እነሆ ሰኔ ግም ሊል ነው። እንኳን አደረሰን! የጸሀይና የሙቀቱ ወር ግንቦት እየተሰበሰበ ነው፤ ደመናው በስፋት እየታየ ዝናብ ማካፋት እየሞካከረው ይገኛል። ሰኔ እና ቀጥሎ የሚመጡት ወራት በአጠቃላይ ክረምቱ ለኢትዮጵያውያን ወሳኝ የመኽር እርሻ የሚከወንባቸው ወርቅ ወራት የክረምት ወቅት ናቸው፤ ሰኔ ደግሞ እንደ መልካምድሩ ሁኔታ ማሳ ማለስለሱ፣ በዘር መሸፈኑ፣ መኮትኮቱ፣ ማራሙ በስፋት መከወን የሚጀመርበት ወቅት ነው።
በተለይ አርሶ አደሩ አስቀድሞ የሚዘሩትን በመዝራትና በመንከባከብ እንዲሁም ማሳ በማዘጋጀት አስቀድሞም በስራ የተጠመደ ቢሆንም፣ ሰኔ ግም ሲል አንስቶ ሙሉ ጊዜውን በስራ ያሳልፋል። ግብርናውን የሚመራው አካል፣ የግብርና ባለሙያው እና ሌሎች ባለድርሻ አካላትም እንዲሁ ለዚህ የመኸር ወቅት አስቀድሞም ዝግጅት ሲያደርጉ ቆይተዋል፤ ሰኔን ይዘው በክረምቱ ደግሞ በጣም ባተሌ ይሆናሉ። ወቅቱ ግብአት ማጓጓዝ፣ ማቅረብ፣ ማከፋፈል፣ መረጃ መስጠት፣ ማስገንዘብ፣ መከታተል በስፋት የሚከወንበት ነው።
በተፈጥሮ ላይ ጥገኛ የሆነ ግብርና ተይዞ ይህን ወቅት በዋዛ ፈዛዛ መመልከት ብሎ ነገር የለም። ከዚህ አኳያ ሁሉም አካላት ባተሌ መሆናቸው ትክክል ነው። ሰኔን በዋዛ ፈዛዛ ያሳለፈ ብዙ ብዙ ያልፍበታል፤ በእዚህ ወቅት መስራት ካልተጀመረ መጪው ጊዜ ይከብዳል። አንድ ሰኔ የገደለውን አስር ሰኔ አይመልሰውም የሚባለውም ለእዚህ ነው። ጎበዞቹ ሰኔ አይበቃቸውም፤ አይቻል ሆኖ እንጂ በቢደሩም አይጠሉ።
ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ክረምት /የመኸር ወቅት/ እንዲህ ነው። ሁሉም ኢትዮጵያዊ የትኛውም ቡድን በእዚህ ላይ አንድ አይነት አመለካከት ያላቸው ስለመሆኑ የሚጠራጠር አይኖርም፤ የሚገርመው ግን አሸባሪው ትህነግ ግን ከዚህ የለተየ ትርጉም አለው። ከግብሩ መረዳት የሚቻለው ይህን ነው።
ለአሸባሪው ትህነግ ክረምት ወይም ይህ ወርቅ የመኸር እርሻ ወቅት ሌላ ትርጉም አለው። እንደ ሰው፤ ህዝብና አገር የማያስበው ትህነግና አጋሮቹና ተላላኪዎቹ በእዚህ ወቅት የከወኑት፣ ሊከውኑ ያሰቡት እየከወኑ ያሉት ሲታሰብ ክረምት የልማት ሳይሆን የጥፋት ወቅታቸው ነው። ትህነግ ረሀብን ለህልውናው መቆሚያ ያደረገ ቡድን እንደመሆኑ ክረምትን ያህል ወርቅ ጊዜ ለጥፋት እያዋለው ነው።
መከላከያ ሰራዊት ለህግ ማስከበር ትግራይ በነበረበት ወቅት የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር የግብርና ኃላፊዎች የትግራይ አርሶ አደር የመኸር ወቅት ግብርናውን በአግባቡ የሚፈጽምበት ሁኔታ እንዲመቻች ጠይቀው ነበር፤ አንዳንድ ወገኖችም እንደ ማዳበሪያና ምርጥ ዘር ያሉት ግብአቶች በሚፈለገው ልክ በወቅቱ ካልደረሱ ሰላምና መረጋጋት ካልሰፈነ ቀጣዩ የትግራይ ህዝብ እጣ ፈንታ ረሀብ መሆኑን በመጥቀስ ለግብርናው ትኩረት እንዲሰጥ ማሳሰባቸው ይታወቃል። አለም አቀፍ ተቋማት ጭምር ይህን ብለዋል። ይህም ችግር የለውም።
