ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገራችን በሚደረጉ ልዩ ልዩ የኪነጥበብና መሰል ሽልማቶች፤ ለፋሽን ዘርፉ አዲስ እድል በመፍጠር ላይ ይገኛሉ። በሽልማት ስነ ስርዓቶቹ ላይ የሚለበሱ አልባሳትና ልዩ ልዩ የመድረክ ሁነቶች ለዚህ ዘርፍ አይነተኛ ሚና በመጫወት ላይ ናቸው። በተለይም በሽልማት መርሀ ግብሮቹ ላይ የሚታደሙ አርቲስቶችና የመርሀ ግብሩ ተካፋዮች ለዲዛይነሮች ስራ ህዝብ ዘንድ ቀርቦ የመታየት እድል ፈጥሯል።
አርቲስቶችና የዝግጅቱ ተጋባዦች በአዳዲስ ዲዛይን የተሰሩ ባህላዊና ዘመናዊ አልባሳት ተጎናፅፈው መገኘታቸው ከመድረኩ ድምቀት ባሻገር ስራዎቻቸውን ለማቅረብ እድሉን ላጡ ዲዛይነሮች እና ሌሎች የፋሽን ዘርፍ ባለሙያዎች ስራዎቻቸውን ለህዝብ ማቅረብ የሚያስችላቸው አዲስ መድረክ መሆኑ ይገለፃል።
በታዳሚውና በሽልማት ስነ ስርዓቶቹ ላይ በሚሳተፉ አርቲስቶች እንዲሁም ግለሰቦች የሚለበሱ አልባሳት የብዙዎች መነጋገሪያ በመሆን ላይ ይገኛሉ። በቅርቡ በተካሄዱት የጉማና የለዛ ትልልቅ የፊልምና የሙዚቃ ሽልማት ስነ ስርዓቶች ላይ በአርቲስቶችና የሽልማቱ ታዳሚ በነበሩ ግለሰቦች የተለበሱ አልባሳት በተመለከተ በመገናኛ ብዙኋን ብዙ ሲባልበት ከርሟል።
በእነዚህ መድረኮች ላይ አምረውና ደምቀው የተገኙት ባለሙያዎችና ታዳሚው የወደዱትና የመረጡት የየራሳቸው አዲስና ያልተለመደ አለባበስ እንዲሁመ በባህላዊ አልባሳት አምረውና ደምቀው የታዩበት መድረክ ሆኖ አምሽቷል። በማህበራዊ ድህረ ገፆች የለባሾቹ ማንነትና የአልባሳቱ አይነት እንዲሁም ከዲዛይን አዲስነትና የአለባበስ ስርዓት ጋር በማገናኘት አድናቆትም ነቀፌታም ሲቀርብባቸው ታይቷል።
በእርግጥ አልፎ አልፎ እዚያ መድረክ ላይ የታዩት ከማህበረሰቡ ባህልና ወግ የሚጣረሱ የአለባበስ ስርዓች በአንዳንዶች መተቸቱ አልቀረም። ነገር ግን በአብዛኞቹ አርቲስቶችና ታዳሚ የተለበሱ አልባሳት የተለያዩ የማህበረሰባችን ክፍሎች ባህልና ስርዓትን የተከተሉ የማህበረሰቡን ባህልን የሚገልፁና አዳዲስ ዲዛይንና ፈጠራ የተንፀባረቀባቸው ነበሩ። ይሄም መድረኩ የተለያየ ማንነቶችና ባህሎች በተዋበ መልኩ ለህብረተሰቡ የሚተዋወቅባቸው ተመራጭ መድረክ እንዲሆን አድርጎታል።
የመድረኩ ተሳታፊ የነበረች ዲዛይነር ሜላት አየለ በልብስ ዲዛይነርነት ሙያ ከ2 ዓመት በላይ የሰራች ናት። በሽልማት ስነስርዓቱቹ ላይ በታዩ አዳዲስ ዲዛይኖችና አልባሳት እንደተደነቀች ገልፃ፤ በተለይም አርቲስቶች ልዩ ልዩ ዲዛይኖች በማሰራትና በባህል ነክ የአለባበስ ስርዓት አምረውና ደምቀወው መገኘታቸው የመድረኩ ውበት ሆኖ እንዳመሸ ታስረዳለች።
ከዚህ በፊት በነበሩት መድረኮች የራስዋን አዳዲስ ዲዛይን ለታዳሚው በማቅረብ ተሳትፎ እንዳደረገች የምትገልፀው ዲዛይነር ሜላት መሰል መድረኮች ለልብስና ለሌሎች የፋሽን ዘርፍ ባለሙያዎች መልካም እድል እንደፈጠረላቸው ታስረዳለች። እነዚህ መድረኮች የልብስ ዲዛይነሮች በአዲስ መልክ የሰሩዋቸው አልባሳት እና ዲዛይኖች ለማስተዋወቅ እንደሚጠቀሙበት የምትገልፀው ዲዛይነር ሜላት፤ በመደበኛነት አዳዲስ ዲዛይኖች ከሚተዋወቁበት የመድረክ ትርኢት (ፋሽን ሾው) ባሻገር ልዩ ልዩ የሽልማትና ትልልቅ መድረኮች ዲዛይነሮች የራሳቸውን የፈጠራ ስራ የሚያስተዋውቁበት አጋጣሚ እንደሚፈጥርላቸው ታስረዳለች።
