በአገር ግንባታ ላይ የላቀ ዋጋ ካላቸው ጉዳዮች አንዱ የሀሳብ የበላይነት ነው። አብዛኞቹ የአለማችን ስልጡን አገራት ከኢኮኖሚ የበላይነት ባለፈ ሉዓላዊነታቸውን የገነቡት በዚህ የላቀ እውነታ ውስጥ በማለፍ ነው።
አሁን ላለችውም ሆነ ነገ ለምትፈጠረው አገራችን የሃሳብ የበላይነትን የመስፈን ጉዳይ ወሳኝ እንደሆነ ይታመናል። በተለይ እንደ እኛ አገር በብሔርና በቋንቋ፣ በባህልና በወግ፣ በታሪክና በስልጣኔ ለተሳሰረ ማህበረሰብ የሚያስፈልገው እንዲህ አይነቱ ፖለቲካዊና ማህበራዊ እሳቤ ነው።
አብዛኞቹ ችግሮቻችን ንትርክ ወለድ ናቸው። አብዛኞቹ ዝቅታዎቻችን ከበላጭ ሀሳብ ይልቅ ለእኔነት ሀሳብ እጅ የሰጡ ናቸው። በአጠቃላይ አሁን ላይ እየተሰቃየንባቸው ያሉ መከራዎቻችን ሁሉ ከላቀ ማህበራዊ እሳቤ እጥረት የመነጩ ስለመሆናቸው ተጠራጣሪ አለ ብዬ አላስብም። እስካሁን ድረስ እየጎዱን ያሉ ነገሮች ሁሉ እያወቅናቸው ልብ ያላልናቸው ነገሮች ናቸው።
አንድን ነገር ማወቅና መረዳት የተለያየ ነገር ነው። ብዙዎቻችን በትምህርት፣ በልምድ በተለያየ መንገድ ብዙ ነገር ልናውቅ እንችላለን የምናውቀውን ነገር የተረዳን ግን ጥቂቶች ነን። አሁን ላይ አገር እየፈረሰች ያለችው ብዙ በሚያውቁ ግን ደግሞ የሚያውቁትን ባልተረዱ ጥራዝ ነጠቆች ነው። ህዝባችን ሁሉ ነገር በድህነት ላይ ቁምጥና ሆኖበት ያለው ከአብራኩ በወጡ አዋቂ ነኝ ባይ አላስተዋዮች ነው። መረዳት ስቃይ ሆኖ አያውቅም። መረዳት አቅጣጫው ወደ መፍትሄ ነው።
እኛ ኢትዮጵያውን እያወቅናቸው ግን ደግሞ ባልተረዳናቸው ማህበራዊ ስቃይ ውስጥ ነን። ተረድተናቸው ግን ደግሞ መፍትሄ ባልሰጠናቸው ፖለቲካዊና ማህበራዊ ችግሮቻችን ውስጥ ነን። እኚህን ስቃዮቻችንን ከማወቅ አልፈን እስካልተረዳናቸው ድረስ ከእዬዬ ባለፈ ለመፍትሄ የሚሆን አቅም አናገኝም። እኚህን ችግሮቻችንን ከመረዳት አልፈን መፍትሄ እስካልሰጠናቸው ድረስ ከአበሳ አናመልጥም። መጀመሪያ ችግሮቻችንን እንረዳቸው። ከዛ በጠረጴዛ ዙሪያ እንቀመጥ። ስንቀመጥ ግን በምክክር በችግሮቻችን ላይ የበላይ እንድንሆን እንጂ ባለመስማማት ሌላ ችግር ለመፍጠር አይደለም።
ሰው ካሰበ፣ ሰው ከተፋቀረ፣ ሰው ከተነጋገረ የማይፈታው ችግር የለም። በፍጥረታት ታሪክ ውስጥ ከሰው ልጅ የሚበልጥ ችግር አልተፈጠረም። ችግሩ የእኛ ፍቅር ማጣት ነው። ችግሩ የእኛ ራስ ወዳድነት ነው። ችግሩ የእኛ ሁሉንም አለመግባባት በጦርነት ለመፍታት መሞከራችን ነው። ችግሩ የእኛ አለመነጋገር ነው። ችግሮቻችንን ከተረዳናቸው ከእኛ በታች ናቸው። ካልተረዳናቸው ደግሞ ከእኛ በላይ ሆነው እያሰቃዩን ይኖራሉ። ምስጢሩ የመረዳትና ተረድቶም በምክረ ሀሳብ መፍትሄ መስጠቱ ላይ ነው።