መንግስት ይህን ሁሉ ግምት ውስጥ በማስገባት ለክልሉ ያስፈልጋል ከተባለው በላይ ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ አቀረበ። ይሁንና ትህነግ እርዳታ በበቂ ሁኔታ መቅረቡና የግብርና ስራው በሚገባ የሚከወንበት መደላድል መፈጠሩ አልተመቸውም። እሱ ጉዳዩ እኛ ከምናውቀው የመኸር እርሻ ጋር አይደለምና። እሱ የራሱ የመኸር እርሻ ነበረው።
አያያዙን የተመለከተው መንግስትም ለግብርናው እና ለእርዳታ አቅርቦቱ ይበልጥ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር አንዲሁም የትግራይ ህዝብ ትህነግን ቆም ብሎ እንዲያጤነው በማሰብ የተናጠል የተኩስ አቁም በማድረግ ትግራይን ለቆ ሲወጣም እንደዚያው ምቹ ሁኔታውን ሌላ የጥፋት ድግስ ያዋለ እንደመሆኑ ክረምትንና የመኸር ወቅትን ለእሱ የእንጀራ ገመዱ የሚበጥስበት አርጎ ነው የሚመለከተው።
አጋጣሚውን ግብርናውን ከማሳለጥ ይልቅ እሱ የመኸር እርሻዬ ላለው ጦርነት የጦር ትርኢት ማሳየት፣ መሳሪያ ማወዛወዝ፣ አታሞ መደለቅ፣ መተንኮስ ውስጥ በመግባት ተጠቀመበት፤ የአማራና አፋር ክልሎች የተለያዩ ዞኖችን ወረረ። በዚህም ንጹኃን ዜጎችን በአሰቃቂ ሁኔታ ጨፈጨፈ፤ ህጻናትን፣ አዛውንቶችን ጨምሮ በርካታ ሴቶችን አስገድዶ ደፈረ። ሚሊዮኖችን አፈናቀለ።
ጥሪታቸውን፣ ሀብት ንብረታቸውን ዘረፈ፤ አወደመ፤ እንደ አይናቸው ብሌን የሚመለከቷቸውን የእርሻና የወተት ከብቶቻቸውን አርዶ በላ። የትምህርት የጤና እና የመሳሰሉትን መሰረተ ልማቶች ዘረፈ፤ አወደመ።
በአንዳንድ አካባቢዎች የዘር ወቅት አስተጓጎለ፤ የደረሰ ሰብል ዘረፈ፤ በወቅቱ እንዳይሰበሰብ አደረገ፤ የአማራ ክልል የተለያዩ ዞኖች አርሶ አደሮችን የአፋር ክልልን ህዝብ ግብርና ስራ አውኮ ረምርሞ ነው በጦርነቱ አይቀጡ ተቀጥቶ የተረፉትን ወታደሮቹን ይዞ ወደ ትግራይ የተመለሰው።
በዚያ ክረምት የአርሶ አደሩን አቅም ብቻ ሳይሆን የመላውን የግብርናውን ተዋንያን አቅም ጭምር ግብርናው ላይ መረባረብ ሲገባ የትግራይን አርሶ አደርና ልጆቹን ለጦርነት ማግዶና አስፈጅቶ አይኑን በጨው አጥቦ ድል አድርጌ ነው የተመለስኩት ብሎ ወደ ትግራይ ተመለሰ። የእሱ የመኸር እርሻ ያ ነበር። ይህ ሁሉ የሆነው የአገሪቱ ኢኮኖሚ ዋና ምንጭ የሆነው ግብርና የመኸር እርሻ በሚያከናወንበት ውድ ጊዜ ነው።
