በብዕሩ የወደፊቱን የሚያሳይ፣ ያለፈውን የሚገልጥ፣ የነበረውን የሚያጎላ ድንቅ ሰው ነበር። ግጥሞቹ ምስል ፈጥረው የሚታዩ፣ ጣዕም ኖሯቸው የሚቀመሱ፣ በተለየ ዜማ ለጆሮ የሚጥሙ የጥበብ ከፍታ ላይ የሚቀመጡ ድንቅ ናቸው። የግጥምና ቲያትር ድርሰቶቹም ዛሬ ድረስ ብዙዎች ጋር ደርሰዋል።
ሥራዎቹ ለእልፎች የሕይወትም የጥበብም መማሪያ ሆነዋል። ለኢትዮጵያ ሥነጽሑፍ ያበረከተው አስተዋፅዖ ኃያልነቱ፣ በኢትዮጵያ ሥነጽሑፍ ውስጥ ያለው ቦታ ትልቅነት ለጥበብ ቤተሰቦች መንገር፤ የሚያውቁትን እውነት እንደመድገም ይቆጠራል። የኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ ቀንዲሉ የዓለም ሎሬት ፀጋዬ ገብረመድህን።
ይህ ታላቅ ባለቅኔ የካቲት 1998 ዓ.ም ኒውዮርክ ውስጥ ሕይወቱ ብታልፍም ጥሎ ያለፋቸው ኃያል ሥራዎቹ በትውልዶች ውስጥ ተደጋግመው ስሙን የሚያስጠሩ ናቸው። የጥበብ ሥራዎቹ ዘመናትን ተሻግረው ትላንት ዛሬና ነገን ይገልጣሉ።
“… አዎን፣ ብቻዬን ነኝ ፈራሁ
እሸሸግበት ጥግ አጣሁ
እምፀናበት ልብ አጣሁ
እማማ ኢትዮጵያን መንፈሴ፣ ተፈትቶ
እንዳይከዳት ሠጋሁ … ”
እነዚህና መሰል ጥልቅ ሀሳብና መልዕክት ባላቸው የግጥም ሥራዎቹ ከፍ ያለው ሎሬት ፀጋዬ ገብረመድን፤ ስለ እናት ሀገሩና ምድሩ፣ ስለፍቅሩና መተሳሰሩ ብዙ ሰብኮ በልዩነት ቅኔን ተቀኝቶ አለፈ። ግን ደግሞ ተደጋግሞ ስለሱ ሊወራ ተደጋግም የእርሱ የብዕር ውጤቶች ሊዘከሩ ይገባልና፤ በዚህ ታላቅ የኪነጥበብ ሰው ስም አምቦ ላይ በአምቦ ዩኒቨርሲቲ ቅጥር ግቢ ውስጥ የባህልና የኪነጥበብ ማዕከል ተመሠረተ። ስያሜውም ‹‹ሎሬት ፀጋዬ ገብረመድህን የባህል ጥናትና ምርምር ማዕከል›› ተሰኘ።
በውቧ አምቦ ከተማና ዙሪያዋ ያሉ ወጣቶች እዚያ በኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ ዋርካ በሆነው ለቅኔ መታሰቢያነት በተቋቋመው ማዕከል ተሰባስበው ጥበባዊ አምሮታቸውን በመወጣት ላይ ይገኛሉ። ኪናዊ ፍቅር ያደረባቸው የጥበብ አፍላዎች ተጠራርተው፣ ጥበብ የጠራቻቸው ባለሙያዎች ተሰባስበው ከማዕዱ መቋደስ ከጀመሩ ውለው አድረዋል።
በዚህ ታላቅ የባህል ጥናትና ምርምር ማዕከል በተለይም በአጠቃላይ ሥነ ጽሑፍ፣ በትወና፣ በዝግጅት፣ በሙዚቃ፣ ቲያትርና ውዝዋዜ ጥበቦች ለወጣቶች ስልጠና በመስጠት ላይ ይገኛል። በማዕከሉ ውስጥ የኪነጥበብ ቡድን ኃላፊ የሆነው ወጣት ዘርዓይ ከበደ ማዕከሉ በአካባቢው የኪነጥበብ ፍላጎት ያላቸው ወጣቶች በማሰባሰብ በ6 ልዩ ልዩ መስኮች ስልጠና በመስጠት ላይ እንደሚገኝ በመጠቆም በሚሰጠውም ስልጠና ወጣቶችን ከመሻታቸው ጋር በማገናኘት የሥነ ጽሑፍ መነሳሳት እንደተፈጠረ ይገልፃል።
