በቅርቡ ሲካሄድ የነበረው የአልጄራዊያን የለውጥ እንቅስቃሴ የዓለምን ቀልብ የሳበ ነበር፡፡ በአገሪቱ የነበረው ሰላማዊ የለውጥ እንቅስቃሴ፣ የመንግሥት ተቃውሞ ወይስ ማህበራዊ ለውጥ የሚሉት ጉዳዮች ሰፊ መወያያ አጀንዳ ነበሩ፡፡ ከአስር ዓመት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ አልጄራዊያን የወደፊት እጣ ፈንታቸው የወሰኑበት ወቅትም ነበር፡፡
የአገሪቱ ወታደራዊ ኃይል የህዝቡ ጥያቄ በአግባቡ የተረዳው ባለመሆኑ ህዝቡ የሚያስተዳድረውን መንግሥት ያለምንም ጥያቄ እንዲቀበል ጫና ሲፈጥር ነበር። ይህ የሆነው የአገሪቱ ፕሬዚዳንት አብዱላዚዝ ቡተፍሊካ ለአምስተኛ ጊዜ እንደሚወዳደሩ ካሳወቁ በኋላ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ፕሬዚዳንቱ ከእአአ 2013 ጀምሮ መንቀሳቀስና መስራት አቅቷቸው እንደነበር ይታወቃል፡፡ ከእአአ 2011 የአረብ ጸደይ ጀምሮ በአልጄሪያ በሚገኙ ከተሞች በተደጋጋሚ ህዝባዊ አመፆች በስፋት አስተናግደዋል፡፡ በቅርብ ወራት ውስጥም አጠቃላይ ህዝባዊ አመፆች በአገሪቱ ከተሞች ተካሂደዋል፡፡
በተቃውሞው ላይ ህፃናት ጭምር የተሳተፉ ሲሆን ተቃውሞውን ያልተቀላቀሉ የገበያ ማዕከላት ሱቆቻቸውን እንዲዘጉ ተደርገዋል፡፡ ተማሪዎችም ቀድመው ትምህርት እንዲዘጋ በማድረግ ተቃውሞውን ተቀላቅለዋል፡፡ የተቃውሞው መፈክር የሚታወቅና ትክክለኛ የአገር መሪ መምጣት አለበት የሚል አንድምታ ያለው ነበር፡፡
‹‹ህዝቡ የሚፈልገው ገዥው መንግሥት እንዲወርድ ነው›› ይህ መፈክር በሁሉም የአገሪቷ ከተሞች የተሰራጨ ሲሆን እአአ 1950 እና 1960 ላይ የፈረንሳይ ቅኝ አገዛዝ እንዲወርድ በተደረገው ተቃውሞ ከነበረው ‹‹20 ዓመታት ብዙ ነው›› መፈክር እኩል ተቀባይነት ያገኘ ነበር፡፡ ይህ ሁኔታ የአልጄሪያ መንግሥት ህዝቡ ፍራቻ ውስጥ ገብቷል ብሎ እንዲያምን አድርጎታል፡፡
እአአ 1990 በአገሪቱ ደም አፋሳሽ ግጭት ተከስቶ ስለነበር ያም ሁኔታ እንዳይደገምና የአገሪቱ ወታደሮች ምርጫው በሰላም እንዲጠናቀቅ ግፊት አሳድረዋል፡፡ የአልጄሪያ መንግሥትም የጭለማ ዓመታት ከሚባለው ጊዜ ተምሮ ህዝቡን በአግባቡ ከማገልገል ይልቅ ቀድሞ የነበረውን ጭቆና በመመለስ ሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በማካሄድ በአገሪቱ ሁከት እንዲፈጠርና ህዝቡ ስጋት ውስጥ እንዲገባ አድርጓል።
ህዝቡ ያካሄደው ተቃውሞ በሰላማዊ መንገድ ሲሆን የጦር ኃይሉ እና ፖሊስ ተቃውሞውን ለመበተን ሙከራ አድርገው ነበር፡፡ ህዝቡ ከፖሊስም ይሁን ከጦር ኃይሉ ጋር ወንድማማች መሆኑን የሚገልፅ መፈክሮችን ይዞ ወጥቷል፡፡ የመንግሥትን ስህተት ህዝቡ በማይሆን መንገድ ነበር የተረዳው፡፡ ቀደም ብሎ በነበረው የርስበርስ ጦርነት ወቅት አብዛኛው አሁን ተቃውሞ የሚሰማው ወጣት ያልተወለደና ህፃን የነበሩ ናቸው፡፡ በአሁን ወቅት ስራ እጥነት፣የተለያዩ እድሎች አለማግኘት እና በአገሪቱ ያለውን ድህነት ለመፍታት መንግሥት የአገሪቱን የተፈጥሮ ሀብት በአግባቡ እየተጠቀመ አይደለም የሚሉት ጉዳዮች ተቃውሞ አስነስተዋል፡፡
