የዛሬው መንደርደሪያ ታሪካችን እውነተኛ ገጠመኝ ነው ። በእርግጥ በየቀኑ የሚገጥም ገጠመኝ ስለሆነ እምብዛም እንደ ልዩ ገጠመኝ የሚወሰድ አይደለም። “የባለ ጉዳይ ቀን” ተብሎ በተመደበው እለት አንድ ባለሥልጣንን ለማግኘት ወረፋ ይዘው የተሰለፉት ባለጉዳዮች አግዳሚው ወንበር ላይ ተደርድረዋል።ባለሥልጣኑ የእንትን ቀን በሚባል ቀን ምክንያት በባለጉዳዮች ቀን በአጠገባቸው ባለው አዳራሽ ውስጥ ናቸው ።
ባለጉዳዮቹ እየጠበቁ ይመጣሉ የተባሉት ባለሥልጣንም ሳይመጡ ሰባት ሰዓት ደረሰ ። የአዳራሹ ስብሰባ አልቆ ባለሥልጣኑ እየተጣደፉ ወደ ቢሯቸው ገቡ ። ባለሥልጣኑም በወከባ የተወሰኑትን ጉዳዮች በግርድፉ አይተው፤ ባለጉዳዩን በአግባቡ ማናገር ሳይችሉ ቀርተው በችኮላ መንፈስ የምሣ ሰዓት ነው ብለው ሄዱ። ከሰዓት ይመለሱ ይሆናል ጠብቁ የተባሉት ባለጉዳዮች እስከ ዘጠኝ ሰዓት ጠበቁ፤ የዚህ ባለታሪክም ከእለቱ ዘጠኝ ሰዓት ሲል ቦታውን ለቀው ወደ ቤታቸው ሄዱ ።
እኒህ ባለጉዳይ መኪናቸው ውስጥ ገብተው ወደ ቤታቸው እየሄዱ ይህን የመሰለ መጉላላት እንዳይኖር በቀላሉ መልስ ሊሆኑ ስለሚችሉ ነገሮች እያሰቡ ነበር። የመጀመሪያው አማራጭ ዛሬ ባለሥልጣኑ አይችሉም በሌላ ቀን ተመለሱ የሚለው አንዱ ነው ። ሌላው እርሳቸው ባይኖሩ እርሳቸውን ተክቶ ችግሮችን ሊፈታ የሚችል ሰው መወከል መቻል ነው ። የውክልና አሰራር ጉዳይ ለማስፈጸም ብቻ በሆነበት ሀገር ውስጥ ሥራን በውክልና የማሰራት ልምድ አለመኖሩን አስተውለው የጎደለን ነገር ብዙ መሆኑን አሰቡ ። ሌላኛው ቀላል የባለጉዳይን መጉላላት ሊቀንስ የሚችለው አላስፈላጊ ስብሰባዎችን ማስወገድ ነው ። እያንዳንዱ ቀን “የእንትን ቀን” እያልን እናክብር ብንል ኑሯችን ሁሉ አዳራሽ ውስጥ ይሆናል ። አንድ ኃላፊነት ያለበት ግለሰብ ሁሉም መድረኮች ላይ መገኘት የለበትም ። ነገር ግን እጅግ በተመረጡ የስብሰባዎቹ ተጽእኖ የባለሥልጣኑ ወንበር የተሰጠውን ኃላፊነት ወደፊት የሚያራምድ በሆኑ ቦታዎች ላይ ብቻ መገናኘት ። ኃላፊነትን በሚመጥን ደረጃ ላይ የሆኑ መድረኮች ላይ መገኘት። ነገሮችን በክብደታቸው ቅደም ተከተልነት ግምት ማድረግ አለመቻል ትልቁ የሀገራችን አመራሮች ችግር እንደሆነም አሰበ ።