ከዚህ ሁሉ ጥፋት መማር ያልፈለገው ይህ ቡድን የክረምት ወቅትን እንደ ጦርነት ስትራቴጂ መያዙ ይነገርለታል፤ እናም ዘንድሮም ያንን ጦርነት ለመድገም የጦርነት አታሞውን እየደለቀ ነው። ክረምቱ ለአውሮፕላንና ድሮን አይመችም፤ ይሄኔ ነው ጦርነት መግጠም የሚል ግምገማ እንዳለውም ይነገራል። ዘንድሮም እንደ አምናው ሁሉ የመኸር የግብርና ስራ በሙሉ አቅም በሚካሄድበት በዚህ ወቅት ይህን የተሳሳተ መንገድ በመከተል ጥፋቱን ሊደግም አቅዷል። ይህ ስትራቴጂ ታዲያ የአሸባሪው የመኸር እርሻ በሚል መጠራት ይኖርበታል።
ጦርነት የሚከፍት የትኛውም ቡድን ጦርነት ለመጀመር ይመቸኛል የሚለው ጊዜ እንደሚኖረው ይታመናል። የፈለገው ቢሆን ግን በዋና የአዝመራ ወቅት ጦርነት ውስጥ አይገባም። እንዲህ አይነቱ ወቅት አይደለም ጦርነት ለመክፈት ለመከላከል እንኳ አመቺ ጊዜ ተብሎ የሚወሰድ አይመስለኝም። ነገሮች አፍጠው አግጠው አልፈው ሌላ ችግር ሊያስከትሉ ይችላሉ ተብሎ ካልታመነ በቀር ይህ አይነቱ የአዝመራ ወቅት ለጦርነት አይታሰብም።
ሁሌም ጦርነት የማይለያቸው የአረቡ አለም አንዳንድ አገሮች የተለያዩ ቡድኖች በጾም ወይም በበአላት ወቅት የተኩስ አቁም ሲያደርጉ እንሰማለን። ወደ እኛው አገር ጉድ ስንመጣ ግን ነገሮች ግራ ናቸው። ደቡብ ጎንደር ላይ ከአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በርካታ ሰዎች ተገኝተው የደብረ ታቦር በአልን በሚያከብሩበት ወቅት ደብረ ታቦር ላይ ከባድ መሳሪያ ተኩሶ ሕይወት አጥፍቷል እኮ፤ ንብረት አውድሟል። ይህ ቡድን አሸባሪ ተብለው የሚታወቁ የአረብ አለም ቡድኖች ያላደረጉትን የሚያደርግ ከይሲ ነው።
እናም ለአገርና ህዝብ የኢኮኖሚ መሰረት የሆነው ግብርና ለትህነግ ምኑም አይደለም። የአሸባሪው የመኸር እርሻ ጦርነት ነው። የእሱ የመኸር እርሻው ጦርነት፣ የእርዳታ እህል መለመን እንዲሁም ራሱ እያጠፋ የኢትዮጵያ መንግስትን መክሰስ ነው።
ኢትዮጵያውያን የመኸር እርሻቸውን በሚገባ ለመከወን ስለማዳበሪያና ስለምርጥ ዘር አቅርቦትና ስርጭት፣ በዘር ስለሚሸፈን ማሳ ማስፋፋት፣ ስለግብርና ሜካናይዜሽን/ ትራክተር፣ ኩታ ገጠም ማሳ፣ወዘተ./፣ ስለአረንጓዴ አሻራ፣ ነጋ ጠባ በሚነጋገሩበት በአሁኑ ወቅት ትህነግ ዶሮ ብታልም ጥሬዋን አንዲሉ ይህን ታላቅ የመኸር ወቅት አንዳለፈው አመት ሁሉ በጦርነት ኢትዮጵያን ለማመስ እየተዘጋጀበት ይገኛል።
እናም ክረምቱን ተገን በማድረግ ኢትዮጵያውያንን ለሶስተኛ ጊዜ በመውጋት የመኸር እርሻውን ለማካሄድ እየተዘጋጀ ይገኛል። የኢትዮጵያ መንግስትና ኢትዮጵያውያን እንዳለፉት ጊዜያት ሁሉ የመኸር የግብርና ስራቸውን ባቀዱት ልክ እያስኬዱ የዚህን የአገር፣ የልማትና የሰላም ጸር እቅድ ቅዠት ያደርጉታል። የአሸባሪው የመኸር እርሻ አሁንም ይመክናል!
ዘካሪያስ ዶቢ
አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 29 ቀን 2014 ዓ.ም