የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ከተቋቋመ ከ1933 ዓ.ም ጀምሮ ላለፉት ሰማንያ አንድ ዓመታት ታላላቅ ሀገራዊ ሁነቶችን የሚገልጹ ፎቶግራፎችን ሰንዷል። ድርጅቱ ከሰሞኑ ከ1960ዎቹ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ የተከናወኑ ታላላቅ ሀገራዊ ሁነቶችን የሚያስቃኝ የፎቶግራፍ አውደ ርዕይ በማቅረብ ላይ ይገኛል።
‹‹ስለ ኢትዮጵያ›› የተሰኘውን የፎቶግራፍ አውደ ርዕይና የፓናል ውይይት በአስራ አንድ የኢትዮጵያ ከተሞች ለማቅረብ አቅዶ ወደተግባር የገባ ሲሆን ፤ በዚሁ መሰረት ዝግጅቱን በምስራቅ ኢትዮጵያ የተመረጡ ከተሞች አቅርቧል። በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ አንድ ብሎ የጀመረውን የፎቶግራፍ አውደ ርዕይና የፓናል ውይይት በድሬዳዋና ሐረር ከተሞችም ደግሞታል።
በድርጊትና በጊዜ ቅደም ተከተል ተደራጅተው ለእይታ የቀረቡት እነዚህ ፎቶ ግራፎች የሀገሪቱን የግማሽ ክፍለ ዘመን ፖለቲካዊ ውጣውረዶች፣ ማህበራዊ ክንዋኔዎች፣ ሃይማኖታዊና ባህላዊ እሴቶች ወዘተ የሚያስቃኙ ናቸው።
ጠቅለል አድርገን ስንመለከታቸው በንጉሱ ዘመን፣ በደርግ ዘመን፣ በኢህአዴግ ዘመን እና በአሁኑ ወቅትም ያሉትን ነባራዊ ሁኔታዎች የዳሰሰ ሲሆን በተለይም አሁን የመጣውን ሀገራዊ ለውጥ ተከትሎ ያለውን ፈተና ድልና ተስፋም የሚያሳዩ ናቸው።
የዘውድ አገዛዙን ዙፋን ከነቀነቁ የሕዝብ ጥያቄዎች መካከል መሬት ላራሹ ፤ የጎጃም አርሶአደሮች የግብር ይቀነስልን አመጽ እና የወሎ ረሃብ ተጠቃሽ ናቸው። የተማሪዎችን ተቋውሞ ተከትሎ ወታደራዊው መንግሥት ንጉሡን ከሥልጣን አውርዶ ወንበር የያዘበትን ሁኔታ ፤ የነጭና የቀይሽብር ግፎች ፣ የእድገት በሕብረት ዘመቻ ፣ የሲያድባሬን ወረራ ለመቀልበስ የተደረገውን ጥሪ እና የተሰጠውን ምላሽ የሚያሳዩ ፎቶግራፎች በአወደ ርዕዩ ላይ ተካተዋል።
ከደርግ ወድቀት በኋላ ሥልጣን የተቆጣጠረው ሕወሓት መራሹ የኢህአዴግ መንግሥት በ27 ዓመት የሥልጣን ቆይታው ሕገመንግሥት አርቅቆ ከማስጸደቅ ጀምሮ ለይስሙላህ ያከናወናቸው ምርጫዎችና የምርጫው ውጤት መጭበርበሩን ተከትሎ በተለይም ለተቃውሞ የወጡ የአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶች ላይ የተፈጸመው ግድያ፤ በ‹‹ ኢሬቻ ሆራ ቢሾፍቱ›› መርሃ ግብር ላይ የሞቱና የተጎዱ ሰዎችን እንዲሁም በኦሮሚያና በአማራ ክልል ኢህአዴግን በመቃወም የተቀጣጠሉት ተቃውሞዎች፤ በፎቶግራፍ አውደ ርዕዩ ከተካተቱ ታሪካዊ ክስተቶች የሚጠቀሱ ናቸው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርም ደሳለኝ ሰላማዊ በሆነ መንገድ ሥልጣናቸውን ሲያስረክቡ፤ ሕወሓት መራሹ ሥርዓት በሕዝቦች ተቃውሞና ትግል ተገርስሶ አዲሱ የለውጥ አመራር ሥራ ሲጀምር፤ በፖለቲካ ምክንያት ከሀገር የኮበለሉ ግለሰቦችና ድርጅቶች ወደሀገራቸው ሲመለሱ እና የትጥቅ ትግል ሲያደርጉ የነበሩትም ሰላማዊ ትግል እንዲያደርጉ ጥሪ ቀርቦላቸው ሲገቡ ፤ በፖለቲካ አመለካከታቸው ምክንያት የታሰሩ ሲፈቱ የነበረውን ሁኔታ ፎቶግራፎቹ ያስታውሳሉ።
