ዝክረ ሰሙነ ቀብር፤
አበውና እመው፤ “አቤቱ ፈጣሪ ሆይ ሞቴንና አሟሟቴን አሳምርልኝ” የሚሉት የተለመደ የሠርክ ጸሎት አላቸው። ይህ የተማጽኖ ጸሎት ካዘቦት ቀናት መቃተት ከፍ ብሎ የብዙኃን ምኞት ወደ መሆን ደረጃም ያደገ ይመስላል። ምኞት ብቻም ሳይሆን “አሟሟቱ በክብር እንዲጠናቀቅ” ጭምር “የስዕለት ኪዳን የሚገባ” ዜጋም ይጠፋል ተብሎ አይታሰብም። ብዙኃን ዜጎች በዚህን መሰሉ “አሟሟቴን አሳምርልኝ” ምልጃ ከመማረካቸው የተነሳም ጉዳዩ በማኅበረሰባችን ውስጥ ሥር የሰደደ እምነት ወደ መሆን ደረጃ የተሸጋገር ሳይሆን እንደማይቀርም ይገመታል። ሞት በቀጠሮ ያለመምጣቱ እንጂ ነገሩ ባልከፋ ነበር።
በሀገራችን ብሔረሰቦች ዘንድ ሞትና የቀብር ሥነ ሥርዓት ልዩ ቦታና አትኩሮት እንደሚሰጠው ቢታወቅም ክዋኔው ግን ከቦታ ቦታ፣ ከአካባቢ አካባቢ እንደሚለያይ የታወቀ ነው። በአንዳንድ አካባቢ ለሟቹ የሚደረገው የሽኝት ባህልና የቀብር አፈጻጸም ሥነ ሥርዓት ለቀናት የሚሰነብት ሆኖ ዝግጅቱም በስፋት የሚተገበር ነው። የሟቹ ታሪክ ምንም ይሁን ምን ሙገሳና ክብር ግን አይጓደልበትም። በአንዳንድ አካባቢዎች አስከሬን የሚሸኘው በፉከራ፣ በቀረርቶና በጭብጨባ ጭምር ታጅቦ ነው። የፉከራውም ሆነ የቀረርቶው ይዘት ግን የግድ በሟቹ/ቿ ግለሰብ ላይ ብቻ ላያተኩር ይችላል። መገፋት፣ የፍትሕ እጦት፣ የበደል ቁጭት ያለበት ቤተሰብ፣ ወዳጅ ዘመድ ወይንም ጎረቤት የቀብሩን ሥርዓት ምክንያት አድርጎ ብሶቱን የሚገልጽባቸው በርካታ አጋጣሚዎች የተለመዱ ናቸው።
ይህ ርዕሰ ጉዳይ ብዙ ስለሚያጽፍ ለጊዜው ገደብ አበጅቶ በሙሾ ረገዳ ላይ ብቻ ለማተኮር ይሞከራል። ሙሾ፡- የለቅሶ ቅንቀና፣ ዥመራ፣ ግጥም፣ ዜማ፣ ቁዘማ፣ እንጉርጉሮ፣ ረገዳና ጭብጨባ የታከለበት በቀብር ወቅት የሚፈጸም ክዋኔ መሆኑን መዛግብተ ቃላቱ ይተነትናሉ። በተለይም በከተሞች አካባበቢ (ለገጠሩ ባህል ብዙም እውቀት ስለሌለኝ ነው) የዕለት እንጀራቸውን በሙሾ አውራጅነት ላይ የመሰረቱ በርካታ ሴትና ወንድ “ስልጡን ባለሙያዎች” መኖራቸው የታወቀ ነው።
እነዚህ ቀብር አድማቂ አስረጋጆች ውሏቸው ማስለቀስ እንጂ እነርሱ በነጋ በጠባ ገንዘብ ለከፈላቸው ሁሉ እንደማያለቅሱና የእምባ መዋጮ እንደማይለግሱ በሚገባ ይታወቃል። ይህ ጸሐፊ ባደገበት የምዕራቡ አዲስ አበባ ክፍል ዝናቸው የናኘ በርካታ አስለቃሾች እንደነበሩ ያስታውሳል። ከሦስት አሠርት ዓመታት በፊት የዚሁ የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ተወዳጅ እህት በነበረችው የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ጋዜጣ ላይ ይህንን ርዕሰ ጉዳይ በተመለከተ ስለ ሙሾ አውራጆቹ ዝርዝር ጉዳዮች እንደጻፈም ያስታውሳል።