እኛ አገር ችግሮቹን በምክክር ያሸነፈ ፖለቲከኛ የለም። እኛ አገር ልዩነቱን በእርቅ የፈታ ቡድን የለም። ችግሮቻችንን ለፖለቲካ ትርፍ ነው የምንጠቀማቸው። እኛ አገር ችግሮቻችን ሌላ ችግር እንዲፈጥሩ እሽሩሩ ነው የምንላቸው። እኛ አገር ፖለቲከኞቻችን ስልጣን መያዝ የሚፈልጉት የማህበረሰቡን ችግር አጉልቶ በማውጣት ነው። ይሄን ድንቁር፤ አላዋቂነት ነው ።
የእኛ እውቀት ምን አይነት ነው? በእውቀታችን አገርና ህዝብ ከሚያስጨንቁት ውስጥ ነን ወይስ ያወቁትን በመረዳት ለመፍትሄ ከሚቆሙት ውስጥ? አገር ወዳድ የሆናችሁ ሁሉ ይሄን ጥያቄ በመመለስ ለአገራችሁ ብርሃን መሆን ይቻላችኋል። አንድን ነገር ለማወቅ ሳይሆን ለመረዳት ሆነን እንቅረበው። አንድን ነገር ስንረዳው መነሻ ምንጩን ብቻ ሳይሆን መድረቂያውንም እንደርስበታለን። መድረቂያውን ተረዳንው ማለት ለከበቡን ችግሮች መፍትሄ መስጠት እንችላለን ማለት ነው። ስለዚህም እንደ ዜጋ፣ እንደ መንግስት ችግሮቻችንን ከማወቅ አልፈን ልንረዳቸው ይገባል። መፍትሄ ያለው በመረዳት ውስጥ ነው።
አገር ማለት ምን ማለት እንደሆነች ብንረዳ ኖሮ ዛሬ ላይ ይሄን ሁሉ መከራ ባልፈጠርንባት ነበር። መረዳት ከማወቅ እጅግ ይበልጣል። ማወቅ እውቀት ሲሆን መረዳት ግን ጥበብ ነው። ማወቅ መነሻ ሲሆን መረዳት ግን መድረሻ ነው። ሕይወታችንን በማወቅ ሳይሆን በመረዳት መኖር ያስፈልጋል። አገራችንን በማወቅ ሳይሆን በመረዳት ውስጥ እናፍቅር። መረዳት ሕይወትን ውብ የሚያደርግ የመጨረሻው የብስለት መለኪያ ነው። አንዳንድ ሰዎች ያወቃችኋቸው ሲመስላችሁ ሌላ ሰው ሆነው ግራ አጋብተዋችሁ አያውቁም? ይሄን ሁሉ ጊዜ አብሬው ሆኜ ላውቀው አልቻልኩም ያላችሁት ሰው የለም? አለ እንደምትሉኝ እርግጠኛ ነኝ። በቃ ማወቅ ማለት እንዲህ ነው…ውስን።
በመረዳት ጥበብ ውስጥ እንገንባ። መከራዎቻችንን በመረዳት ሀሳብ ውስጥ እናሸንፍ። እየፈረስንና እየባከንን ያለነው በትንሽ እውቀት ነው። ለአገርና ለህዝብ ስጋት ሆነን የቆምንው ወንዝ በማያሻግር እውቀት ነው። ለአገር ስጋት የማይሆን እውቀትና ጥበብ ያስፈልገናል። ለትውልድ ጠንቅ ያልሆነ ፖለቲካና ፖለቲከኛ ያስፈልገናል። አንዳንዶች ዋሽተው ያስታርቃሉ፣ አንዳንዶች ደግሞ ዋሽተው ያጣላሉ። አሁናዊ የአገራችን መልክ እንዲህ አይነት ነው።
አገር የተሰራችው በእኔና በእናንተ እውቀትና መረዳት ነው። አገር የምትፈርሰውም በእኔና በእናንተ ፍቅር ማጣት ነው። ፍቅር ያስፈልገናል። ኢትዮጵያ ከምትባል ከአንድ እናት ማህጸን የበቀልን ጉራማይሌ መልኮች ነን። እንደ ርብቃ ልጆች መጋፋት ሳይሆን በመነጋገር መተቃቀፍ ነው የሚያዋጣን። በዚህ እውነት ውስጥ አዲስ ሰማይና ምድርን እንገንባ።
