የዛሬው የፍረዱኝ አምድ ዝግጅታችን በመዲናችን በአዲስ አበባ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ፣ ወረዳ ስድስት በተለምዶ ጎፋ ሰፈር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በአንድ ቤተሰብ መካከል የተፈጠረ ውዝግብን ይዳስሳል። በደል ተፈጽሞብናል ሲሉ ለአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍል አቤት ያሉት የ86 ዓመት አዛውንት የሆኑት እማሆይ አለምነሽ ወንድምአገኘሁ እና ልጃቸው ወይዘሮ መድሃኒት ሃይሌ ናቸው።
የ86 ዓመት አዛውንቷ እማሆይ አለምነሽ ወንድምአገኘሁ፣ በንፋስ ስልክ ክፍለ ከተማ፣ ወረዳ ስድስት በ834 የቤት ቁጥር ነዋሪ ናቸው። በዚህ ቤት አምስት ልጆችን እና በርካታ የልጅ ልጆችን በማሳድግ ለወግ ለማዕረግ እንዳበቁበት አዛውንቷ ይናገራሉ።
ይሁን እንጂ በአሁን ወቅት ወይዘሮ በቀለች ሃይሌ የተባለችው ልጃቸው እና ልጆቿ (የልጅ ልጆቻቸው) ልጆቻቸውን እና የልጅ ልጆቻቸውን ካሳደጉበት ቤት ሊያስወጧቸው እንደሆነ ይናገራሉ። በእርጅና ዘመናቸው እጦርበታለሁ፤ እቀበርበታለሁ ካሉት ቤት ፍትህን እና ሞራልን ባልተከተለ አኳኋን ሊያባርሯቸው መሆኑን ያስረዳሉ።
«በዚህ እድሜዬ ለጎዳና ከመዳረጌ በፊትም የኢትዮጵያ መንግስት እና ህዝብ የተፈጸመብኝን አሳዛኝ ድርጊት በመመልከት ይፍረደኝ!» ሲሉ ለአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍል አቤት ብለዋል። የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍልም ከሰዎች እና ከሰነዶች ያገኛቸውን መረጃዎች ዋቢ በማድረግ የኢትዮጵያ ህዝብ ግራ እና ቀኙን በማየት መፍረድ ይችል ዘንድ ዝግጅት ክፍሉ የደረሰበትን ሙሉ የምርመራ ውጤት እነሆ ብሏል። መልካም ንባብ።
ውዝግብ የፈጠረው ቤት የኋላ ታሪክ
የሻለቃ ባሻ ሃይሌ ቡሊ ከዛሬዋ አቤቱታ አቅራቢ እማሆይ አለምነሽ ወንድምአገኘሁ ጋር ሁለት ጉልቻ የመሰረቱት በአጼ ኃይለስላሴ ዘመነ መንግስት ነበር። ጥንዶቹ በትዳር ዘመናቸው በቀለች ሃይሌ ፣መድሃኒት ሃይሌ ፣ ፍቃዱ ሃይሌ ፣አየለች ሃይሌ እና ሰለሞን ሃይሌ የተባሉ አምስት ልጆችን ወልደው ለመሳም ቻሉ። የሻለቃ ባሻ ሃይሌ ወታደር በመሆናቸው ከባለቤታቸው ወይዘሮ አለምነሽ ወንድምአገኘሁ እና ከአምስት ልወጆቻቸው ጋር በካምፕ ውስጥ መኖር የውዴታ ግዴታ ነበር። ስለሆነም ከልጆቻው ጋር ለበርካታ ዓመታት በካምፕ አሳልፈዋል።
የሻለቃ ባሻ ሃይሌ ቡሊ ከአጼ ሐይለስላሴ ዘመነ መንግስት ጀምሮ እስከ ደርግ ዘመነ መንግስት የመጀመሪያ አምስት አመታት ድረስ እናት ሀገራቸውን በውትድርና አገልግለዋል። በንጉሱ ዘመን በሰሩት ወታደራዊ ጀብዱም በአዲስ አበባ ከተማ የመኖሪያ ቤት እንዲሰጣቸው በመንግስት ይወሰናል። በዚህም አሁን ላይ ጎፋ መብራት ሃይል ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ ባዶ ቦታ ተሰጣቸው። ጎፋ ሰፈር አሁን ያለበት ደረጃ እጅግ ጥሩ ቢባልም የሻለቃ ባሻ ሃይሌ ቡሊ የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ ሲሰጣቸው ግን አካባቢው ጫካ እና ያልለማ ነበር። የሻለቃ ባሻ ሃይሌ ቡሊ ቤት ሰርተው ቤተሰባቸውን በራሳቸው ቤት ለመኖር ከነበራቸው ጉጉት ያልለማውን ጫካ መንጥረው ለቤት መስሪያ አዘጋጁት። ነገር ግን በስንት ውጣ ውረድ ጫካ መንጥረው ያለሙትን ቦታ ለመብራት ሀይል ልማት ሊውል በመታሰቡ ቦታውን ለመንግስት እንዲለቁ ተደረገ።