ከሀገር ቤት አስከ ውጭ ሀገር ድረስ በተለያዩ ጉዳዮች የተደረጉ የድጋፍና የተቋውሞ ሰልፎች ፤ የብልጽግና ፓርቲ ምስረታና የሕወሓት ማፈንገጥንም እንዲሁ ፎቶ ግራፎቹ ይናገራሉ።
በተለይም አሸባሪው የሕወሓት ቡድን በሰሜን እዝ መከላከያ ሠራዊት ላይ የፈጸመውን ክህደትና ያደረሳቸውን ግፎች ፤ በአማራና አፋር ንጹሃን ዜጎች ላይ የፈጸማቸውን ሰቆቃዎች ፤ ያወደማቸውን ንብረቶች፤ ፎቶግራፎቹ ቁልጭ አድርገው ያሳያሉ።
መንግሥት በወሰደው ሕግ የማስከበር ርምጃ በሶስት ሳምንት ውስጥ የተገኘውን ድል፤ የመልሶ ግንባታና ርዳታ ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በግንባር ተገኝተው ወታደራዊ አመራር ሲሰጡ የነበረው ሁኔታ በፎቶግራፎቹ ይገለጻል።
ኢትዮጵያ የውስጥና የውጭ ጫናዎችን ተቋቁማ ለመጀመሪያ ጊዜ ነጻ ፍትሃዊ፣ ተአማኒና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ አካሂዳ የብልጽግና መንግሥትን መመስረቷን፤ በፈተና ውስጥ ሆኗም ታላላቅ ሀገራዊ የልማት ሥራዎች መሠራታቸውን ከፎቶ ግራፎቹ መረዳት ይቻላል።
በጅግጅጋ፣ ድሬዳዋና ሐረር ከተሞች የተከናወኑትን የፎቶግራፍ አውደ ርዕዮች ተከትሎ የፓናል ውይይቶች ተካሂደዋል። በውይይቱ ላይ የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የጦር መኮንኖች ፣ ባለሀብቶች፣ አርቲስቶች ፣ ደራሲዎች ፣ ወጣቶች፣ ተማሪዎች እና እንደውይይቱ ርእሰ ጉዳዩ ጥሪ የተደረገላቸው ሌሎች አካላትም ተሳትፈዋል።
በክልል ደረጃ የተካሄደ የመጀመርያ መድረክ
የፎቶግራፍ አውደ ርዕዩ ለመጀመሪያ ጊዜ በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ በተከፈተበት ወቅት የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጌትነት ታደሰ አላማውን ሲናገሩ ‹‹ጊዜው ምክክርን፣ ሰላምንና አንድነትን የሚፈልግ ስለሆነ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የበኩሉን ለመወጣት ይህንን የውይይትና የሰላም መድረክ ጀምሮታል›› ብለዋል።
በአውደ ርዕዩ የተካተቱት ፎቶ ግራፎች በየዘመናቱ የተነሱ ጥያቄዎች ምን እንደነበሩ፤ በዘመኑ የነበሩ መሪዎች ጥያቄውን የመለሱበት መንገድ ምን እንደሚመስል የሚያስታውሱ ናቸው። የሚያስታውሱ ብቻ ሳይሆኑ ከዚያ እስከዚህ ድረስ የመጣንበት መንገድ ምን እንደሚመስልና በየሥርዓተ መንግሥቱ ያለውን ሁኔታ እንድናነጻጽር የሚያደርጉ ናቸው።
እንደ አቶ ጌትነት ገለጻ፤ የፎቶ ግራፉ አውደ ርዕዩ በዋናነት ያካተተው በንጉሱ ዘመን፣ በደርግ ዘመንና በአህአዴግ ዘመን የነበረውን የህዝብ ጥያቄና የሥርዓት ለውጥ ሲሆን፣ አሁን ያለውን ሀገራዊ ለውጥ ተከትሎ ያጋጠመውን ፈተና ፣ ድልና ተስፋ የውይይቱ ትኩረት አድርጎ ስለ ኢትዮጵያ ቀጣይነት ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ማስቻል ነው።
