በቀደመው ዘመን በኢትዮጵያ እንደ መምህርነት የተከበረ ሞያ አልነበረም ቢባል ማጋነን አይሆንም። መምህር የእውቀት ብርሃን ፈንጣቂ በመሆኑ በተማሪዎች፣ በወላጆች ብሎም በማህበረሰቡ ዘንድ ትልቅ ከበሬታ ነበረው። እንደውም መምህር ያገባች ሴት የታደለች በመሆኗ ‹‹የኛ ልጅ ኩሪ ኩሪ አገባሽ አስተማሪ›› ተብሎም በሰርጓ ላይ ይዘፈንላት ነበር።
ይሁንና በግዜ ሂደት የመምህርነት ሞያ እያነሰ፤ ለመምህር የሚሰጠውም ክብር እየኮሰሰ ዛሬ ላይ ደርሰናል። ከጥቂት አመታት በፊት ለትጉህ መምህራን በየዓመቱ ሲሰጥ የነበረው የእውቅና ሽልማት መርሃግብርም ተቋርጧል። እንደሻማ እየቀለጠ ለብዙዎች ህይወት ትልቅ አስተዋፅኦ የሚያደርገው መምህር ዛሬም ተገቢውን ክብር እያገኘ አይደለም።
ቢዘገይም አልረፈደም ነውና ነገሩ ከአንድ ዓመት በፊት የተማሪዎች፣ የመምህራንና የወላጆች አገር አቀፍ የመመሰጋገንና የመደናነቅ ቀን በኢፌዴሪ ትምህርት ሚኒስቴርና ቅን ኢትዮጵያ በተሰኘ ማህበር ትብብር መከበር ጀምሯልⵆ ዘንድሮም ይኸው ቀን ተማሪዎች፣ መምህራን፣ የተማሪ ወላጆችና ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት በተገኙበት ለሁለተኛ ግዜ ከሰሞኑ ተከብሯል።
ተማሪ እድላዊት አለማየሁ በየካ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት የአራተኛ ክፍል ተማሪ ናት። ቀደም ሲል ለስነ ዜጋና ስነ ምግባር ትምህርት እምብዛም ትኩረት አልነበራትም። ይሁንና በአሁኑ ግዜ የሚያስተምራት የስነ ዜጋና ስነ ምግባር መምህሯ ትምህርቱን በእጅጉ እንድትወደው አድርጓታል።
የትምህርት አሰጣጡ ሳቢ በመሆኑ በራስ መተማመኗ ጎልብቶ በትምህርት ቤት በሚዘጋጁ የስነፅሁፍና ኪነጥበባዊ ፕሮግራሞች ላይ ቀርባ ስራዎችን እንድታቀርብም አግዟታል። ለዚህ ደግሞ የመምህሩ አስተዋፅኦ ጉልህ በመሆኑ ከልቧ ታደንቀዋለች። በብዙ መንገድ አበረታቷት ለዚህ ስላበቃትም ታመሰግነዋለች።
በተለይ ደግሞ እርሱ የሚያስተምርበት ስልት የተለየ በመሆኑና ትምህርቱንም የሚሰጠው በምሳሌ እያስደገፈ በመሆኑ ለእርሱ ያላት አድናቆት ከፍ ያለ ነው። እርሷን ጨምሮ ሌሎች ተማሪዎች አገራቸውን እንዲያውቁና ቁጭት ተሰምቷቸው ጠንክረው እንዲሰሩ አድርጎ ስለሚያስተምርም ከሌሎች መምህራን አብልጣ ትወደዋለች።
ተማሪ እድላዊት ከስነ ዜጋና ስነምግባር መምህሯ በተጨማሪ በአማርኛ ቋንቋ ላይ በደምብ እንድትሰራና ቋንቋ ወሳኝ መሆኑን በማወቅ ስለኢትዮጵያ የተለያዩ ታሪኮችን እንድትረዳ በማድረጉ ረገድ የአማርኛ ቋንቋ መምህሯም አሰተዋጽኦ ከፍተኛ ነውና ለዚህች መምህር ከፍተኛ ከበሬታ አላት። ለእርሷ እዚህ መድረስ የመምህሮቿ አስተዋፅኦ ብቻ ባለመሆኑ በተለያየ መንገድ ድጋፍ ያደረጉላትን ወላጆቿንም ታመሰግናለች።
ወይዘሮ አልማዝ ቦጋለ በየካ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት የሚማሩ የሁለት ተማሪዎች ወላጆች ናቸው። ለልጆቻቸው የትምህርት ውጤት መሻሻል የመምህራን አሰተዋፅኦ ከፍተኛ በመሆኑ ለመምህራን ያላቸው አድናቆት የተለየ ነው። በተለይ ደግሞ መምህራን ልጆቻውን እንደባህሪያቸውና እንደትምህርት አቀባበላቸው ስለያዙላቸውና እውቀት ስለመገቧቸው መምህራንን ያመሰግናሉ።
