የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በዓለም ሕዝብ ላይ ጥርሱን እንደነከሰ ነው። የሚሊዮኖች ሞትና የብዙ ሚሊዮኖች ስቃይ የሰማው ጆሯችን አሁንም ይህንን አይነቱን ዜና በጥቂቱም ቢሆን ከመስማት አላረፈም።
የሰማነውን እያየን በስጋት መኖር ከጀመርን ዓመታት ተተካክተዋል። የሕክምናው ማኅበረሰብ ከኮቪድ 19 ወረርሽኝ ጋር የገጠመው ጦርነትም ገና መቋጫውን አላገኘም። አሸናፊነቱም ገና አልታወቀም። ሆኖም አሁንም ውጊያው እንደቀጠለ ነው። ምክንያቱ ይህ አስከፊ ቫይረስ ከዓለም ላይ አለመወገዱ ነው።
ዛሬ የብዙዎችን በሕመሙ መያዝ መሰቃየት ለመተንፈስ መቸገር ባስ ሲልም ለሞት መዳረግን በዓይናችን እያየን ነው። የተማመንባቸው በርካታ የስነ ልቦና አቅሞቻችን ብሎም ማኅበራዊ መስተጋብሮቻችንና ባህላዊ እሴቶቻችን ሁሉ ከዚህ በሽታ ሊታደጉን አቅም የተሳናቸው ነው የሚመስሉት፤
ሕዝብ ዘንጋ ማለቱን እየጠበቀም እንደ ረመጥ የተዳፈነው የበሽታው ወላፈን እየተስፋፋ ዛሬም ለሌላ እልቂት ሊያዘጋጀን ዳር ዳር እያለን ያለ ይመስላል ። ከጥቂት ወራት በፊት ጋብ ያለ የመሰለው የአገራችን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ዛሬም እንደትላንቱ የሆስፒታል አልጋዎቻችንን ሊያጨናንቅ ብሎም ሕዝብን ሊፈጅ እንደገና የማንሰራራቱ ዜናም እየተሰማ ይገኛል። በመሆኑም አሁን ከጅምሩ ጥንቃቄ ያላደረግንበት ኮሮና ኋላ እንደ ዛሬ ዓመቱና ሁለት ዓመቱ የሆስፒታሎቻችን አልጋዎች ሞልተው የት ልንታከም ነው የሚለው ጭንቀት ውስጥ ስንገባ አይደለም መንቃት ያለብን ዛሬውኑ እንጂ።
ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም በነበረው መረጃ ከቱኒዚያ ቀጥላ በአፍሪካ በርካታ ሰዎች በቫይረሱ የተያዙባት አገር መሆኗ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፤ በእስከ አሁኑ ምርመራ ማለትም እስከ ሰኔ 2 ቀን 2014 ዓ.ም ድረስ 4 ሚሊዮን 968 ሺ 76 ሰዎች የላብራቶሪ ምርመራ ያደረጉ ሲሆን ከእነዚህም መካከል 12 ሺ 996 ሰዎች የኮሮና ቫይረስ ተገኝቶባቸዋል ፤ እስከ አሁን ባለው መረጃም በበሽታው ምክንያት ሕይወታቸውን ያጡ ሰዎች ቁጥር 7 ሺ 516 ሆኖ የተመዘገበ ሲሆን ከበሽታው ያገገሙት ደግሞ 456 ሺ 492 ሰዎች መሆናቸውን ከጤና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ከዚህ የምንረዳው ከዚህ ቀደም ባሉት ወራቶች ምርመራው ቢደረግም በበሽታው ተይዘው የሚገኙ ሰዎች መጠን እጅግ አናሳ የነበረ መሆኑን ነው። ዛሬ ላይ ግን ከፍ የማለት ሁኔታ ታይቶበታል ። በዚሁ በሰኔ 1 ቀን 2014 ዓም ብቻ 4ሺ 678 ሰዎች የኮሮና ቫይረስ ምርመራ ተደርጎላቸው 634 ቱ ሰዎች በሽታው ተገኝቶባቸዋል። ከእነዚህ መካከልም 16ቱ በጽኑ ታመዋል። ጠፍቶ የነበረው የሟች መጠንም አንድ ሰው ሕይወቱ በማለፉ ዳግም ሊመዘገብ ችሏል።