ጎጂ ነገሮችን ጨምሮ በሕይወታችን የምንፈልጋቸው ማናቸውም መልካም ነገሮች በእኛ አስተሳሰብ በእኛ ጭንቅላት የሚፈጠሩ ናቸው። ራሳችንን ለመልካም ነገር ካዘጋጀንው መልካም ነገርን መውረስ እንችላለን፣ በተመሳሳይ መንገድ ራሳችንን ለክፉ ነገር ካስገዛንው ያንኑ ስሜት ወደ ራሳችን እናመጣለን። የምናስበው ማንኛውም ነገር ነገ ላይ ሕይወታችን ሆኖ ወደ እኛ ይመጣል።
የነገ አለማችን ዛሬ በምንሆነው አሁናዊ ነገር የተዋቀረ ነው። ነገ ላይ ለአገርና ለወገን አስፈላጊዎች እንድንሆን በዛሬ ሕይወታችን ላይ ዋጋ ወዳላቸው ነገሮች መመልከት ይኖርብናል። አሁን ላይ አገር እየጎዱ ያሉት እኩይ ሀሳቦች ናቸው። “የእባብ ልጅ እባብ” እንደሚባለው እኩይ ሀሳቦች ደግሞ እኩይ ድርጊትን ነው የሚፈጥሩት። በበጎ ሀሳብ በጎውን እኛን መፍጠር እንችላለን።
በበጎው እኛ በኩል ደግሞ በጎዋን ኢትዮጵያ መፍጠር ይቻለናል። ስለዚህም በጎ እናስብ። ጎዳናችን የሚቀናው፣ ነጋችን ብሩህ የሚሆነው ዛሬ በምንሆነው ነገር ነው። የዛሬ የአገራችን ስቃይ የትላንት የፖለቲካ አስተሳሰብ ነው። ከከሰረ ሀሳብ ውስጥ የተዋጣለት ሕይወት አይገኝም። እንደአገር ሳንገዳገድ ወደፈለግንበት የምንሄደው ሩቅ የሚያደርስ ቀና እሳቤ በውስጣችን ሲኖር ነው።
ሀሳባችን እንድንገዛው እንዲገዛን አንፍቀድ ። የሀሳቡ ባሪያ.. የስሜቱ ሎሌ የሆነ ሰው መልካም መጨረሻ የለውም። ሀሳቦቻችን መንገድ ጠራጊዎቻችንም መንገድ ዘጊዎቻችንም ናቸው። ዛሬ ላይ በብዙ ደስታና ስኬት ከፍታ ላይ ወጥተው የምናያቸው እነሱ ትላንት ላይ መልካም ሀሳብ የነበራቸው ሰዎች ነበሩ።
ከስህተት ሁሉ ስህተት ያለ አላማ መኖር ነው። ያለአላማ መኖር የዚህ ዓለም የመጨረሻው ስህተት ነው። በሕይወት ጉዞ ውስጥ የምንደነቃቀፍባቸው እንቅፋቶች ሁሉ ከዚህ አላማ አልባ ማንነት ውስጥ የወጡ ናቸው። አላማ ራስን በግብረገብነት ውስጥ ማኖር ነው። አላማ ራስን ጠቃሚና አስፈላጊ አድርጎ ማቆም ነው። አላማ የአገር ፍቅር አንዱ ማሳያ ሆኖም ይቆጠራል።
ዛሬ ላይ አገር እየጎዱ ያሉት አላማ የሌላቸው ሰዎች ናቸው። ዛሬ ላይ በብሔር ሽፋን አገር እየበጠበጡ ያሉት አላማ የሌላቸው ግለሰቦችና ቡድኖች ናቸው። አገር አላማ ያለው ትውልድ፣ አላማ ያለው ዜጋ ትሻለች። ሕይወት ምን ያክል ውድና እጅግ ድንቅ ተፈጥሮ እንደሆነ የምንረዳው ከከንቱነት ርቀን ራሳችንን በአላማ ስናኖር ነው። ከትላንት እስከዛሬ አገራችን ላይ የደረሱ ጥፋቶች ሁሉ ከዚህ ማንነት ውስጥ የወጡ እንደሆኑ ምስክር አያሻንም። ያለአላማ መኖር እንስሳዊ ባህሪ ነው። የጭካኔና የስግብግብነት መገለጫ ነው። ስንፈጠርም በምክንያት ነበር። ምክንያታችን ደግሞ በታላቅ ዋጋ መኖር ነው። ታላቅ ዋጋ ያለው ደግሞ በአላማ ውስጥ ነው።
