‹‹ለአገር እድገትና ብልፅግና የሴቶች ሁለንተናዊ ተሳትፎ ወሳኝ ነው›› ሲባል ብዙ ጊዜ ይደመጣል።በሚነገረው ልክ ግን አሁንም ድረስ በተሟላ መልኩ ሴቶችን ያሳተፈ የልማት እንቅስቃሴ ሲካሄድ አይታይም።የሴቶች ሁለንተናዊ ተሳትፎም ሙሉ በሙሉ ተረጋግጧል ማለት አይቻለም።ይሁንና ከለውጡ በኋላ ሴቶችን በአመራርነት በማሳተፍ፣ በማህበራዊና በፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይም በንቃት እንዲሳተፉ በማድረግ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴዎች እየታዩ መጥተዋል።
ሴቶች ሃብት ንብረት እንዲያፈሩ የተሰሩ ሥራዎችም ገና ብዙ ቢቀራቸውም በዚህ ለውጥ ጊዜ ጭላንጭሎች ታይተዋል።በተለይ ደግሞ ሴቶችን በከተሞች አካባቢ ሁሉን አቀፍ በሆነ መልኩ ተጠቃሚ ማድረግ ለከተሞች እድገትም ሆነ ገፅታ ግንባታ አይነተኛ ሚና ይጫወታል።በመሆኑም በዚህ ላይ ትኩረት አድርጎ መስራት ከፌደራልም ሆነ ከክልል መንግስታት ብዙ ይጠበቃል።
ይህንኑ ታሳቢ በማድረግም የሲዳማ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ርእሰ መስተዳደር ጽህፈት ቤት ከሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽህፈት ቤትና ከከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን መምሪያ ጋር በመቀናጀት “የሴቶች ተጠቃሚነት በከተማ ገፅታ ግንባታ ወሳኝ ሚና አለው” በሚል መሪ ቃል ከሰሞኑ የንቅናቄ መድረክ በሀዋሳ ከተማ አካሂዷል።
የንቅናቄው ዋነኛ አላማም ሴቶች እንደከተማ ልማት በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ላይ እና በገፅታ ግንባታ ሥራ ላይ ያላቸውን ተጠቀሚነትና እኩልነት ለማረጋገጥ መሆኑ ተነግሯል። በዚህ የንቅናቄ መድረክ የክልል ከተሞች ሥራ ኃላፊዎች፣ ልዩ ልዩ የማህበረሰብ ክፍሎች፣ አመራሮች፣ የእምነት ተቋማትና ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ተሳትፈው ለሴቶች ተጠቃሚነት ጠቃሚ ግብአቶች ተሰብስበዋል።
ወይዘሮ ደሚቱ እጀታ በሐዋሳ ከተማ አስተዳደር አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ፍላዴልፊያ ቀበሌ ታጋይ መንደር ነዋሪ ናቸው።በሚኖሩበት መንደርም የመንደር ተጠሪ ሲሆኑ፤ የመሰረታዊ ድርጅት አመራርም ናቸው።ከውሃ አጣጫቸው ጋርም ጋብቻ መስርተው አምስት ልጆችን አፍርተዋል።
በዚህ የለውጥ ሂደት ውስጥ ከሌሎች የመንደሩ ሴት ነዋሪዎች ጋር በመሆን ሥራዎችን እያከናወኑ እንዲሚገኙና በአሁኑ ጊዜ ሴቶች በብዙ መልኩ ተጠቃሚ መሆናቸውን ይገልፃሉ።ሴቶች ከወንዶች እኩል መስራት እንደሚችሉና እርሳቸውም ሆኑ እርሳቸው በሚኖሩበት መንደር ውስጥ ያሉ ሌሎች
ሴቶች የተሰጣቸውን እድል ተጠቅመው በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ላይ በመሰማራት ውጤታማ እየሆኑ እንደሚገኙም ይናገራሉ።በአመራርነትም በመሳተፍ የመምራት ብቃት እንዳላቸው እያረጋገጡ መሆናቸውንም ይጠቅሳሉ።
እርሳቸው በሚኖሩበት መንደር የሴቶች የሶስትዮሽና የልማት መሰረታዊ ድርጅት ቡድን መኖሩንና ምሽት ላይ ለጥበቃ ከወንዶች እኩል እንደሚወጡ ያስረዳሉ።በመንደራቸው ሴቶች የከተማ ግብርናና የከብት እርባታ ዘርፍ ውስጥ በመሳተፍ ከወንዶች እኩል የራሳቸውን ሃብት እያፈሩ እንደሚገኙም ይጠቅሳሉ።በተመሳሳይ ሴቶች በአመራርና በውሳኔ ሰጪነት በመንደሩ ንቁ ተሳትፎ እያደረጉ እንዳሉም ወይዘሮ ደሚቱ ይናገራሉ።
ሴት በቅድሚያ ቤቷንና ልጆቿን መምራት አለባት የሚሉት ወይዘሮ ደሚቱ፤ ቤቷንና ልጆቿን መምራት ከቻለች አካባቢዋን ከፍ ሲል ደግሞ አገሯን ለመምራት ምንም እንደማያዳግታት ያመለክታሉ።ነገር ግን አሁንም በተሳሳተ አመለካከት፣ በፍርሃትና በይሉንታ ምክንያት ወደኋላ የቀሩ ሴቶች መኖራቸውን አልሸሸጉም።
