«›አሉ!fi እያልን፣ ካልሆነ ሥፍራ አንገኝ»
እንደ ሀገር ካደከሙን፣ ካጠወለጉን፣ ካታከቱንና ግራ ካጋቡን ወቅታዊ ችግሮቻችን መካከል “አሉ! ተባለ! ተባባሉ!” እንደሚባሉት “የአንደበት ቫይረሶች” የከፋ ወረረሽኝ አጋጥሞናል ለማለት በእጅጉ ያዳግታል። “በአሉ!” የወሬ አውሎ ነፋስ ያልተፍገመገመ፣ ያልቆሰለ ወይንም ተስፋ እስከ መቁረጥ ደርሶ ነገረ ዓለሙ ያልጨለመበት አትዮጵያዊ ወጣት፣ ጎልማሳ፣ ወይንም አረጋዊ/አራጋዊት ፈልጎ ለማግኘት እጅግም አያዳግትም።
ከገጠር እስከ ከተማ፣ ከአደባባይ እስከ የምናኔ ዋሻ፣ ከትምህርት ቤት እስከ ሐኪም ቤት፣ ከላይ ቤት እስከ ታች ቤት፣ ከሀገር ደጅ እስከ ባዕድ ምድር “በተባለ!” ወሬ ቀበቶው ያልላላ፣ ወይንም ማተቡ ያልሰለለ ሰው ማግኘት ተከቻለ አሁንም ያ ሰው “ጀግና” ወይንም የተለየ ፍጡር አለያም ከማሕበረሰቡ ሸሽቶ የሚኖር መጻተኛ መሆን ይኖርበታል። እሱውም ቢሆን “አሉ! ተባለ!” ለሚለው ሹክሹክታ ጆሮውን ያለማዋሱን እርግጠኛ መሆን አይቻልም።
ሀገር “በአሉ! በተባለ! በተባባሉ!” ጤና አጥታ ማደሯ “ኑሯችን ስለሆነ” እመኑ አትመኑ ብሎ ለመሟገት ተከራካሪና አከራካሪ እንጋብዝም። የዕለት እንጀራችን መሸመቻ ገበያው “በአሉ!” ወረርሽኝ ተናግቶና አብዶ ጨርቁን ጥሎ መወፈፉን የሚክድ ሰው ይኖራል ተብሎ አይታመንም። “ቅቤ ሻጭ ድርቅ ማውራቱ”፣ “ጨው ነጋዴ በዶፍ ዝናብ” ማመካኘቱ ባህል እስኪሆን ድረስ ተቀብለን ማቀባበል እንግዳችን አይደለም።
የሚያዛጉ ሰዎች ቁጥር በርከት ብሎ የሚያስተውል ሰው “የቡና ዋጋ መወደድን” በአዋጅ ቢለፍፍ፣ “ኑግ፣ ሰሊጥ፣ ተልባ ወይንም የሱፍ አበባ ከነገ ጀምሮ እንደማታበቅል ምድሪቱ ምላለች” ብሎ “በአሉ” አውሎ ነፋስ ወሬ በአየሩ ላይ የሚበትነውን ሰው እህ ብለን አድምጠን ዘይት ለመግዛት የወረፋ ሰልፍ የምናራዝም ብዙ ዜጎች አንጠፋም። የሠፈራችን አድባር እማማ አበዛሽ ደጋግመው እንደሚሉት፤ “ጤፍን ያስወደደው፣ ሸቀጦቻችንን ያናረው ሌላ ሳይሆን ‹አሉ!› እያልን የምናሟርትበት አንደበታችንና የወሬ ማመላለሻዋ ሞባይላችን በጥምረት በከፈቱብን ጦርነት አማካይነት ነው።”
የፖለቲካውና የአክቲቪዝሙ አየርና ምህዳርም “በአሉ! በተባባሉ!” ቫይረስ ተለክፎ አልጋ ላይ ከዋለ ሰነባብቷል። “አሉ” ለክፎናል፣ መርዞናል፣ ጤና ነስቶንም ያስቃዠናል። “አሉ!” የሚል መርዶም ይሁን ዜና ሳያቀብልና ሳይቀባበል የዋለ ዜጋ በሀገር ውስጥም ሆነ በባዕድ ምድር ጮኸን ብናጣራም ሰሚ እስከማይኖር ድረስ ሁሉም በደዌው ተሸንፎና ተረትቶ ከተልፈሰፈሰ ሰነባብቷል።
