በኢትዮጵያ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የኩላሊት ታማሚ የበዛ ይመስላል። በቅርብ የምናውቃቸው ሰዎችም የኩላሊት ህመም እንዳጋጠማቸውና ህክምና እንደሚያስፈልጋቸው፤ ወይም ህክምና እየተከታተሉ እንደሆነ መስማትም የተለመደ ሆኗል። ምን አዲስ ነገር ተፈጥሮ ይሆን? የተፈጠረውን አዲስ ነገር፣ ወይንም ደግሞ ሰዎች ሁሉ የኩላሊት ህመም ታማሚዎች የሆኑበትን ምክንያት ከማንሳታችን በፊት ”የኩላሊት ተግባር ምንድን ነው?” የሚለውን እንመልከት።
አስቀድመን የኩላሊት ዋናው ተግባር በሰውነታችን ውስጥ ያለውን ተስተካክሎት (ሚዛን) መጠበቅ መሆኑን በመሰረታዊነት መያዙ ተገቢ ነው።
ብዙ ሰው ኩላሊትን ሲያስብ ሽንት ነው ትዝ የሚለው። ነገር ግን ኩላሊት ከዚያ ባሻገር ብዙ ተግባራት አሉት። ለምሳሌ በሰውነታችን ውስጥ የሆርሞን ምርት፣ የንጥረ ነገሮች ምርትና ምጣኔ፣ የሰውነት ፈሳሽን ምጣኔ እና ሌሎች በርካታ ተግባራትን ከሚያከናውኑት የሰውነት ክፍሎች መካከል ኩላሊት ዋናው ነው ማለት ይቻላል። በዚህም መካከልም ኩላሊት ይህን የተስተካክሎት ሥራ ለመሥራት ተፍ ተፍ እያለ ሽንትንም አጣርቶ ተገቢውን የማስወገድ ሥራም እንደሚሰራ ልብ ማለት ይገባል።
ኩላሊት በሚያከናውነው የሰውነትን ተስተካክሎት (ሚዛን) የመጠበቅ ሂደት ውስጥ ሆኖ ደግሞ ተመገብን። ምግብ ኃይል ሆነ፣ ህዋሳት የሚያስፈልጋቸውን ያህል ወሰዱ፤ ኩላሊት የቀረውን ተረፈ ምርት በአንድ መልኩ ይሰበስብና ማጣሪያዎቹን ተጠቅሞ ወደ ማስወገጃ ክፍል ይልካል። ተረፈ ምርቱ በኩላሊት ሚሊዮን ወንፊቶች በኩል ተጣርቶ ያልፍና ከፈሳሽ ጋር ወደ ፊኛ ክፍል ይላካል። እዚያ ከሌሎች ፈሳሾች ጋር ተደባልቆ ሲወጣ ነው ሽንት ሸናን የምንለው።
ጎንና ጎናችን ሥር የተሸጎጡት ሁለቱ ኩላሊቶቻችን የባቄላ ቅርጽ ነው ያላቸው። በመጠን ደግሞ የኮምፒዩተር “ማውዝ” ያክላሉ ይላሉ ባለሙያዎች፤ ከታችኛው የጎድን አጥንቶቻችን ውሸቅ ብለው በግራና በቀኝ ጎናችን የሚገኙት ኩላሊቶቻችን ፈሳሽ ከማመጣጠን እና ተረፈ ምርት ከማስወገድ ሌላ ቫይታሚኖችንና ሆርሞን፤ ካልሺየምና ፎስፌት የሚባሉ ንጥረ ነገሮችን ማምረትና ምጣኔያቸውን የመቆጣጠር ሥራም ይሠራሉ።
