያጣቀስን ብቻም ሳይሆን እየተፈጸሙ ያሉትን እውነታዎች እየዘረዘርን የዚህቺው አሜሪካ ተብዬ ገመና ብንፈትሽ በዚያች አገር የዘረኝነት ከፍታ ጣሪያ እንደነካ ለመገንዘብ ይቻላል፡፡ ጉዳዩ የፖለቲካዊ ሴራ ውጤት ብቻ ሳይሆን የሆሊ ውድ ፊልሞች እና የጥበብ ሥራዎቻቸው ሳይቀሩ ይህንኑ ክፉ ደዌ እያግለበለቡ አገሪቷን እያመሱ ስለመሆናቸው ማስረጃዎችንና መረጃዎችን በገፍ ማቅረብ ይቻላል፡፡
<<እከሌ ሲታማ ለእኔ ብለህ ስማ!>>
የዘረኝነቱ ወረርሽኝ እኛም ቀዬ በቅሎ፣ ተኮትኩቶና አድጎ ፍሬ ማፍራት ከጀመረ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ “ዘርህና ብሔርህ ከእኔ ዘርና ብሔር ያነሰ ነው፤ እኔና አንተ በማይታረቁ ቅራኔዎች ተወጥረን የኖርን ነን ወዘተ.” በሚሉ ፖለቲካ ወለድ ትርክቶች ሳቢያ አገራችን ያለፈችባቸውንና እያለፈችባቸው ያሉትን መከራዎች እንደ ዘበት እየሰማንና እያስተዋልን “በእንባና በሆቸ ጉድ!” ሀዘንና ግርምት እንደቆዘም አለን፡፡
በዚህ የዘረኝነት ክፉ ጦስ የምን ያህሎቹን ወገኖቻችንን የእልቂት መርዶ እንደሰማን፣ የምን ያህሉን ስደትና መፈናቀል እንደባጀን እንዘርዝር ብንል እንኳ ከብዛቱ የተነሳ ማስቸገሩ አይቀርም፡፡ የዕለት ሪፖርቶችን እየሰቀጠጠንና እያስነባን ማድመጣችንን ለማረጋገጥም “ያየ ወይንም የሰማ” ተብሎ የሚጠራ ምስክር አያስፈልግም – የሁላችንም ጉዳይ ስለሆነ፡፡
ምን ያህል ወገኖቻችን በግፈኛ ዘረኞች ጭዳ እንደሆኑ፣ ምን ያህሉ ከኖረበት አካባቢውና ቀኤው እንደተፈናቀለ፣ ንብረቱና ሀብቱ ወድሞ በአንድ ጀንበር ለልመና እንደተዳረገ ብዙ ማስረጃዎችን መዘርዘር ይቻላል፡፡ ዘረኝነት ጥንብ ነው፣ ይሸታል፣ ይከረፋል፣ ደዌውም በቀላሉ የሚፈወስ አይደለም፡፡
ይህንን መሰሉን የዘረኝነት ጥዩፍ ባህርይና የሚያስከትለውን አደጋ በተመለከተ ከፈረንጆች የጥናት ሊትሬቸር፣ ከዓለም አቀፍ ተቋማትና መገናኛ ዘዴዎች ጭምር ሪፖርትና ዜናዎችን በመቃረምና በማንበብ አእምሯችን ጢም ብሎ ስለሞላ ደግመን ደጋግመን እየከለስን ጉዳዩን እንደ እለት ስንቅ ተሸክሞ መዞሩ ብዙም አስፈላጊ አይመስለንም፡፡
እስቲ ሌላውን ገጽታ እንፈትሸውና የዘረኝነትን ክፉ ወረርሽኝ ለማየት እንሞክር፡፡ ቅዱስ መጽሐፍ “ወደ ግብዣ ቤት ከመሄድ ይልቅ ወደ ልቅሶ ቤት እንድንሄድ” ይመክረናል፡፡ ምክንያቱን ሲያብራራም “እርሱ ለሰው ልጆች ፍጻሜ ማሳያ መልካም መስታወት” መሆኑን በማስረገጥ ጭምር፡፡ በማስከተልም ሰው የፈለገውን ያህል ሺህ ዓመት በምድር ላይ ቢኖር ፍጻሜው የታወቀ ነው፡፡ “አፈር ነውና ወደ አፈር መመለሱ አይቀርም፡፡”
የተሸከመው ገላ የአፈር ቁልል ከሆነ ዘንዳና ሁሉም ሰው ወደዚያው አፈር እንጂ የተለየ የበድን ማረፊያ እንደሌለው እውነት ሆኖ እያለ የሰው ልጅ በብሔሩ፣ በጎሳውና በማንነቱ ሌላውን የፈጣሪ አምሳል እንዴት አሳንሶና አዋርዶ ለመመልከት የሞራል ድጋፍ ሊያገኝ ተቻለው? ነፍስ ይማር እና ድምጻዊት ብዙነሽ በቀለ ቀደም ባሉት ዘመናት የምትታወቅበት አንድ ዝነኛ ሙዚቃ ነበራት፡፡
