መጠሪያ ስማቸው ደስታ የሆኑ ግለሰቦች ከስማቸው አወጣጥ ጀርባ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ከደስታ ፍለጋ ጋር የተገናኘ አንዳች ምክንያት የመኖሩ ምክንያት ሰፊ ነው። ደስታ በሚል ስም የሚጠራ የአጸደህጻናት ተማሪ ህጻን መምህርቱ ለምን ደስታ እንደተባለ ትጠይቀዋለች። ለጥያቄው የህጻኑ ምላሽ ዝምታ ነበር። በሌላ ቀንም በተመሳሳይ ሁኔታ መምህርቷ ህጻኑን ትጠይቀዋለች፤ በዚህ ጊዜ ህጻኑ ተማሪ ምላሽ መስጠት የሚያስችለው አቅም በማጣቱ ፊቱን አዙሮ አንገቱን ደፋ። የህጻኑ ሁናቴ ትኩረቷን የሳበው መምህርት ከህጻኑ ቤተሰብ መስማት እንዳለባት ታስብና ወላጆቹን ታስጠራለች።
በጥሪው መሰረት የልጁ እናት እንደሆነች በቅጽ ላይ ስሟ የተጠቀሰ እናት ትምህርት ቤት ግቢ ውስጥ ይገኛሉ። መምህርቷም ህጻኑ ላይ የምታየውን ሁኔታና ለዚህ እንደ መነሻ የወሰደችው የህጻኑን የስሙን ጉዳይ መሆኑን አስረዳች። መምህርቷም “ከልጅዎ ስም ጋር በተገናኘ ልጅዎትን ስሜታዊ የሚያደርገው ጉዳይ ምን ይሆን?” ስትል በትህትና ጠየቀች። በተመሳሳይ ሁኔታ እናት ምላሽ ከመስጠት ዘገየች። በዝምታ ውስጥ ተዋጠች። አይኖቿን እምባ ሞሉት። ከለቅሶ በኋላም መናገር ጀመረች።
“የደስታ እናት እኔ አይደለሁም። እኔ አሳዳጊው ነኝ፤ የእናቱ እህት ወይንም የደስታ አክስት። እናቱ በህይወት የለችም። እናቱ በገጠማት የጤና ችግር ምክንያት ከደስታ መወለድ ጋር በተገናኘ ህይወቷን አጥታለች። ዶክተሮቹ ከእናቲቱ ወይንም ከልጁ አንዱን ማዳን ይችሉ ነበር። እናት ምርጫዋ ልጇን ማዳን ሆነ። ለልጁ ደስታ የሚል ስም አወጣችለት። ‘ደስታ ህይወቴን ሰጥቼሃለሁ፤ አንተ በደስታ ኑር፤ ህጻን ብትሆንም በአይኔ አይቼህ ባላውቅህም የአንተን ህይወት መስዋእት አድርጌ የእኔ መኖርን አልመረጥኩም’ አለች። ለልጇም ማስታወሻ ጽፋ አለፈች። ልጁም ተወለደ፤ ይህን ታሪክም ቀስ በቀስ እየሰማ እንዲያድግ አባቱ ስለፈለገ አባቱ ነገረው። እናቱን ባሰበ ጊዜ ስለተደረገለት ስጦታ ይገረማል። በልጅነት አዕምሮው ይህን ታሪክ መነገሩ ትክክል ባይመስለኝም እውነታው ግን ይህ ነው።” አለች።