በአጠቃላይ ኩላሊት፣ የንጥረ ነገር ሚዛን ማስተካከል፤ ተረፈ ምርት ማስወገድ፣ የደም ማነስ ችግር እንዳይኖር ክትትል ማድረግ፣ የደም ግፊትና የስኳር መጠንም በተዘዋዋሪ የመቆጣጠር ብርቱ ሥራ የሚሠራ እጅግ ጠቃሚ ክፍል ነው።
ኩላሊት ባተሌ ነው። ፋታ የለውም። ቀን ከሌት ይደክማል። ልክ 24 ሰዓት እንደሚሠራ የልብስ ማጠቢያ (ላውንደሪ) ማሽን አድርጋችሁ አስቡት። ለምሳሌ በእያንዳንዱ ኩላሊት ውስጥ በየ30 ደቂቃው ሙሉ ደማችን አንድ ዙር ይታጠባል። 5 ሊትር ደም ማለት ነው። ተረፈ ምርቱን የሚያስወግደው በዚህ የአጠባ ሂደት መሆኑን ደግሞ ለጽሁፉ የተጠቀምንባቸው የተለያዩ ጽሁፎች ያመለክታሉ።
ልባችን ከሚረጨው ደም ውስጥ 20 ከመቶ በቀጥታ ወደ ኩላሊታችን የሚሄደው ያለ ምክንያት አይደለም። ኩላሊት ከባድ ሥራ ስለሚሠራ ነው። ደም ይፈልጋል። በሙሉ ሰውነታችን ከሚዞረው ደም 20 ከመቶ በቀጥታ ወደ ኩላሊት የመሄዱ ነገር የኩላሊትን ባተሌነትን ይጠቁማል።
ይህ ባተሌ የሆነው የሰውነት ክፍላችን ደግሞ በተለያዩ ምክንያቶች ይታመማል። የእሱ መታመም ደግሞ የሰውነታችንን ሚዛን እንዳይጠበቅ ከላይ ያነሳናቸው ሥራዎች በሙሉ በአግባቡና በስርዓቱ እንዳይከወኑ በማድረግ ለህመም ይዳርገናል። ታዲያ ኩላሊታችን ችግር ውስጥ ስለመግባቷ በምን ማወቅ እንችላለን?
ኩላሊት አብዛኛውን ጊዜ ጽኑ የኩላሊት ህመም ላይ ካልደረሰ በስተቀር በጠቅላላው ምልክት አያሳይም። ይህ ደግሞ ሰዎች ችግራቸውን በቶሎ እንዳያውቁት ከማድረጉም በላይ ህመሙ ጽኑ ሁኔታ ላይ ሲደርስ ማገገሙ ከባድ እንዲሆን ያደርገዋል።
ብዙ ሰዎች ኩላሊታቸው መታመሙን የሚያውቁት ለሌላ በሽታ ሕክምና ሆስፒታል ሲሄዱ ነው። ሥር የሰደደ ወይም ጽኑ የኩላሊት ህመም ደረጃ ላይ ሲደረስ ግን ኩላሊት በጎ እንዳልሆነ በምልክቶች ማየት ይቻላል። ለምሳሌ እግር ያብጣል፣ ጠዋት ጠዋት ዓይን ያብጣል፤ የፊት ማበጥ ሊያጋጥም ይችላል፣ ቶሎ የድካም ስሜት ይሰማል፣ መጫጫን ያጋጥማል፣ በዚህ መካከል የአጥንት መሳሳትም ሊኖር ይችላል። ይህ የሚሆነው ብዙውን ጊዜ ኩላሊት ፈሳሽ ማመጣጠን ሥራው ሲስተጓጎልበት መሆኑን ማወቅ ያስፈልጋል።
በሌላ በኩልም የምግብ ፍላጎት ማጣት፣ የድካምና የማቅለሽለሽ ስሜት መሰማት፣ የደም የግፊት መጠን መጨመር፣ የደም ማነስ ምልክት መታየት ተጨማሪዎቹ በመሆናቸው እነዚህ ምልክቶች ሲታዩ ኩላሊት የከፋ ደረጃ እንደደረሰ ተገንዝቦ ወደ ህክምና ተቋም መምጣትም ያስፈልጋል።