ይህ በእንዲህ እያለ ጎፋ ሰፈር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ቀደም ብሎ ሌተናል ኮሎኔል በቀለ ባልቻ በተባሉ የጦር መኮንን በርስትነት ሲተዳደር የሚኖር አንድ ቦታ ነበር። ኮሎኔሉ በርስትነት ሲያተዳድሩት የነበረውን ቦታ በመተው ሌላ ቦታ ላይ ቤት ይሰራሉ። ይህን ተከትሎ ለመብራት ሃይል ልማት በሚል ጫካ መንጥረው ያለሙትን ቦታ የተነጠቁት የሻለቃ ባሻ ሃይሌ ቡሊ፣ ሌተናል ኮሎኔል በቀለ ባልቻ በርስትነት ይዘውት የነበረው ቦታ ይሰጠኝ ሲሉ በ1966 ዓ.ም ለጽህፈት ሚኒስቴር ያመለክታሉ። ጉዳዩም በጽህፈት ሚኒስቴር ተቀባይነት አግኝቶ በሰኔ ወር 1966 ዓ.ም በቁጥር 3661/8/116/01 ለአዲስ አባባ ከተማ ማዘጋጃ የተባለው ቦታ እንዲሰጣቸው ማዘዣ ደብዳቤ ተላከ። የአዲስ አባባ ከተማ ማዘጋጃም 116/3ዕ/67 በቀን 7/2/1967 ዓ.ም ለርስት እና መሬት ቅየሳ ዋና ክፍል ደብዳቤ ተጻፈ። በደብዳቤውም ሻለቃ ባሻ ሃይሌ ቡሊ የጠየቁት ጥያቄ ተቀባይነት ስላገኘ እንዲፈጸምላቸው የሚያዝዝ ነው። በዚህም መሰረት ኮሎኔሉ በይዞታነት ሲያስተዳድሩት የነበረው አምስት መቶ ካሬ ሜትር ለሻለቃ ባሻ ሃይሌ ቡሊ በ1967 ዓ.ም ተሰጡ።
የአምስት ልጆች አባት የሆኑት ሻለቃ ባሻ ሃይሌ ቡሊ፣ በ1971 ዓ.ም ለግዳጅ በምስራቅ ኢትዮጵያ ግዛት ስር በምትገኘው ገዋኔ እየተባለች ወደ ምትጠራው አካባቢ ለግዳጅ ተላኩ። በዚሁ ዓመት ሻለቃ ባሻ ሀይሌ በግዳጅ ላይ እያሉ አምስት ልጆቻቸውን ተመልሰው ላያዩ ይችን ምድር ተሰናበቱ።
የሻለቃ ባሻ ሃይሌ ቤተሰቦች የካምፕ ህይወትም በዚሁ አመት አበቃ። ወይዘሮ አለምነሽ እና ልጆቻቸው የካምፕ ህይወትን በመተው ዛሬ ላይ ውዝግብ በተነሳበት ቦታ አመሩ። ይህን ተከትሎ የሻለቃ ባሻ ሃይሌ ቡሊ ባለቤት የሆኑት ወይዘሮ አለምነሽ ወንድምአገኘሁ የልጆቻቸው ሞግዚት መሆናቸውን በ1972 ዓ.ም በህግ አሳወጁ። ወይዘሮ አለምነሽ ወንድምአገኘሁ እና ልጆቻቸው ህይትን ያለሻለቃ ባሻ ሃይሌ ሊያስቀጥሉ ግድ ሆነ።
በወቅቱ ለሀገራቸው ሲሉ መሰዋዕት የሆኑ የወታደር ልጆች በውጭ ሀገር በመሄድ እንዲማሩ መንግስት እድሉን ያመቻች ስለነበር ወይዘሮ መድሃኒት እና አቶ በፍቃዱ ሃይሌ የተባሉት የሻለቃ ባሻ ሃይሌ ልጆች በ1972 ዓ.ም ለትምህርት ወደ ሀገረ ኩባ ተላኩ።
ወደ ሀገረ ኩባ የተላኩት የሻለቃ ባሻ ሃይሌ ልጆች አቶ በፍዱ ሃይሌ እና ወይዘሮ ማህሌት ሃይሌ በቤተሰብ ናፍቆት ሳቢያ በተፈጠረ መጨናነቅ ለከፍተኛ ድብርት እና ህመም ተዳረጉ ። በሀገረ ኩባ በባይታወርነት እየተሰቃዩ መኖር እንዲያበቃ በመወሰን ወደ ሀገራቸው ለመመለስ የሚመለከተውን አካል ጠየቁ። በዚህም አቶ በፍዱ ሃይሌ በ1977 ዓ.ም ወደ እናት ሀገራቸው ሲመለሱ ፤ ወይዘሮ ማህሌት ሃይሌ ደግሞ ወንድማቸውን ተከትለው 1978 ዓ.ም ወደ ኢትዮጵያ ተመለሱ።
