በ2023 የኮትዲቯር አፍሪካ ዋንጫ ለመሳተፍ የአገራቱ ብሔራዊ ቡድኖች ከሳምንቱ አጋማሽ ጀምሮ ጨዋታዎችን እያከናወኑ ይገኛሉ። በማጣሪያ ውድድሩ በምድብ አራት ከግብጽ፣ ጊኒና ማላዊ ጋር የተደለደለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም የመጀመሪያውን የማጣሪያ ጨዋታ ትናንት ከሜዳው ውጪ አድርጓል።
በማጣሪያ ጨዋታው በአንጻራዊነት የምድቡ ቀላል ተጋጣሚ የሆነውን የማላዊ ብሔራዊ ቡድንን በሜዳው ቢንጉ ብሔራዊ ስቴድየም የገጠሙት ዋልያዎቹ ሁለት ለአንድ በሆነ ውጤት ተሸንፈዋል። ሶስት ፍጹም ቅጣት ምቶች በተቆጠሩበት ጨዋታ ዋልያዎቹ በመጀመሪያው አጋማሽ ሁለት ግቦች ተቆጥሮባቸዋል። በሁለተኛው አጋማሽ እጅግ አስደናቂ ጨዋታ ያሳዩት ዋልያዎቹ የማስተዛዘኛዋን ግብ በፍጹም ቅጣት ምት በአቡበከር ናስር አማካኝነት ማስመዝገብ ችለዋል።
በመጀመሪያው አጋማሽ በተከላካይ መስመር ስህተትና ጥንቃቄ ማነስ የሁለት ፍጹም ቅጣት ምቶች ሰለባ የሆኑት ዋልያዎቹ ከሜዳቸው ውጪ በጨዋታው የነበራቸውን የበላይነትና አስደናቂ እንቅስቃሴ አለማድነቅ አይቻልም። ምናልባትም የጨዋታ የበላይነትና የቋስ ቁጥጥር ብልጫ ወደ ውጤት የሚቀየር ቢሆን ዋልያዎቹ ትናንት አሸናፊ በሆኑ ነበር።
ባለፉት አምስት ጨዋታዎቹ አንድ አሸንፎ አንዱን በአቻ ውጤት ደምድሞ በቀሪዎቹ ሽንፈት የገጠመው የማላዊ ብሔራዊ ቡድን በሜዳውና በደጋፊው ፊት በዋልያዎቹ እንደተወሰደበት ፍጹም የበላይነት የሚፈልገውን ሶስት ነጥብ ይዞ መውጣቱ እድለኛ ያደርገዋል ቢባል ማጋነን አይሆንም።
ዋልያዎቹ በሚችሉት አጨዋወት የተሻለ የግብ እድል ፈጥረው የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ጥረዋል ።የአሰልጣኝ ውበቱ ስብስብ ሀሳቡ ተጋጣሚን በኳስ ቁጥጥር መብለጥና ይህንንም በተግባር ማሳየት መቻል መሆኑ ትልቅ እድገት ነው ።በዚህም ኢትዮጵያ በማንኛውም አፍሪካ ቡድን የማይናቅ ስብስብ እንዳላት አሳይታለች ።
ባለፉት አምስት ጨዋታዎች በሶስቱ አቻ ተለያይተው ሁለቱን በሽንፈት የደመደሙት ዋልያዎቹ በአንጻሩ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ ቢያሳዩም ማራኪ ጨዋታቸው ደጋፊያቸውን ከማስደሰት የዘለለ ወደ አፍሪካ ዋንጫው የሚያስጉዛቸውን ተስፋ የሚያለመልም አልሆነም።
የዋልያዎቹ የትናንት ጨዋታን ሽንፈት የበለጠ የሚያስቆጭ ያደረገው ካፍ የኢትዮጵያን ስቴድየሞች በማገዱ ቀሪዎቹን የማጣሪያ ጨዋታዎች በገለልተኛ ሜዳ ማድረጋቸው ነው። ዋልያዎቹ ምናልባትም የትናንቱን ጨዋታ ቢያሸንፉ ከቀናት በኋላ ሁለተኛ የማጣሪያ ጨዋታቸውን በምድቡ ጠንካራ ከሆነችው ግብጽ ጋር እዚያው ማላዊ ላይ ገጥመው ቢሸነፉ እንኳን ማካካሻና የአፍሪካ ዋንጫ ጉዟቸው ላይ ተጨማሪ ተስፋ ይሆን ነበር።
ባለፉት በርካታ ዓመታት የዋልያዎቹ የግብ አዳኝ በመሆን ጥሩ ግልጋሎትን ሲሰጥ የነበረው ወሳኙን አጥቂ በሥነምግባር ጉድለት በስብስባቸው ያላካተቱት አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ከአስራ አንድ ጨዋታ አንድ ብቻ አሸንፈዋል። የትናንቱን ጨዋታ በማሸነፍ ይህን ክብረወሰን የማሻሻል እድላቸውም በጥቃቅን ስህተቶች መክኗል። በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ ዋልያዎቹን ባለፉት አስር ወራት እየመሩ ሱዳንን ብቻ በወዳጅነት ጨዋታ አሸንፈዋል። ከዚያ ጨዋታ ወዲህ ግን በነጥብም በአቋም መፈተሻ ጨዋታም ማሸነፍ አልቻሉም። አስራ አንድ ጨዋታ አድርጎ አምስት ተሸንፏል፣ አምስት አቻ፣ አንድ ሱዳንን አሸንፈናል።
“ዘ ፍሌምስ” በሚል ቅጽል ስም የሚታወቀው የማላዊ ብሔራዊ ቡድን ባለፈው የአፍሪካ ዋንጫ ከምድቡ ማለፍ ችሎ ነበር። አስራ ስድስት ውስጥ ገብቶ በሞሮኮ ተሸንፎም ነበር ከአፍሪካ ዋንጫ የተሰናበተው። ዋልያዎቹ ከማላዊ ጋር እኤአ ከ2003 ጀምሮ በተለያዩ ውድድሮችና በወዳጅነት ጨዋታዎች የትናንቱን ጨምሮ ሰባት ጊዜ ተገናኝተዋል። ማላዊ ሶስት ጊዜ በማሸነፍ የበላይነቱን ስትይዝ ኢትዮጵያ አንድ ጊዜ ረትታለች። አራት ጊዜ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል።
ዋልያዎቹ ከማላዊ ጋር በነጥብ ጨዋታ ለመጨረሻ ጊዜ የተገናኙት እኤአ 2014 ላይ ለአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ሲሆን ማላዊ በሜዳዋ 3ለ2 ስታሸንፍ ኢትዮጵያ ላይ 0ለ0 ተለያይተዋል። ሁለቱ ቡድኖች ለመጨረሻ ጊዜ የተገናኙት ባለፈው ዓመት በወዳጅነት ጨዋታ ባህርዳር ላይ ሲሆን ኢትዮጵያ 4ለ0 አሸንፋ እንደነበር ይታወሳል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 29 ቀን 2014 ዓ.ም