ዛሬ ዛሬ ልምምዱ የደበዘዘ ይምሰል እንጂ የሙሾ ድርደራና ደረት ማስደቃቱ ሙሉ ለሙሉ ቀርቷል ለማለት ያደግታል። የሟች የቅርብ ዘመዶች ከገደብ አልፈው ፊታቸውን እንዲነጩና በርካታ ጊዜያትም በገላቸው ላይ ጉዳት እንዲያደርሱ ሙሾ አሙሽዎቹ አስለቃሾች ምክንያት ይሆናሉ እየተባለ ቢወገዝና የሕግ ቁጥጥር እየተደረገበት ለቅጣት ሰበብ እስከመሆን ቢደረስም ክዋኔው ግን ዛሬም ድረስ ከባህሉ ውስጥ ተሟጦ ጠፍቷል ለማለት ያዳግታል።
የሙሾ ደርዳሪ አስረጋጆች ለአስለቃሽነት አገልግሎታቸው የሚከፈላቸው የገንዘብ መጠን እንደተጠበቀ ሆኖ ሀዘንተኞቹ የሚያቀርቧቸው ሌሎች ማትጊያዎችም እንደሚሟሉ ማሕበረሰቡ በሚገባ ያውቀዋል። ለምሳሌ፡- ለአስለቃሽነት አገልግሎት የሚመረጠው ግለሰብ በቅድሚያ ማነቃቂያ እንዲሆን ጠጅ፣ ጠላም ሆነ አረቄ እንዲቀርብለት ይደረጋል። ከቀብር በፊትም ሆነ በኋላ (አስከሬኑ አፈር ቀመሰም አልቀመሰ) ተገቢው የምሳ አቅርቦት የተለመደ ነው። እናም በአስለቃሾች (ሴትም ሆነች ወንድ) የሚጠይቀው ዳረጎት በሚገባ ከተሟላ በኋላ የሚቀጥለው ተግባር “ወደ ሥራ” ገብቶ ዋይ ዋይ እያሰኙና ለማስመሰል ያህል ደረትን ነካ ነካ እያደረጉ ለቀስተኛውን በእንባ ማራጨትና ፊት ማስነጨት ዋና ግቡ ነው። “አልቃሽ ያስለቅሳል እንጂ አያለቅስም” የሚባለውም ስለዚሁ ነው።
ለቅሶ እያለ ከቤት፤ ማድላት ለጎረቤት፤
በወቅታዊው የሀገሬ አሳሳቢ ጉዳዮች ላይ መቆዘም ስጀምር ፈጠኖ የሚታወሰኝ “ሕዝብን ማስለቀስ እንጂ፤ ራሳቸው የማያለቅሱ” ብዙ አስረጋጆች እንደ አሸን የመፍላታቸው ጉዳይ አንዱና ጊዜ ወለዱ መከራችን ነው። እነዚህ አስለቃሾች የሕዝቡን ስሜት እየኮረኮሩ በማጯጯህ ደረት ለማስደቃት የተካኑ ናቸው። በእነርሱ ቤት “ሁሉም ሀገራዊ ጉዳይ ሞቶ ለቀብር ጊዜ የሚጠብቅ ነው።” ሞተ፣ ተቀበረ እያሉ በሚቀባዥሩባቸው ሀገራዊ ጉዳዮቻችን ላይ ዜጎች እምባ እንዲራጩና ተስፋ እንዲቆርጡ የማይጠቀሙበት ዘዴ አይኖርም። ራሳቸውን የሚጠሩትም አንድም አክቲቪስት አለያም ፖለቲከኛ ወይንም ጋዜጠኛ እያሉና እያሰኙ ነው።