የመምህራን ክትትል ከፍተኛ በመሆኑና እርሳቸውም ከመምህራን ጋር በየግዜው እየተገናኙ በልጆቻቸው ትምህርት አቀባበልና ባህሪ ጋር በተገናኘ መረጃ ስለሚለዋወጡ ለልጆቻቸው ውጤት መሻሻል ትልቅ አስተዋፅኦ አድርጎላቸዋል። ልጆቻቸው ብዙ ነገሮችን እንዲያውቁ እያገዟቸውና እያበረታቷቸው ስለሚገኙም ለመምህራን ያላቸው ምስጋና ከፍተኛ ነው።
ወይዘሮ አልማዝ በልጆቻው ውጤትና ባህሪ ላይ መሻሻል በመምጣቱ መምህራንን ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ የትምህርት ቤቱን ሰራተኞችንም ያመሰግናሉ። በቤት፣ በሰፈርም ሆነ በትምህርት ቤት ልጆቻቸው መልካም ስነ ምግባር ያላቸውና በትምህርታቸውም ጎበዝ በመሆናቸው ልጆቻቸውንም ያመሰግናሉ።
መምህር እዮብ ሽፈራው በየካ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት የአራተኛ ክፍል የእንግሊዘኛ ቋንቋ ያስተምራል። እርሱ እንደሚለው በመምህራን፣ ወላጆችና ተማሪዎች መካከል የሚደረገው መመሰጋገንና መደናነቅ ፕሮግራም ብቻ ተይዞለት የሚደረግ አይደለም። መምህራን ከተማሪዎቻቸው የሚማሩት ነገር በመኖሩና መምህራንም ለተማሪዎቻቸው የሚሰጧቸው ትምህርት በመኖሩ ተማሪዎች በብዙ መንገድ ሊመሰገኑ ይችላሉ።
ለአብነትም ሃሳብን ለመግለፅ አንድ ተማሪ ማግኘት በራሱ ትልቅ ነገር በመሆኑ ተማሪን ማመስገን ያስፈልጋል። ከስራ ባለፈ ተማሪዎችን በምክንያት ማመስገን የሚያስፈልግ በመሆኑ ‹‹እኔ በስራዬ ማስተካከል ያለብኝን አስተካክዬ ዛሬ ብቁ መምህር መሆን ስለቻልኩ ተማሪዎቼን ማመስገን›› እፈልጋለውም ይላል መምህር እዮብ።
መምህር እዮብ እንደሚለው ዝቅተኛ፣ መካከለኛና ከፍተኛ አቀባበል ያላቸው ተማሪዎች አሉ። ይሁንና በአብዛኛው መምህራን ከፍተኛ የትምህርት አቀባበል ያላቸውን ተማሪዎች ይወዳሉ። ከዚህ በተቃራኒ ግን እርሱ ሁሉንም ተማሪዎቹን እንደሚወድና አንዳቸውን ከአንዳቸው እንደማያበላልጥ ይናገራል። ሁሉም መምህር ይህን ማድረግ እንዳለበትም ያሳስባል።
ለተማሪዎች ውጤትና ባህሪይ መሻሻል ወላጆችም ትልቅ አስተዋፅኦ አላቸውና ወላጆች ገና ልጆቻውን ከወለዱበት ግዜ አንስቶ ትልቅ መስዋዕትነት በመክፈላቸው ሊመሰገኑ ይገባል ይላል መመህር እዮብ።በተለይ እርሱ በሚያስተምርበት ትምህርት ቤት ውስጥ ያሉት አብዛኛዎቹ ተማሪዎቹ በዝቅተኛ የኑሮ ሁኔታ ላይ የሚገኙ መሆናቸውን እንደሚረዳና ወላጆቻው ለራሳቸው ልብስና ጫማ ሳያምራቸው ለልጆቻቸው ሁሉንም አሟልተው ስለሚያስተምሩ ሊደነቁና ሊመሰገኑ እንደሚገባ ይናገራል።
ዶክተር መሰለ ሃይሌ የቅን ኢትዮጵያ ማህበር የቦርድ ሰብሳቢ ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት መምህራንን፣ ተማሪዎችንና ወላጆችን የማመስገንና የማድነቅ ሀሳብ የመጣው ቀደም ሲል የነበረው ታታሪ ሰዎችን የማመስገንና የማድነቅ ባህል እየቀዘቀዘ በመምጣቱ ነው።
በኢትዮጵያ ውስጥ ቅንነት አለ ወይስ የለም የሚለውን በመመርመርና ኢትዮጵያ በርካታ የቅንነት ታሪክ እንዳላት ለማረጋገጥ ከዘጠኝ የዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰሮች ጋር በመሆን ጥናት ተካሄደ።