ሁላችንም ዘጠኝ ሰዓት ድረስ ያልተመለሰው ባለሥልጣንን ኮቴ ተከትለነው አብረን እንውጣ ። ግለሰቡ ምሳ በልቶ ከሰዓት በኋላ ምናልባት የመብራት ቤቱን ስልክ ክፍያ ሊከፍል አስቀድሞ ከቢሮ እንደወጣ እናስብ ። የመብራት ክፍያ ሊከፍል የሄደበት ቦታ ላይ እንደእርሱ ዘጠኝ ሰዓት የወጣ አገልግሎት ሰጪ ገጥሞት እየተጉላላ ይሆናል ። በዚህ ጊዜም ባለሥልጣኑ ስለ ሥራ ሰዓት አክብሮ የመስራት ችግርን ያነሳል፤ በእርግጠኝነት ስለ ደንበኞች አገልግሎትም ያነሳል፤ በእርግጠኝነት ደስ በማይል ስሜት ውስጥ መሆኑን የሚገልጽ አካላዊ እንቅስቃሴም ያደርግ ይሆናል ። መብራት ተቋርጦ ከሆነ ደግሞ ችግሩ አይጣል ነው።ባለጉዳይ በመሆን ውስጥ ያለ ውጣ ውረድ፤ ባለጉዳዩ እርሱ በሌላ ባለጉዳይ ላይ የሚፈጽመው ውጣ ውረድ።
በምናባችን አንድ ነገር ደግሞ እናስብ ባለጉዳይ ያለጉዳይ ሆኖ ተሰልፎ ሲውል ። ባለሥልጣኑን ለማናገር ከተሰለፉት መካከል ምንም ጉዳይ የሌለው ዝም ብሎ ባለሥልጣኑን ለማግኘት በማሰብ ብቻ የተሰለፈ ሰው ይኖር ይሆን? አይመስለኝም ። እንደው አለ ብለን እናስብና ይህ ግለሰቡም ወደ ባለሥልጣኑ ቢሮ ገባ ። ከእዚያ ጉዳዩ ምን እንደሆነ ሲጠየቅ “አይ እንዲሁነው” ቢል፤ ወይንም “እርስዎን ሰላም ለማለት ነው” ቢል ወዘተ የሚፈጥረው ስሜት ምን ይሆን ። እያንዳንዱን ደቂቃ በጥንቃቄ ለሥራው ለሚጠቀም ሰው አጋጣሚው የሚያበሳጭ ሊሆንም ይችላል ።
በህይወት ጉዞ ውስጥ ባለጉዳይ መሆን እና ያለ ጉዳይ መሆን ምን እንደሆነ እናነሳለን ። በዚህ ጽሁፍ ህይወትን ከጉዳዮቻችን ጋር እንመለከታለን ። በጉዳይ በተሞላ የሩጫ ዘመን ውስጥ ስንኖር ባለጉዳይነትም ሆነ ያለጉዳይነት ከሁላችንም የራቀ አይደለም ። በቅድሚያ ባለጉዳይ፤
ባለጉዳይ
ጉዳይ የሌለው ሰው የለም፤ ሁሉም የየራሱ ጉዳይ አለው ። በአውቶብስ ውስጥ ያሉትን ሰዎች አቁመን ብንጠይቅ የሚሰጡን ምላሽ ይኖራቸዋል ። አንዳንዱ ወደ ትምህርት ቤት፤ አንዳንዱ ወደ ህክምና፤ ሌላው ወደ ገበያ ወዘተ ሁሉም ጉዳይ አለው ። በህይወት ጉዞ ውስጥ ወደ ምድር ስንመጣ የምናልፍበት ውጣ ውረዱ ውስጥ በሙሉ ጉዳይ አለ ። በጡረታ ጊዜም ሳይቀር ጉዳይ አለ። የትላንቱን በጥሞና መርምሮ ከትላንት የተማርነውን አጠገባችን ላሉት የማስተማር፤ የመምከር፤ ጤንነትን የመጠበቅ፤ መጽሐፍን የመጻፍ ወዘተ ።
ጉዳይ ሁሉም ያለው መሆኑን ከተስማማን ባለጉዳዩን ከጉዳዩ ነጥለን በመሞከር ወደ ዋናው ሃሳባችን እንግባ። አንባቢው ራሱን እንደ ባለጉዳይ ይመልከት፤ አንዳች ፋይዳ እንዳለው ፍጡር ። ከአንድ ጉዳይ ያለፈ አንዳች ነገር በህይወት ውስጥ ሊያከናውን የማይችል ሰው የለም። ሁሉም ሰው የየራሱ እምቅ አቅም ያለው፤ የየራሱ ቀለም፤ የየራሱ ውበት የለው ፍጡር ነው ።