የማሕበረሰቡ ለቅሶና ዋይታ ደስታ የሚፈጥርላቸው እነዚህን መሰል “ዘመናዊ አስለቃሾች” ዳረጎታቸውን የሚያገኙት ከተለያዩ የጎረቤትና የሩቅ ጠላቶች ዘንድ ነው። ለዲሞክራሲ ትንታኔ የፈጠኑ፣ ለትችት ምላሳቸውን ያሰሉ፣ ለበጎነት የተኮነኑና “ሁሌም ሀገር ሞታ እንድትቀበር” ለሰይጣን የሚካድሙ “ሙሾ አሙሽዎች” ሀገር ጤና ውሎ እንዲያድር በፍጹም ፍላጎት የላቸውም። ሕዝብም ተረጋግቶ ሲኖር ማየት ይቀነቅናቸዋል።
የእነርሱ ደስታ ሕዝብ በትንሽ በትልቁ ሲማረር መስማት ነው። ማስለቀሱን እንጂ አብሮ ማልቀሱ እርማቸው ስለሆነ ፉከራቸውና ቀረርቷቸው ሁሌም “ሀገር ፈጥና ትሙትና እንቅበራት” የሚል ይዘት ያለው ነው። ሀገሬ በስንቱ ደዌ እንደማቀቀች ትኖራለች!? ሕጉና ሥርዓቱም ጠበቅ ብሎ በአስለቃሾች ላይ አስተማሪ እርምጃ ከመውሰድ ይልቅ እስከ መቼ እንዳሸለበ እንደሚኖር ሊገባን አልቻለም።
እነዚህ “የማሕበረሰብ አስለቃሾች” እንደ ሕዝቡ ርሃብ አያውቁ፣ ጥማት አይሞክራቸው፣ ሁሌም ጠግበው እንዳገሱ ነው። የአይዞህ ባዮቻቸው ዳረጎት ልባቸውን ስላሳበጠና የሚሰክሩበት “የፕሮፓጋንዳ ወይን ጠጅ” አናታቸው ላይ ወጥቶ ስላሰከራቸው፤ የፈለጉትን ተናግረውና ሰርተው ቢውሉ ሃይ ባይ ተቆጪ የሌለ እስኪመስል ድረስ ሲፋንኑ የሚባጁት በየአደባባዮች ላይ ነው።
ብዙዎቹ አስለቃሾች ኑሯቸውን የሚገፉት በሁለት ባላ ላይ ተንጠልጥለው ስለሆነ የኑሮ ጉድለትም ሆነ የገቢ ጠብሽ አያውቃቸውም። ብዙውን ጊዜ ሕዝቡን ወደ ተስፋ ማስቆረጥ የቀብር ስሜት ውስጥ ይከቱትና እነርሱ ግን በማግሥቱ በግራና በቀኝ በያዙት ፓስፖርት አንዱን መዘው ወደ ክፉ ቀን ማረፊያቸው እብስ ይላሉ። ነገር ሲቀዘቅዝም ቀድሞ አደባባይ በመታዬት ገና ከአውሮፕላን እንደወረዱ በሙሾ ግጥም እምባ ማራጨቱን ይጀምራሉ። እውነት እንነጋገር ከተባለ መንግሥትም ቢሆን እንደ በኩር ልጅ እሹሩሩ እያለ ለማባበል የሚፈጥነው እነዚህኑ አስለቃሾች እስኪመስል ድረስ ግራ ያጋባል።
ስለ እውነት እንመስክርና “የእጃችንን አሻራ በምድራችን ላይ በትነን” በሙያችን ለማገልገል የሀገርን ጥሪና የሕዝብን የድረሱልኝ አደራ አክብረን ከተመቻቹ ሀገራት ጓዛችንን ሸክፈን የመጣን በርካታ ዜጎች የአስለቃሾቹን ያህል ትኩረትም ሆነ ግምት የተሰጠን ስለመሆኑ ያጠራጥራል። “ከአልቃሾቹ ይልቅ የአስለቃሾችን እምባ እያበሰች” ሀገሬ እስከ መቼ እንደምትጓዝ መልሱ ርቆብን ግራ እንደተጋባን እነሆ ዕድሜያችንን እንደቆጠርን አለን።