መምህርቷ ይህን ታሪክ ስትሰማ ተረበሸች፤ በእርሷ ህይወት ውስጥ የሚቆጫትን አንድ የታሪኳን ገጽ አስታውሳት፤ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ እያለች ያስወረደችውን ጽንስ። “በቅድሚያ ማርገዝ አልነበረብኝም፤ ከተረገዘ በኋላ ግን ማስወረድ አለነበረብኝም” ብላ አምርራ ትጸጸታለች። ውርጃውን በፈጸመች ጊዜ በህልም የሚያምር ህጻን እየመጣ “ለምን አልፈልግህም አልሺኝ?” እያለ ይጠይቃትም ነበር። አንዳንድ ቀን ደግሞ ከብዙ ህጻናት መካከል አንዱን ህጻን ነጥላ አውጥታ ስታባርረውና መጨረሻ ላይ ገደል ውስጥ ሲገባ እርሷ ግን ተረጋግታ ለመራመድ ስትሞክር ነገርግን ስትረበሽ ትመለከት ነበር።
የደስታ አክስት ለመምህርቷ ታሪኩን ከነገረች በኋላ ደስታን ሰላም ብላ ወደ ቤት ተመለሰች። መምህርቷም ለራሷ ‘ሁሉም ቤት ለካንስ የተለያየ ታሪክ አለ፤ አንዳንዱ ቤት የጭካኔ ሌላው ቤት ደግሞ የርህራሄ። እኔ ቤት ያለው የጭካኔ ነው’ ብላ እንደተለመደው ራሷን ወቀሰች። በእምባ በታጀበ አይኗ ሆኖ ወደ ተማሪዎች ስትመለከት ደስታ ከተማሪዎች ጋር እየተጫወተ ነው። እርሱ ዛሬ ልጅነቱን ይኖር ዘንድ መስዋእት የሆነችውን እናት አሰባት። መስዋእትነቱ ቀጥሎ የእህቷን ልጅ የምታሳድገው አክስትም። ደ ስታን በምን …?
ደስታን በምን እንፍጠር፤ ደስታን በምን እናብዛ፤ ደስታን በምን እናጋባ፤ ደስታን በምን እንጠብቅ በሚሉ የጥያቄ ዝርዝር ውስጥ ሆነን ቀጥሎ ያለውን ክፍል እናንብብ። በቅድሚያ ግን ለራሳቸው መቆም ለማይችሉቱ እንዴት ደስታ መሆን እንደሚቻል የማሰብን አስፈላጊነት እናስብ።
እናት ስለማታውቀው ደስታ
ደስታን ስናስብ ድምጽ ለሌላቸው ድምጽ መሆንን እናስብ። የሚባዛ ደስታ ስለሌሎች ሲሆን በዋናነት ደግሞ ስለራሳቸው መናገር ስለማይችሉቱ። ስለራሳቸው መናገር የሚችሉት አካላት የሚባሉ አካላት ድምጽ የሌላቸውን ድምጻቸውን ሊያፍኑ ይችላሉ፤ እንዲሁም ድምጽ መሆንም ይችላሉ። ድምጽ ያላቸው በትክክለኛው ቦታ ላይ ድምጽ መሆን እንዲችሉ ማሰቡ አስፈላጊ የሚሆነው ለእዚህ ነው። ድምጽ ያላቸው ሰዎችን ማወቅ፣ መቅረብ፣ ድምጽ ስለሌላቸው ማስረዳትና ድምጽ ማድረግ ስራውን ፍሬያማ ያደርገዋል።
በዙሪያችን ያሉ ስለራሳቸው ምንም ማድረግ የማይችሉትን ማወቅ ወይንም መረዳት ቀዳሚው የደስታ ምንጭ ነው። በራሳችን ጫማ ሆነን ስናስብ በፈጣሪ ዘንድ የምንታየው ማድረግ በምንችለው ደረጃ ነውና እርሱን ማሰብ አለብን። አንድ ህጻን ልጅ ከአንድ አዋቂ ጋር እኩል ልናይ አንችልም፤ ወጣትን ከ ባልቴት ጋር እኩል ልናይ አንችልም፤ ድምጽ ያላቸውን ከሌላቸው የምናይበት ብዙ መንገድ አለን። ድምጽ ለሌላቸው ድምጽ ለመሆን የምናወጣው ሃብት ውስን በመሆኑ ድምጽ የሌላቸውን መለየት ያስፈልጋልና ትኩረታችን ይሰጠው።