ራስን በጉዳይ ውስጥ ብቻ የመመልከት ችግር የብዙዎቻችን ችግር ነው ። ራስን ወደ መጥላት የሚያመጣ፤ ያሳኩትን ነገር በመቁጠር ውስጥ ለህይወት ትርጉም የመስጠት ችግር ። እኔ ስለ ምንድን ነው ያለሁት ብሎ ራስን ጠይቆ፤ ምላሹም አሉታዊ ሲሆን ራስን መጥላት ይከተላል ። ሰው በውስጡ ያሉትን እያንዳንዱን አካላቱ ቢመረምር እንዴት ግሩም ፍጥረት መሆኑን ይረዳል ። በአንጎል ውስጥ፤ በልባችን ውስጥ፤ በሆድ እቃችን ወዘተ ውስጥ ያሉት አካላት ጥምረትን ስናይ የሰው ልጅ እንዴት ባለ ውስብስብ አካላት እንደተደራጀ ስናይ እንገረማለን፤ በእርግጥም መገረምም ይኖርብናል ። ይህን ሰው ከጉዳዩ ለይተን ስናየው ታላቅነቱን እንመለከታለን ።
ስኬትን በአከናወነው ነገር ውስጥ ለማየት የምናደርገው ሂደት የራሳችንን አቅም አስቀድመን አይተን በትክክለኛው መንገድ ውስጥ እንዳንሆን አድርጎናል ። ከጉዳይ ያለፈን ህይወት ለመኖር የራእይ ህይወት አስፈላጊ ነው፤ የትልቅ መስል ህይወት ።
የራዕይ ህይወት፤ የትልቅ ምስል ህይወት
ህይወትን በጉዳይ ውስጥ ከማየት፤ ህይወትን በራዕይ ውስጥ ማየት እጅግ ይለያል ። በነገ ውስጥ ራሳችንን የምናይበትን ቦታ ዛሬ ላይ መቅረጽ መቻል በጉዳይ ውስጥ ተውጠን ጉዳይ ገድለን ጉዳይ እየተካን ከመኖር በእጅጉኑ ይለያል ። በተስፋ ውስጥ የሚኖር ሰው እያየው የሚራመደው፤ ከውስጡ እየሰማው የሚኖርለት፤ ከጉዳይ ስብስብ ከፍ ያለ እይታ ያስፈልገዋል። እያየ የሚራመደውን ነገር አለማግኘት ማለት የእለት ጉዳይን ከየአቅጣጫው ተቀብሎ ለማስፈጸም በመባከን መኖር ተደርጎም ሊወሰድ ይችላል። በነገው ተስፋ ቆርጦ በዛሬው አኩርፎ እንዲሁ በዛሬ ውስጥ የመኖር ግራ የመጋባት ህይወት ።
አንባቢ ሆይ ራስህን በነገ ውስጥ እንዴት በትልቅ ምስል ውስጥ ታያለህ? በሥራ የት ደረስህ? በትዳር ህይወትህ የት ደርሰህ? በማህበራዊ አስተዋጾህ የት ደርሰህ? ከዛሬ የጉዳይ ስብስብ ከፍ ያለ ። በግልጽ መዳረሻችንን በትልም ምስል ውስጥ ዛሬ ላይ መመልከት መቻል ለህይወት ጉዞ ውጤታማነት ትልቁ ግብዓት ነው። እያንዳንዱን ቀን በውጤታማነት መጠቅም የሚያስችል ግብዓት ።