ኩላሊት ዝምተኛ ነው። ወዲያው አክሙኝ አይልም። ይህ ሁኔታ ደግሞ ያዘናጋል። ስለዚህ ማንኛውም ሰው ቢያንስ በዓመት አንድ ጊዜ ኩላሊቱን ቢታይ ጥሩ ስለመሆኑም ባለሙያዎች ይመክራሉ።
በተለይም የደም ግፊት፣ ስኳር፣ ከፍተኛ ክብደት (ውፍረት)፣ ሌላ ተጓዳኝ ህመም ያለባቸው ሰዎች ከሌሎች በተለየ ሁኔታ ለኩላሊት ህመም ተጋላጭ ስለሚሆኑ ባይታመሙ እንኳን በየጊዜው ኩላሊታቸውን ቢታዩ ኋላ ከሚመጣው ችግር መዳን ይቻላል።
ለብዙዎቻችን ተራ የሚመስለንን ግን ለኩላሊት ጤናማ መሆን እጅግ በጣም ወሳኝ የሆነው ነገር ሽንት እንደመጣ መሽናት ነው። ሽንት ስንቋጥር ኩላሊት ላይ አላስፈላጊ ጫና እንፈጥራለን። ጫናው እየበዛ ሲሄድ ደግሞ የኩላሊት መድከምን ያመጣል።
ሌላው ለኩላሊት በሽታ ተጋላጭ የሚያደርገን ነገር አመጋገባችን ነው። የከፋ የኩላሊት ህመም ሲኖር የሚመከሩ የአመጋገም ዓይነቶች አሉ። ምክሩ መምጣት ያለበት ግን ከሐኪም ነው። ነገር ግን በደፈናው ፕሮቲን ለኩላሊት ጥሩ አይደለም ብሎ ከመመገብ መራቅ ለሌላ ችግር ለመጋለጥ መወሰንም ስለመሆኑ ማወቅ ያስፈልጋል። ሁል ጊዜ ጠቆር ያለ ቢጫ ቀለም ያለው ሽንት የምንሸና ከሆነ ራሳችንን ‘በቂ ውሃ እየጠጣሁ ነው ወይ?’ ብለን መጠየቅ አለብን።
ከምንሸናው ሽንት የሚያመጣው ጠረን ከወትሮው የተለየ ከሆነና ጠንከር ካለ ምናልባት የአንዳች ኢንፌክሽን ምልክት ስለሚሆን ራሳችንን መጠየቅ ይኖርብናል። በተለይ ሴቶች በዚህ ረገድ ለኢንፌክሽን ስለሚጋለጡ ሽታውን በተለየ ትኩረት ሊያጤኑት ይገባል ።
ብዙ ሰው ውሃ ባለመጠጣት ይታመም ይሆናል እንጂ ብዙ ውሃ በመጠጣቱ ችግር ላይ የሚወድቅ ሰው እምብዛም የለም፤ በመሆኑም በአማካይ በቀን ከ2 እስከ 3 ሊትር ውሃ እንድንጠጣ ይመክራል። ይህን መጠን በአንድ ጊዜ መጠጣት ላይኖርብን ይችላል።
ይህ እንዳለ ሆኖ በተለይም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአዲስ አበባ ዋና ዋና ጎዳናዎች ላይ የኩላሊት ህመምተኞችን እያስቀመጡ ”የእርዳታ እጃችሁን” ዘርጉ ማለት እየተለመደ ነው። በሌላ በኩልም በቤተሰብ፣ በጓደኛ በቅርብ በምናውቃቸው ሰዎች ላይም የኩላሊት በሽታ እየተከሰተ ይገኛል፤ ለምን እንዲህ በዛ የሚለው ነገር እራሱን የቻለ ጥናትን የሚፈለግ ቢሆንም ሁለት ምክንያቶች ያሉ ግን ይመስላል። አንዱ የአኗኗር ዘይቤያችን መቀየሩ ሲሆን ሌላው ደግሞ የምርመራ አቅማችን መጨመሩ ሊሆን እንደሚችል ይገመታል።