ይህ ርእሰ ጉዳይ ከሦስት ዐሠርት ዓመታት በፊት በሀገር ፍቅር ቴያትር ቤት ለሕዝብ የቀረበን አንድ ድንቅ ተውኔት ያስታውሰኛል። የተውኔቱ ርዕስ “አሉ!” የሚሰኝ ነበር። የቴያትሩ መቼት (Setting) በተቀነበበት አካባቢ የሚኖረው ማሕበረሰብ ማን እንደፈጠረው በማይታወቅ “የወሬ ቱማታ” ቀልብያውን ስቶ “ጉድ ተፈጥሯል” እያለ ሲቀባበል፣ ሲተረማምስና በጭንቀት ተውጦ ሲቃትቱ ተመልካቹ በሳቅ ይንፈራፈር ነበር።
ምናልባትም ይህ ጸሐፊ እጅግ ተማርኮባቸው ደጋግሞ ካያቸው ቴያትሮች መካከል “ከባልቻ አባነፍሶ” ቀጥሎ ሁለተኛው ተውኔት ይህ ሳይሆን አይቀርም። የብርሃኑ ዘርይሁን የቴያትር ድርሰት የሆነውን “ባልቻ አባነፍሶን” እግረ መንገዴን የጠቀሱኩት “ከሰደበኝ መልሶ የነገረኝ ገደለኝ” የሚል ድንቅ አባባል ትዝ ብሎኝ ነው።
“አሉ!” ተብሎ የተጠቀሰው ያ ተውኔት ዛሬ ተመልሶ ለመድረክ ቢበቃ እንኳንስ ተመልካቹ እየተፍነከነከ ሊዝናና ቀርቶ ማግጠጡን እንኳን እርግጠኛ መሆን አይቻልም። ለምን ቢሉ “ሁሉ ቃልቻ ማን ይሸከም ስልቻ” ሆኖብን ሁሉም ዜጋ ኑሮዬ ብሎ የገበረለት ባህርይው “በአሉ! በተባለ!” ክፉ አየር ስለተበከለ ከኮሜዲነቱ ይልቅ እውነትነቱ ይበልጥ ስለሚጎላ ተመልካች ስለማግኘቱ ዋስትና መስጠት ያዳግታል።
“በአሉ እና ተባለ” ጌሾና እንክርዳድ የተጠመቁ የጊዜያችን ሃሜቶችና ወሬዎች የምን ያህሉን ሰው ናላ እንዳዞሩ፣ የስንቱን ትዳር እንደበተኑ፣ ስንቱን ለበቀልና ለቁርሾ እንደዳረጉ፣ ምን ያህሉን አወፍፈው ጨርቁን እንዳስጣሉት ደፋር ተመራማሪ ተገኝቶ የጥናት ውጤቱን ቢሰንድልን በራሳችን ማፈር ብቻም ሳይሆን ለተከታዩ ትውልድም ትምህርት በሆነ ነበር።
ይህ እንደ ሱስ ያስገበረን የማሕበራዊ ሚዲያ ዘመን ከእጃችን ያስጣለን ብዙ እሴቶች ቢኖሩም አንዱና ምናልባትም ተቀዳሚው ጉዳይ “ስግብግብ ጆሮ” እንዲኖረን ማድረጉ ነው። ነፍሰ ሄሩ የሙዚቃ ጠቢብ ጥላሁን ገሠሠ “ስግብግብ አለች ጆሮዬ” ብሎ ያንጎራጎረው ዛሬ ከአርካይቭ ወጥቶ ብናደምጠው የሁላችንንም ጓዳና ጎድጓዳ በሚገባ ስለሚዳስስ የምናደምጠው ተሻምተን ይሆን ነበር። ለዘነጉትም ሆነ ትዝ ለማይላቸው አንባቢያን የግጥሙን ጥቂት ስንኞች እናስታውስ።
«ሰው ሁሉ እንዳይሆን፣ ፍጹም ደመኛዬ፣
እያጣራ ይስማ ስግብግብ ጆሮዬ።
ጎጂ ጠቃሚውን እያግበሰበሰ፣
ከጤናዬም ተርፎ ቤቴን አፈረሰ።
ልክስክሱን ሁሉ እያጠራቀመ፣
ይኼው እስከ ዛሬ አንጀቴ ታመመ።
ዘልቆ ሳይረዳ የጆሮን ምሥጢር፣
ጥላቻን ያተርፋል ፍጡር በፍጡር።»
“አሉ! ተባለ!” በሚል ባልተረጋገጠና ረብ የለሽ አንደበታቸው የወሬ ዘር ቋጥረው ማለዳ ላይ “በስግብግ ጆሮዎች” ማሳ ላይ ለመዝራት የሚተጉ ዜጎችን የሚወክል አንድ ታሪክ ከቅዱስ መጽሐፍ ውስጥ ማስታወሱ ቦታው ይመስለናል፤ እንጥቀሰው።