ሁለት ልጆቻቸውን ወደ ሀገረ ኩባ የላኩት እናት ወይዘሮ በቀለች ሃይሌ፣ ወይዘሮ አየለች ሃይሌ እና አቶ ሰለሞን ሃይሌ ከተባሉት ልጆቻቸው ጋር አብረው ይኖሩ ነበር ። በቤተሰቡ ውስጥ የነበረው ፍቅር ለሰፈር የሚያስቀና ነበር ።ከውርስ ጋር ተያይዞ አንዳቸው አንዳቸውን መጠራጠር ብሎ ነገር አልነበረም። ወደ ኩባ የሄዱት ልጆች ወደ ሀገራቸው ሲመለሱ ያረፉትም በእናታቸው እና በአባታቸው ቤት ነበር።
ቀንን ቀን ሲወልደው ወይዘሮ በቀለች ሃይሌ የተባሉት የቤተሰቡ የመጀመሪያ ልጅ እናታቸውን ወይዘሮ አለምነሽን በምስጢር ቤቱን እንዲያወርሷቸው ይጠይቃሉ። ወይዘሮ አለምነሽም ለማንም ጉዳዩን ሳያሳውቁ እና ሳይሰሙ በ1985 ዓ.ም ቤቱን ለወይዘሮ በቀለች ብቻ ያወርሳሉ።
ነገሩን በምስጢር ማድረጋቸው እየቆየ የከነከናቸው እናት ለልጃቸው ያወረሱትን ቤት ከልጃቸው መውሰድ ፈለጉ። ቤቱን እንድትመልሳልቸውም ልጃቸውን ይጠይቃሉ። ልጅም ቤቱ የእኔ እንጂ ያንቺ ስላልሆነ ቤቱን እንድመልስልሽ የመጠየቅ መብት የለሽም ይላሉ።
ይህን ተከትሎ አራቱ ልጆች ስለጉዳዩ ሳያውቁ እና ሳይሰሙ እናት ወይዘሮ አለምነሽ በ2000 ዓ.ም በውርስ የሰጠኋትን ቤት ትመልስልኝ ሲሉ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ወሰዱት። ጉዳዩ በፍርድ ቤት ሲታይ ቆይቶ እናት በፍርድ ቤት ክርክር ይረታሉ። እናትን የፍርድ ባለዕዳ እንዲሆኑ ያደረጋቸውም ቤቱን ለልጃቸው ካወረሱት በርካታ አመታት በመቆጠሩ የይርጋ ጊዜ ገደብ አልፎበታል በሚል ነበር።
እውነት እና እሳትን አፍኖ ማቆየት ይቻል እንደሆን እንጂ እስከመጨረሻው መደበቅ አይቻልም እንዲሉ በ2006 ዓ.ም የሻለቃ ባሻ ቡሊ አራቱም ልጆች ስለጉዳዩ ይሰማሉ። የሰሙትን ማመን የከበዳቸው የሻለቃ ባሻ ልጆች እንዴት እንደዚህ ይሆናል? ሲሉ እናታቸውን እና እህታቸውን ይጠይቃሉ። እናት ሳያውቁ ተታልለው ለወይዘሮ በቀለች እንዳወረሱ እና ጉዳዩን በደንብ ከተረዱ በኋላ ግን በስጦታ ያወረሱትን ቤት ለማስመለስ እስከፍርድ ቤት መሄዳቸውን ለልጆቻቸው ያስረዳሉ።
ይሁን እንጂ በብቸኝነት ቤቱን የወረሰችው ልጅ ደግሞ ቤቱ የእርሷ እንደሆነ እና ስለቤቱ ማንም እንደማያገባው አስረግጠው ለወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው ይነግሯቸዋል። ይህን ተከትሎ በፍቅር እና በመተሳሰብ አንቺ ትብሽ አንተ ትብስ ብሎ ሲኖር የነበረው ቤተሰብ በመካከሉ ክፉኛ ነፋስ ገባው። ቤሰተቡ በከፍተኛ ደረጃ መግባባት ራቀው።
ይህ በእንዲህ እያለ እናት ወይዘሮ አለምነሽ ወንድምአገኝ በ1971 ዓ.ም ባለቤታቸው በግዳጅ ላይ መስዋታቸውን ተከትሎ በ1972 ዓ.ም ቤተሰቡን ለማሳድግ የሞግዚነት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት ከህጋዊ አካል የተቀበሉ ቢሆንም በቤቱ ላይ ህጋዊ ወራሽነታቸውን የሚያሳይ ማስረጃ ባለመኖሩ ቤቱን ከባለቤታቸው በውርስ ስለማግኘታቸው የሚያረጋግጥ የባለመብትነት የምስክር ወረቀት ይሰጠኝ ሲሉ በ2006 ዓ.ም ለንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ አመለከቱ። ክፍለ ከተማውም ህጋዊ ወራሽ ስለመሆናቸው ቤቱንም በውርስ ከሻለቃ ባሻ ሃይሌ እንደወረሱት የሚገለጽ ምስክር ወረቀት በ2006 ዓ.ም ይሰጣቸዋል።
ይህ በእንዲህ እያለ ቤቱ የአባታችን ስለሆነ ለእኛም ይገባናል ሲሉ የሻለቃ ባሻ ሃይሌ ልጅ የሆኑት ወይዘሮ መድሃኒት፣ አቶ ሰለሞን፣ ወይዘሮ አየለች እና አቶ በፍቃዱ ለፍርድ ቤት አቤት አሉ።