ሴቶች እነዚህን ጎታች ምክንያቶች ወደኋላ ትተው ወደፊት መውጣት እንዳለባቸው የሚመክሩት ወይዘሮ ደሚቱ፤ እርሳቸው በሚኖሩበት መንደርም በልማት ቡድን በኩል የጋራ ውይይት እንደሚካሄድና ሴቶች በቤታቸው ያለው ችግር ምን እንደሆነ እንዲያወሩና አጥሮ የያዛቸውን ነገር ሰብረው እንዲወጡ የማስተማር ሥራ እንደሚሰራ ያብራራሉ።
የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ልማትና ኮንስትራክሽን መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ ታሪኩ ታመነ እንደሚናገሩት፤ የሴቶች ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት መረጋገጥ ለከተማ ልማትና ለአገር ገፅታ ግንባታ ትልቅ ሚና አለው።በዚህም ሴቶች በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊና በፖለቲካዊ ጉዳዮች ተጠቃሚ እንዲሆኑ በሐዋሳ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን መምሪያ በኩል ሰፊ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ።
ትልቁ ሀብት መሬት እንደመሆኑ መጠንና በተለይ ደግሞ በከተማ ከሚሰሩ ሥራዎችና ሴቶችም እንደቅሬታ ከሚያቀርቧቸው ችግሮች አንዱ የመሬት ባለቤትነት ጥያቄ ነው።ከዚህ አንፃር ሴቶች መብቶቻውን ለመጠቀም፣ ከቤተሰብና ከውርስ ጋርም ያሉ ጉዳዮች ችግር እንዳይሆኑባቸው ለማድረግ ይሰራል።ይህም የሚሆነው ነገሮቹ የህግ ማዕቀፍ ሆነው እንዲቀጥሉ በማድረግ ነው።በተለይ በከተማ አስተዳደር የመሬት ምዝገባ ላይ ሴቶች በአግባቡ እኩል መብት እንዲኖራቸው ህጋዊነቱን ሊያረጋግጡ እንደሚገባም ይመክራሉ።
በዚህም በሐዋሳ ከተማ ባለፉት ዓመታት ከ12 ሺህ በላይ የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ ሥራ ተሰርቷል።በዚህ ዓመት ደግሞ ከ5 ሺህ በላይ የሚሆን የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ ሥራ ተከናውኗል።በአንዳንድ የከተማዋ ክፍለ ከተሞችም ሥራው ሙሉ በሙሉ ተጠናቋል።በተለይ ደግሞ መናኸሪያ ክፍለ ከተማ ባህል አዳራሽ አካባቢ ሥራዎች ተጠናቀዋል።አሁን ደግሞ በምስራቅ፣ መሀልና አዲስ ከተማ ክፍለ ከተሞች ላይ የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ ሥራው በትኩረት እየተከናወኑ መሆኑንም ይናገራሉ።
የከተማው የመረጃ አያያዝ ሥርዓት ትልቅ ፋይዳ ያለው በመሆኑና ለገቢ ሥራም ጭምር አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ሴቶች ለዚህ ሥራ ድጋፍ እንዲያገኙና ይህም ሲረጋገጥ በቀጣይ ህጋዊ የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ በእጃቸው እንዲኖራቸው ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሆነም ያስረዳሉ።
ሴቶች በኢኮኖሚ ተጠቃሚ በሚያደርጓቸው ሥራዎች ላይ፣ በፖለቲካ አመራርነት ላይም ራሳቸውን ማብቃት እንዳለባቸው፤ በተመሳሳይ በማህበራዊ ጉዳዮች ላይም ግምባር ቀደም ሆነው የራሳቸውን መብት ማስጠበቅና በተለይ ለከተማዋ ለሐዋሳ ውብና ፅዱ መሆን አስተዋፅኦ የሚያበረክቱ በመሆናቸው በዚህ ረገድ ሰፋፊ ሥራዎች በመምሪያው በኩል እየተከናወኑ እንዳሉም ይገልጻሉ።
እንደ ኃላፊው ማብራሪያ፤ የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ልማትና ኮንስትራክሽን መምሪያ በከተማ ከሚከናወኑ በርካታ የኮንስትራክሽን ፕሮጀክቶች ውስጥ ሴቶችን በማሳተፍ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እያደረገ ይገኛል።በተለይ ደግሞ በዩ አይ ዲ ፒ በሚደገፈው የኮብል ስቶን መንገድ ሥራ ፕሮጀክት ሰፊ ቁጥር ያላቸው ወጣቶች የሚሳተፉ ሲሆን፤ በዚህ ሥራ ውስጥ ሴቶች ሃምሳ ከመቶ እንዲወዳደሩ በማድረግ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ተደርጓል።
