
አዲስ አበባ፡- በዘንድሮው ዓመት ትኩረቱን ማስፋፋት ላይ አድርጎ ሊተገበር የታቀደው የሰቆጣ ቃል ኪዳን በ2014 በጀት ዓመት በ214 ወረዳዎች ማስፋፊያ ሥራው መጀመሩን ጤና ሚኒስቴር አስታወቀ ።
ጤና ሚኒስቴር የ2014 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈፃፀሙን በትናንትናው ዕለት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለጤና፣ ማኅበራዊ ልማትና ባሕልና ስፖርት ቋሚ ኮሚቴ አቅርቧል ።
ሪፖርቱን ለቋሚ ኮሚቴው ያቀረቡት በጤና ሚኒስቴር የፖሊሲ ፕላን ክትትልና ግምገማ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ናኦድ ወንድይራድ፤ በዘንድሮው ዓመት የሰቆጣ ቃልኪዳን ላይ ትኩረት ለማድረግ ታቅዶ የነበረው ማስፋፋት ላይ መሆኑን በመግለፅ 240 ወረዳዎች ላይ የማስፋፊያ ሥራ ሊሠራ እንደነበር ጠቁመው በነበረው ሀገራዊ ሁኔታ ምክንያት የማስፋፊያ ትግበራው 214 ወረዳዎች ላይ መጀመሩን ተናግረዋል ።
የሰቆጣ ቃል ኪዳን ለማስፋፋት በተደረጉ ጥረቶች አገልግሎቱ ሁሉንም ክልሎች ባማከለ መንገድ ተጀምሯል ያሉት አቶ ናኦድ ከአፍሪካ ልማት ባንክ ጋር በመነጋገርም የቃል ኪዳኑ ዋና ዋና የሚባሉ ሥራዎች በ17 ወረዳዎች ላይ ተጀምሯል ሲሉ ገልፀዋል ።
ከዚህ ጋር በተያያዘ በሕፃናት የአስተዳደግና የአመጋገብ ሥርዓት ላይ ሚኒስቴሩ በዕቅዱ መሠረት ክትትል ሲያደርግ እንደቆየም ገልፀዋል ።
አቶ ናኦድ እንዳሉት፤ ሚኒስቴሩ የሥርዓተ ምግብ አገልግሎትን ማስፋፋትን በተመለከተ ዕድሜያቸው ከሁለት ዓመት በታች ለሆኑ 2 ሚሊዮን 542 ሺህ 623 ሕፃናት ላይ የሕፃናት ዕድገት ክትትል አድርጓል። በተጨማሪም ለእናቶቻቸው የአመጋገብ ምክር አገልግሎትም ሰጥቷል ።
በሌላ በኩል በሕፃናት ጤና እና ክብካቤ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ ተሠርቷል፤ በዚህም የፀረ አምስት ክትባቶችን በሀገር አቀፍ ደረጃ 98 በመቶ የሚሆኑ ሕፃናት አግኝተዋል ። የኩፍኝ በሽታ ሽፋንም 91 በመቶ ማዳረስ ተችሏል ብለዋል አቶ ናኦድ ። ሁሉንም የክትባት ዓይነቶች የወሰዱ የሕፃናት ሽፋንን በተመለከተም 88 በመቶ መድረሳቸውን ጠቁመዋል ።
የጨቅላ ሕፃናት ጤና አገልግሎትን በተመለከተ ዕድሜያቸው ከአምሥት ዓመት በታች የሆኑ 1 ሚሊዮን 234 ሺህ 497 ሕጻናት የኒሞንያ ክትባት እንዲያገኙ ማድረግ ተችሏልም ብለዋል ።
የሕፃናት ክትባት ሽፋንን ከፍ ለማድረግ ከፍተኛ ርብርብ ሲደረግ ቆይቷል ያሉት ዳይሬክተሩ፤ በሕፃናት ክትባት ላይ ዝቅተኛ አፈፃፀም የነበራቸው በየወረዳዎች ያሉ 349 ጤና ተቋማት ተለይተው እንዲያሻሽሉ ለማስቻል ክትትልና ድጋፍ እንዲሁም የገንዘብ እና አስፈላጊው ድጋፍ ሁሉ ተደርጎላቸዋል ። በተጨማሪም የዘመቻ ሥራዎችን አቅዶ በማሠራት ሥራውን እንዲያሻሽሉ እና አጠቃላይ የክትባት ሽፋኑ ላይ ለውጥ እንዲመጣ ማድረግ ተችሏል ብለዋል ።
ሚኒስቴሩ በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት የቤተሰብ ምጣኔ ደረጃን ወደ 71 በመቶ ለማሳደግ አቅዶ ሲሠራ መቆየቱን የጠቀሱት ዳይሬክተሩ በዘጠኝ ወራት ውስጥ አገልግሎቱን 67 በመቶ መድረስ ተችሏል ያሉ ሲሆን ይህም ከዕቅድ አንፃር ሲታይ አፈጻፀሙ 94 በመቶ እንዲደርስ አድርጓል ብለዋል ።
እንደ አቶ ናኦድ ገለፃ፤ ከ8 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሴቶች የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት ተጠቃሚ ሆነዋል ። ከክልል ክልል በንፅፅር ሲታይም በኦሮሚያ 87 እና በሲዳማ 89 በመቶ የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት በመስጠት ከሁሉም ክልሎች የተሻለ አፈፃፀም አላቸው ሲሉ አብራርተዋል ።
ከዚህ ጋር በተያያዘ በሠለጠነ ባለሙያ የሚሰጥ የቅድመ ወሊድና የድሕረ ወሊድ አገልግሎትን በጤና ተቋማት ሲሰጥ መቆየቱንና 1 ነጥብ 46 ሚሊዮን በላይ እናቶች በሠለጠነ ባለሙያ አገልግሎቱን ማግኘት መቻላቸው ተገልጧል ።
በሀገር አቀፍ ደረጃ የቅድመ ወሊድ አገልግሎት ለ2 ነጥብ 16 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ነፍሰ ጡር እናቶች መስጠት ተችሏል ።ይህም ከሽፋን አንፃር ሲታይ ወደ 66 በመቶ የሚሆኑ እናቶች አገልግሎቱን ማግኘታቸውን የሚያሳይ ነው ብለዋል ።
ውብሸት ሰንደቁ
አዲስ ዘመን ሰኔ 2 ቀን 2014 ዓ.ም