በፍርድ ቤት የነበረው ክርክር እና ውሳኔ
ከባለውርስ ባለመብትነት ጋር ተያይዞ በፍርድ ቤት የነበረው ክርክር ከመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት እስከ ሰበር የደረሰ ሲሆን፣ ከስምንት አመት በላይ የፈጅቷል። ከመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በነበረው የፍርድ ቤት ክርክር ወይዘሮ መድሃኒት ሃይሌ፣ አቶ ፍቃዱ ሃይሌ፣ ወይዘሮ አየለች ሃይሌ እና አቶ ሰለሞን ሃይሌ ከሳሽ፤ እናት ወይዘሮ አለምነሽ ወንድምአገኘሁ እና ወራሽ እህት በቀለች ሃይሌ በቀደም ተከተል አንደኛ እና ሁለተኛ ተከሳሽ ሆነው ተከራክረዋል። በፍርድ ቤት በነበረው ክርክር ከሳሽ ቤቱ የአባታችን ስለሆነ እና እኛም አንደኛ ደረጃ ህጋዊ ወራሽ ስለነሆን ከቤት ውርስ ጋር ተያይዞ የሚከናዎኑ ማናቸውም አይነት ተጠያቂሚ የሚያደርጉ መብቶች እኛንም ይመለከተናል አሉ። እናትም የመጀመሪያ ልጄ የወሆነችው ወይዘሮ በቀለች እኔ ያልተማርኩ በመሆኔ እኔን በማታለል ቤቱን ከልጆች ደብቃ ነው የወረሰችው። በመሆኑም ቀሪ ልጆቼም በቤቱ የሚኖራቸው መብት ይከበርላቸው ሲሉ ከሳሽ ልጆቻቸውን ደግፈው ቆሙ።
ሁለተኛ ተከሳሽ የሆኑት ወይዘሮ በቀለች በበኩላቸው፤ አራቱም ልጆች በወራሽነት ያልተመዘገቡ ስለሆኑ እና ከጅምሩ ቤቱ የእኔ እንጂ የእናታችንም ሆነ የአባታችን የሻላቃ ባሻ ሃይሌ ቤት ስላልሆነ ከሳሽ ወንድም እና እህቶቼ ከውርስ ጋር ተያይዞ ያነሱት የይገባኛል ጥያቄ አግባብነት የለውም ሲሉ ተከራከሩ።
ቤቱን የወረሱት ልጅ ከመጀመሪያም ጀምሮ ቤቱ የእኔ እንጂ በውርስ የተገኘ አይደለም ማለታቸውን ተከትሎ ጉዳዩን የያዘው ፍርድ ቤት ቤቱ የማን ነው? የሚለውን ለማጣራት ጉዳዩን ለውርስ አጣሪ አካል መራው። ይህን ተከትሎ የውርስ አጣሪው አካል ቤቱ በ1967 ዓ.ም ለሻለቃ ባሻ እንደተሰጣቸው እና በ1971 ዓ.ም ሻለቃ ባሻ በግዳጅ ላይ እያሉ በማረፋቸው በ1972 ዓ.ም እናት ወይዘሮ አለምነሽ ደግሞ ቤቱን የልጆች ሞግዚት ሆነው እንዳስተዳደሩት እንዲሁም በ1985 ዓ.ም ወይዘሮ አለምነሽ ለተከሳሽ ወይዘሮ በቀለች በስጦታ ውል ማስተላለፋቸውን ገልጾ ፤ ይሁን እንጂ በፍታብሄር ህግ ቁጥር 1195(1) መሰረት ከቤቱ ጋር ተያይዞ የምስክር ወረቀት ያገኘ ሰው በማይንቀሳቀስ ንብረት ሆኖ እንደሚቆጠርለት ስለሚደነግግ ቤቱን በስጦታ ውል እናት ስላስተላለፉት እና ቤቱን በመተመለከተ ወይዘሮ በቀለች የምስክር ወረቀት በህግ ከተፈቀደለት አካል ስለተሰጣቸው ከ1985 ዓ.ም ጊዜ ጀምሮ ወይዘሮ በቀለች የሚያስተዳደሩት የግል ንብረት እንጂ የውርስ ንብረት አይደለም ሲል መለሰ።
ይሁን እንጂ ፍርድ ቤት ባደረገው ተጨማሪ ምርምራ የውርስ አጣሪው የደረሰበት ውሳኔ ትክክል አይደለም በሚል ተቀባይነት ሳያገኝ ቀረ። ይህ የፍርድ ቤት ውሳኔ ከመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት እስከ ሰበር ሰሚ ችሎት ድረስ የጻና ሆነ።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ሁሉም ልጆች የወራሽነት ማረጋገጫ ከፍርድ ቤት እንዲያመጡ ተጠቀ። አራቱም ከሳሽ ልጆች የመጀመሪያ ደረጃ ወራሾ መሆናቸው ተረጋገጠ ። ይሁን እንጂ ከሻለቃ ባሻ ሞት በኋላ ወደ ኩባ ያልሄዱት ልጆች የወራሽነታቸው መብታቸው በይርጋ ታገደ።