“እነሆ ዘሪ ሊዘራ ወጣ። እርሱም ሲዘራ አንዳንዱ በመንገድ ዳር ወደቀ፤ ወፎችም መጥተው በሉት። ሌላውም ብዙ መሬት በሌለበት በጭንጫ ላይ ወደቀ። ጥልቅ መሬትም ስላልነበረው ወዲያው በቀለ፣ ፀሐይ በወጣ ጊዜ ግን ጠወለገ፣ ሥርም ስላልነበረው ደረቀ። ሌላውም በእሾህ መካከል ወደቀ፣ እሾሁም ወጣና አነቀው። ሌላውም በመልካም መሬት ላይ ወደቀ አንዱም መቶ፣ አንዱም ስድሳ፣ አንዱም ሠላሳ ፍሬ አፈራ። የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ።”
ይህ ግሩም ታሪክ ብዙ ቁምነገሮች ሊተላለፉበት ተፈልጎ የተነገ ምሳሌ ነው። ለጊዜው መንፈሳዊ ትርጉሙን ለእምነቱ አስተማሪዎች በመተው ምሳሌውን ለመመልከት የምንሞክረው “በአሉ!” ኮሮጆ የተሞላ የወሬ ዘር ለመዝራት ማልደው የሚወጡትን ግለሰቦች በአእምሯችን እየሳልን ይሆናል።
እነዚህ “አሉ! ወይንም ተባለ!” የሚል ዘር የሚበትኑት “የወሬ አዝማሪ” ገበሬዎች ዘራቸውን የሚበትኑት ባገኙበት ቦታ ሁሉ ነው። በጭንጫ ልብ የሚመሰል ጠንካራ ሰብእና ያላቸው አንዳንድ ግለሰቦች እነዚህን መሰል የወሬ ትጉሃን የሚያስተናግዱት ጆሯቸውን ደፍነው ነው። ያወራሉ አያደምጧቸውም፤ ይቀባጥራሉ አይሰሟቸውም። ስለዚህም “የአሉ!” ማራገፊያ ስለማይሆኑ ሰብእናቸው በትንሽ በትልቁ የማይነዋወጥ ዓይነቶች ስለሆኑ ተረጋግተው ይኖራሉ።
ሌሎችም አሉ መንገድ ለመንገድ እየዞሩ “የወሬ እንክርዳዳቸውን” ሲዘሩ ቢያስተውሏቸውም ቁብ አይሰጧቸውም። እንዳላየ ሆነው ንቀው ያልፏቸዋል። አንዳንዶችም አሉ፤ “ልባቸውን በእሾህ በሚመሰል” የብረት አጥር አጥረው “ለአሉ! ተባለ! ተባባሉ!” ሃሜቶችና ወሬዎች ቁብ የማይሰጡ።
እጅግ የሚያስገርሙት ግን “የአሉ! ሱስ” የተጠናወታቸውና ያልተረጋገጠ ወሬ ተቀብለው ለማቀበል ልባቸው እጅግ ለም የሆነ። የሚቀበሉትን የፈጠራ ወሬ ከድምጽ በላቀ ፍጥነት ተቀብለው “ነገሩን ሳያጣሩ ለመቶ፣ ለስልሳና ለሠላሳ” ጆሮዎች ለማፍጠን የሚተጉ። እንደነዚህ ዓይነት ሰዎች እንደ በካይ ቫይረስ ያልተገለጠ በሽታ ስላለባቸው ለታዩ የሚገባቸው በጥንቃቄ ነው።
ዛሬ ሀገራችንን እያተረማመሰ ያለውን ችግር ጠለቅ ብለን ብንፈትሽ ዋናው በሽታ “በአሉ” የሚተላለፉ ወሬዎችና ሃሜቶች የሚፈጥሩት ወጀብ እንደሆነ በቀላሉ መረዳት ይቻላል። ከርእሰ ብሔር እስከ ርእሰ መምህር፣ ከሃይማኖት መሪዎች እስከ ምእመን፣ ከባለ ሀብት እስከ ለፍቶ አዳሪ፣ ከምሁር እስከ ተማሪ፣ ከነጋዴ እስከ ቢሮክራት ወዘተ. ፈጠራ በታከለበት የ“አሉ” ወሬ ስሜቱ ያልተጎዳ፣ መንፈሱ ያልተሰበረ፣ አልፎም ተርፎ ለብዙዎች መዘባበቻ መሆኑ ቅስሙን ሰብሮ በጉዳት ያላነከሰ ስለመኖሩ ያጠራጥራል።