በመቀጠል ደስታን ለመጠበቅ የሚረዳንን ነጥብ እናንሳ። ከጎደለው ይልቅ የሞላውን የመመልከት አተያይ።
የሞላውን መመልከት
እንደ አንድ ዜጋ በአገራችን ውስጥ የጎደለን ነገርን እንዘርዝር ብንል መዳረሻችን ቀላል አይመስልም። የተወሰኑትን እንጥቀስ ብንል ድህነት፣ የትምህርት ተደራሽነት፣ ጎጂ ባህሎች፣ የሴት ልጅ መደፈር፣ የሥራአጥ ቁጥር፣ የፖለቲካ አለመረጋጋት፣ ወዘተ ብለን ልንዘረዝር እንችላለን። ለእያንዳንዱ የጉድለት ዝርዝር ተገቢውን መፍትሄ የመፈለጉ ሂደት ስንገባ የመሰረት ጉዳይ አግጦ ይወጣል።
የጎደለው ሰላም ከሆነ የውስጥ ሰላም ያላቸው ሰዎች መብዛት የመፍትሄው መንገድ እንደሆነ ማህተመ ጋንዲ ይናገራሉ። “በአገራት መካከል ሊኖር የሚገባ ሰላም በግለሰቦች መካከል ባለ መሰረት ያለው ፍቅር ይመሰረታል” ይላሉ ማህተመ ጋንዲ። አገራት የግለሰቦች ስብስብ ናቸው። ግለሰቦች በውስጣቸው የሚሆን ሰላምና ፍቅር መሰረት ሆኖ ወደ ሰላም ያደርሳል። እያንዳንዱን ግለሰብ የሰላም ሰው አድርጎ የማሳደግ በድምር ውጤቱ የአገርን እንዲሁም የአገራትን ሰላም መጠበቅ ነው። ይህም ደስታን ለመጠበቅ እንዲሁም ለማብዛት የራሱን አስተዋጾ ይኖረዋል።
በሳሙኤል አዳምስ አገላለጽ ደግሞ “ለህዝብ ነጻነትና ደስተኝነት ሃይማኖትና የሞራል ሰው መሆን ጥብቅ መሰረት ነው።” ደስታን ለማግኘት ከጉድለት በላይ የሞላውን ለማየት ከተለመደው ስሌታዊ ኑሮ ወጥቶ የእምነትን ወይንም የሃይማኖትን መንገድ ማሰብ ተገቢነት እንዳለው የሚያስረዳ አባባል ነው።
የጉደለውን ነገር በሚገባ ዘርዝሮ ማስረዳት ለሁላችንም የቀለለ ይመስላል። የመፍትሄ መንገዱን ግን መፈለግ ለሁሉም ቀላል ነው፤ እርሱም መሰረትን መመስረት ነው። መሰረቱ ጠንካራ በሆነ ቁጥር የሚታነጽበት ከፍታው ይጨምራል። ከህንጻው ውጫዊ ውበት በላይ ሸክምን በመሸከሙ የምንደነቅበት መሰረቱ ላይ ነው።
አተያይን ከጎደለው ወደ ሞላው በማድረግ፤ ላለን ነገር ቦታን በመስጠት ደስታን እናብዛ። አጠገባችን ያለው ሰው ከጎደለው ይልቅ ያለውን ነገር እንመልከትለት። እምቅ አቅምን በመረዳት ውስጥ የሚፈጠር ደስታ።
አቅምን በመመንዘር
