ከሁሉ አስቀድመን ለሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር ብያኔ እናስቀምጥ። ብያኔውንም በሁሉም ዘንድ ተቀባይነትን ባገኘውና እየተሰራበት ካለው እንውሰድ። ”ሕገ-ወጥ የገንዘብ ፍሰት በጠቅላላው የአንድን አገር ድንበር አቋርጦ ሕገ-ወጥ በሆኑ መንገዶች የተገኙ ገንዘቦች የሚዘዋወሩበት መንገድ ነው። በሙስና፣ በኮንትሮባንድ፣ በወንጀል ድርጊትና ቀረጥ ላለመክፈል የሚዛወር ሂሳብ ነው።” በዚሁ ወደ ጉዳያችን እንዝለቅ።
ከኢኮኖሚ ምሁራን ጀምሮ፣ የሚመለከታቸው ሁሉ እንደሚሉት፤ እኛም እንደምናውቀው ችግሩ አገሪቱን ለበጀት ጉድለት ከማጋለጡም በተጨማሪ መፍትሄ ሳይገኝለት በምጣኔ ሀብት እድገቷ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ማሳደሩ በሳይንስ የተረጋገጠ ነው። እውነቱ ይህ ሆና ሳለ፣ ቁጥጥሩ ከመቼውም ጊዜ በላይ ተጠናክሮ ቀጥሏል ተብሎ በሚነገርበት በዚህ ወቅት፣ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በሕገ ወጥ መንገዶች ገንዘብ የማሸሽ እና የማዛወር ሙከራ ተባብሶ መቀጠሉ የሚያስገርም ብቻ ሳይሆን የሚያሳዝንም፤ የሚያሳስብም ነው።
ምን ላይ እንደተደረሰ ባናውቅም፣ ኤፕሪል 8፣ 2021 ”ፖሊስ ባደረገው ምርመራ የተቀየረው የብር ኖት 174ሺህ 350 ብር፣ እንዲሁም 605ሺህ 550 ሐሰተኛ የኢትዮጵያ ብር በማዘጋጀት፣ በመገልገልና በማዘዋወር የተጠረጠሩ ግለሰቦች ላይ ሰባት መዝገቦችን በማደራጀት እያጣራ መሆኑን ገልጿል፡፡” የሚል ዜና ሰምተን ነበር።
”በተመሳሳይ በአዲስ አበባ 99ሺህ 852 የአሜሪካን ዶላር፣ 3ሺህ 555 ድራም፣ 210 ዩሮ፣ 2ሺህ 553 ሪያል፣ 5ሺህ 495 የሱዳን ገንዘብ፣ 1ሺህ 800 የኤርትራ ናቅፋ፣ 500 የደቡብ አፍሪካ ራንድ፣ እና ከ474ሺህ 500 ብር በላይ በተደረገ ብርበራ” መያዙን ሰምተናል።
ሲቀጥልም፣”ከ1ሚሊዮን 9መቶ ሺህ (1,900,000) በላይ ብር እንዲሁም የአሜሪካ ዶላርና የኤርትራ ናቅፋ በቁጥጥር ስር መያዙን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን” አስታወቀ (ኤፕሪል 14፣ 2020) በማለት ሲል አስታውቆናል”። የአገራችን እውነታ ይሄንን ይመስላል። ለትህትና ሲባል ”ይመስላል” አልን እንጂ ”ነው”።
ዜናዎቹ ቀጥለዋል፤ የቅርቦቹን ትተን የቀድሞዎቹን እንከታተል።