የእለቱ የክብር እንግዳ የሕዝብ ተወካዮች አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ የፓናል ውይይቱን ሲያስጀምሩ እንደተናገሩት ፤ ‹‹ስለ ኢትዮጵያ›› የተሰኘው የፎቶግራፍ አውደ ርዕይና የፓናል ውይይት ስለኢትዮጵያ ሰላምና ብልጽግና ያገባኛል የሚለውን ጽንሰ ሐሳብ የያዘ ነው ብለዋል። በያገባኛል መንፈስ በመነጋገርና በመወያየት መሄድ ከተቻለ አገርን ማስቀጠል ይቻላል ብለዋል።
ያለንን በቅጡ መጠቀም ያልቻልነው መስማማት ስላልቻልን ነው ያሉት አቶ ታገሰ ጫፎ ተቀራርበን በመነጋገርና የችግራችንን ሰንኮፍ ነቅለን በመጣል ለብልጽግና ጉዟችን ራሳችንን ከወዲሁ ማዘጋጀት እንደሚጠበቅብን ተናግረዋል፤ ለዚህ ደግሞ ምክክርና ውይይት የግድ እንደሚል ገልጸዋል። የተዘጋጀው መድረክም ቀጣይ ለሚኖረው ሀገራዊ የምክክር መድረክ በር ከፋች ሊሆን ይችላል ብለዋል።
ኢትዮጵያን ለማሻገር በሰላምና በደህንነት ጉዳዮች መረባበረብ ማስፈለጉን ተናግረው እንዲህ አይነቱ መድረክም ችግሮችን ለመቅረፍ ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ጠቅሰዋል። የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ይህን የመሰለ የፎቶግራፍ አውደ ርዕይና የፓናል ውይይት ማዘጋጀቱ የሚያስመሰግነው እንደሆነ ገልጸዋል።
የሱማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እና የመድረኩ አወያይ አቶ ሙስጠፌ መሃመድ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ ማንነትና ብዝሃነት ተፈጥሯዊ ስለሆኑ መካድ አይቻልም፤ ስለዚህ የባህልንና የሃይማኖት ልዩነትን ማክበር አስፈላጊ ነው፤ ኢትዮጵያ አንዱ የሌላውን ጉዳይ በማክበር ረገድ ችግር የሌላባት አገር እንደመሆኗ ይህንኑ ማስቀጠል የግድ ይላል ብለዋል። መቻቻልን በማስቀጠል አንዱ ክልል ከሌላው ክልል ጋር በመቀራረብ መልካም የሆነውን መማማር አስፈላጊ እንደሆነ ተናግረዋል።
ለአንድ ክልል አንድ ቋንቋ መናገርና አንድ ብሔር ብቻ መሆን በራሱ ለሰላም ዋስትና አይሰጥም ያሉት አቶ ሙስጠፌ፤ አንድ ቋንቋ ተናጋሪ እንዲሁም አንድ አይነት ሃይማኖት ተከታይ የሆኑ ሲገዳደሉ እንደሚስተዋሉ ገልጸው ሰላም የሚሰፍነው ሁሉም የየራሱን ኃላፊነት ሲወጣና በትዕግስት የተሻለውን አቅጣጫ ይዞ መጓዝ ሲችል ነው ብለዋል።
በፎቶግራፍ አውደ ርዕዩና በፓናል ውይይቱ ላይ የብልጽግና ፓርቲ የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ እና የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አብረሃም አለኸኝ የመነሻ ጽሑፍ አቅርበው ውይይት ተካሂዶበታል። የውይይት መነሻውን መሰረት በማድረግ ከተሳታፊዎች ጠቃሚ ሃሳቦች ተንሸራሽረዋል።
ሁለተኛው የፎቶግራፍ አውደ ርዕይና የፓናል ውይይት
ሁለተኛው የፎቶግራፍ አውደ ርዕይና የፓናል ውይይት በድሬዳዋ ከተማ ሲካሄድ ትኩረቱን ያደረገው በኢኮኖሚው ዘርፍ በተለይም በኢንዱስትሪው ልማት ላይ ነበር። በመድረኩ ላይ የፌዴራልና የክልል መንግሥታት ከፍተኛ ባለሥልጣናት፣ ባለሀብቶችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታድመዋል።
