እነዚህ ፍርደኞች እነሱ ጋር ያለ እውነት ፈጽሞ የማይታወቅ፤ ስለነሱ ተግባርና እውነት ፈፅሞ መረጃ የሌለው የሚፈርድባቸው ናቸው።እነዚህ ሚዛን አልባ ፈራጅ በመንጋ በመሆን በዘመቻ መልክ የሚበየንባቸው የማህበራዊ መገናኛ ብዙኃን ፍርደኞች ያሳስቡኛል። እነሱ አደረጉ ወይም አሉ በሚባለው ብቻ ተነስቶ ጉዳዩን ሳይመረምር ሁሉም የራሱን ፍርድ ይሰጥባቸዋል። አልፎ አልፎ ካልሆነ በቀር እነዚህ ላይ በእያንዳንዱ መገናኛ ብዙኃንና ማህበራዊ መገናኛዎች ሁሉ ተመሳሳይ እርግማንና ትችት ሰለባዎች ናቸው።
በነገራችን ላይ እነዚህ የሳይበር ፍርደኞች ለፍርድ ያበቃቸውን ጉዳይ ዞር ብሎ የሚመረምር ያደረጉትን ተግባር ምንነት “በትክክለኛ መረጃ ይጣራ” የሚል የዚህ ሞገድ ተሳታፊ መኖሩ እስኪያጠራጥር ድረስ በዘመቻ ይኮነናሉ። እነዚህ ጉዳያቸው ባላወቀ አካል የሚበየንባቸው በአንድነት የሚብጠለጠሉ እድለቢሶች ናቸው። የሆኑትና ሆኑ የተባሉበት ትክክለኛ ሁነት ይለያያል። እውነቱን ማወቁ ፈራጁ አያገባኝም ያለ ይመስላል። ሁሌም የሰሩት ሥራ ትክክል አለመሆኑን አንስቶ መርገም እነሱ ላይ መፍረድ ነው ዋንኛ ተግባርና ልማዱ።
ሰሞኑን በዜና መልክ በተለይ በትልልቅ መገናኛ ብዙኃን የዜና ማሰራጫ ገፃቸው ላይ አትመውት ሰዎች ሲቀባበሉበት የነበረውን ዜና አይቼ አንድ ሀሳብ ወደውስጤ ሰረፀ። ዜናው እንዲህ የሚል ነበር። “በሃሰተኛ ገንዘብ ነዳጅ ቀድቶ ለማምለጥ የሞከረው አሽከርካሪ ከቆመ ተሽከርካሪ ጋር በመጋጨቱ ሕይወቱ ማለፉን የአዲስ አበባ ፖሊስ ገለፀ።” በእርግጥ ዜናው ላይ ላዩን ሲታይ ብዙ ከማመራመር ይልቅ በማህበራዊ ድህረ ገፆች ሰዎች ሲያዘዋውሩትና አስተያየት ሲሰጡበት እንደነበረው “ይሄ አጭበርባሪ ዋጋውን አገኘ” የሚያስብል ይመስላል።
ወገን አያችሁ የብዙዎቻችን እርግማን ይህና መሰሉ ነበር። እዚህ ላይ ነው የኔ ጉዳይ ወገን። ይህ ዜና የተሰራበት መንገድ አልያ ዜናውን ያዘጋጀውና ያስተላለፈው ግለሰብ አልያም ተቋም ምን አስቦ አልያም ምን ለማስተላለፍ ፈልጎ ነው? የሚለውን ለመገመት እንሞክር። አንድም የሰውየው ከስነምግባር ውጪ መሆንና ማጭበርበሩን አንስቶ፤ ይህ ክፉ ተግባሩ በራሱ የበለጠ ክፉ ነገር አስከተለበት። ወይም በገጠመኙ አንስቶ ሌላውን ለማስተማር በማለም ሊሆን ይችላል። ሁለተኛው የሚዲያው ዓላማ ብንገምት አዳዲስና የተለያየ ነገር ለአድማጩ አቅርቦ ይበልጥ አድማጭና ተመልካች ማግኘት ወይም መሰል ሌላ አላማ ሊሆን ይችላል፤ ብለን ከዚህ ብዙ ያልራቁ ብዙ ተመሳሳይ ግምቶችን እንሰጥ ይሆናል።