ማንም ተራ ሰው በምድር ገጽ ላይ የለም። በትላንት መንገድ አቅማችን እንደምንጠብቀው የተመነዘረ ላይሆን ይችላል። ነገርግን ደስታን ከመፍጠርና ከማብዛት አንጻር ሊሆን ግን እድል አለው። ደስታን ማብዛት ሲታሰብ የሚሆነው ሌላ ነገር እምቅ አቅምን ማውጣት መቻል ነው። ሰው እምቅ አቅሙን በአግባቡ ማውጣት የሚችልበት እድልን ቢያገኝ ውጤታማ መሆኑ ጥርጥር የለውም። እንደ ኢትዮጵያ ባሉ የወጣት አገር ውስጥ እምቅ አቅምን ማውጣት አለመቻል ከአገር እድገት አንጻር ያለው ኪሳራ ከፍተኛ ነው። ከኪሳራውም መካከል ደስታ የራቀው ህዝብ መብዛት አንዱ ነው። የሰው ኃይል አንዱ የኢኮኖሚ ማሳለጫ ግብዓት በመሆኑ እምቅአቅምን ወደ ውጤት መቀየር የመቻል አካሄድ ትርጉሙ ላቅ ያለ ነው። ጠንካራ የሰው ሃይል ሲኖር ሌላውን የኢኮኖሚ ማሳለጫ ካፒታልን፣ መሬትን እንዲሁም ቴክኖሎጂን የሚያንቀሳቅስ ሆኖ እናገኘዋለን።
እምቅ አቅማችን እንዲወጣ የሚፈልገው አጋጣሚ አለ። ያን አጋጣሚ ዛሬ ያለበት የምቾት ቀጠና መዳረሻችን አድርገን ልንይዘው አይገባም። በመሆኑም እምቅ አቅማችንን ለማውጣት ስናስብ መገፋትን አብረን ልናየው እንችላለን። በመገፋት ምክንያት እምቅ አቅማቸውን የሚገድሉትን አይተን ይሆናል። በመነሻ ታሪካችን ላይ ያለው ደስታ ከተደረገለት ታላቅ ስጦታ ተነስቶ እርሱም በጊዜው እምቅ አቅሙን ለመልካም ነገር ሊያውለው ራእይ ይሰንቅ ይሆናል። በደስታ ውስጥ ያለው ሃዘንም እንዲሁ ሌላ አቅም ነው። ጆን ስትሪልንግ የተባሉ ሰው እንዲህ አሉ “ሃዘን የራሱ የሆነ ውድ የሆነ ሃሴት ነው፤ መንቀሳቀስ ሲጀምር ጠንካራ የሆነ የህይወት ውስጣዊ ክፍል መንቀሳቀስ ይጀምራል።” ትላንት ውስጥ የመጣንበት ሃዘንም እንዲሁ ጠንካራ የሆነውን ውስጣዊ ክፍላችንን ያንቀሳቅሰዋል። አንቀሳቅሶትም ለአላማችን ጨካኝ ሊያደርገን ይችላል፤ በፈተና ውስጥ ጥርሳችንን ነክሰን በጽናት እንድንቆም እንዲሁ።
ልንረዳው የሚገባ እውነት እምቅ አቅም የሌለው ሰው የለም። ሁሉም ሰው ሊወጣና ሊመነዘር የሚችል እምቅ አቅም አለው። አቅሙን እንዴት ባለመንገድ ማውጣት እንዳለበት መረዳት አይኖረው ይሆናል እንጂ አቅም ሳይኖረው የሚኖር ሰው የለም። ሃዘን ከሌለ ዘምባባ የለም፤ ወጀብ ከሌለ ዙፋን የለም፤ የሚያበሳጭ ሳይኖር ክብር የለም፤ መስቀል ሳይኖር አክሊል የለም ብለን ስናስብ የሚገጥመን እያንዳንዱ መገፋት ወደ ተሻለ ነገር ሊያስገባን ዋዜማው ላይ እንዳለን እንረዳለን።