በርካታ ጥናቶች በአላማ መኖርን የትልቅ ነገር ማሳያ እንደሆነ ነው የሚናገሩት በተቃራኒው ደግሞ ሰው ያለ አላማና ያለ ራዕይ የሚኖር ከሆነ እንስሳዊ ባህሪን እየተላመደ በዙሪያው ላሉ ጨካኝና አስደንጋጭ መሆን ይጀምራል ይላሉ። ይሄ ብቻ አይደለም አላማ የሌለው ሰው ለመኖር የሚያጓጓ ነገር ስለሌለው ሀሳቡ ሁሉ ጎጂና አውዳሚ በመሆኑ ለሀገር ስጋት ፈጣሪ ነው በማለት ያክላሉ፡፡
አላማ ያለው ሰው ስህተት አይሰራም ስህተት ቢሰራ እንኳን ለመታረምና ለመስተካከል ራሱን ያዘጋጀ ነው። አላማ በማወቅ ተጀምሮ በመረዳት የሚጠናቀቅ ነው። በትንሽ እውቀት ውስጥ ትልቅ አላማ የለም። ትልቅ አላማ ያለው በትልቅ እውቀትና በትልቅ መረዳት ውስጥ ነው። ራሳችሁን ትልቅ በጣም ትልቅ እጅግ በጣም ትልቅ አድርጋችሁ ፍጠሩ። የሕይወትን ትርጉም ከምትረዱበት ቁም ነገር አንዱ ለራሳችሁ ክብርና ዋጋ በመስጠት በምትኖሩት ዛሬ ነው።
ዛሬ ላይ እኔና እናንተ በምንሆነው ነገር ነው አገራችን የምትፈጠረው። የአገራችን ፈጣሪ እኔና እናንተ ነን። ጠንካራ አገር ለመፍጠር በአላማ የተቃኘ ጠንካራ ሀሳብ ያስፈልገናል። እኛ ማለት የነገ ሀገራችን ፈጣሪዎች ነን። እኛ ማለት የነገ አለማችን መሀንዲሶች ነን፡ ለምንገነባው ብሩህ ነገ ጥሩ ግንበኛ መሆን ይጠበቅብናል። በባህሪና በስነ ምግባር በአላማም የታነጸ ጥሩ ዜጋ ሊወጣን ይገባል።
ዛሬ ላይ አገራችን ኢትዮጵያ ከምንም በላይ የሀሳብ የበላይነት የምትሻበት ጊዜ ላይ ነን። ልዩነትን የሚያጠብቅ የላቀ ሀሳብ ከእያንዳንዳችን ያስፈልጋል። በመከነ ሀሳብ የመከነች አገር ለመፍጠር በፍሬከርስኪ የሚንቀሳቀሱ ሞልተዋል። በሀሳባቸው ዘቅጠው አገር ለማዝቀጥ ታጥቀው የተነሱ የእንግዴ ልጆች እዛም እዚም አሉ። እኚህን ግለሰቦች በሀሳብ ማሸነፍ ይኖርብናል።
እኛ የአገራችን የነገ እጣ ፈንታ ወሳኞች ነን። እኛ የአገራችን የማዕዘን ድንጋዮች ነን። አላማ ባነገበ..በላቀ ሀሳብ እናሸንፍ። ከእኛ ውጭ በእኛ ላይ ሀይል ያለው ማንም የለም። አላማ ካለን በሰከነና ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ማሸነፍ እንችላለን። ከመጠላላት ውጭ ያለውን ዓለም በምክንያታዊነት መቃኘት ያስፈልጋል። ብዙዎቻችን መብቶቻችንን ለማስከበር ከፍቅር ይልቅ ጥላቻን፣ ከመነጋገር ይልቅ ሀይልን የምናስቀድም ነን።
ይሄ አይነቱ አካሄድ ለሀገራችን ሲጠቅም አላየንም። ይልቅ በእወቀትና በሰለጠነ መንገድ ለችግሮቻችሁ መፍትሄ በመስጠት ከሌሎች የተሻልን እንደሆንን ማሳየት ይኖርብናል። ጦርና ጎራዴ አውዳሚ ናቸው። ጥላቻና ሀይል በወንድማማቾች መካከል ትርፍ የላቸውም። ትርፋችን ያለው በሀሳባችን ውስጥ ነው። ትርፋችን ያለው በአንድነታችን ውስጥ ነው።