በአግባቡ እውቂያ ያለን አንድ ወዳጄ በነጋ በጠባ ሙሾ እያሞሸ ሲማረርና ሌሎቹም እንዲማረሩ ሲያደርግ አስተውዬው ድርጊቱ አግባብ እንዳልሆነ ስመክረው የሰጠኝ መልስ በእጅጉ የሚያሳፍር ብቻም ሳይሆን የማንነቱን ሰብእና ጭምር እንድፈትሽ አጋጣሚውን ፈጥልኛል። “እውቀቴን ላካፍል ሀገር ብዬ ብመጣ የጥልፍልፉ ብዛት አላላውስ አለኝ! እዚያው ሀገሬ ተመልሼ መሄዱ ሳይሻል አይቀርም” ብሎ ሲያማርር አድምጬው “ልክ ነህ የሀገራችን ቢሮክራሲና አገልግሎት ለማግኘት የሚኬድባቸው መንገዶች ጥልፍልፍና ውስብስብ ናቸው። አንተም እኮ ሀገር ብለህ የመጣኸው ይሄ ችግር ስላለ ተጋፍጠህ እንድታሸንፍ እንጂ፤ ችግር እየዘረዘሩ ሙሾ ለማውረድማ ሺህ ምንተ ሺህ አስለቃሾች መቼ አጣን!” ብዬ ምርር ስልበት የሰጠኝን መልስ እዚህ ዐውድ ላይ መጥቀሱ ቦታው ባይሆንም ከወዳጅነቱ ራሴን ለመለየት ግን ጥሩ ምክንያት ሆኖኛል።
ደግነቱ የልቡ ሞልቶለት ይመስለኛል፤ የተመቻቸ ወንበር ተሰጥቶት “ሹመት ያዳብር” የሚሉትን ወዳጆቹን ለማስተናገድ ሸብ እረብ ሲል ይስተዋላል። “ኢትዮጵያ ሀገሬ ሞኝ ነሽ ተላላ የሞተልሽ ቀርቶ…” አለ ቀረርቶኛው የሀገሬ ሰው። ይህንን “የቀድሞ ወዳጄንና” በርካታ አስለቃሽ ሙሾ አስረጋጆችን ባሰብኩ ቁጥር የሚከተለው የተውሶ ግጥም ትዝ ስለሚለኝ እያረርኩ በለሆሳስ ደጋግሜ አነበዋለሁ።።
“አንድ ሕዝብ ተነስቶ፤ ሙሾ አሙሺውን አለው፣
ወጊድ ከፊታችን!
እኛ ስንጨነቅ ስለ እለት ኑሯችን፣
አንተ የምትዘፍነው ስለ ቀብራችን፤
ዘፈን ከሆነማ ወፏም ታዜማለች፣
ሙት መንፈስ ለማንቃት እየቀሰቀሰች።”
ብለን! ብለን! ያቃተንን ስሞታ ዛሬም ኢትዮጵያ ትሰማን ከሆነ እነሆ ይድረስ ብለናል። ሙሾ አሙሺዎች በድብቅ ሳይሆን በአደባባይ፣ በስውር ሳይሆን በሚዲያ ፊት እየቀረቡ ብሶታችንን እያጋነኑ “በማር በተለወሰ አንደበት” በመቀስቀስ ዛሬም ድረስ ማስለቀሳቸውን ስላልተው ጉዳዩ የሚመለከተው ክፍል ባይዘናጋ ይሻል የመስለናል። ዳሩ በእነርሱ ሙሾ እዬዬ ብለን እምባችን ከብሌናችን ከረጢት ውስጥ ተንጠፍጥፎ ስላለቅ እያረርንና እየከሰልን ያለነው ደረቅ ዐይናችንን እያጨናበስን ነው።
ነፍሰ ሄሩ ደራሲያችን በዓሉ ግርማ ለካንስ የሚከተለውን እንጉርጉሮ ከትቦልን ያለፈው ቢቸግረው ነው።
“እምባ እምባ ይለኛል፤ ይተናነቀኛል፣
እምባ ከዬት አባቱ፤ ደርቋል ከረጢቱ።
ሳቅ ሳቅም ይለኛል፤ ስቆ ላይስቅ ጥርሴ፣