የመንግሥት የአሰራር መዋቅር በሙስና የተያዘ መሆንና የከተሞች ፖሊስ ህዝቡን ማዋከብ በቀጣይ አገሪቱ እጣ ፈንታ ላይ ተፅዕኖ አሳድሯል፡፡ የአልጄሪያ መንግሥት ከአስርት ዓመታት በፊት ተከስቶ የነበረው የርስበርስ ጦርነት እንዳይደገም ማስጠንቀቂያ ቢሰጥም ሰሚ ያገኘ አይመስልም፡፡ ህዝቡ የመንግሥትን ማስጠንቀቂያ ችላ ብሎ ተቃውሞውን ቀጥሏል፡፡
እአአ 2019 መጋቢት 11 ላይ በተደረገ ከፍተኛ የህዝብ ተቃውሞ ፕሬዚዳንት አብዱላዚዝ ቡተፍሊካ ለአምስተኛ ጊዜ እንደማይወዳደሩ፣ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አህመድ ኦዩአሂ ከስልጣን እንደሚለቁና አጠቃላይ ካቢኔው እንደሚበተን አስታውቋል፡፡ በዚህ ውሳኔም ከዳር እስከዳር አልጄራዊያን ደስታቸውን ገልፀዋል፡፡ ነገር ግን ህዝቡ ተቃውሞው አላቆመም በየአደባባዮች ‹‹ይሄ የመጀመሪያና ቀጣይነት ያለው ነው›› ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
ለመጀመሪያ ጊዜ ለውጥ በአገሪቱ ከመጣ አስርት ዓመታት በኋላ ህዝቡ ያለውን ስልጣን ያጣጣመበትና የተጠቀመበት ወቅት ነበር፡፡ ነገር ግን ለህዝቡ ይሄ አስፈላጊውና የመጀመሪያ ድል ሲሆን መንግሥት ቀድሞ እርምጃዎችን ወስዶ ገደብ አስቀምጧል፡፡ ቡተፍሊካ ከስልጣን አልወረዱም፡፡ ነገር ግን የፕሬዚዳንትነቱን ቆይታ ለማራዘም የሚያስችል ህግ እያዘጋጁ ነው፡፡ በስልጣን የሚቆዩትም ለፓርቲው ጊዜ ለመግዛት እንዲያስችላቸውና የተነሱ ሁከቶችን እንዲረጋጉ ለማድረግ ሲሆን የለውጥ እንቅስቃሴዎቹን በአሸናፊነት ወይ ጫና በማሳደር ለመቆጣጠር ፍላጎት አላቸው፡፡ ይህ ጉዳይ ለሳምንት ወይ ለወራት ጥያቄ ሆኖ ይቆያል፤ የሚሉ መረጃዎች ወጥተዋል፡፡ የአገሪቱ መንግሥት በድንገተኛ ጉዳይ ተጠምዷል፡፡
ለቡተፍሊካ አስተዳደር የተቀመጠ አማራጭ ነገር የለም፡፡ ገዥው ፓርቲ ቡተፍሊካን ለሌላ የስልጣን ዓመት ለማቆየት ኃላፊነት መውሰድ አልፈለገም፡፡ ገዥው ፓርቲ ጠቃሚ የሚባሉ ደጋፊዎቹን ያጣ ሲሆን በተለይ ተፎካካሪ ፓርቲዎች፣ የብሄራዊ ሙሀጀዲን ድርጅት እንዲሁም የቀድሞ ወታደሮች ማህበር ይገኙበታል፡፡ የብሄራዊ ነፃነት ግንባር ታዋቂ ሰዎችም በአስተዳደሩ በመማረራቸው ወደ ህዝብ ተቀላቅለዋል፡፡ ዲጃሚላ ቦሂሪድ እና ዞሀራ ድሪፍ ወደ ህዝቡ ከገቡ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ አሁን ያሉት ሁኔታዎች እንደሚያሳየው የአገሪቱ ወታደራዊ ኃይል ቁጥጥር ማድረግ እንዳቃተው ምልክቶች ታይተዋል፡፡
የአገሪቱ አስተዳደር የሚታዩትን ተቃውሞዎች ለመመለስ ሰላማዊ ሰልፈኞች እንዲከፋፈሉ በማድረግ የቀድሞ ተሰሚነቱን መመለስ ይጠበቅበታል፡፡ የሚያደርጋቸውን ማሻሻዎች በማቆም ህገ መንግሥቱን በመጠቀም እርምጃ መውሰድ ይኖርበታል፡፡ ለዚህ ሁሉ ግን የተቃውሞ ሰልፉ ላይ የሚታዩት ነገሮች ወሳኝነት አላቸው፡፡
በአጠቃላይ በአገሪቱ ያለው ዋነኛ ድክመት የአገሪቱ ገዥ ፓርቲ አማራጭ ይዞ አለመንቀሳቀሱ ነው፡፡ የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች ተቃውሞውን የሚደግፉ ሲሆን በተጨማሪም የሶሻሊስት አራማጅ ሆነዋል፡፡ ይህም ሁኔታ በዋና ከተማው ያለውን የኃይል ሚዛን አዛብቶታል፡፡ የአገሪቱ የንግድ ማህበር በአሁን ወቅት በጦር ኃይሉ እየተመራ ይገኛል፡፡ የእስልምና አክራሪ ቡድኖች እአአ 1990 በተደረገው ለውጥ ድርሻቸው ተሽሮ አሁን ባለው መንግሥት እንዲዳከሙ ተደርጓል፡፡