በጥናቱ ውጤት መሰረትም ኢትዮጵያ መልካም በማሰብ ሰፊ ባህል ያላት አሁን ግን በርካታ ነገር እንደሚጎድል አረጋግጧል። ቀስበቀስ አሉታዊ የማሰብ ባህል እየጨመረ እንደመጣ፣ አንድ ሰው ጥሩም ቢያደርግ ብዙ የማድነቅ ባህል እንደሌለና ቢሳሳት እንኳን አበረታቶ ከስህተቱ እንዲታረም የማድረግ ሁኔታ እንደሌለ ለማወቅ ተችሏል። በዚህ መስፈርት ማህበሩ ቢቀጥል የሚል ሃሳብ መጥቶ በርካታ ሂደቶችን አልፎ ቅን ኢትዮጵያ ማህበር ሊመሰረት ችሏል።
ዶክተር መለሰ እንደሚናገሩት ማህበሩ ሶስት አላማዎችን ይዞ የሚንቀሳቀስ ሲሆን እነዚህም በዜጎች መካከል ቅን አስተሳሰብን ማስረፅ፣ የመከባበር ስሜት እንዲኖር ማድረግና የመመሰጋገንና ማድነቅ ባህል እንዲጎለብት ማስቻል ናቸው። በዚሁ ዓላማ መሰረት ማህበሩ ስራውን ሲጀምር ያስቀደመውም ትምህርት ቤቶችንና ባህል ሚኒስቴርን ነበር።
በትምህርት ሚኒስቴር መረጃ መሰረት ወደ 27 ሚሊዮን የሚጠጉ መምህራንና 1 ሚሊዮን የሚሆኑ መምህራን አሉ። ከዚህ አንፃር ቅንነት ላይ ትልቅ ስራ ቢሰራ አገርን መለወጥ ይቻላል። ተማሪዎችም ትምህርትን መቅሰም ብቻ ሳይሆን ለትምህርት ቤታቸው ባለቤት ሊሆኑ ይገባል። ቅን ማሰብም ይጠበቅባቸዋል።
ይህ በመምህራን፣ በወላጆችና ተማሪዎች መካከል የመመሰጋገንና የመደናነቅ ቀን ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ላይ በስፋት ተከብሯል። ዘንድሮም በአገር አቀፍ ደረጃ ተከብሯል።
በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል በተፈጠረው ግጭት ምክንያት ግን ቀኑን እንደአምናው በስፋት ማውራት አልተቻለም። ሆኖም ቀኑ በነዚህ አካባቢዎች በግጭቱ ምክንያት የተፈናቀሉ ተማሪዎችንና ከስራ ገበታቸው ውጪ የሆኑ መምህራንን በማሰብ እንዲከበር ተደርጓል። በቀጣዮቹ አመታት የአገሪቱ ሰላም እየተረጋገጠ ሲሄድ ደግሞ ቀኑን ከዚህ የበለጠ ለማክበር ታስቧል።
ዶክተር መለሰ እንደሚሉት በመጀመሪያ ተማሪዎች ትምህርትን ፈልገው በመማራቸው፣ መልካም በመሆናቸውና መልካም በማሰባቸው ሊደነቁና ሊመሰገኑ ይገባል። በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ መምህራን የቀለም አባት በመሆናቸውና የወላጆችን ኃላፊነት ተረክበው ተማሪዎችን በማስተማራቸው ሊደነቁ ይገባል። በተለይ ደግሞ በዜጎች ማንነት ላይ መምህራን ትልቅ ተፅእኖ ስላላቸውና ለፍተው ስለሚያስተምሩ ሊመሰገኑ ይገባል።
መምህር ሲባል የተሻለ ደሞዝ አግኝቶ ሌላ ቦታ ማስተማር የሚችል ቢሆንም በትንሽ ደሞዝ ለፍቶ ስለሚያስተምር ተማሪዎች ወላጆቻቸውን ሊያመሰግኑ ይገባል። በሶስተኛ ደረጃ ለተማሪዎች ምግብና ልብስ ገዝተው ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ያደረጉ ወላጆች በመሆናቸው ሊደነቁ ይገባል። በተለይ በዚህ ግዜ ወላጆች ከጎደላቸው ላይ አውጥተው ለተማሪ ልጆቻቸው የሚያስፈልጋቸውን ሁሉ አሟልተው በማስተማራቸው ሊመሰገኑ ይገባል።
ከዚህ አንፃር ይህን መልካም ነገር በመያዝ በሰፊው ማስቀጠል ያስፈልጋል። የማመስገንና የማድነቅን ባህል በተማሪዎች፣ በመምህራንና በወላጆች ውስጥ ማስረፅም ያስፈልጋል። ይህ ጉዳይ የአንድ ቀን ባለመሆኑ ባህሉን ሁሌም ልምድ ማድረግ ይገባል።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 29 ቀን 2014 ዓ.ም