እምቅ አቅም መውጣት ሲጀምር ለውጥ በህይወታችን እንዲሁም በሌሎች ፊት ይሆናል። እምቅ አቅምን በሌሎች ጫማ ውስጥ ለመቆም መጠቀም ደግሞ ወሳኙ ተግባር ነው። ሌሎች እምቅ አቅማቸውን አውጥተው እንዲመነዝሩት በማድረግ ደስታን የሚያበዛ።
አንዳችን በሌላችን ጫማ ውስጥ
መዳረሻችን ደስታ የሞላበትን ግለሰባዊ፣ ቤተሰባዊ፣ ማህበረሰባዊ ኑሮን መኖር ከሆነ ለሌሎች በመኖር ውስጥ ደስታን መፈለግ አለብን። ይህም አንዳችን በሌላችን ጫማ ውስጥ በመኖር የሚገለጽ ሆኖ እናገኘዋለን። በመጪው ህዳር ወር የሚጀመረውን አገራዊ መግባባት ስናስብ እንደ አገር መግባባት እንዲሆን የምናሻው ነገር እንዳለ ሆኖ አድካሚ ጉዞ የሚጠብቀን መሆኑ ግን አያጠያይቅም። አንዳንዶች የአገራዊ ምክክር ሂደቱ አስር አመት ሊፈጅ ይችላሉ ሲሉም ከወዲሁ ሲገምቱ እናደምጣለን። አስርም አመት ይፍጅ ሦስት አመት ቀላል ሂደት አለመሆኑ ግን ለሁላችንም ግልጽ ይመስላል። የተለየ ሃሳብን ሰምቶ ማስተናገድ የሚያስችል ባህል በሌለን ሁኔታ ውስጥ ሆነን ሳለ ሂደቱ ቀላል ሊሆን እንደሚችል አናስብም። መፍትሄ የሌለው ስጋት ግን አይደለም። አንዳችን በሌላችን ጫማ ውስጥ መሆንን እሴት ባደረግን ጊዜ ወደፊት ማለትን እንችላለን፤ ምክክሩ ወደ ማህበረሰባዊ እድገትና ሰላም ሊያደርሰን ይችላል።
አንዳችን በሌላችን ቁስል ውስጥ ስንሆን በመረዳዳት ላይ የተመሰረተ መቀራረብ መፍጠር እንችላለን። ይህም ወደ ማህበረሰባዊ ደስታ ያደርሰናል። ችግርን እንኳን በሚዛኑ በመዳኘት ችግርን በፍጥነትና በጥራት እየፈቱ አንዱ ስለሌላው እየኖረ በጋራ ደስታን የሚፈጥሩበት፤ የሚጠብቁበት ህይወት።
ችግርን በብልሃት
የደስታ ተቃራኒው ሃዘን ነው። ሃዘን ደግሞ ማንም አይፈልገውም። በችግር ውስጥ አልፎ መገኘት ፍላጎታችን ባይሆንም የምናልፍበት ግን ነው። ደስታን ማብዛትን ስናስብ፤ ደስታን መጠበቅን ስናስብ ችግርን የምናይበትንና የምንፈታበትን መንገድ እያሰብን ነው።
የደስታ ሰዎች ችግርን ሲፈቱ ግለሰቡን ከችግሩ ለይተው ይመለከታሉ። ግጭት የሚመጣው በሰው በኩል መሆኑ ግልጽ ነው። ነገርግን ግጭትን ለመፍታት እንቅስቃሴ ስናደርግ የግጭቱ ምክንያት የሆነው ነገር ላይ በማተኮር መፍትሄን መስጠት። ይህ መንገድ ደስታን ቶሎ ለመመለስና ለማጽናት ይረዳል። ነገሮችን ከገለልተኛ አቅጣጫ ማየት ሌላው የጠፋብንን ደስታ መልሰን እንድናገኝ በሚያደርግ ሁኔታ ችግርን ለመፍታት የሚረዳ ነው።