የመድረኩ አወያይ የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ እንደተናገሩት፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ከሌሎች አገራት ኢንቨስትሮች በተሻለ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን የመደገፍ ጽኑ ፍላጎት እንዳለው ተናግረዋል።
የሀገር ውስጥ እና የውጭ ባለሀብቶች ለኢኮኖሚው ያስፈልጋሉ ያሉት ሚኒስትሩ፤ ሁለቱንም በቅንጅት እንዲሠሩ በማድረግ በተለያዩ የኢንዱስትሪ ፓርኮችም ውጤት ማምጣት ተችሏል። ይሁንና የመንግሥት ዋና ዓላማ የሀገር ውስጥ ባለሀብቱን በመደገፍና በማብቃት አቅሙ እንዲጠናከር ማድረግ ነው ብለዋል።
የሀገር ውስጥ ባለሀብቱ ይበልጥ እንዲጠናከር ድጋፍ ይደረግለታል ሲባል ግን ኢንዱስትሪው በሀገር ውስጥ አቅም ብቻ ይሳካል ማለት አለመሆኑንም ገልጸዋል። የፋይናንስ፤ የቴክኖሎጂና መሰል አቅማችን ገና ውስን በመሆኑ ከውጭ ባለሀብቶች ጋር ተቀናጅቶ መሥራት ያስፈልገናል ብለዋል።
የአምራች ኢንዱስትሪውም ሆነ የአገልግሎት ዘርፉ የሚያድገው በዋናነት በግል ባለሀብቱ ተሳትፎ መሆኑን የተናገሩት ሚኒስትሩ፤ በመንግሥት በኩልም መሠረተ ልማትን ማስፋት፣ የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ፣ የውጭ ምንዛሬ አቅርቦትን በማሳደግ ረገድ አቅም በፈቀደው ልክ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል። በመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ያለውን ቢሮክራሲ ለማቅለልም የተሻለ እየተሠራ ነው ብለዋል።
የሀገር ውስጥ ባለሀብቱ አቅም ሲጠናከር መዋዕለ ንዋያቸውንም መልሰው ለሀገር ለማዋል ያስችላቸዋል ያሉት ሚኒስትሩ የሥራ ዕድሎችን በስፋት የመፍጠር አቅም ይኖራቸዋል ብለዋል።
በዚህ አግባብ ሲታይ ከኢንተርፕራይዝ አንስቶ እስከ ከፍተኛ ኢንቨስትመንቶች ድረስ መንግሥት የመስሪያ ቦታ በማመቻቸት፣ የውጭ ምንዛሬ አቅርቦትን በማሳደግ፣ በልዩነት የተመረጡ የንግድ ስራዎች ላይ ኢትዮጵያውያን ብቻ እንዲሠሩ የተለያዩ ድጋፎችን ያደርጋል ሲሉ ሚኒስትሩ አስረድተዋል።
እንደ አቶ አህመድ ሽዴ ገለጻ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ባለሀብቱን ከመደገፍና ምርታማነትን ከማሳደግ አኳያ ያለው ችግር የፖሊሲ ሳይሆን ያሉትን ፖሊሲዎች በጥራት ማውረድና መፈጸም ላይ ነው።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል የዘርፉን እንቅስቃሴ የሚገልጽ ጽሁፍ ሲያቀርቡ እንደገለጹት፤ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ችግርን ለመፍታት የመጀመሪያውና መሠረታዊው መፍትሄ የአገር ውስጥ ምርትን ማሳደግ ነው።
አሁን የኢንዱስትሪዎች የምርታማነት አቅም 50 በመቶ እንደሆነና በተለያዩ ምክንያቶች የተፈጠረው የማምረት አቅም ማነስ በሚፈለገው ደረጃ ምርት እንዳይቀርብ ማድረጉን ገልጸዋል። በቀጣይ የአምራቹን አቅም ወደ 85 በመቶ ለማድረስ ውጥን መያዙን ጠቁመዋል።