ለፕሬዚዳንትነት የሚወዳደሩ የተፎካካሪ ፓርቲ እጩዎች ህዝባዊ መሰረት የላቸውም፡፡ እነዚህ ሁኔታዎች የለውጥ እንቅስቃሴውን የተዳከመ፣ የተከፋፈለ እና ስትራቴጂ የጎደለው እንዲሆን አድርጓል፡፡ እአአ 1950 በየግድግዳዎቹ ላይ የተፃፉ መፈክሮችና አሁን ያለውን የተቃውሞ ሰልፍ ላይ ታዋቂ የሆነው ‹‹አንድ ጀግና ነው፤ ያለው እሱም ህዝቡ ነው›› የሚለው መፈክር በጉልህ በየአደባባዩ ተሰቅሏል፡፡ ማስታወስ የሚያስፈልገው የተቀሰቀሰው ተቃውሞ የአገሪቱን አስተዳደር አስደንግጧል፡፡
ተቃውሞውም የዓለም አቀፍ ትኩረት አግኝቷል፡ ቀድሞ አማራጮችን ከማስቀመጥ በፊት የገዥው ፓርቲ ስልጣን መረጋገጥ አለበት፡፡ በአልጄሪያ ህዝብ ወደ አደባባይ እንዲወጣ የሚያደርጉ ሁለት በሮች አሉ፡፡ የመጀመሪያው መሰረታዊ ለውጥ የሚያመጡ ነገሮች ቢኖሩም እነሱን በመቃወም አለመቀበል፡፡ ይህ ማለት ግን ገዥውን ፓርቲ መጣል ያስችላል ወይም አማራጭ ተተኪ ማፈላለግ ያስችላል ማለት አይደለም፡፡ ነገር ግን አብዛኛው ህዝብ ወደ ቤቱ ለመመለስ የሚችለው ገዥው ፓርቲ ትክክለኛ ለውጥ እና ወደ ዴሞክራሲ የሚወስድ መንገድ መፍጠር ከቻለ ብቻ ነው፡፡
ህዝቡ ለውጥ ካልመጣ አንነቃነቅም የሚል ሀሳብ ይዞ ይገኛል፡፡ ሁለተኛው ሰላማዊ ሰልፈኞቹ እራሳቸውን የሚያስተዳድሩበት አደረጃጀት ፈጥረዋል፡፡ ለምሳሌ ስራ አስፈፃሚዎች፣ የህትመት ስራ ቡድን እና የድረገፅ አንቀሳቃሾች የሚገኙበት ሲሆን በነዚህ አደረጃጀቶች ክርክሮች፣ መረጃዎች እንዲሁም በምርጫ ሁኔታ ላይ ውይይቶች ተደርገዋል፡፡ ይህ እንቅስቃሴ ከስር ጀምሮ የሚመጣ አመራር ለመፍጠር የሚያግዝ ሲሆን ለቀጣይ ለውጥ የጀርባ አጥንት የሚሆኑ ወጣቶችንም ያፈራል፡፡ የአልጄራዊያን ታሪክ ሲታይ ሁለት እውነታዎች በሁሉም አዕምሮ ውስጥ ይመጣል፡፡
የመጀመሪያው ከህዝብ ኃይል በላይ የሆነ ምንም ነገር የሌለ ሲሆን ይህ ኃይል መንግሥትን ከምንም ነገር የበለጠ ያስፈራዋል፡፡ መንግሥት በሁሉም ነገር የሚደነግጥ ከሆነ በሚመጡ ነገሮች በፍጥነት ይወድቃል፡፡ ሁከት የፈጠረው አካል ስልጣን ከተቆጣጠረ ማንኛውንም ነገር በመሞከር አደገኛ የሆኑ ነገሮችን ለማስወገድ ጥረት ያደርጋል፡፡ እንደ አልጀዚራ ዘገባ በአሁን ወቅት በአልጄሪያውን ፊት የተቀመጠው ነገር የነበረውን በማስወገድ አዲስ የመተካት ጉዳይ ነው፡፡ ይህ ስራ በጣም ከባድ ነው፡፡ ነገር ግን ማንኛውም ዜጋ በአግባቡ የተዘጋጀ ባይሆንም ህዝቡ 132 ዓመት ከፈረንሳይ አገዛዝ ለመውጣት መጣራቸው፣ ስምንት ዓመት ነፃነታቸውን ለማግኘት መዋጋታቸው እና 10 ዓመት የርስበርስ ጦርነት ማድረጋቸው ሲታይ ህዝቡ ለነጻነቱ ተጋድሎ እንደሚያደርግ ማሳያ ናቸው፡፡ አሁንም ዜጎች ክብራቸውን ለማስጠበቅና የተሻለ ነገ ለመፍጠር ትግል እያደረጉ ይገኛሉ፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 16/2011
መርድ ክፍሉ