በሆነ ነገር አተያያችን ሚዛናዊ ካልሆነ ወይንም ገለልተኛ ካልሆነ ሙሉ ምስሉን ማግኘት ስለማንችል አስቸጋሪ ቢሆንም በገለልተኛ ሜዳ ላይ ራሳችንን ብናስቀምጥ ወደ ደስታችን ያደርሰናል። ደስታችንን ከነጠቀው ከችግሩ ይልቅ የመፍትሄን መንገድ ማየት ላይ ማተኮር ሌላው የችግርን በብልሃት ነጥብ ነው።
ሁልጊዜ በተለመደው መንገድ ውስጥ ብቻ ነገሮችን ማድረግን ከማሰብ፤ ከተለመደው መንገድ ውጭ መፍትሄ ሊኖር እንደሚቻል ማመን ያስፈልጋል። ችግርን ለመፍታት ስንነሳ አማራጭ የችግር መውጫ ሃሳቦች ሊኖሩ እንደሚችሉ በማመን መንቀሳቀስ ተገቢነት ይኖረዋል። ግጭቱ መፍትሄ የሌለው አድርጎ ከመቁጠር ይልቅ የመፍትሔ መንገዶችን ሊኖሩ እንደሚችሉ አስቦ መንገዶችን በመፈለግ መስራትን ይጠይቃል። የመጀመሪያውም ሁለተኛውም የዓለም ጦርነት ከችግሩ ይልቅ መፍትሄው ላይ በማተኩር መንገድ ወደ እልባት መድረስ ትምህርት የተወሰደባቸው ናቸው። ችግር ውስጥ በመቆየት ሰፊ ውድመት ይከተል ይሆናል እንጂ ወደ መፍትሄ አያደርስም። ዛሬም ደስታችንን ለመጠበቅና ለማብዛት ከችግሩ ውስብስብነት ይልቅ የመፍትሄ መንገድ ላይ እናተኩር። ችግሩ አስሬ ቢወራ በራሱ መፍትሄ አይደለምና።
አስቸጋሪ ቢሆንም ሰላማችንን ለማግኘት ደስታችንን ለመጨመር መፍትሔዎች ላይ ለመስማማት አስተዋጾ ማድረግ አስፈላጊ ነው። አንዳንድ ሰዎች ግጭት ለመፍታት ተነስተው ነገርግን የመስማሚያ ነጥቡ ላይ በአቋም መድረሳቸውን መቀበል ሳይፈልጉ ይታያሉ። ነገርግን ብዙ አማራጮችን ካዩ በኋላ ወደ መፍትሄ የደረሱበትን መንገድ ተቀብሎ እውቅና መስጠት ተገቢ ነው። መፍትሔ ላይ ተደርሷል ተብሎ ነገርግን በቀጣይ እዚያው ቦታ ላይ በመገኘት ችግሩ እንዲያገረሽ የሚያደርገው የተወሰደው የመፍትሔ መንገድ ላይ እውቅና አለመስጠት ሲሆን ነው። ስለሆነም መፍትሔ ላይ የተደረሰበትን ነጥብ እውቅና ሰጥቶ መነሳት ተገቢነት ይኖረዋል።
ዛሬ ደስታችንን ፈትሸን ደስታችንን ላይ የተፈጠረ ችግር ካለ ምንጩን እንፈትሽ። የምናገኘውም ምላሽ ደስታን በምን ብለን የጠየቅናቸውን ጥያቄዎች የሚመለስ ይሁን። ደስታ ከውስጥ የሚመነጭ ስለሆነ ከውስጣችን ሰላም ጋር እንስማማ። ሌሎችን እንደ እራሳችን ቆጥረን በመቀበል ሳይሆን በመስጠት ውስጥ የደስችንን ትርጉም እናስፋ። ዛሬም ሆነ ነገ የደስታ ሰዎች ሆነን እንድንገኝ ለሁላችሁ መልእክቴ ይህ ነው።
በአገልጋይ ዮናታን አክሊሉ
አዲስ ዘመን ግንቦት 27/2014