<<አሸብርቆ ደምቆ እንደ ፀሐይ፣
ተውቦና አጊጦ የምናይ፣
የዛሬው አበባ ገላችን፣
ነገ የአፈር ቀለብ ነው ስጋችን፣
ምንም ብንጓጓለት፣ ብንስገበገብለት፣
ይፈርሳል በጊዜያቱ፣ ሥጋ ነውና ከንቱ፡፡>>
የዚህን ዜማ ግጥም የደረሰው የማንዶሊኑ ጠቢብ አየለ ማሞም ሆነ ዜማውን በተስረቅራቂ ድምጽ የተጫወተችው ብዙነሽ በቀለ፤ ሁለቱም ዛሬ በሕይወት የሉም፡፡ ከእነርሱም በኋላ ብዙዎች አልፈው ከመቃብር በታች ውለዋል፡፡
መቃብር ቀይ፣ ጥቁር፣ ቢጫ፣ ጠይም እያለ ልዩነት ሳያደርግ የሰው ልጆችን በሙሉ በድን ከማስተናገድ ሥራው ቸል ብሎ አያውቅም፡፡ “አፈር ነህና ወደ አፈር ትመለሳልህ” የሚለው መለኮታዊ ትዕዛዝ ለማንም የሚቀር ጥሪ አይደለም፡፡ በዘረኝነት አብደው ጨርቃቸውን የጣሉት ሕመምተኞች እንዴት ይህ ተፈጥሯዊ እውነታ ሊሰወርባቸው ቻለ?
እያንዳንዱ ሰው የተሸከመው ገላ አፈር ከሆነ ዘንዳ በዚያ አፈር ላይ ምን ተዘርቶ ቢበቅል እንደሚሻል እንዴት ይጠፋቸዋል፡፡ “የእናት ምድር አፈር ቸር ነው።” የእህል ዘር ቢዘሩበት እጥፍ አድርጎ መልሶ ይክሳል፡፡ አበባ ቢዘራበት አበባ ያበቅላል፡፡ እሾህ ከተዘራበትም መልሶ የሚያሳፍሰው ምርት እሾህ ነው፡፡ እንክርዳድም ቢዘራበት እንደዚያው፡፡ ዘረኝነትም እንደዚያው ነው። በማሳው ላይ የሚዘራው ጥላቻ ስለሆነ ምርቱም ያው ጥላቻ ነው፡፡ የማመዛዘን ልዩ ችሎታ የተለገሰው የሰው ልጅ እንዴት “ሟች ገላ” ተሸክሞ እንደ ነዋሪ ፍጡር በዘረኝነት አብዶ ይከንፋል፡፡ የውስጥ መታወር እንደ መንጋ ስለሚመራ ቆም ብሎ ማሰቡ ማስተዋል ነው፡፡
ማንነትን በክፋት በክሎ በጥላቻ ያደፈ የዘረኝነት ልክፍት ልክ እንደ ሕክምናው በማስተዋል ዲያሊስስ መታጠብ እስካልቻለ ድረስ ተጎጂ የሚሆነው ዞሮ ዞሮ ራሱ በዘረኝነት የተለከፈው ግለሰብ ወይንም ቡድን ነው፡፡ የዘረኝነት ክፉ ደዌ የሚፈወሰው የሰብዓዊነት ክብርን ተቀብሎ “እከሌም እንደ እኔው ሰው ነው፤ ያ ቡድንም እንደኔው ቡድን ሰብዓዊ ነው” የሚል እምነትን በውስጥ ማጎልበት ሲቻል ብቻ ነው፡፡ ቆሻሻና የተበከለ ደም ከኩላሊት ውስጥ እንዲወገድ በዲያሊስስ እንደሚታጠበው ሁሉ ቆሻሻው ዘረኝነትም በፍቅርና በመቀባበል ታጥቦ ሊነጻ ይገባል፡፡ ይህ ገለጻ ጊዜያዊ ስሜት የሚሟሟቅበት መቆስቆሻ ሳይሆን እውነታ ነው፡፡
ለዘር ማንነት ክብርን መስጠት፣ የራስ የሆነን ማድነቅና ማድመቅ በራሱ ክፋት የለበትም። ማንኛውም ሰው የተገኘበት ዘር፣ ባህል፣ ቋንቋ ወዘተ. አለው፡፡
የራሱን አክብሮ እንደሚጠብቅና እንደሚንከባከብ ሁሉ የሌላውንም እንዲሁ በእኩልነት ተቀብሎ ሊያደንቅና ሊያከብር ይገባል፡፡ ይህ ነው ከዘረኝነት መፈወሻው የዲያሊስስ ምሥጢሩ፡፡ ሰላም ይሁን !
(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን ሰኔ 8 /2014