በፊልም ሽልማት ስነስርዓት መድረኮቹ ላይ የተለበሱ አብዛኛው አልባሳት ስርዓታዊና በብዙዎች የሚመረጡ መሆናቸውን ጠቅሳ፤ ከማህበረሰባችን የአለባበስ ስርዓት ውጪ የሆኑ አልባሳትን መታየታቸው በብዙዎች ቢኮነንም የለባሹ ምርጫና በራሱ ያምርብኛል ብሎ የወሰነውን ለብሶ መገኘቱ ብዙም ችግር እንደሌለው ታስረዳለች።
ዲዛይነር ቤተልሄም ካሳሁን እዚህ ላይ የተለየ አስተያየት አላት፤ በእርግጥ አልባሳቱ በተዋንያን አልያም በሙዚቃ ባለሙያዎቹ ተወደው ቢለበሱም በመርሀ ግብሩ ላይ የተገኘው ማህበረሰብ ባህልና ማንነት የሚያንፀባርቁ ቢሆኑ የሚመረጥ ቢሆንም ከመድረኩ አዲስነት አንፃር ግን አዳዲስና ያልተለመዱ ዲዛይኖች በመታየታቸው ተቃውሞ የላትም። ነገር ግን ከባህል እጅግ ያፈነገጡት ለእሷም ቢሆን ያልተወደደ ተግባር ነው። ከዚህ ጋ በተያያዘ አልፎ አልፎ ከታየው ወጣ ያለ አለባበስ ውጪ አብዛኛው ታዳሚና አርቲስቶች በአዲስ ዲዛይንና ባህል ነክ ሆነው የሚማርኩ መሆናቸውን አስረድታለች።
በተለይም ተዋንያን እና ድምፃዊያን የሚለብሷቸው አልባሳት በዲዛይን አዲስነታቸው ባህል ተኮር መሆናቸው በበጎነቱ እጅግ መነጋገሪያ የመሆናቸው ያህል በተለያየ መገናኛ ብዙኋን ባህልን ያላገናዘቡ እጅጉን ወጣ ያሉ አልባሳት በአንዳንድ ታዋቂ አርቲስቶችና ግለሰቦች መለበሱ በማህበራዊ ሚዲያዎች አስተያየት ሲሰጥባቸው ከርሟል።
በመድረኮቹ ላይ የታዩት ያለፈ ዘመን አስታዋሽ አልባሳትም ድምቀት ነበሩ። የፋሽን ትርጓሜ በትርጉም ሰጪው እይታ ላይ ይወሰናል፤ የምትለው የፋሽን ዲዛይነርዋ ሜላት ሀይሉ በተለይ በአሁኑ ወቅት እጅጉን ተለዋዋጭና አዳዲስ ዲዛይኖች በበረከቱበት ወቅት አንድ ወቅት ፋሽን ተደርጎ ያለፈና እጅጉን የተወዳጅ አልባስ በሌላ ጊዜ በድጋሚ እንደ አዲስ ፋሽን ሆኖ ሊቀርብ መቻሉ እንደ ማስረጃ ታቀርባለች። በእነዚህ መድረኮች ላይ የታዩ አንዳንድ አልባሳትም ድሮን የሚያስታውሱ ነገር ግን ዛሬም አዲስ ፋሽን ሆነው በሰዎች የተወደዱ መሆናቸውን ትጠቅሳለች።
በተለያዩ የመብራት ቀለሞች ባሸበረቁ መድረኮች ላይ ተገኝተው ከበሬታ ከሽልማት ጋር የሚቸሩ የጥበብ ሰዎች በመድረኩ ላይ ለብሰውት የሚገኙት አልባሳት የተለየ ዕድል እንደፈጠረላቸው የሚናገሩት የልብስ ዲዛይን ባለሙያዎች፤ በዚህም ተጠቃሚ እንደሆኑ ያስረዳሉ። ዲዛይነር ቤዛዊት የልብስ ዲዛይነሮችና ባለሙያዎች ያንን መድረክ የራሳቸውን አዲስ ዲዛይን ማሳያ፤ ለገበያቸውም ማስታወቂያ መስሪያ አድርገው እንደሚጠቀሙበት ታስረዳለች።በመሆኑ መድረኮቹ ስራቸውን ወደ ህዝብ ማድረሻ አንዱ መንገድ መሆኑን ዲዛይነት ቤዛ ትናገራለች።
ለፋሽን ኢንዱስሪው ላይ ያሉ ባለሙያዎች የተፈጠረው ይህ አዲስ መድረክ ሰፍቶና ተጠናክሮ ቢቀጥል መልካም መሆኑን ሚያስረዱት ባለሙያዎቹ፤ የሰሩዋቸው አዳዲስ ዲዛይኖችና ስራዎች ማሳያ መድረክ በማጣት እንደሚቸገሩ ያስረዳሉ። መሰል መድረኮች መፈጠራቸው ግን እንደ አዲስ እድል እንደሚጠቀሙበትና በዚህም ለውጥ እያዩ መሆኑን ይናገራሉ።
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 29 ቀን 2014 ዓ.ም