የይገባኛል ክርክሩም ኩባ በሄዱት ወይዘሮ መድሃኒት ሃይሌ እና አቶ ሰለሞን ሃይሌ ከሳሽ እናት ወይዘሮ አለምነሽ እና ወራሽ ልጃቸው ወይዘሮ በቀለች ተከሳሽ ሆነው ቀረቡ። ክርክሩም እስከሰበር ሰሚ ችሎት ዘለቀ።
በክርክሩም ቤቱን በስጦታ ያወረስኩት ያልተማርኩ ስለሆነ በማታለል እና በማጭበርበር ነው ሲሉ እናት ለሁሉም ለፍርድ ቤቶች አስረዱ። ይሁን እንጂ የቤቱን ግማሽ ወይዘሮ በቀለች በስጦታ መውረሳቸውን እና አሁን ላይ ደግሞ የእናት ቤቱን የማስመለስ ህጋዊ መብት በይርጋ የተገደበ መሆኑን አስገንዘቦ በውርስ ለወይዘሮ በቀለች የተሰጠው ግማሽ ቦታ ለወይዘሮ በቀለች እንዲሰጥ ሰበር ሰሚ ችሎቱ ወሰነ። ግማሹ የሻለቃ ባሻ ሃይሌ ድርሻ ደግሞ ለሶስት ማለትም ወይዘሮ መድሃኒት ሃይሌ ፣ አቶ ሰለሞን ሃይሌ እና ለወይዘሮ በቀለች እንዲከፋፈሉ ሰበር ሰሚ ችሎቱ ወሰነ።
በዚህ ውሳኔ መሰረት የቤቱ ግማሽ እናት ለወይዘሮ በቀለች በስጦታ ውል ያወረሱት ስለሆነ በወይዘሮ በቀለች ወራሽነት እንዲጸና እና ግማሹ የአባት ድርሻ ደግሞ ለሶስት እንደተካፈሉት ተወሰነ።
ወይዘሮ መድሃኒት ሃይሌ ፣ አቶ ፍቃዱ ሃይሌ ፣ ወይዘሮ አየለች ሃይሌ እና አቶ ሰለሞን ሃይሌ ቦታውን እናታችን ከአባታችን ያገኘችው እንጂ በራሷ ያፈራችው ስላልሆነ ለአንድ ልጇ ብቻ የማውረስ መብት የላትም። ቤቱ የአባታችን ስለሆነ እና አባታችን ሲሞት አሁን ለክርክር የቀረቡት ልጆች ለአቅመ አዳም እና ለአቅመ ሄዋን ያልደረሱ ስለነበር እናት ልጆችን በሞግዚትነት ለማስተዳደር ቤቱን በሃላፊነት ተሰጣት እንጂ አልወረሰችም። ስለሆነም የራሷ ልላሆነ ንብረት ማውረስ አትችልም ሲሉ ተከራከሩ።
በመጨረሻም ክርክሩን ሲያዳምጥ የነበረው ፍርድ ቤት የአከራካሪው ቤት ግማሽ የሚሆነው እናት ለወይዘሮ በቀለች ያወረሱት ስለሆነ ለወይዘሮ በቀለች የተሰጠው ቦታ ባለበት አንዲጸና እና ግማሹ የአባታቸው ድርሻ ደግሞ ከእናታቸው ውርስ ያገኙትን ወይዘሮ በቀለችን ጨምሮ ለሶስት እንዲከፋፈሉ ተወሰነ።
ለአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍል አቤት እንዲሉ ያስቻሉ አስገዳጅ ምክንያቶች
የፍርድ ባለእዳን ወይዘሮ መድሃኒት ሃይሌን እና እናታቸውን እማሆይ አለምነሽ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል አቤት እንዲሉ ያስገደዳቸው አንደኛው አብይ ምክንያት ከውርስ የተገለሉት ወይዘሮ አየለች ሃይሌ እና አቶ ሰለሞን ሃይሌ በእናት እና በአባት አንድ በመሆናቸው አንደኛ ደረጃ ህጋዊ ወራሾች መሆናቸው እየታወቀ ኩባ ሀገር ስላልሄዱ ብቻ ከአባታቸው ድርሻ የወራሽነታቸው መብታቸው በይርጋ መታገዱ ትክክል አይደለም። ወይዘሮ አየለች ሃይሌ እና አቶ ሰለሞን ሃይሌ ከአባታቸው የወራሽነት ባለመብትነታቸው ከወይዘሮ በቀለች ጋር ተመሳሳይ ሆኖ ሳለ በይርጋ መታገድ ካለበት የወይዘሮ በቀለችም በይርጋ መታገድ ሲገባው ከላይ የተጠቀሱት የቤተሰቡ አባል የወራሽነት መብት ነፍጎ ለወይዘሮ በቀለች ብቻ በይርጋ የማይታገድበት መንገድ ፍትሃዊ አይደለም።