እኔ ዜናው ላይ ከዚህ ከላይ ከተቀመጡ አላማዎች ከፍ ያለ የሚመስለኝ ምክንያታዊ ምልከታ ማካፈል ስለፈለኩ ነው ይህንን ገጠመኝ እዚህ ጋር ማንሳቴ። እስኪ ሰውየው ጋር ከመገናኘቱ በፊት ሊሆን የሚችል ምን አልባትም ሊገጥመው የሚችልን ጉዳይ እንመልከት።
ይህ አደጋ ደርሶበት የሞተው ግለሰብን ትንሽ ወደ ኋላ መልሰን ከመሞቱ 1 ሰዓት በፊት ሊገጥመው የሚችልን ገጠመኝ ነው ብለን እናስብ ለጊዜው። እዚህ ላይ ግን እኔ ሰውየው ለማጭበርበር አልሞከረም እያልኩ አይደለም፤ግን ሰውየው ሊያጭበረብር ፈልጎ ላይሆን ይችላል ብዬ እገምታለሁ።
አደጋው የደረሰው አልያም ጉዳዩ የተፈፀመው ከለሊቱ 6፡30 አካባቢ ነው። ሰውየው የላዳ ሹፌር ነው። ምን አልባት ሰውየው እዚያ ማደያ ውስጥ ከመግባቱ ጥቂት ደቂቃዎች በፊት ለማደያው ከፍሎት የነበረው እውነተኛ ያልሆኑ የብር ኖቶች አገልግሎት ከሰጠው ሰው ተቀብሎ ቢሆንና፤ ገንዘቡ በስህተት ከሰው እንደተቀበለ አስቀምጦት ወደማደያው ሲገባ ለነዳጅ ቀጂው ሰጥቶ ሲወጣ አደጋው ደርሶበት ቢሆንስ? ብዬ አስባለሁ።
ምን አልባትም እንደተባለው ሰውየው ለማጭበርበር ሞክሮ ሲያመልጥ አደጋ ደርሶበት ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ሰውየው ኖሮና ተይዞ ጉዳዩ ቢመረመርና እውነቱን ብናውቅ መልካም ነበር። ግን ደግሞ ሰውየው የሞተው እዚያው ከማደያው ብዙ ሳይርቅ ተጋጭቶ ስለሆነ የተነገረን ዜና እንዲህ ነው ሲባል ተቀብለን ሟቹን ከመርገም ባለፈ ምን አልባት እንዲህ ቢሆንስ አለማለታችን ግን አስገርሞኛል። ደግሞ ማታ ሞቶ በደንብ ምርመራና ከጀርባው ሊከሰት የሚችለው ነገር ሳይሰላ ጠዋት ነው ዜናው የታወጀው።
እኛ በተለይ በአብዛኛው የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚ ከምክንያት የራቁ እጅጉን ለመንጋነት የቀረቡ ፍርድ ሰጪዎች እንጂ ጉዳዮችን ስንመለከት ምን አልባት ሌላ አይነት መነሻና ያላወቅነው ገጠመኝ ሊኖረው ይችላል ብለን ማስላቱ ላይ ብዙም ነን። ጉዳዮችን በተነገረን ልክ በቀጥታ ከማየት ይልቅ ከበስተጀርባ ሌላ ያላየነው እውነት ሊኖር ይችላል የሚል ልምድ ከእኛ ርቋል። በዚህም የመንጋ ፍርድ ፈራጆች በማናውቀው ጉዳይ ፍርድ ሰጪዎች ሆነን አርፈነዋል።
