ለአምስት ተከታታይ ቀናት በሞሪሽየስ አዘጋጅነት ሲካሄድ ቆይቶ ከትናንት በስቲያ በተጠናቀቀው ሃያ ሁለተኛው የአፍሪካ አትሌቲክስ ቻምፒዮና ኢትዮጵያ አምስተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች። በቻምፒዮናው በ4 ወርቅ፣ 6 ብርና 4 ነሃስ በአጠቃላይ 14 ሜዳልያ መሰብሰብ የቻለው የኢትዮጵያ ልኡካን ቡድን ዛሬ ወደ አገሩ ሲመለስ በአራራት ሆቴል በሚደረግለት የአቀባበል መርሃግብር ላይ እንደሚሸለም ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ኢትዮጵያ ከሃምሳ በላይ አትሌቶችን በአጭር፣ መካከለኛና ረጅም ርቀቶች፣ በ3ሺ ሜትር መሰናክል፣ በርምጃና በሜዳ ተግባራት ውድድሮች በቻምፒዮናው አሳትፋለች። በዚህም አትሌት ሞገስ ጥኡማይ በወንዶች 10ሺ ሜትር የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳሊያ ማስመዝገብ የቻለ ሲሆን ጭምዴሳ ደበሌ በዚሁ ውድድር የብር ሜዳሊያ ማጥለቅ ችሏል። በወንዶች 3ሺ ሜትር መሰናክል ኃይለማርያም አማረ የወርቅ ሜዳሊያ ሲያስመዘግብ ታደሰ ታከለ በዚሁ ውድድር የብር ሜዳሊያውን ወስዷል። አትሌት ኃይለማርያም አማረ በቻምፒዮናው የመጨረሻ ቀን ውድድርም በ5ሺ ሜትር ሁለተኛውን የወርቅ ሜዳሊያ በማጥለቅ በሞሪሽየስ አስደናቂ ጊዜን ማሳለፍ ችሏል። አራተኛው የወርቅ ሜዳሊያ በሴቶች 3ሺ ሜትር መሰናክል በአትሌት የወርቅውሃ ጌታቸው ሲመዘገብ በዚሁ ውድድር ዘርፌ ወንድማገኝ የብር ሜዳሊያ ማጥለቅ ችላለች።
በሴቶች ስምንት መቶ ሜትር አትሌት ነጻነት ደስታ የብር ሜዳሊያ ያስመዘገበች ሲሆን በሴቶች 5ሺ ሜትር በተመሳሳይ አትሌት ፋንታዬ በላይነህ የብር ሜዳሊያ ማጥለቅ ችላለች። በ20 ኪሎ ሜትር የሴቶች ርምጃ ውድድር አትሌት የኋልዬ በለጠው ተጨማሪ የብር ሜዳሊያ ስታስመዘግብ በተመሳሳይ የወንዶች ውድድር አትሌት ዮሐንስ አልጋው የነሐስ ሜዳሊያ ማጥለቅ ችሏል። በሴቶች 10ሺ ሜትር መሰረት ገብሬ፣በ1500 ሜትር ሴቶች አያል ዳኛቸው፣1500 ሜትር ወንዶች አዳነ ካሳይ የነሐስ ሜዳሊያ ያስመዘገቡ አትሌቶች ናቸው።
ኬንያውያን አትሌቶች ለበርካታ አስርት ዓመታት በአፍሪካም ይሁን በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚካሄዱ የ3ሺ ሜትር መሰናክል ውድድሮች በሁለቱም ጾታ ፍጹም የበላይነት እንዳላቸው ይታወቃል። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን ይህ ታሪክ በግል ውድድሮች ጭምር እየተገለበጠ እንደመጣ በርካታ ማሳያዎች አሉ። በ22ኛው የአፍሪካ አትሌቲክስ ቻምፒዮና ሞሪሺየስ ላይ በርቀቱ የተመዘገበው ውጤትም አንዱ ማሳያ ሆኗል። ኢትዮጵያውያን በሁለቱም ጾታ በርቀቱ የወርቅና የብር ሜዳሊያዎችን በማጥለቅ የኬንያውያን ባህል የሆነውን ውድድር እየወረሱ እንደሚገኙ አስመስክረዋል።
በዚህ የአፍሪካ ቻምፒዮና በርምጃ ውድድሮች በሁለቱም ጾታ የተመዘገቡ ውጤቶችም ለኢትዮጵያ አበረታች ሆነው የተጠቀሱ ሲሆን ባልተለመዱ ርቀቶችም በርካታ የዲፕሎማ ውጤቶች ተመዝ ግበዋል። ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ አሁንም ባልተለመዱ ርቀቶችና ውድድሮች ወደ ውጤታማነት መምጣቷ አበረታች የመሆኑን ያህል ውጤታማ በሆነችባቸው ርቀቶች ውጤቷ እየሳሳ መሄዱ አሳሳቢ እንደሆነ በሞሪሺየሱ ቻምፒዮና ታይቷል። ኢትዮጵያ ውጤታማ ባልነበረችባቸው ርቀቶች አዳዲስ ክብሮችን የማሳካቷን ያህል ቀድሞ ውጤታማ በሆነችባቸው ውድድሮች በጥንካሬዋ ብትቀጥል ምናልባትም በዚህ የአፍሪካ ቻምፒዮና የተሻለ ውጤት ይዛ የማጠናቀቅ እድል ይኖራት ነበር። ያም ሆኖ አሁን የተመዘገበው ውጤት ቀላል ቦታ የሚሰጠው አይደለም።
በአጠቃላይ በሃያ ሁለተኛው የአፍሪካ አትሌቲክስ ቻምፒዮና ኬንያ ባህሏ የሆነው የ3ሺ ሜትር መሰናክል ውድድርን በሁለቱም ጾታ በኢትዮጵያ የበላይነት ቢወሰድባትም 10 ወርቅ፣ 5 ብር፣ 8 ነሐስ በአጠቃላይ 23 ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ ቀዳሚውን ደረጃ ይዛ አጠናቃለች። ደቡብ አፍሪካ በ9 ወርቅ፣ 13 ብር፣ 14 ነሐስ በአጠቃላይ በ36 ሜዳሊያዎች ሁለተኛ ሆና አጠናቃለች። 5 ወርቅ፣ 3 ብር፣ 3 ነሐስ በአጠቃላይ 11 ሜዳሊያ የሰበሰበችው ናይጄሪያ ሶስተኛ ደረጃን ይዛ ጨርሳለች። አልጄሪያ ከኢትዮጵያ በልጣ ለማጠናቀቅ 5 ወርቅ፣ 3 ብር፣ 1 ነሐስ በአጠቃላይ 9 ሜዳሊያ መሰብሰብ ችላለች።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ሰኔ 7 /2014