ሌላው የፍርድ በለዕዳ የሆኑትን ወይዘሮ ማህሌት እና እናታቸውን ወደ አዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍል ለአቤቱታ ያበቃቸው ነገር እናት ወይዘሮ አለምነሽ ወንድምአገኘሁ ባለቤታቸው ሻለቃ ባሻ ሃይሌ ቡሌ እንደሞቱ በአመቱ በህግ የተፈቀዳላቸው ለአቅመ አዳም እና ለአቅመ ሄዋን ያልደረሱ ልጆችን በሞግዚትነት እንዲንከባከቡ እንጂ ከሻለቃ ባሻ ሃይሌ ቤቱን እንዲወርሱ አይደለም። ወራሽ ስለመሆናቸው የሚያሳይ ሰነድ የለም ። ከሻለቃ ባሻ ሃይሌ ቤቱን በህጋዊ መንገድ መውረሳቸው የሚመለከተው አካል አረጋግጦ ምስክር የሰጣቸው በ2006 ዓ.ም ነው። ይሁን እንጂ ይህ ህጋዊ የውርስ ሰነድ በሌለበት እናት ወይዘሮ አለምነሽ ወንድም አገኘሁ በ1985 ዓ.ም ለለልጃቸው ለወይዘሮ በቀለች ሃይሌ አውርሰዋል። ይህ ደግሞ በግልጽ የሚታይ የህግ ክፍተት ያለበት ሆኖ ሳለ ፍርድ ቤቱ ወይዘሮ በቀለች ከእናታችን በስጦታ ያገኘናቸውን ውርስ በይርጋ ለወይዘሮ በቀለች ማገዱ አግባብነት የለውም።
ሌላውና በሶስተኛ ደረጃ የፍርድ ባለእዳዋ ወይዘሮ ማህሌት እና እናታቸውን ወደ አዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ለአቤቱታ ያመጣቸው አብይ ጉዳይ ደግሞ ከፍርድ ቤት ውሳኔ በኋላ የተተገበረው የፍርድ የአፈጻጸም አካሄድ ነው። የቦታው ግማሽ ለሶስት እንዲከፍል ፍርድ ቤት ትዕዛዝ እያለ ፍርድ አፈጻጸም ዳይሬክቶሬት ቢሮ በዓይነት ከማካፈል ይልቅ ቤቱ ጨረታ በማውጣት እንድንካፈል ለማድረግ ሲጥር ይስተዋላል። ይህ ደግሞ እናታችንን በዚህ አድሜዋ ጎዳና ላይ የሚጥል ነው ።
ቦታው በጨረታ ይሸጥ ቢባል እንኳን የፍርድ አፈጻጸም ለጨረታ ያወጣው የቦታው ልኬት ትክክል አይደለም። ቦታው በካርታ 500 ካሬ ሜትር ይሁን እንጂ የክፍለ ከተማው የመሬት አስተዳደር ባደረገው የማጣሪያ ልኬት መሰረት የቦታው ስፋት 680 ካሬ ሜትር ነው። ይሁን እንጂ ህግ አፈጻጸም ቦታው 500 ካሬ ሜትር እንደሆነ በማስመሰል ቦታውን በአይነት ከማካፈል ይልቅ በሃራጅ እንዲሸጥ ጨረታ አወጣበት። የፍርድ አፈጻጸም ቢሮ አካሄድ ትክክል ስላልሆነ ጉዳዩ እንደገና እንዲታይልኝ ሲሉ ለፍርድ ቤት እንደገና አቤት ማለታቸውን ወይዘሮ መድሃኒት ይናገራሉ። ፍርድ ቤትም ጉዳዩ እንደገና እንዲታይ ለፍርድ አፋጻጸም ዳይሬክቶሬት ቢሮ መጻፉን ያስረዳሉ።
የፍርድ አፈጻጸም ዳይሬክቶሬት ቢሮም የፍርድ ቤት ትዛዝን ተቀብሎ እንደገና ጨረታ አወጣ። ይሁን እንጂ የፍርድ አፈጻጸም ዳይሬክቶሬት ቢሮ አጠቃላይ የቦታው ስፋት 680 ካሬ ሜትር ሆኖ ሳለ የተስተካከለ ከክፍለ ከተማ የተሰጠን የቦታ ልኬት 580 ካሬ ሜትር ነው በማለት የቦታው ግማሽ 290 ካሬ ሜትር ለወይዘሮ በቀለች በመስጠት፤ ግማሹን 290 ካሬ ሜትር ደግሞ ለሁለተኛ ጊዜ የሐራጅ ማስታወቂያ በማውጣት ሊሸጥብን ነው። ይህ ደግሞ እናታችንን ጎዳና ላይ የሚጥል ውሳኔ ነው ሲሉ የፍርድ ባለእዳዋ ይናገራሉ ።
እናታችን የነርቭ ችግር ያለባት ስለሆነች እና ከወይዘሮ በቀለች ውጭ ያሉ ልጆቿም ተከራይተን የምንኖር በመሆናችን በኪራይ ቤት ደግሞ የነርቭ ችግር ያለበትን እና ራሱን ችሎ የማይጻዳዳን ሰው ለማኖር አከራዮች ፍቃደኛ ስለማይሆኑ እናታችን ለጎዳና ልትዳረግብን ስለሆነ የኢትዮጵያ ህዝብ እና መንግስት ይድርስልን ሲሉ የፍርድ በለእዳዋ ይጮኃሉ።
ፍርድ አፈጻጸም ዳይሬክቶሬት ቢሮ ምላሽ
