ባለፉት ሁለት ሳምንታት በሐዋሳ ከተማ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲካሄድ በቆየው የኢትዮጵያ ወጣቶች ኦሊምፒክ አዲስ አበባ ከተማ የሜዳሊያ ሰንጠረዡን ቀዳሚ ሆና አጠናቃለች። የበርካታ ስፖርተኞች መቀመጫ የሆነችው አዲስ አበባ ከዚህ ቀደም በሚካሄዱ አገር አቀፍ ውድድሮች ከሌሎች ክልሎች አኳያ ውጤቷ የሚመጥናት እንዳልሆነ በተለያዩ አጋጣሚዎች ሲነገር ነበር። ይሁን እንጂ በዚህ የመጀመሪያ የወጣቶች ኦሊምፒክ ከተማዋ ከሌሎች ተሳታፊዎች የላቀ ውጤት በማስመዝገብ በሰፊ ልዩነት ልታጠናቅቅ ችላለች።
አዲስ አበባ በአጠቃላይ 44 የወርቅ፣28 የብርና 32 የነሐስ ሜዳሊያ በድምሩ 104 ሜዳሊያ በመሰብሰብ ነው ቀዳሚ ሆና ያጠናቀቀችው። የመጨረሻውን የወርቅ ሜዳሊያ ያስመዘገበችውም የኦሊምፒኩ የመዝጊያ መርሐግብር ላይ በተካሄደው የሴቶች እግር ኳስ ፍጻሜ አስተናጋጁ ሲዳማ ክልልን በመለያ ምት በመርታት ነው። አዲስ አበባን ተከትሎ ኦሮሚያ ክልል በ27 ወርቅ፣23 ብርና 25 ነሐስ በአጠቃላይ በስልሳ አምስት ሜዳሊያ ሁለተኛ ሆኖ ማጠናቀቁን አረጋግጧል።
ደቡብ ክልል በ9 ወርቅ፣13 ብርና 21 ነሐስ በድምሩ በ43 ሜዳሊያ ሶስተኛ ደረጃን ይዞ የሚያጠናቅቅ ሆኗል። ጋምቤላ፣አፋር፣ሶማሌና ደቡብ ምእራብ ክልሎች በዚህ የመጀመሪያ የኢትዮጵያ ወጣቶች ኦሊምፒክ አንድም የወርቅ ሜዳሊያ ሳያስመዘግቡ ያጠናቀቁ ናቸው። ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገበው የአዲስ አበባ ልኡካን ቡድን ትናንት ወደ አዲስ አበባ ተመልሶም በከንቲባ ጽህፈት ቤት ደማቅ አቀባበል እንደተደረገለት ታውቋል።
“እውነተኛ ዕድሜ ለኢትዮጵያ ስፖርት ዕድገት “ በሚል መሪ ቃል የተካሄደው ይህ አንደኛው የኢትዮጵያ ወጣቶች የኦሊምፒክ ከሁለት የከተማ አስተዳደሮችና ዘጠኝ ክልሎች የተውጣጡ ከስድስት ሺ በላይ ስፖርተኞችን አሳትፏል። ውድድሮቹም ከኦሊምፒክ ስፖርቶች አትሌቲክስ፣ እግር ኳስ፣መረብ ኳስ፣ ቅርጫት ኳስ፣ እጅ ኳስ፣ ብስክሌት፣ ቦክስ፣ጅምናስቲክና ወርልድ ቴኳንዶ ፉክክር የተደረገባቸው ሲሆን ከኦሊምፒከ ስፖርቶች ውጪ ቼዝ፣ ኢንተርናሽናል ቴኳንዶና ውሹ መካተታቸው ታውቋል።
አዲስ አበባ የቀጣዩና ሁለተኛውን የኢትዮጵያ ወጣቶች ኦሊምፒክ አዘጋጅ በመሆንም ከሲዳማ ክልል አርማና የኦሊምፒክ ችቦውንም በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ የመዝጊያ መርሐግብር ላይ ተረክባለች። ቀጣዩ የወጣቶች ኦሊምፒክ ከሁለት ዓመት በኋላ ይካሄዳል።
በመዝጊያው መርሐግብሩ ላይ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ዶክተር አሸብር ወልደጊዮርጊስ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ወጣቶች ኦሊምፒክ ባለፉት ሁለት ሳምንታት ባካሄዳቸው በርካታ ውድድሮች ከመቼውም ጊዜ በበለጠ መቀራረብንና መተሳሰብን ፣ ብርቱ ፉክክርንና ውጤትን በከተማ አስተዳደሮችና በክልሎች መካከል በማሳየት በድምቀትና በታላቅ ስኬት መጠናቀቁን ገልጸዋል። እስካሁንም መሰል ውድድሮች በአገር አቀፍ ደረጃ አለመካሄዳቸው የሚያስቆጭ መሆኑን የተናገሩት ፕሬዚዳንቱ የኢትዮጵያን ስፖርት ማሳደግ ከተፈለገ ወጣቶች ላይ ትኩረት ያደረጉ መሰል ውድድሮች በየጊዜው መካሄድ እንዳለባቸው አብራርተዋል።
በመዝጊያ ሥነ ሥርዓቱም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማህበር ፕሬዚዳንት መቶ አለቃ ፈቃደ ማሞ እንዲሁም የሲዳማ ክልል ከፍተኛ አመራሮችና የየክልሉ ስፖርት አመራሮች ተገኝተዋል:: የአፍሪካ ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴዎች ማህበር(አኖካ) ዋና ጸሐፊ አህመድ ሃሺም በልዩ እንግድነት የመዝጊያ ሥነሥርዓቱ ላይ የተገኙ ሲሆን ኢትዮጵያ በቀጣይ ዓመት የአፍሪካ ወጣቶች ኦሊምፒክን እንድታዘጋጅ ለኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የማመልከቻ ደብዳቤ እንደሚያስገቡ ተጠቁሟል።
አራተኛውን የአፍሪካ ወጣቶች ኦሊምፒክ ኢትዮጵያ እንደምታዘጋጅ ቀደም ሲል ተገልጾ እንደነበር የሚታወስ ሲሆን ግልጽ ባልሆነ ምክንያት ውድድሩ በግብጽ አዘጋጅነት ሊካሄድ እንደሚችል ሲነገር ቆይቷል። ይሁን እንጂ ግብጽም ይህን ታላቅ ውድድር እንደማታዘጋጅ የተገለጸ ሲሆን ኢትዮጵያ ዳግም አዘጋጅ እንድትሆን ዋና ጸሐፊው ጥያቄ እንደሚያቀርቡ ታውቋል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ሰኔ 6/2014