በዙሪያህ ወዳሉት ልጆች ተመልከት፤ በእነርሱ ህይወት ውስጥ የምንመለከተው አንድ አስደናቂ ነገር አለ፤ እርሱም የራእይ ህይወታቸው ነው ።በዙሪያቸው ካለው ነገር ተነስተው አሻግረው የፊታቸው ያሉትን ቀናት የሚመለከቱ ። ልጅ አባቱንና እናቱንእያየ አባትነትን ይመለከታል ። አባት ሲሆን ያለበትን ኃላፊነትም ይረዳል። በዙሪያው ያሉ ሰዎች ይዘውት ከሚመጡት የጉዳይ ክምር ይልቅ ነገን አሻግሮ የሚመለከትበትን መነጽር ያገኛል ። ጉዳይን ሊያስፈጽም ሲንቀሳቀስ የሚገኘው በትልቁ ምስል ውስጥ ይሆናል ። ትልቁን ምስሉን ህዝብን በአግባቡ ማገልገል ብሎ ያሰበ ባለጉዳይን አጉላልቶ በሥራ ሰዓቱ ጉዳይ ከማስፈጸም ይልቅ እያንዳንዱን ደቂቃ በጥንቃቄ በመጠቀም ምሳሌ ይሆናል ።
በዙሪያህ ያሉትን ልጆች ስትመለከታቸው የተስፋ መቁረጥ ህይወት አታስተውልባቸውም ። ምክንያቱም ተስፈኞች ስለሆኑ ። በነገውስጥ ብዙ ነገሮችን የሚያዩ ተስፈኞች ። ነገን ሲያዩ ጭንቀት አያድርባቸውም፤ ነገርግን ወዳልደረሰቡት ለመድረስ የሚመጡ የእድል ቀናት ሆነው ከመረዳት ውጭ አማራጭ የሌላቸው፤ በጥቃቅን ጉዳዮች ተይዘው የማይውሉ፤ አሁን ያስለቀሳቸውን ከአፍታ በኋላ የሚረሱ ። ከልጅነት እድሜ ተወጥቶ ወደ ኃላፊነት እድሜ ሲደረስ አዲስ ነገን የማየት አቅም እየደበዘዘ ይሄዳል፤ ትልቅ ምስል የመመልከት አቅምም እንዲሁ ። ምክንያቱም በተፈጥሮ በነገውስጥ እንድናይ የተሰጠን እያለቀ ሁሉንም ነገር ላይ ደርሰን ከእዚያስ ለሚለው ጥያቄ ምላሽ መስጠት የሚሳነን ስለሚሆን ። እዚህ ጋር ተፈጥሮ በእድሜ ውስጥ በነገውስጥ ከምትሰጠን ራእይ ባሻገር ራእይ መፍጠር እንዳለብን መረዳት የሚኖርብን ። የሁለተኛ ክፍል ተማሪ ወደ ሦስተኛ ክፍል ውስጥ በመግባት ውስጥ ስላለው ተስፋ እያየ እንድንሄድ ከሚያደርገን ተስፋ ባሻገር ተስፍን በራዕይ ውስጥ በመፍጠር በጥቃቅን ነገሮች ሰዎች ከመጎተት እንዲሁም ተስፋ ውስጥ ማግኘት ይገባናል ። እርሱም የራእይ ህይወት ነው ።
የራዕይ ህይወት፤ የተስፋ ህይወት
ከጉዳይ በላይ የሆንክ ሰው መሆንህ ትርጉም የሚኖረው በራዕይ ውስጥ ነው ። በራዕይ ውስጥ ለራስህ ቦታ መስጠት ስላለ ። ራእይ በአንድ ሰው ህይወት ውስጥ ያለውን ሃይል ለመረዳት እንድንችል የሚባክን ሰዓት አያስፈልገንም ። ራዕይ ሃይል አለው፤ ተስፋን ለመፍጠር የሚሆን ግብዓት ። ዛሬ የምንፈተንበት የኑሮ ውድነቱ አንድን ነገር አቅዶ ለመጀመር የሚሆን ምልከታን አይሰጥም ። በሰዎች መካከል መተማመን አለመኖር ደግሞ ከኑሮ ባሻገር ማህበራዊ መስተጋብራችንን አደጋ ውስጥ ጥሎታል ። በሰዎች የተጎዱ ሰዎች በፍጹም ነጋቸው ውስጥ ብርሃንን ሳይሆን ጭልምተኝነትን ቢያዩ ልንፈርድባቸው አንችልም፤ የተስፋ ጉዞቸው ቢጨልምም እንዲሁ ። በነገ ውስጥ ተስፋን ማየት እንድንችል ዛሬ ልንሰራ የሚገባንን እንስራ ከተባለ ግን ተጽእኖዎችን በሙሉ አልፎ ወደ ፍጻሜው እንዲመጣ የምንተጋለት ራዕይ ያስፈልገናል፤ ጥሩ ባለጉዳይ የሚያደርግ፤ ከጉዳይ በላይ የሚያኖር ። ለሥራ ህይወታችን የሰጠነው ራዕይ ይህን ያህል ሰው ተመርቆ ሥራ ማግኘት አልቻለም ብለን በጨለማ ውስጥ ከማስቀመጥ እኔ እንዲህና እንዲያ አይነት ሥራ የሚሰራ ሰው እሆናለሁ ብሎ ለእርሱ የሚያስፈልገውን ትጋት በማድረግ ወደ ህልማችን ለመቅረብ በእያንዳንዱ ሰከንድ መጠጋት ያስፈልጋል። ባለራዕዮች ልዩነታቸው ከጨለማው አሻግሮ ማየት የሚችሉ መሆናቸው ነውና። ራዕይን ተከትሎ የተግባር ሰውነት አስፈላጊ ነው ። እርሱም ለመማርና ለመተግበር ዝግጁ በመሆን ውስጥ የሚገለጽ ።
ያለጉዳይ መሆን፤ የጥፋት መንገድ
በመነሻታሪካችን ውስጥ ያለጉዳይ ስለመሆን አንስተን ነበር ። ባለሥልጣን ቢሮ ጉዳይ ሳይኖረው የገባን ሰው በማሰብ ። በህይወት ውስጥም ጉዳይ መሰናከያ እንደሚሆን፤ ያለ ጉዳይ መሆንም እንዲሁ ወደ ጥፋት መንገድ ይመራል ። ሰዎች አዎንታዊ አስተሳሰብ ኖሯቸው ጥሩ የሚባል ሥራ እንደሚሰሩ ሁሉ ለምንም ነገር ደንታ ቢስ በሆነ ህይወት ውስጥም በማለፍ ጥፋትን ሊያመጡም ይችላሉ ። ጥፋት ሆን ተብሎ እንዲሁም ሳይታሰብበት ሊሆን ይችላል ።
አንዳንድ ሰው በዘመኑ ሁሉ ሰርቶ የሚያልፈው ጥቂት ነገር ሊሆን ይችላል፤ ዋናው ጉዳይ ጥቂትም ሆነ ብዙ መሆኑ አይደለም ነገርግን ሊሆን የተገባውን ሆኖ ማለፉ እንጂ ። ያለጉዳይ መሆን ፈጽሞ የማይቻል ቢሆንም የምንኖርለት ዓላማን ሳይዙ መኖር ግን በህይወት ውስጥ ያጋጥማል ። እናት ስለ ልጆቿ፤ ወንድምና እህት እንደ ወንድምና እህትነታቸው፤ አሠሪ ለሠራተኛው ወዘተ የሚያደርጉት ነገር ሁሉ ትርጉሙ ብዙ ነው ። ይህ ትርጉም ፍሬ የሚኖረው ኑሯችን ውስጥ ዓላማ በሚይዘው ቦታ ነው ። አባት ልጆችን ወልዶ አስቀምጦ በልጆቹ ላይ ዓላማ ከሌለው የሚሰጠውን ትርጉም ማሰብ ከባድ ነው ።
አንባቢ ሆይ፤ በጉዳይህ እስረኛ ሆነህ ለራስህ ቦታን ከመስጠት አትቆጠብ እንዲሁም ጉዳይ የሌለህ ሆነህ እንዲሁ የምትኖርም አትሁን ። ታላቁ ቀመር የሚዛን ቀመር ነው፤ ሚዛኑም በወርቃማው ህግ ውስጥ የሚገለጽ ። የዓላማ ኑሮ ማጠቃለያው በአጠገባችን ካለው ሰው ጀምሮ ለ ሰው ትርጉም ያለው ሰው መሆን። የእሴት ህይወት ።