ጉዳዩን በበላይነት ሲከታተሉት የቆዩት በፍርድ አፈጻጸም ዳይሬክቶሬት ቢሮ የቴክኒክ ክፍል ባለሙያ አቶ እስማኤል ኢብራሂም ይባላሉ። የቴክኒክ ክፍል ባለሙያው የሰጡትን ምላሽ እነሆ፡-
እንደ አቶ እስማኤል ገለጻ፤ የፍርድ አፈጻጸም ዳይሬክቶሬት ቢሮ በፍርድ ቤት የሚወሰኑ ውሳኔዎችን በክፍለ ከተማ ከሚገኙ መረጃዎች ጋር በማመሳከር የፍርድ አፈጻጸም ስራዎች ይከናወናሉ።
በዚህም መሰረት የፍርድ አፈጻጸም ቢሮው ከፍርድ ባለእዳ ወይዘሮ መድሃኒት እና በፍርድ ባለመብት ወይዘሮ በቀለች ጋር ተያይዞ ተፈጠረ የተባሉ ችግሮችን እንዴት እንደተፈጠሩ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል አብራርተዋል።
አንደኛው ወይዘሮ መድሃኒት ጥያቄ ቦታው በአይነት ያካፍሉን የሚል ነው። ይህን ለምን በዓይነት ለማካፈል አልተቻለም? ሲል የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍል ይጠይቃል። በፍርድ አፈጻጸም ዳይሬክቶሬት ቢሮ የቴክኒክ ክፍል ባለሙያ የሆኑት አቶ እስማኤል እንደሚሉት፤ በአዲስ አባባ መሬት አስተዳደር መመሪያ መሰረት አንድ ቦታ ራሱን ችሎ ሊለማ የሚችለው 150 ካሬ ሜትር እና ከዚያ በላይ ስፋት ሲኖር ብቻ ነው። እነወይዘሮ መድሃኒት ለሶስት ይካፈሉት ተባለው ቦታ 290 ካሬ ሜትር ነው። ይህ ደግሞ ለሶስት ሲካፈል በአዲስ አባበ ከተማ አስተዳደር መመሪያ መሰረት ራሱን ችሎ መልማት ስለማይችል በዓይነት ለማካፈል አይቻለም።
የፍርድ አፈጻጸም ዳይሬክቶሬት ቢሮ የመጀመሪያ ምርጫው የፍርድ ቤት ውሳኔዎችን በዓይነት ማካፈል ነው። ይህ አልሆን ሲል በስምምነት ቦታው ተሽጦ እንዲካፈሉት ይደረጋል። ይህ አልሆን ሲል ደግሞ በሃራጅ ጨረታ ይወጣበት እና ቦታው ተሽጦ ፍርድ ቤት በወሰነው መሰረት ለእያንዳንዳቸው የድርሻቸው እንዲሰጣቸው ይደረጋል።
የእነ ወይዘሮ መድሃኒትም በአንደኛው እና በሁለተኛው አማራጭ የፍርድ አፈጻጸሙን ማስኬሄድ ባለመቻሉ የፍርድ አፈጻጸም ዳይሬክቶሬት ቢሮው ሶስተኛውን አማራጭ ለመምረጥ ተገዷል።
የፍርድ ባለእዳዋ ወይዘሮ መድሃኒት ቤቱ መሬት ላይ ያለው ልኬት 680 ካሬ ሜትር ሆኖ ሳለ በካርታ ላይ ያለውን 500 ካሬ ሜትር ነው በማለት 250 ካሬ ሜትር ብቻ እንድንወስድ እየተደረገ ነው። በዚህ ደግሞ ለጨታ የቀረበው ቦታ ርካሽ እንዲሆን ያደርግብናል ሲሉ ይጠይቃሉ። ስለዚህ ምን ይላሉ? ሲል የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍል ዳይሬክቶሬት ቢሮውን ይጠይቃል።
እውነት ነው ለመጀመሪያ ጊዜ በፍርድ አፈጻጸም ጨረታ የወጣበት በ500 ካሬ ሜትር ስፋት ብቻ ነበር። ነገር ግን የፍርድ በለእዳዋ ከክፍለ ከተማ አስጽፈው ባመጡት ደብዳቤ ቦታው 580 ካሬ ሜትር እንደሚለካ ስለተረጋገጠ የመጀመሪያው 250 ካሬ ሜትር ላይ የወጣው ጨረታ ተሰርዞ ለሁለተኛ ጊዜ ተስተካከልሎ 290 ካሬ ሜትር በሚል በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጨረታ ወጥቷል።