ስርጭቱ በሕዝቡ ውስጥ ይፋዊ በሆነ መልኩ የተሰራጨ ስለሆነ ከክልል ክልል ይለያይ ይሆናል እንጂ ሁሉም ቦታ ላይ ስለመኖሩ ግን አያጠያይቅም። የኮቪድ ሕክምና ማዕከሎቻችን በታካሚዎች ተሞልተው፤ ድንገተኛ ክፍሎቻችን በሕክምና ፈላጊዎች ተጨናንቀው ፤የኦክስጂንና የመተንፈሻ አጋዥ ሜካኒካል ቬንቲሌተር እጥረት ብዙዎችን ለስቃይና ሞት ሲዳርግ ፤ የሕክምና ማዕከላት መጀመሪያ ኦክስጂን ለሚያስፈልጋቸው እየተባሉ የሕክምና ልዩነት እንዲፈጠር ሲያስገድድ የነበረበት ሁኔታ ዛሬ ቢያልፍም አስተምሮ ያለፈው ነገር ግን አለ ። እናም ወደዚህ ችግር ላለመግባት ሁላችንም ቆራጥ መሆን አለብን።
ይህ ቫይረስ መዘናጋታችንን አይቶ ዳግም ለሶስተኛ ጊዜ መጥቶ እንዳይጎዳን ልንጠነቀቅም ይገባል። ለመጠንቀቅ ትልቁ መንገድ ደግሞ ከማን እንደያዘን እንኳን አናውቅምና የግል ጥንቃቄያችንን ከማድረግ በቀር አስተማማኝ አማራጭ የለንም።
በሽታው በአንድ በኩል በሕዝቡ ሕይወትና የሕክምና ሥርዓቱ ላይ ያሳደረው ጫና ከፍተኛ መሆን፤ በሌላ በኩል ደግሞ አሁንም ልናመጣ የሚገባን የግንዛቤና የአመለካከት ለውጥ መኖሩ ግልጽ ነው። ሞት በየበሩ ቆሞ እያንኳኳ “ኮሮና የለም” ከሚል አስተሳሰብ ልንወጣ ይገባል። ለመኖሩም ለሚያስከትለው ሞትም እኛው እራሳችን ያለፉትን ሁለት ዓመታት በማየታችን ብቻ በቂ ምስክሮች ከመሆናችንም በላይ ዛሬም ጤና ሚኒስቴር በሚያደርሰን የየቀን የምርመራ ውጤትና ሪፖርት በቅርበት እያያንና እየሰማን ነው።
በዓለም ላይ ይህ ሁሉ ሰው ሞቶ ከፍተኛ የሆነ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ተከስቶ እያየን ያየነውን የሰማነውን አምነን እንዳንቀበል ዛሬም በተሳሳቱ ግንዛቤዎች እንዲሁም ኮሮና የለም በሚል አጉል ነገር ዋጋ መክፈል የለብንም። በእርግጥ በሀገራችን ብዙዎችን ሲ ያ ስ ተ ና ግ ድ የ ነ በ ረው ት ል ቁ የ ኮ ቪ ድ ሕክምና ማዕከል ኤካ ኮተቤ ሆስፒታል ከወራት በፊት ማዕከሉ ውስጥ ምንም አይነት የኮሮና ቫይረስ ታማሚ አለመኖሩን ይፋ አድርጎ ነበር። በዚህ ዜና ደስ ብንሰኘም ብዙ ርቀት ግን አልሄድንም ፤ ወዲያውኑ ወደ ሕክምና ማዕከሉ መግባት ያለባቸው የኮቪድ ታማሚዎች ተገኙ። በመሆኑም እኛን የሚያዋጣን በሽታው አለ ብሎ ጥንቃቄ ማድረጉ ብቻ ነው።
ለጤና የምንከፍለው ዋጋ አብዛኛውን ጊዜ ለመኖር ካለን አቋም ወይም ፍላጎት ይመነጫል፤ ነገር ግን ረጅም እድሜን በጤና ለመኖር ስናስብ ልንከተላቸው የሚገቡ ወይም አስፈላጊ የሆኑ የጤና አጠባበቅ ዘዴዎች አሉ እነሱን አጓድሎ ግን ረጅም ዓመት መኖርን መመኘት ትርፉ ድካም ብቻ ነው።
ወጣት ዮሐንስ እሸቱ በአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ነው። በሞባይል ቤት ጥገና ሥራ የሚተዳደር ሲሆን እንደ ኮሮና በሽታ የሚንቀው ነገር እንዳልነበር ይናገራል። ገና ያን ጊዜ ቫይረሱ ሀገራችን ገባ ሲባል ሰዎች ሲጨነቁ ንግድ ቤቶች ሲዘጉ መጠጥ ቤቶች የሰዓት ገደብ ሲጣልባቸው እኔ ምንም አይመስለኝም ነበር ሥራዬንም እሠራ ነበር። የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ እንኳን የማደርገው ትራንስፖርት ላይ ስገባ ግዴታ ስለሆነ እንዲሁም በመንገድ ላይ ፖሊሶች እንዳያስቆሙኝ ስል ነበር በማለት በወቅቱ ለኮሮና ቫይረስ ሰጥቶት የነበረውን ግምት ያወሳል።
በሽታው ወደ ሀገራችን ከገባ ከዓመት በኋላ ግን ወጣት ዮሐንስ እሱነቱን እስከሚስት የሚያደርስ ሕመም ታመመ ። ባደረገው ምርመራም የኮሮና ቫይረስ ተገኘበት። በወቅቱ ይላል ወጣቱ በሕይወቴ አይቼው ይገጥመኛልም ብዬ የማላስበው አይነት ሕመም ነበር ያመመኝ። መላ ሰውነቴ የእኔ አልነበረም ትኩሳቱ፣ ቅዠቱ፣ ላቡ፣ እራስ ምታቱ፣ ቁርጥማቱ ብቻ ብዙ ነገር ከባድ ነበር በማለት ያስታውሳል።