አምራች ዘርፉ ከአጠቃላይ የአገሪቱ ጂዲፒ የስድስት ነጥብ ስምንት በመቶ ድርሻ እንዳለው የጠቆሙት አቶ መላኩ፤ ድርሻውን ወደ 17 ነጥብ ሁለት በመቶ ለማሳደግ እየተሠራ እንደሚገኝና ይህም ምርታማነትን ከማሳደግ ባለፈ የውጭ ምንዛሪ እጥረትንም ለማቃለል አይነተኛ መፍትሄ ይሆናል ብለዋል።
መንግሥት ዘርፉን ለማጠናከር በ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› ንቅናቄ የአቅም ማጠናከር ሥራ እያከናወነ መሆኑን አስታውቀዋል።
የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ኃላፊ አቶ ጀማል አህመድ በግሉ ዘርፍ ባለው የአምራች ኢንዱስትሪ ተግዳሮትና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ባቀረቡት ጽሁፍ እንደገለጹት፤ መንግሥት ለሀገር ውስጥ ባለሀብቶች የሚያደርገውን ድጋፍ ማሳደግ እንዳለበት ጠቅሰዋል። በተለይም የውጭ ምንዛሪ አቅርቦትን በፍትሐዊነት ለአምራች ኢንዱስትሪዎች በማቅረብ ዘርፉን ማሳደግ ይገባል ብለዋል።
በአምራች ኢንዱስትሪዎች ላይ የሚያጋጥሙ ዘርፈ ብዙ ችግሮች መኖራቸውን የጠቆሙት አቶ ጀማል መንግሥት ከግሉ ዘርፍ ጋር ያለውን ትብብር እያጠናከረ ከሄደ በአምራቾች ላይ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በመቅረፍ ምርታማነትን ማሳደግ እንደሚቻል አመልክተዋል።
በፓናል ውይይቱ የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ከድር ጁሀር የከተማዋን ኢንቨስትመንት አማራጮች እንቅስቃሴ የሚያሳይ ጽሁፍ አቅርበዋል።
ሦስተኛው የፎቶግራፍ አውደ ርዕይና የፓናል ውይይት
ሦስተኛው መድረክ በዩኔስኮ የሰላም፣ የፍቅርና የአብሮነት ከተማ ተብላ በተመዘገበችው ሐረር ከተማ ተካሂዷል። የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ አውደ ርዕዩን በከፈቱበት ወቅት እንደተናገሩት፤ ከፎቶ ግራፍ አውደ ርዕይ በርካታ ቁም ነገሮችን መማር እንደሚቻል ጠቅሰው ፎቶግራፎቹ በሀገራችን የተከሰቱ ዋና ዋና ሁነቶችን፣ ከዘውዳዊው አገዛዝ ጀምሮ የነበሩ መንግሥታት ምን አይነት ባህሪያት እንደነበራቸውና በተለያዩ ጊዜያት የነበሩ የሕዝብ ጥያቄዎችና ትግሎችን በአጭር ሰዓት ውስጥ ማስረዳት የሚችሉ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በመክፈቻ መርሃ ግብሩ የተገኙት የኢትዮጵያ ብዙኃን መገናኛ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መሐመድ እድሪስ በበኩላቸው፥ አውደ ርዕዩ ትናንትን ከዛሬ፣ ዛሬን ከነገ ያዋሃደ ትልቅ ሀገራዊ ፕሮጀክት መሆኑን ጠቅሰው፤ በአውደ ርዕዩ ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ያሳለፈቻቸውን ማሕበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ውጣ ውረዶችን መመልከታቸው ተናግረዋል።