ይህን ተከትሎ የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍል የፍርድ በለዳዋ የሚሉት ቦታው 680 ካሬ ሜትር ይለካል ነው። እዚህ ላይ የእናንተ ምላሽ ምንድን ነው? የፍርድ አፈጻጸም ስራችን የምናከናውነው ከክፍለ ከተማ የመሬት አስተዳደር በሚገኙት መረጃዎች መሰረት ነው። የክፍለ ከተማው የመሬት አስተዳደር ደግሞ የላከልን ደብዳቤ ቦታው በካርታ 500 ካሬ ሜትር እንደሆነ እና በመሬት ላይ ልኬቱ ደግሞ 580 ካሬ ሜትር መሆኑን ነው። ስለዚህ እኛ ክፍለ ከተማው ከላከልን መረጃ ውጭ እንዴት ልናካፍል እንችላለን? ሲሉ ይጠይቃሉ። ክፍለ ከተማው የቦታው ልኬት 680 ካሬ ሜትር ነው የሚል ከሆነ በእኛ በኩል ለማካፈል ችግር የለብንም።
የፍርድ ባለመብት ወይዘሮ በቀለች ሃይሌ ቤተሰቦች ምላሽ
ብሩክ ግርማ ይባላሉ፤ የፍርድ ባለመብቷ የወይዘሮ በቀለች ሃይሌ ልጅ ናቸው:: የፍርድ ባለእዳ የሆኑት ወይዘሮ መድሃኒት እና አንደኛ ተከሳሽ የነበሩት እማሆይ አለምነሽ እንደሚሉት፤ የተፈረደው ፍርድ ቤቱን እንድንካፈል የሚያዝዝ ነው። በዚህም የፍርድ ባለመብቷ ወይዘሮ በቀለች እናታችንን እማሆይ አለምነሽን ጎዳና እንድትወጣ እያደረጉ ነው ይላሉ። እዚህ ላይ የእርስዎ አስተያየት ምንድን ነው? ሲል የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍል አቶ ብሩክን ጠየቀ።
ክርክሩ ከተነሳበት ጊዜ ጀምሮ እናታችን ወይዘሮ በቀለች ካደገችበት ቤት በፍርድ ባለእዳዋ ወይዘሮ መድሃኒት እና ወንድሞቿ በግፍ እንድትወጣ ተድርጓል። በዚህም እናታችን ወይዘሮ በቀለች ሃይሉ ክርክሩ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ በኪራይ ቤት እየተቸገረች እንድትኖር ተፈርዶባት ቆይቷል። በመጨረሻም ክርክር ከተነሳበት ቤት የሚገባትን ድርሻ በፍርድ ቤት ተወስኖላታል። ይህ ማለት እናታችን ወይዘሮ በቀለች እናቷን ወይዘሮ አለምነሽን ጎዳና አውጥታ ትጥላለች ማለት አይደለም። እናታችን እንደማንኛውም ልጅ እናቷን የመርዳት ሃላፊነቷን አለባት ። የፍርድ ባለእዳዎች እንደሚሉት እናታችን እናቷን ጎዳና ላይ የምትጥል ሰው አይደለችም ። ምክንቱም ወይዘሮ በቀለች ሰባዊነት የተላበሰች ሰው ከመሆኗም ባለፈ እናቷን ወይዘሮ አለምነሽ መርዳት ሞራላዊ ግዴታዋ መሆኑን ጠንቅቃ ትገነዘባለች ሲሉ ይናገራሉ።
እንደሚታወቀው፤ የፍርድ ባለ እዳዎች ክርክር ከተነሳበት ቤት በወራሽነት ተጠቃሚ ናቸው። ስለሆነም እነርሱም እንደ ልጅ እናታችንን ሊረዱ ይገባል። እኛም እንደ ልጅ የሚደርስብንን ሃላፊነት እንወጣለን ሲሉ ይገልጻሉ።
በፍርድ ቤት የተወሰነው ውሳኔ ቦታው ይከፈል የሚል ነው። ነገር ግን ቦታው መከፈል ስለማይችል ጨረታ ወጥቶበታል። በጨረታ ከተሸጠ ደግሞ እማሆይ አለምነሽ መኖሪያ አያገኙም የሚል ስጋት በፍርድ ባለዳዎች በኩል ይነሳል። እማሆይ አለምነሽ በእድሜ የገፉ ከመሆናቸው አንጻር የሚቆዩት ጊዜ እምበዛም እንደማይሆን ይገመታል። ስለሆነም ከሞራል አንጻር እናታችሁን ለምን ፍርድ ቤት እንድትካፈሉት ባዘዘው ቦታ ቀሪ እድሜያቸውን እንዲያሳልፉ አታደርጉም? ሲል የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍል የወይዘሮ በቀለችን ልጅ አቶ ብሩክን ጠየቀ።
አቶ ብሩክም እኛ የፍርድ ቤት ውሳኔን መሻር አንችልም። ቤቱ መከፈል አይችልም። ስለሆነም በጨረታ ተሽጦ መከፈል አለበት። ይሁን እንጂ እኛም እንደ ልጅ እናታችን ጎዳና እንዳትወጣ የበኩላችንን ለመርዳት ዝግጁ ነን።
ሙሉቀን ታደገ
አዲስ ዘመን ሰኔ 1/2014