እሴታችንን መለየት መቻል
እያንዳንዳችን እንዲኖረን የምንፈልገው ከሌላው መቀበል የምንፈልገው አለ፤ እኛም መስጠት የሚጠበቅብን፤ የእሴት ህይወት ። በጉዳዮች መካከል ተውጠን እንዳንጠፋ፤ የህይወት ጉዞም ከዓላማ መስመር ውጭ እንዳይሆንብን የሚያደርግ ። ከትላንት ወደዛሬ የመጣ በውስጣችን እውቅና የሰጠነው እሴት አለ ። ተቋማት ራዕያቸውን ለማሳካት የሚረዳቸውን እሴት ዘርዝረው ይፋ ያደርጋሉ ። በግል ህይወታችን ውስጥ የራሳችን ያልናቸውን እሴቶች እንዲሁ ሊዘረዘሩ የሚችሉ ሆነው እናገኛቸዋለን ። ቆጥረን የምናውቃቸው፤ በየቀኑ እየጨመርን ሄደን የጥንካሬያችን አካል የምናደርጋቸው ጥንካሬያችንን ስንቆጥር የምናገኛቸው ።
የባለጉዳዩ ጥንካሬ
ማጠቃለያችን ጉዳይ የሌለው ሰው የለም፤ አንተም አለህ፤ በትልቅ ዓላማ ውስጥ የሚኖር ባለ ጉዳይነት ። በእሴት ውስጥ በተገነባ ጥንካሬ ውስጥ ወደ ፍጻሜው የሚደርስ ። ጥንካሬን በማወቅ የሚያስፈልግም ጥንካሬም አለ ። ባለጉዳዩ ጥንካሬውን አለማወቅ የህይወትን አቅጣጫ ድንግዝግዝ ውስጥ ከሚጨምሩት ነገሮች መካከል ዋናው ነው ። መፍትሔው ደግሞ ጥንካሬን ማወቅ ።
ጥንካሬ ሌላ ጥንካሬን የሚወልድ ሆኖ ሥራ ላይ ሲውል ወደ ውጤት የሚያመራ ነው፤ ውጤቱም ባለጉዳይን የማያጉላላ ። እያንዳንዱ ሰው የራሱን ጥንካሬ ከማየት ምናልባትም የሌሎችን የማየት አቅም ሊኖረው ይችላል ። በመሆኑም ሌሎች ስለጥንካሬያችን እንዲሁም ድክመታችን የሚነግሩንን በጥሞና ማድመጥ በትልቅ ምስል ውስጥ ወደ ፍሬ መድረስ እንችላለን ።
በህይወት ጉዞ ውስጥ በድንግዝግዝ እየተራመድክ እንደሆነ ካሰብክ ዛሬ ቆመህ ለራስህ ምላሽ ስጥ፤ ምላሹም ጥንካሬህን በማወቅ ውስጥ በዓላማ መኖር ይሁን ። ሆነን ማለፍ የምንፈልገውን ማድረግ የምንችል መሆናችን የሚወሰነው በጥንካሬያችን ውስጥ በእሴት ነው ። አንድ ሰው ሁሉንም ነገሮች መሆን ባይችልም አንዳች በልዩነት ሊያደርገው የሚችለው ነገር መኖሩን ግን መረዳት አለበት። ስለሆነም ለራስ ቦታ እንስጥ፤ ከምንሰራው ሥራ ውጭ የሚሆን ቦታ መስጠት ። ባለጉዳይ መሆን፤ ነገርግን ከባለጉዳይነት በላይ ለራስ ቦታ የሰጠ ። በጥቃቅን ጉዳይ የማይያዝ፤ ትልቅ ምስል ያለው ። የህይወት ባለጉዳይነት!
በአገልጋይ ዮናታን አክሊሉ
አዲስ ዘመን ሰኔ 4 /2014