በተለይም በማሕበራዊ ሚዲያ የሚሰራጩት የወሬ ሱናሚዎች እንዴት አደብ እንደሚገዙ ሀገራዊ ምክክር ካልተደረገበት በስተቀር በዚህ ፍጥነት የሚቀጥል ከሆነ ጉዳቱ በቀላሉ የሚታይ አይሆንም። አበው እንደሚሉት “ወደቀ ሲባል፤ ተሰበረ የሚሉ”፣ “ታመመ ሲባል፤ ሞቶ ተቀበረ” በማለት ሕዝብን የኀዘን ከል ለማስለበስ ሥራዬ ብለው የሚተጉት እየተለዩ አስፈላጊው የእርምት እርምጃ እስካልተወሰደ ድረስ የት አድርሶ እንደምን እንደሚያንኮታኩተን ለመገመት አይከብድም።
በመሠረቱ ሀገሪቱን እያመሰና እያተረማመሰ ያለው የወሬ ሽምቅ ተዋጊዎቹ የማሕበራዊ ሚዲያ መድረኩ ዛሬ እንደ ቀላልና እንደ ዋዛ በቸልታ ቢታለፍ ነገ ውጤቱ ሥር ከተሰደደ በኋላ እንንቀልህ ቢሉት መልሶ የሚገዳደረው ነቃዩን ስለመሆኑ አስታዋሽ አያስፈልገውም። ከቀድሞው የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች መካከል የአንዱን አብዮተኛ ተማሪ ሁለት የግጥም ስንኝ ማስታወሱ የላይኛውን ሃሳብ ይበልጥ የሚያጎላ ይመስለናል።
«ነቅናቂው ነቅንቆ፤ ቢያነቃንቀው፣
የተነቀነቀው ነቅንቆ ጣለው።»
ዛሬ “በእንቁላል” ደረጃ የምናያቸው ችግሮች ነገ “በበሬ ወለደ” የፈጠራ ወሬ የሀገርን ዋልታ አናግተው አደጋ ላይ እንዳይጥሉን “ነግ በእኔን” ልናስብ ይገባል።
መቼም “አሉ!” እየተባለ ለሚነዛው ወሬ ሁሉ የሚመለከተው መንግሥታዊ አካል ማስተባበያ ለመስጠት አይስነፍ ብለን መደምደሙ ተገቢ እንዳልሆነ አይጠፋንም። ቢሆንም ግን በሀገር ደህንነት፣ በወታደራዊ ጉዳዮች፣ በዲፕሎማሲ፣ በእምነትና በሃይማኖቶች፣ በሕዝቦች የእርስ በእርስ ጤናማ ግንኙነቶች ላይ ቤንዚን እያርከፈከፉ፣ ክብሪት እየጫሩ ጠብና አመጽ ሊቀሰቅሱ ምክንያት የሚሆኑ የ“አሉ! ተባሉ!” ወሬ ፈብራኪዎች መረጃ በማነፍነፍ በሚተጋው ክፍል በኩል ማስተባበያ ሊሰጥ፣ ሀሰቱም ሊጋለጥ ግድ ይመስለናል።
በተለይም እንደ ፋሽን በየተቋማቱ “የኮሚዩኒኬሽን ባለሙያዎች” የሚል ባጅ በደረታቸው ላይ የተንጠለጠለላቸው “ምንግዴዎች” ቢያንስ ደመወዝ የሚከፍላቸው ተቋም “በአሉ!” አልባሌ ወሬ ሲጠቃና ሲታመስ አብረው ከሚያሙ ይልቅ ሙያቸውን አክብረው እውነቱን በማሳየት የታዳጊነት ኃላፊነታቸውን ቢወጡ ኅሊናቸው ሰላም ያገኛል።
«ዘንድሮ፣ ዘንድሮ፣ ዘንድሮ፣ ዘንድሮ፣
የስንቱ ተወርቶ የስንቱ ተነግሮ።
በዚያኛው ›ተናደንfi ጥቂት ሳንቆይ፣
የዚህኛው ›ወሬfi አያስቅም ወይ?»
እያልን “የአሉ! ተባለና ተባባሉ” የሰደድ እሳት ከስር ከስሩ ሳይስፋፋ ለማክሰም እስካልጨከንን ድረስ “ነበልባሉ” በሚሰጠን ጊዜያዊ ሙቀት “እህ!” እያልን በማድመጥ በቸልታ የምናልፍ ከሆነ መዘዙ ስለሚከፋ ውጤቱ የሚበጅ አይሆንም። “ልብ ያለው ልብ ይበል” ማጠቃለያ ምክራችን ነው።
ሰላም ይሁን!
በ(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን ግንቦት 27/2014