ወጣት ዮሐንስ ለኮሮና የሰጠሁት ዝቅ ያለ ግምት ሞት ደጃፍ አድርሶ ነው የመለሰኝም ይላል። ዛሬ ላይ ቆሞ ሲያስበውም በሥራው እስከማፈር የደረሰ ጸጸት ይሰማዋል። ምክንያቱም የጤና ባለሙያዎች የሚሰጡትን ምክር ሰምቼ ቢሆን ኖሮ ለዛ አይነት ሕመም አልጋለጥም ነበርም ሲል መፀፀቱን ይናገራል።
እስከ አሁን ድረስ ቀዝቀዝ ያለ ነገር ስጠጣ ብሎም አየሩ የሚበርድ ሲሆን ድምጼ ይዘጋል፡፡ ብዙም ጤንነት አይሰማኝም የሚለው ዮሐንስ ሰዎች እንደ እኔ ግዴለሽ ሆነው ራሳቸውን አደጋ ላይ መጣል የለባቸውም የሚል ምክሩንም ያስተላልፋል።
“በሚያልፍ ነገር የማንም ሕይወት መጥፋት የለበትም” የሚለው ዮሐንስ እኔ በወቅቱ ሞቼ ቢሆን ኖሮ ተረስቼ ነበርም ይላል። አሁንም ኮሮና ጠፍቷል እያልን እየተዘናጋን
ነው። ነገር ግን በሽታው ሙሉ በሙሉ ጥሎን አልሄደም እንደውም አድፍጦ የእኛን መዘናጋት እየጠበቀ ያለ ይመስለኛል ።በመሆኑም ለሶስተኛ ጊዜ መጥቶ ጉዳት ሳያደርስብን ሁላችንም ልንጠነቀቅ ይገባልም ብሏል።
አዎ ካልደረሰብን አናምንም ካልሆነ በቀር በየቤታችን ቢያንስ አንድ ወይም ሁለት ሰው በዚህ በሽታ ያልተሰቃየ አለ ብሎ መገመት ከባድ ነው። በመሆኑም ሁላችንም ለሀገራችንም ለራሳችንም ለቤተሰባችንም በማሰብ በሽታው ዳግም አገርሽቶ ችግር ላይ ሳይጥለን በፊት ልንጠነቀቅ ይገባል።
በሀገራችን አሁንም ስርጭቱ እየጨመረ ይገኛል። ̋ኮቪድ የለም” ማለቱም እንደማያዋጣ የሕክምና ባለሙያዎች እየተናገሩ ነው። በቅርቡ እንኳን የኤካ ኮተቤ አጠቃላይ ሆስፒታል በማኅበራዊ ትስሰር ገጹ እንዳሰፈረው የኮቪድ 19 በሽታ ጋብ ያለ መስሎ ዳግም ለመነሳሳት ዳር ዳር እያለ በመሆኑ ሁሉም የተለመደ ጥንቃቄውን ያድርግ ሲል መክሯል።
ራስን ከዚህ ወረርሽኝ ለመጠበቅ የበሽታው ምልክቶች ካለባቸው ሰዎች መራቅ፣ በሚያስነጥሱና በሚያስሉበት ወቅት ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ፣ እጅን አዝወትሮ መታጠብ፣ ከሌሎች ሰዎች አካላዊ ርቀትን መጠበቅና እና እንደ ከዚህ ቀደሙም ባይሆን ማኅበራዊ ግንኙነቶቻችን በመጠኑ ማድረግ ያስፈልጋል። እነዚህንና ሌሎች ጥንቃቄዎች ማድረግ እራስን ለመጠበቅ ብቻ ሳይሆን የቫይረሱን ስርጭትም ለመግታት ይረዳል። ካልሆነ ግን የቫይረሱ ስርጭት ዳግም ለሶስተኛ ጊዜ ተከስቶብን በአገራችን ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ኑሯችን ላይ ጫና ማሳደሩ አይቀሬ ነው።በመሆኑም ጠንካራ የጤና ሥርዓት የዘረጉትን ያደጉ ሀገሮች ሳይቀር የሚያሽመደምደው ኮቪድ ዳግም እንዳይጎዳን በማድረግ በኩል ሁላችንም ኃላፊነት አለብን።
በአጠቃላይ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ልክ ቫይረሱ መኖሩ የተሰማ ጊዜ ያሳየውን አይነት የጥንቃቄ ሁኔታ አጠናከሮ መቀጠል ካልተቻለ ቀላል የማይባል የሰው ሕይወት ሊያሳጣ እንደሚችል ዶክተሮች ስጋታቸውን እየተናገሩ ነው።
እፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን ሰኔ 4 /2014