አሸባሪው ሕወሓት መራሹ ችግር ፈጣሪ ቡድን እንደ አገር ጦርነት አውጆብን ሁሉ ነገር ወደ ጦር ሜዳ ከሆነ አመታት እየተቆጠሩ ነው። በእነዚህ ጊዜያት ውስጥ ኢትዮጵያ እንደ አገር ሃብት ንብረቷን ከማጣቷ፣ የጀመረችውን ልማት ከማስተጓጎሏ ባሻገር አምራች የሆነውን ወጣት ሀይሏን እንዲሁም ሌላውን ዜጋዋን ለመገበር የተገደደችበት ወቅት ሆኗል።
ለህዝብ ጥቅም ቆሜያለሁ በሚል የውሸት ብሮፖጋንዳ ያጣውን ስልጣን መልሶ ለማግኘት ቆሜለታለሁ የሚለውን ህዝብ እያፈነና እያሰቃየ ያለው ሕወሓትም ዛሬም የጥፋት ድግሱን እየደገሰ ስለመሆኑ የአደባባ ሚስጥር ከሆነ ውሎ አድሯል ። ከጥፋት ድግሱ ተጠቃሚ የሚሆነውም ማን እንደሆነ የተሰወረ ጉዳይ አይደለም ።
ዛሬ ላይ በትግራይ ትልልቅ ከተሞች ውስጥ ህዝብ እንደጉድ እየታፈሱ ወታደራዊ ስልጠናን እንዲወስድ ይደረጋል፤ ልጄን አልሰጥም ያሉ ወላጆች በአገራቸው ላይ መሆናቸውን እስኪጠራጠሩ ድረስ ከፍተኛ የሆነ እንግልትና ስቃይ እየደረሰባቸው ስለመሆኑ ተደጋግሞ እየተነገረ ነው። ባስ ሲልም ሰዎች ያለምንም ምክንያት ጎዳናዎች ላይ ህይወታቸው እንዲጠፋ እየተደረገ ነው። ይህ የወንበዴ ቡድን ይህን ሁሉ የሚያደርገው እንደሚለው እውነት ለትግራይ ህዝብ ነው? መልስና ፍርዱን ለእናንተ እተወዋለሁ።
ህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ ከዚህ ቀደም ማለትም የትጥቅ ትግል ብሎ በጀመረበት ጊዜ በርካታ የትግራይ ወጣቶችን ገብሯል። በዚህ ጊዜ ልጆቹን ያጣው የትግራይ ህዝብ ገና ቁስሉ አልጠገገለትም፤ እንባው አልደረቀም፤ ነገር ግን ዛሬም ለሌላ እልቂት ልጆችህን አምጣ እየተባለ ነው።
ይህ ቡድን መደበቂያ ሲያጣ ከመሃል አገር ፈርጥጦ የትግራይን ህዝብ እንደጠቀመ በማስመሰል ጉያው ተወትፎ ያልበላውን እያስተፋው ከእህት ወንድሞቹ ጋር ደም እያቃባው ነው። ቡድኑ ምን ጊዜም ከራስ ወዳድነቱ ወጥቶ ከጥፋቱ ተምሮ ህዝብን ለመካስ አገርን ዳግም እንድታንሰራራ ለማድረግ አንዳችም ሃሳብም እቅድም የለውም፤ ምክንያቱም እሱ ስልጣን ላይ ካልወጣ አገር ለእሱ ምንም ስላልሆነች ።
አሁን የትግራይ ህዝብ በአመፅ፣ በጭቆናና በአሸባሪነት የልጆቹን ህይወትና ለአመታት ደክሞ ያፈራውን ንብረት እየተነጠቀ ነው። ለዓመታት የዘለቀው ከባድ በደል፣ ወንጀልና አፈና ዛሬም ተጠናክሮ በመቀጠል ህዝብ ሌላ ስቃይ ውስጥ እንዲገባ እየሆነ ነው ።