ከራሳችን ስህተት ይልቅ የሌሎች ስህተት አግዝፈን ማየታችን ብዙ ጊዜ የበለጠ ስህተት ውስጥ ይጥለናል። በምድር ላይ ስንኖር አብዛኞቻችን ስህተት መስራታችን እውነት ነው፤ፍፁምነት የሰው ልጅ ባህሪ ሊሆን አይችልም። ስህተት መቀነስ እንጂ ፈጽሞ ማጥፋትም አንችልም። ግን ደግሞ ስህተቶቻችንን ወይም የሌላውን ስህተት ለማረም የምንሞክርበት ሂደት ላይ ነው ልዩነቱ። ሰዎች መሳሳታቸው ስላገዘፍን አልያም ስለኮነን ብቻ ስህተቱ ይታረማል ማለት አይደለም።
በዚሁ ሰሞን አንዲት ታዋቂ ቴሌቪዥን ላይ ትሰራ የነበረች ጋዜጠኛ በማህበራዊ ሚዲያ የሚረግማትና ስህተትዋን አጉልቶ ለማሳየት በዚያም ውስጥ እኔ ከስህተት የራኩ ነኝ ብሎ ሊነግረን ያልሞከረ በጣም ጥቂት ነው። ልጅትዋ በይፋ የሰራችው ስህተት መሆኑንና ባላሰበችው መልክ በሌሎች ቪዲዮው መውጣቱን ገልፃም፤ለምን እንዲህ አደረገች የሚለው ወቀሳና ነቀፌታ ቀጥሎ ነበር።
አብዝተን ስህተት ውስጥ የምንወድቀው ፍፁም ትክክል ነን ብለን በምናምንበት ጉዳይ ነው። ይሄም ሁለት መልክ አለው አንደኛው እርግጠኛ የሆንበት ጉዳይ ጥንቃቄ እንዳናደርግ የበዛ የራስ መተማመን ውስጥ አድሶን አልያም ደግሞ ያወቅነው የመሰለን ጉዳይ አልያም ተረድተነዋል የምንለው ጉዳይ ብዙም ትኩረት ሰጥተን ባለማየታችን። እኛ ከስህተት የራቅን ባንሆንም ብዙ ጊዜ እነዚህ ናቸው የስህተቶቻችን መነሻ ምክንያት ።
በማህበራዊ ሚዲያ ላይ የምንሳተፍ የሳይበር ፍርደኞች ደግሞ የሌላው ስህተትና ጉድፍ አብዝተን የምንተቸው እኛ ንፁህና ከስህተት የጠራን ነን ብለን በማሰባችን ነው። ነገር ግን የእያንዳንዳችን ጓዳ ቢመረመር ከምናወግዘውና ተፀይፈን ከምንገልፀው ነውር ከፍ ያለ ነውር ባለቤት ሆነን እንገኛለን። በሰዎች ላይ የምንበይነው አልያም የምንፈርደው ፍርድ አገናዝበንና ምን አልባትም እኛ ከፊት ከምናየውና እውነት ካልነው ጉዳይ በተቃራኒው የሆነ እውነት ሊኖር ይችላል ብለን መገመት ይኖርብናል።
ወገን በእያንዳንዱ ጉዳይ ላይ የራሳችን ፍርድ ሰጪና ተንታኝ መሆን እንዴት እንችለዋለን። እኛ የሚመለከተንና የራሳችን የሆነ ጉዳይ ካልሆነ በቀርስ እንዴት የማናውቀውን ጉዳይ መዳኘት እንችላለን። ዳኝነት ሁለት መሰረታዊ ጉዳዮች አሉት። የመጀመሪያው እውነት ለማወቅ መጣር፣ ትክክለኛው ጉዳይ ለመለየት መስራትና እዚያ እውነት ላይ ቆሞ ፍርድ መስጠት ነው። እኛ ዳኝነታችን አልያም ፈራጅነታችን ሁለቱን ያማከለ ካልሆነ ፍርዳችን የተዛባ ነው። አበቃሁ፤ ቸር ይግጠመን።
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን ግንቦት 27/2014