ቪኦኤ (28.02.2022) እንዳቀረበው፣ ህገወጥነቱ ከጥሬ ገንዘብም ባለፈ ኢትዮጵያ በጅቡቲ መስመር ብቻ አምስት አይነት የነዳጅ ምርቶችን የምታስገባ ሲሆን በየአመቱም 4ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ነዳጅ እንደምታስገባ ይታወቃል። ይህ በኢኮኖሚው ላይ የሚፈጥረው ጫና አንሶ ጭራሽ ”ኢትዮጵያ ለውስጥ ፍጆታ ከውጪ የምታስገባው የነዳጅ ምርት በሕገ ወጥ የንግድ ሰንሰለት ወደ ጎረቤት አገራት ለገበያ እየቀረበ በመሆኑ ይህ ሲደረግ ቢገኝ ነዳጁም፣ ያንን የጫነው ተሽከርካሪም በክልል የፀጥታ ኃይሎች እንዲወረስ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ አሳስበዋል።” የሚል ዜና ሰምተናል። (ደግነቱ ኢትዮጵያ ትልቅ አገር መሆኗ በጀ እንጂ ጅቡቲን የምታክል ብትሆን፣ እንደ ሙስናው ብዛት፣ ገና ድሮ የለችም ነበር።)
ይህ ብቻ አይደለም፣ ኢዜአ (ሀምሌ 27/2013) ”አሸባሪው የሕወሓት ቡድን ከአዲስ አበባ እስከ ቶጎውጫሌ በዘረጋው ህገ-ወጥ የዶላርና የገንዘብ ዝውውር ኔትዎርክ፣ ሲጠቀምባቸው የነበሩ ሰነዶችና ገንዘብ ከነተጠርጣሪዎቹ መያዙን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ገለፀ፡፡ […] ዶላሩን ከአዲስ አበባ በጥቁር ገበያ እየሰበሰቡ መንግስትን እንዲዳከም ሲሰሩ የተደረሰባቸው መሆኑንም ተጠቁሟል፡፡
አሸባሪው ቡድን ቀድሞ በሰራው ኔትዎርክ አማካኝነት በንግድ ተቋማት የሚሰበሰቡትን ዶላሮች በህገ-ወጥ መንገድ ከአገር እንዲወጣ በማድረግ ለሽብር ቡድኑ ዋነኛ የፋይናንስ ምንጭ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ […] ፖሊስ ከወንጀል ድርጊቱ ጋር ቀጥተኛ ተሳትፎ አድርገዋል ያላቸውን 6 አለም አቀፍ የገንዘብ አስተላላፊ ድርጅቶችና 11 ግለሰቦች ከ14 ባንኮች የተከፈቱና 10 ሚሊዮን 276ሺህ 496 ብር ከያዙ ከመቶ በላይ የባንክ የሂሳብ ደብተሮች ጋር በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ መጀመሩን አስታውቋል፡፡
ጁንታው በአዲስ አበባ ህጋዊ አሰራርን ሽፋን በማድረግ መንግስት እንዲዳከምና ከውጭ ወደ አገር ውስጥ ለሚያስገባቸው ጥሬ እቃዎች የዶላር እጥረት እንዲያጋጥመው እንዲሁም የኑሮ ውድነትን አባብሶ ህዝብ በመንግስት ላይ እንዲነሳ ለማድረግ የሞከረ መሆኑንም ፖሊስ ደርሼበታለሁ ብሏል፡፡ የሽብር ቡድኑ በአገር ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጫና በመፍጠር የኑሮ ውድነት እንዲባባስ ማድረጉም ተናግሯል፡፡” (ከላይ ”በዚህ ከቀጠለች …” ያልነው ያለ ምክንያት እንዳልሆነ ልብ ይባል ዘንድ እንጠይቃለን።)
ከላይኛው ዜና መረዳት እንደሚቻለው ህገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውሩ የሚያስከትለው ጣጣ በቀላሉ የሚታይ አይደል። አገሪቱን የዶላር እጥረት እንዲያጋጥም፣ የአገሪቱ ኢኮኖሚ እንዲሽመደመድ፣ የኑሮ ውድነት እንዲባባስ … ማድረግ ድረስ የዘለቀ አደጋን ያስከትላል።
ከአህጉሪቱስ አኳያ?