ከዚህ በተጨማሪም የትግራይ ህዝብ ወገኑ የሆነው ሌላው ህዝብ የላከለትን ምግብ ፣ መድሃኒት፣ የህክምና ቁሳቁስ እንዲሁም ለልጆቹ የሚመግብውን አልሚ ምግብ በጠቅላላው የሚያስፈልገውን ነገር ሁሉ እንዳያገኝ በማድረግ ረሃብና ሰቆቃን እንደ ጦር መሳሪያ እየተጠቀመ ያለ አመጸኛ ቡድን ሆኗል ።
የሕወሓት የፍትህ ችግር እስከ ዛሬም ህዝቡን ሲያደቅ ነበር ዛሬም ህዝቡ ፍትህ ተጓሎበት የመኖሩ እጣ ፈንታ ጥያቄ ውስጥ ወድቋል ። እዚህ ላይ ልብ ሊባል የሚገባው ይህንን ሁሉ በደል በህዝቦች ላይ የሚያዘንበው ሕወሓት ቡድን እንጂ አምላክ አይደለም እንደ ማንኛውም ፓርቲ በአንድ ወቅት አገር ሲያስተዳድር የነበረ በህዝብ ጥያቄ መሰረት ደግሞ ከመንበረ ስልጣኑ የተባረረ ተራ ቡድን ነው። ታዲያ ይህ ቡድን ህዝቡን እንደ ህዝብ በልቶ ከመጨረሱ በፊት እልባት መስጠት የትግራይ ህዝብ የተሳነው ለምን ይሆን?
ይህ ቡድን በሰላም መኖር የማይችል ሁከትን ብጥብጥ የህልውናው መሰረት ነው ።ይህንንም እኛ ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳንሆን መላው ዓለም በተጨባጭ የሚያውቀውና የሚረዳው ነው ፤ ታዲያ ምነው መፍትሔው ራቀ? የእኔ ብቻ ሳይሆን የብዙዎቻችን ጥያቄ ነው።
አሁን ላይ የትግራይ ህዝብ ልጆቹን ከእልዕቂት ሊታደግ ይገባል። ህዝብም በቃህ ከላዬ ላይ ውረድ ማለት መቻል አለበት። ይህ ምናልባት ከሕወሓት መሰሪ አካሄድ አንጻር ቀላል ላይሆን ይችላል ። “ነገር ግን ድር ቢያብር…….! ነውና ህዝብ እንደ አንድ ሆኖ ከተነሳና ካበረ የሚያቅተው ነገር ስለሌለ በአንድ መነሳቱ የዘመናት ጠላቱ የሆነውን ይህንን አሸባሪ ቡድን ከላዩ ላይ አውርዶ ለመጣል መንገድ የሚሆነው ይመስለኛል።
በሌላ በኩልም በተመቸ ኑሮና በነጻነት እየኖረ ያለው የትግራይ ዲያስፖራም ስለ አያቶቹ ፣ እናቶቹ እህት ወንድሞቹ ብሎ ከገባበት አጉል መንገድና አስተሳሰብ በመውጣት እንዲሁም ምን እየሰራሁ ነው? በማለት ቆም ብሎ ሊያስብና ከህሊናው ጋር ተታርቆ ከወገኑ ጎን ሊቆም ይገባል።
ይህንን በማድረግ እንደ አምላክ ተፈርቶ ወይንም ደግሞ በህዝብ ላይ ፈላጭ ቆራጭጥ ሆኖ ለያዥ ለገላጋይ ያስቸገረውን የወንበዴ ስብስብ ከሁላችንም ላይ ማውረድ በቃህ ማለት እንደ ህዝብ ተሰባስበንና ተረባርበን አገራችንን በማሳደግ አገሮች የደረሱበት ደረጃ መድረስ እኛም እንደሌሎቹ ጠግበን መብላት፣ ተርፎን ማበደር ልጆቻችንን አስተምረን ለአገር ለወገን የሚተርፉ ማድረግ በጠቅላላው ኢትዮዸያን የቀደመ ገናናነቷ እንዲመለስ ማድረግ አለብን ። አበቃሁ!
በእምነት
አዲስ ዘመን ሰኔ 3 /2014