የሰላም ሚኒስትሩ አቶ ብናልፍ አንዷለም የውይይት መድረኩን መርተዋል። የባሕልና ስፖርት ሚኒስትሩ አቶ ቀጄላ መርዳሳ፣ የፌዴራልና የክልል የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ ምሁራን፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶች፣ ተማሪዎች የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍል ተወካዮች፣ ታዋቂ ግለሰቦችና ተጋባዥ እንግዶች በውይይቱ ላይ ተገኝተዋል።
የሐረሪ ክልል ባህል፣ ቱሪዝምና ቅርስ ቢሮ ኃላፊ አቶ ተወለዳ አብዶሽ፣ የሕግ ባለሙያና ጠበቃ አቶ ቀለመወርቅ ሚደቅሳ እንዲሁም ዶክተር ወዳጄነህ መሃረነ የውይይት መነሻ ሃሳቦችን አቅርበዋል።
ጽሁፎቹ በኢትዮጵያውያን የሥነ-ልቦና ውቅርና የጋራ እሴቶች ላይ ትኩረታቸውን ያደረጉ ነበሩ። በውይይቱም ከትውልድ ወደ ትውልድ የተላለፉና ሀገርን በአንድነት ያስቀጠሉ የጋራ እሴቶችን አሟጦ መጠቀም እንደሚገባ ከተሳታፊዎች ተገልጿል። የጋሞ አባቶች የግጭት አፈታት ተሞክሮ ማሳደግ እንደሚስፈልግ፤ በየማሕበረሰቡ ጥቅም ላይ የሚውሉ መልካም እሴቶችን ማሳደግ እንደሚገባ ከተሳታፊዎች ተገልጿል።
በትውልዶች መካከል ያለውን ክፍተት እንዴት መሙላት እንደሚገባ ፤ በእድሜ ደረጃቸው ተለይተው በአዳራሹ ውስጥ የተቀመጡ ተሳታፊዎች የሚወክሉትን ትውልድ ተንተርሰው ሃሳብ ሰጥተዋል።
የሰላም ሚኒስትሩ አቶ ብናልፍ አንዱዓለም በማጠቃለያ ንግግራቸው ብዝኃነትን ያላከበረና ለብዝኃነት እውቅና ያልሰጠ ትውልድ አንድ እርምጃ ወደፊት መጓዝ እንደማይችል ተናግረዋል።
“እኔ አውቅልሃለሁ” ማለትና መገፋፋት ለሀገሪቷ እንደማይበጅ የገለጹት አቶ ብናልፍ ትውልዱን በሥነ- ምግባርና በእውቀት መቅረጽ ፤ የሰለጠነች፣ ዴሞክራሲ የሰፈነባት፣ ሰላሟ የተረጋገጠና የበለጸገች ኢትዮጵያ እውን ለማድረግ ይረዳል ብለዋል።
ወጣቱ ታሪኩን በሚገባ ለማወቅ መትጋት፣ ማንበብና እናትና አባቶቹ እንዲሁም ታላላቆቹን መጠየት እንዳለበትም አሳስበዋል። ኢትዮጵያውያን ዘመናትን የተሻገሩ በርካታ የጋራ እሴቶች ባለቤቶች መሆናቸውን የገለጹት የሰላም ሚኒስትሩ፤ ለዘመናት ያካበትናቸው የጋራ እሴቶች ተጠብቀው እንዲቆዩ የሽማግሌዎች ሚና ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመዋል። በንግግራቸው የጋሞ አባቶችን ለአብነት ጠቅሰዋል።
አቶ ብናልፍ እንደገለጹት፤ አብዛኞቹ የሀገሪቱ ችግሮች ከልሂቃን የሚመነጩ መሆኑን ጠቅሰው ልሂቃን የመፍትሄው አካል ለመሆን መሥራት እንደሚጠበቅባቸውም አሳስበዋል።
በአጠቃላይ ስለኢትዮጵያ በሚል በተዘጋጀው በዚህ የፎቶግራፍ አውደ ርዕይ መነሻነት በሶስት ከተሞች የተካሄደው የውይይት መድረክ የግማሽ ክፍለ ዘመንን ፖለቲካዊ፣ ማሕበራዊና ኢኮኖሚያዊ ውጣ ውረድ ያሳየና ትውልዱ የመፍትሄ ሃሳቦችን በማመንጨት ኢትዮጵያን ወደፊት ለማሻገር በመግባባት ችግሮችን መፍታት እንዳለበት ያመላከተ ነው። መርሃ ግብሩ በቀጣይ ሊደረግ ለታሰበው ሀገራዊ ምክክርና መግባባት መንደርደሪያ መሆን ያስቻለ ነው።
ኢያሱ መሠለ
አዲስ ዘመን ሰኔ 6/2014