ወደ አፍሪካ አህጉር እስከዛሬ ድረስ በእርዳታ መልኩ ከተለገሰው ገንዘብ ጋር ሲነጻጸር ከአፍሪካ የሚወጣው ህገ-ወጥ ገንዘብ በእጥፍ ይበልጣል። እንዴት? እንደሚከተለው።
”የግሎባል ፋይናንሻል ኢንቴግሪቲ (Global Financial Integrity) የተባለ ድርጅትን የሚመሩት ሬመንድ ቤከር አንድ ሰው በህይወቱ ሊያየው ከሚገባ በላይ ከአፍሪካ ገንዘብ በህገ-ወጥ መልኩ ሲወጣ ተመልክቻለሁ፤ በጥናትም አስደግፌ አረጋግጫለሁ ሲሉ በካፒተል ሂል ለተሰበሰቡ ተሳታፊዎች ተናግረዋል።” በማለት ለአየር ያበቃው የአሜሪካ ድምፅ ሬዲዮ ነው።
ሬመንድ “በዚህ እክል እንደ አፍሪካ ክፉኛ የተጎዳ የአለም ክፍል የለም። በአለም ዙሪያ ከታዳጊ አገሮች የሚወጣው ህገ-ወጥ የገንዘብ ፍሰት በአመት 1ትሪሊየን ዶላር ይሆናል፣” ማለታቸውንም በዛው ቶን፤ ጊዜ እና ቦታ ላይ ሆኖ አሳውቆናል። ታዲያ የአፍሪካ ሕዝብ ቢራብ፣ ቢጠማ፣ ቢጎሳቆል … ምን ይገርማል? (ይህ የጁላይ 2010 ጥናት ሲሆን፣ ዛሬ በ2022 ወንጀሉ የት ሊደርስ እንደሚችል ማንም ሊያሰላው የሚችለው ጉዳይ ነው።)
”ከ1970 እስከ 2008 ድረስ ለነበሩት 39 አመታት ከአፍሪካ በህገ-ወጥ መልኩ የወጣው ገንዘብ ወደ 850 ቢሊየን ዶላር ይገመታል። በእርግጥ ይሄ ተመን የማያካትታቸው አጠራጣሪ አሀዞች በመኖራቸው፤ ገንዘቡ ከተባለው ሊበልጥ” ይችላል። ”በዚህ ጥናት መሰረት ኢትዮጵያ ከ16 ቢሊየን ዶላር በላይ ገንዘብ የሸሸ ሲሆን ከአፍሪካ በ13ኛ ደረጃ ትገኛለች። ለንጽጽር ያህል ጎረቤት ኬንያ 7ቢሊየን ዶላር (22ኛ) ጅቡቲ 1ቢሊየን ዶላር (45ኛ) ኤርትራ 117ሚሊዮን ዶላር (51ኛ) ደረጃን ይዘዋል።” እየመረረንም ቢሆን ልንውጠው የሚገባን ”እውነት” ይሄ ነው።
”በአፍሪካ ከፍተኛ ገንዘብ በህገ-ወጥ መልኩ የሚወጣባት አገር ናይጀሪያ ስትሆን 241 ቢሊየን ዶላር፣ ግብጽ 131 ቢሊዮን፣ ደቡብ አፍሪካ 74 ቢሊየን ዶላር በመሆን ከ1-3 ያለውን” ደረጃ የሚይዙ ናቸው፤ ”ኢትዮጵያ ስንተኛ ወጣች?” ብሎ የሚጠይቅ ካለ፤ ”እንደ አያያዟ በቅርቡ 1ኛ …” የሚል ምላሽን ሊያገኝ ይችላልና እዳው ገብስ እንዳልሆነ ሁሉም ሊገነዘበው ይገባል። ይህ ከሆነ ደግሞ ጉዳዩ የግለሰቦች፣ የጥቂት ቡድኖች ወዘተ ሳይሆን የህዝብ ጉዳይ ነውና ማንም ማንንም አይታገስም፤ አያልፍምም። በዚህ በኩል ያለው ህግ የማስከበር ስራ ከፍተኛ ትኩረት የሚሻ ነው።
ያ ከመሆኑ በፊት ግን፣ ወንጀለኞችም ከወንጀላቸው እንዲቆጠቡ፤ ህብረተሰቡም ከፀጥታ ሀይሉ ጋር በመሆን ኃላፊነቱን እንዲወጣ፤ መንግስትም እንደ መንግሥትነቱ የህግ የበላይነትን እንምዲያስከብር ማሳሰቡ የዚህ ፅሁፍ አቢይ ጉዳይ ነው።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ሰኔ 7 /2014