ስቃ እያለቀሰች መከረኛ ነፍሴ።”
የአስለቃሾቻችን የረገዳ ተውኔት በዚህ ቁንጽል ጽሑፍ ብቻ የሚጠናቀቅ አይደለም። ብዙ የሚጻፍለት፤ ብዙም የሚነገርለት ወቅታዊ ፈተናችን ነው። ሀሳቡን ለመለኳኮፍ የተሞከረው ችግሩ ከቀን ወደ ቀን እየከፋ መሄዱ ስለሚያስደነግጠን ነው።
ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ችግር እርግጥ ነው በዓይነትም ሆነ በመጠን የሰፋ መሆኑ ለማንም የተሰወረ አይደለም። የዚያኑ ያህልም እጅግ መልካምና አጓጊ ተስፋዎች እያስተዋልንም ነው። በተለየ ሁኔታ ግን የዓለም ሀገራት ዋነኛ ችግርና ሥጋት ከስንዴ ጋር ተያይዞ የዕለት ዳቦ የማግኘቱ ጉዳይ አሳሳቢ እየሆነ በመጣበት በዚህ ወቅት ሀገሬ “የስንዴ ምርት ከራሷ ተርፎ ወደ ውጭ የምትልክበት ጊዜ ሩቅ እንደማይሆን” የምሥራቹን በተግባር ማረጋገጫነት መስማት ትልቅ ደስታ እንደሆነ ለማንም የሚጠፋ አይደለም። በተለይም ርሃብና ድርቅ ሲያንገበግበን መኖሩ ብቻ ሳይሆን ለባእዳን መሳለቂያ ያደረገን ይህ ታሪክ ሊለወጥ ነው መባል በራሱ ትልቅ ብስራት ነበር።
የእኛዎቹ አስለቃሾች ግን የልባቸውንና የዐይናቸውን ብሌን አሳውረው ይህን ታላቅ የስኬት ጅማሮ ሲተቹና ሲያጥላሉ መመልከት እንግዳ አይደለም። በየአካባቢው የሚመረቁ የተጠናቀቁ ፕሮጀክቶችን ማየትስ? ያስደስታል እንጂ “ደረት ጣሉና እዬዬ በሉ” አሰኝቶ የሚሟረትበት የሙሾ እንጉርጉሮ መሆን ይገባው ነበር። የኑሮን ዳገት መውጣት ተስኖን ጉልበታችን መዛሉ እውነት ቢሆንም ብዙዎቹ አስለቃሾች ግን እነርሱ ሳያለቅሱ እኛን አስለቅሰው በእምባ መራጨቱ ስለሰለቸን በሁሉም ጉዳይ ለጊዜው አደብ ገዝተው ያዘቀዘቁትን ነጠላ ቢጥሉት ይበጃቸዋል። ሟርት ሰለቸን፣ “ሆ! እያሰኙ በመንጋ መነዳቱ እጅ እጅ አለን፣ እነ እከሌን ስደቡ እየተባልን “ጃዝ መባላችን!” የሞራል ስብራት ሆነብን፣ መከራ መተረኩ አስመረረን፣ ስለዚህ አስለቃሾች ሆይ እንኳን ሳታለቅሱ ልታስለቅሱን ቀርቶ አልቅሳችሁ ለማስለቀስ ብትሞክሩም እንኳን እምባችን ስለደረቀ በከንቱ አትድከሙ። ምክንያቱም ሰለቸና። ታከተን እኮ ጎበዝ። የዳረጎት ፍርፋሪ የሚሰጧችሁ “ጌቶቻችሁም” አብልተው ስለሚንቋችሁ፣ እያጎረሱ ስለሚታዘቧችሁ ለኅሊናችሁ እንድታድሩ እነሆ ምክራችንን ተቀበሉ እንላለን። ሰላም ይሁን
(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን ሰኔ 1 /2014