በብዛት ሴቶች ያሉባቸው ማህበራት ተወዳድረው አሸናፊ እንዲሆኑ የማድረግ ስራዎችን በመስራት በርካታ ሴት ወጣቶች ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ ተችሏል።
በሌሎች ፕሮጀክቶችም ድጋፍ በማድረግ የተለያዩ ጨረታዎች ሲወጡ ቅድሚያ ለሴቶች በመስጠት ይበልጥ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ሰፋፊ ሥራዎች ተሰርተዋል።በዚህም በርካታ ሞዴል የሆኑ ማህበራት ተፈጥረዋል።በተለይ በኮብል ስቶን መንገድ ሥራና በሼዶች ውስጥ ገብተው በአገልገሎትና በንግድ ዘርፎች ውስጥ የተሰማሩ ማህበራት ራሳቸውን በማብቃት ረገድ ትልቅ ደረጃ ደርሰዋል።
በዚህ በጀት ዓመት በኮብል ስቶን መንገድ ሥራ ከ200 ሺህ በላይ ወጣቶች የዚህ እድል ተጠቃሚ
ሲሆኑ፤ ከዚህ ውስጥ ከሀምሳ ከመቶ በላይ የሚሆኑት ሴት ወጣቶች ናቸው።
ሴቶች በኮንስትራክሽን ዘርፍ ተሳታፊ ሆነው ተጠቃሚ እንዲሆኑ ከማድረግ በዘለለ መብታቸውን እንዲጠቀሙ በማድረግና በማብቃት ተጨማሪ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ።ከዩ አይ ዲ ፒ በሚመደብላቸው በጀትም ሴቶች የተለያዩ ስልጠናዎችን ወስደው ራሳቸው አዘጋጅተው ራሳቸው እንዲሸጡ እየተደረገ ይገኛል።ከዚህ ባለፈ የሲ አይ ፒ እቅድ ዝግጅት ላይ ሴቶች ለብቻቸው እንዲወያዩ፣ እንዲወስኑ፣ ለየትኛው ፕሮጀክት ቅድሚያ መሰጠት እንዳለበትና ፕሮጀክቱ ሲያልቅ ምን ያህል ሴቶች ተጠቃሚ እንደሚሆኑና መሳተፍ እንዳለባቸው በመምሪያው በኩል ሰፊ ሥራ ተሰርቷል።
በከተማና መሰረተ ልማት ሚንስቴር የሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ዳይሬክቶሬት ከፍተኛ ባለሞያ የሆኑት ወይዘሮ መብራቴ አሰፋ በበኩላቸው እንደሚሉት፤ በሴቶች ዙሪያ የወጡ አዋጆች፣ ደምቦችና መመሪያዎች በአብዛኛው ክፍተት ያለባቸው ናቸው።ከዚህ አንፃር ሴቶች ከመሬት ጋር በተያያዘ ያሉ ህጎችን፣ ደምቦችንና መመሪያዎችን በመገንዘብ ለሌሎች ሴት እህቶቻቸው ማስተማር አለባቸው።
በመመሪያው መሰረት ሴቶች ከመሬት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግም መሬት አዋጅ፣ ደምብና መመሪያ ዙሪያ ያላቸውን ግንዛቤ ሊያሰፉ ይገባል።በተለይ ደግሞ የመሬት ምዝገባ ጥቅሙ ምን እንደሆነና ወደፊት መሬትን በሚገባ አስመዝግቦ ከቤተሰቦቻው ጋር ለሚሰሩ የጋራ ሥራዎች ግንዛቤው እንዲኖራቸው ያስፈልጋል።ስለመሬት ጉዳይ ሴቶች ሰፋ ያለ ግንዛቤ እንዲኖራቸው፤ ተሳታፊም ተጠቃሚም እንዲሆኑ ለማድረግም በርካታ ተግባራትን መከወን ይጠይቃል።
ባለሞያዋ እንደሚገልፁት፤ የሚንስቴሩ የሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ከመሬትና መሬት ነክ ጉዳዮች ጋር በመቀናጀት ስለመሬት የሚወጡ አዋጆችን፣ ደምቦችንና መመሪያዎችን ከመሬት ከፍል በመውሰድ ሴቶች በመብቶቻው ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ሥራዎች ይሰራሉ።በአብዛኛው ሴቶች ከዚሁ ጉዳይ ጋር በተያያዙ መድረኮች ላይ እንዲሳተፉ በማድረግ ሃሳባቸውን እንዲያጋሩ ለመብቶቻውም እንዲሟገቱ የማደረግ ሥራዎችም ይከናወናሉ።
ከታች ጀምሮ በቢሮ ደረጃ ያሉ ሴቶች በመሬት ዙሪያ እምብዛም ግንዛቤ የሌላቸው በመሆኑና አዋጆችን፣ ደምቦችንና መመሪያዎችንም ስለማያውቁ በዚህ ረገድ ግንዛቤ ኖሯቸው እንዲጠቀሙ ለማድረግም እየተሰራ ነው።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ሰኔ 7 /2014