እስካሁን ትርፍ ያለው እየመሰለን በማይጠቅሙን ነገሮች እየከሰርን ኖረናል። እኛም ሳንጠቀም አገርም ሳንጠቅም ስር በሰደደ ድህነት ስንማቅቅ ኖረናል። የእስካሁኑ አገራዊ ገመናችን በእኛው ተለያይቶ መቆም የተፈጠረ እንጂ በምንም የመጣ አይደለም። የሚሰሩ እጆች፣ የሚያስቡ ጭንቅላቶች፣ ለውጥ የናፈቀው መቶ ሀያ ሚሊዮን ዜጋ እያለን ለጥሩ ነገር እድል ሳናገኝ በድህነት ማቀናል። ለዚች ድሀ አገር ተጠያቂዎች እኛ ነን።
ለዚህ ድሀ ህዝብ ሀላፊነትን የምንወስደው እኛ ነን። ሌሎችን ማድመጥ ራስን ከማድመጥ የሚመነጭ ነው። ከአፍራሽ አስተሳሰብ ወጥተን ወደ ሰለጠነ ዘመናዊ እይታ መሸጋገር ይኖርብናል። ማሸነፍን በመሳሪያና በጉልበት ሳይሆን በሀሳብ የበላይነት እንቀበለው። በልዩነት ውስጥ መግባባትን፣ ባለመስማማት ውስጥ መስማማትን ባህል እናድርግ። የምንታገለው ለአንድ አገርና ህዝብ እስከሆነ ድረስ የሚያቀያይመንና ቂም የሚያያይዘን ምንም የለም።
በአገር ስም የሚነግዱ ብዙ እድርባዮች እንዳሉ አውቃለሁ። በአገር ስም ራሳቸውን ለመጥቀም የሚታገሉ ስለመኖራቸው እኔም እናንተም ምስክሮች ነን። አብዛኛው አለመስማማታችንም ከዚህ የመነጨ ነው። አገር የሚለውጡ ትልልቅ ሀሳቦችን እየጣልን በትንሽ ሀሳቦች ላይ ጊዜአችንን የምናጠፋው ለዚህ ነው። አላማችን አንድ አገርና ህዝብ ቢሆን ኖሮ መስማማት አያቅተንም ነበር ።
አላማውን አገር ያደረገ ዜጋ ሰላምን እንጂ ጦርነትን አያውቅም። አላማውን ህዝብ ያደረገ ትውልድ ለጋር ጥቅም በጋራ ይተጋል እንጂ መለያየትን እንደ ትልቅ አላማ ይዞ አይንቀሳቀስም። እኛ ለዚች አገር እንደ ጌዲዮን በጽናት እንቁም። እኔ ያልኩት ብቻ ይሁን ከሚል ኋላቀር አስተሳሰብ ወጥተን የብዙሃኑን ድምጽ የምንሰማበት ሰፊ ጆሮና ጽኑ ልብ እናዳብር። ከእኔነት ወጥተን በላቀ ህዝባዊ እሳቤ ከፊት የቆሙ መሪዎች እንሁን።
የግለሰብ ጉዳይ ከአገርና ህዝብ ጉዳይ አይበልጥም እያልን፤ እኔና እናንተ ከአገር አንበልጥም እያልን ለምን የሀሳብ ልዕልና በውስጣችን ጠፋ ? የሀሳብ ልዕልና ከራስ የሚጀምር ነው። ከአገርና ህዝብ የሚነሳ ነው። አገርና ህዝብን ከፊት ማስቀደም ነው። የአገርና የህዝብን ጉዳዮችን አንደኛ ማድረግ ነው።
አገሩን ያረዳ ህዝቡን ከድህነት መታደግ ያልቻለ እውቀትና ስልጣን በታሪክ ተወቃሽ ከመሆን ባለፈ የሚኖረው ጥቅም የለም። እኛ የአገራችን የነገ ዋስትናዎች ነን። ከእውቀት ወደ ጥልቅ እሳቤ፣ ከጥልቅ እሳቤም ወደ ጥልቅ መረዳት ልናሸጋግራት ይገባል።
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ሰኔ 7 /2014