በከተማዋ የኪነጥበብ ተሰጥዖ ያላቸው በርካታ ሰዎች ይገኛሉ። ይሁን እንጂ ብዙዎች የተቸራቸውን ድንቅ ተሰጥዖ አውጥተውና አዳብረው ለኅብረተሰቡ ለማቅረብ ይቸገሩ እንደነበር የሚገልፀው ወጣት ዘርዓይ ከበደ፣ ማዕከሉ ከተመሠረተ በኋላ ለሙያው ባለቤቶችና ለአዳዲስ ወጣቶች ልዩ ዕድል መፍጠር መቻሉን ያስረዳል። በዚህም በተለያየ የኪነጥበብ መስክ መሳተፍ የሚፈልጉ በከተማዋና በዙሪያዋ የሚገኙ ወጣቶች ተሳታፊ እየሆኑ መምጣታቸውን ይናገራል። ይህም በማዕከሉ ውስጥ ወጣቶች ባህል ነክ የሆኑ የኪነ ጥበብ ሥራዎችን በቲያትር፣ በሙዚቃና ስነ ስዕል በመሳሰሉት የኪነጥበብ ዘርፎች እንዲሳተፉ እድል ሰጥቷቸዋል።
በቀደሙት ጊዜያት በከተማዋ ውስጥ የሚገኙ ወጣቶች በኪነጥበብ ዘርፍ የመሳተፍ ፍላጎት ቢኖራቸውም ምቹ ሁኔታ ስላልነበር የመሳተፉ እድል እንዳልነበራቸው የሚገልፀው ወጣት ዘርዓይ፤ የሎሬት ፀጋዬ ገብረመድህን የባህል ጥናትና ምርምር ማዕከል መመሥረቱ ይህንን ችግር ለመቅረፍ እንዳስቻለ ያብራራል። ከዚህ ቀደም ወጣቶች የኪነጥበብ ሥራዎች ላይ ለመሳተፍ በቤተሰብ ብዙም ፍቃድ እንደማያገኙ በማስታወስም በአሁን ወቅት የተሻለ ግንዛቤ መፍጠር በመቻሉ ወላጆች ልጆቻቸውን ማበረታታት እንደጀመሩ ይናገራል።
በስዕል፣ ሙዚቃና ቲያትር ስልጠና የወሰዱ ወጣቶች ሥራዎቻቸውን በተለያየ መልኩ ለኅብረተሰቡ ማቅረብ ጀምረዋል። በከተማዋ ብዙም ምቹ የሆነ የኪነጥበብ ማቅረቢያ አዳራሾች ባይኖሩም በአምቦ ዩኒቨርሲቲ መሰብሰቢያ አዳራሾችና ልዩ ልዩ ማዕከላት ሥራዎቻቸው ለኅብረተሰቡ እየቀረቡ ይገኛሉ። ሰልጣኞቹ የሚገርም የኪነጥበብ ፍቅርና ተሰጥዖ እንዳላቸው የሚገልፀው ወጣት ዘርዓይ፣ በአካባቢው ለቲያትርና ለልዩ ልዩ የኪነጥበብ ሥራዎች የሚሆኑ መድረኮች ተመቻቸተው የተሻሉና ምቹ አዳራሾች ቢኖሩ በዘርፉ ተዓምር መሥራት እንደሚቻል ይመሰክራል።
ወጣት ጌትነት ጥበቡ በማዕከሉ ውስጥ ሰልጣኝ ሲሆን በስዕልና ቅርፃ ቅርፅ ዘርፍ በመሳተፍ ላይ ይገኛል። ‹‹ማዕከሉ መመሥረቱ ትልቅ እድል ፈጥሮልናል›› የሚለው ጌትነት፤ ከስልጠናው ያገኘውን እውቀት ወደተግባር በመለወጥ ፍላጎትና ምኞቱን ለማሳካት በጥረት ላይ መሆኑን ይናገራል። በሙያው ልዩ ልዩ ክህሎትና የዳበረ ችሎታ ያላቸው ባለሙያዎች ወደ ማዕከሉ እየመጡ ስልጠና የሚሰጥዋቸው በመሆኑም ወጣቶች እራሳቸውን ከጊዜ ወደ ጊዜ በሙያው በማሳደግ ላይ ይገኛሉ።
በአምቦ ከተማ ቀደም ብሎ መሰል የሆነ ስልጠና የሚሰጥ ተቋም ባለመኖሩ ተሰጥዖዋቸውን ለማውጣት ይቸገሩ እንደነበረና ማዕከሉ መመሥረቱ ለብዙ ወጣቶች መልካም ዕድል እንደፈጠረም ያስረዳል። ‹‹በማዕከሉ አማካኝነት ተሰጥዖ ያለን ወጣቶች ተሰባስበን የጥበብ ሥራዎችን በጋራ ለኅብረተሰቡ እንድናቀርብና እራሳችንን በሙያው እንድናሳድግ አድርጎናል›› በማለትም አስተያየቱን ይሰጣል።
በተጨማሪም ማዕከሉ በመመሥረቱ በሚሰጠው ስልጠና ለበርካታ ወጣቶች ሥራ እድል መፍጠሩን ገልፆ፤ ወጣቶቹ በስልጠና ያገኙትን እውቀትና ክህሎት ተጠቅመው ሥራዎችን ለማኅበረሰብ በማቅረብ ተጠቃሚ መሆናቸውን ይናገራል። የስልጠናና መሥሪያ ቁሳቁሶች በአምቦ ዩኒቨርሲቲ አማካኝነት ለሰልጣኞች ድጋፍ እንደሚደረግላቸው የሚገልፀው ወጣት ጌትነት፣ የሠሩትን ልዩ ልዩ የስዕልና ቅርፃ ቅርፅ ሥራዎች በዩኒቨርሲቲው ውስጥ በተለያየ መልኩ ለማሳያነት በተዘጋጁ ቦታዎች ለኅብረተሰቡ ያቀርባሉ።
በማዕከሉ ውስጥ በስዕልና ቅርፃ ቅርጽ ሙያ የሰለጠኑ ወጣቶች በተለያዩ ሀገር አቀፍ መድረኮች ላይ የመሳተፍ እድል ገጥሟቸው እንደነበረ የሚያስታውሰው ወጣት ጌትነት፣ ከዚህ በፊት በባህልና ቱሪዝም አዘጋጅነት በአዲስ አበባ በተዘጋጀ አውደ ርዕይ በማዕከሉ ወጣቶች የተሠሩ ሥራዎች ለእይታ መቅረባቸውን ይናገራል።
ዕድሜያቸው ከ8 አመት በላይ የሆኑ ታዳጊ ወጣቶች ያላቸውን ተሰጥዖ ለማዳበር ወደ ማዕከሉ እየመጡ ስልጠናዎችን እየወሰዱና ኪነጥበባዊ ፍቅራቸውን በመወጣት ላይ ይገኛሉ። በየጊዜው በማዕከሉ ሰልጣኞች የሚሠሩ የስዕልና ቅርፃ ቅርፅ ሥራዎች ለተመልካች የሚቀርቡ ሲሆን ሰልጣኞችም ሥራዎቻቸው ለታዳሚው በነፃ በማስጎብኘትና የሕዝብ አስተያየት በመቀበል እራሳቸውን በማሻሻል ላይ ይገኛሉ።
በማዕከሉ ውስጥ ያሉ የኪነጥበብ ሥራዎች ለማበረታታትና ሰልጣኞች የተሻለ አቅም እንዲኖራቸው በማድረግ ረገድ ማዕከሉ ሰፊ ሥራዎች እየሠራ ይገኛል። የተጠናከረ ድጋፍና ክትትል እንዲኖር በማድረግ ሌሎች ማዕከሉን በተለያየ መልኩ የሚያግዙ ተቋማት አብረውት ቢሠሩና የተሻለ ድጋፍ ማድረግ ቢችሉ ውጤታማነቱ ይበልጥ ሊሆን እንደሚችልም አስተያየቱን ሰጥቷል።
ማኅበረሰቡም በማዕከሉ እየተሰጡ ያሉ አበረታች ሥራዎችን ተረድቶ፤ ልጆቹን ይበልጥ በማበረታታትና በማገዝ በኪነጥበብ ላይ ተሰጥዖ ያላቸውን ወጣቶች ወደ ማዕከሉ ቢልክ እራሳቸውን ብሎም ኪነጥበቡን ለማሳደግ እንደሚረዳ ያስረዳል። ለከተማው ወጣቶች በተለይ ለኪነጥበብ ባለሙያዎች መልካም ዕድል መፍጠር የቻለው ማዕከሉ በጥንካሬው ቢቀጥል የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ እንደሚቻልም ያለውን እምነት ገልጿል።
በማዕከል ደረጃ እጅግ በጣም አበረታች ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን የሚናገረው የኪነጥበብ ቡድን ኃላፊ የሆነው ዘርዓይ፣ በተለይም የወጣቶች የኪነጥበብ ተሰጥዖን ለማሳደግና የተሠሩ ሥራዎችን ኅብረተሰቡ ጋር በማቅረብ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ በርካታ ሥራዎች ማዕከሉ እንደሚሠራ ይጠቁማል።
ነገር ግን በማዕከሉ ትልልቅ ተግባራትና ኪነጥበብን የማሳደግ ተግባር ውስጥ ሌሎች ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው አካላት እንደ ባህልና ቱሪዝም እንዲሁም ከሙያው ጋር የሚሠሩ ተቋማት ድጋፍ ሊያደርጉ እንደሚገባና የማዕከሉን ጥረት መደገፍ እንዳለባቸው አስተያየቱን ይሰጣል። በማዕከሉ ወጣቶች የሚዘጋጁ የኪነጥበብ ሥራዎች ለኅብረተሰቡ ለማቅረብ ከዩኒቨርሲቲው ቅጥር ግቢ ውጪ በከተማው አመቺ ቦታ ባለመኖሩ ሌሎች ተባባሪ አካላት ለዚህ ምቹ ሁኔታ ቢፈጥሩ መልካም ውጤት ማስመዝገብ እንደሚቻልም ያነሳል።
በተለይ የግል ተቋማትና ሆቴሎች ኪነጥበብ ለማኅበረሰቡ የሚያበረክተውን ታላቅ አስተዋፅዖ በመረዳት የኪነጥበብ ባለሙያዎች የተለያዩ መድረኮች እንዲያዘጋጁና ሥራዎቻቸው እንዲያቀርቡ እድል ቢሰጡ መልካም መሆኑን ያስረዳል።
በማዕከሉ ውስጥ ወጣቶች በመሰባሰብና ክህሎታቸውን በስልጠና በማሳደግ በአፋን ኦሮሞና በአማርኛ ቋንቋ የተለያዩ የኪነጥበብ ሥራዎች የሚያቀርቡ ሲሆን በዚህም በከተማዋ ቀድሞ ተቀዛቅዞ የነበረው የኪነጥበብ ሥራዎች በመነቃቃት ላይ በመሆናቸው የተሻለ ኪነጥበባዊ እንቅስቃሴ መፈጠሩን መመልከት ያስችላል።
ከዚያ ከጥበብ ዋርካው የትውልድ ቀዬ እየፈነጠቀ ያለው የኪነ ጥበብ ተስፋ የሚያበረታታ ነውና ማዕከሉና በማዕከሉ ውስጥ ለኪነጥበብ እድገት እየሠሩ ያሉ አካላትን ማበረታታት ይገባል። ከዚህች ውብ አካባቢ የተገኘው ሎሬት ፀጋዬ ትላንት ላይ ዛሬ የምንገኝበትን እውነት ታይቶት ያለንበትን ሁሉ በጥበብ አዕምሮው የገለፀበትና በ1967 ከፃፋው ሀሁ በስድስት ወር እናት አለም ጠኑ ቲያትር ላይ የተወሰደ ግጥሙ የዛሬው የዘመን ጥበብ መደምደሚያ ይሁን።
“…እኛው ነን ፍቅር ያቃተን
እኛው ነን እምነት ያነሰን
እኛው ነን ኅብረት የራቀን
እኛው ነን የባዕድ ክንዶች
አይበቃን ባይ ሆዳሞች፥
የዱብ ዕዳ ፈላስማዎች፥
ቅምጥል የባዕድ ጡቦች
በአርአያ ኢትዮጵያ ሳይሆን፥ በአርአያ ቀኝ ገዥዎች
የታነፅን መጢቃዎች
በወገኖቻችን ላቦት የሰየጠይን ስልጡኖች።
ከታሪክ ከስልጣኔ ፥
ከስነ ባህል ሳይጎለን፡
ለራሳችን ፍቅር ነፍገን፥
እኛኑ ነው ሐቅ የራቀን፥
ትላንትናም ያጨካከነን።
ሐቁን መናገር ስንፈራ፥
ዛሬም ዕምነት የነፈገን፥
እንቶ ፈንቶ ስናወራ፥
እኛው ነን የእኛው መከራ፥
በግፍ መበላለጥ ደግሞ
ደም ማንጠቡ አይቀርም ከርሞ፥
ማለት አለባብሰው ቢያርሱ፥
ደግሞም በአረም ይመልሱ፥”
እንደሚባል ሁሉ፥ለጥፋት ሆነ ለፅድቅም፥ ከቶ ያለኛ የለንም
ምነው እኛ ለእኛ አናውቅም።
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን ሰኔ 2 ቀን 2014 ዓ.ም