በመገናኛ አካባቢ በመኪና ውስጥ ቁጭ አድርገዋት እርዳታ እየተሰበሰበላት ያገኘኋት ወጣት ሀቢባ መሃመድ የኩላሊት ህመም እንዳጋጠማት ካወቀች ቆየት ብላለች። እናም ብዙ ህክምናዎችን አድርጋለች። አሁን በግል ሆስፒታልም የኩላሊት እጥበት (ዲያሊሲስ) ህክምና በመከታተል ላይ ናት። ነገር ግን ከእለት እለት ችግሯ እየባሰ፤ እሷም ለእጥበቱ የምታወጣው ገንዘብ እያጣች በመምጣቷ ነው ጎዳና ላይ ለመውጣት የበቃችው።
“የኩላሊት በሽታ እጅግ ከባድ፤ ነው ለማንም አይስጠው” የምትለው ሀቢባ እሷ ኩላሊቷን ከመታመሟ በፊት ከቤተሰቦቿ ጋር በንግድ ሥራ እንደምትተዳደርና ስለህመሙ ምንም አይነት ግንዛቤ እንዳለንበራት፤ በሽታው እንዳይከሰትባትም ያደረገችው አንዳችም ጥንቃቄ አለመኖሩን ትናገራለች።
አሁን ላይ ቤተሰቦቿ እሷን ለማዳን ብዙ መከራ እንዳዩና ያላቸውን ጥሪት በሙሉ አሟጠው መጨረሳቸውን ገልጻ በተለይም ህክምናው በመንግሥት ሆስፒታል እንደልብ አለመገኘቱ እሷንና መሰሎቿን ከመኖር ወደ አለመኖር እያሻገራቸው ስለመሆኑ ትናገራለች።
አቶ ጌታሁን አበበም በተመሳሳይ የኩላሊት ህመምተኛ ናቸው። በእድሜያቸው ወደ ሽምግልናው እየደረሱ ያሉት አባት ለዚህ ህመም ከመዳረጋቸው በፊት ደም ግፊትና ስኳር እንደነበራቸው ይናገራሉ። አሁን የኩላሊት ህመሙ ሲጨመር ግን ኑሮን ፈታኝ እንዳደረገባቸውና በዚህ ደግሞ እሳቸው ብቻ ሳይሆኑ መላ ቤተሰባቸው እየተፈተነ መሆኑን ያብራራሉ።
እድል ገጥሞኝ ህክምናዬን በጳውሎስ ሆስፒታል ነው የምከታተለው ያሉት አቶ ጌታሁን እንደሳቸው እድል ሳያገኙ በግል ሆስፒታል ዲያሊሲስ እየተሰሩ ጥሪታቸውን የሚጨርሱ ሰዎች በጣም እንደሚያሳዝኗቸው የመንግሥት ሆስፒታሎች የችግሩን አሳሳቢነት ተረድተው አገልግሎቱን ለሁሉም ተደራሽ ማድረግ ቢችሉ በማለት ይጠይቃሉ።
አሁን ”በምኒልክ ሆስፒታል አዲስ የኩላሊት ህክምና ማዕከል ተከፈተ” ሲባል ሰምቻለሁ ያሉት አቶ ጌታሁን ይህ ሁኔታ ምንም እንኳን እሳቸውን የሚጠቅማቸው ባይመስላቸውም ለሌሎች፤ በተለይም ለወጣቶች ትልቅ ችግር ፈቺ እንደሚሆን ተናግረዋል።
የኩላሊት እጥበት ተጠቃሚዎች በመድሃኒት ዋጋ ንረት እንዲሁም በግል የህክምና ተቋማት የተጋነነ ዋጋ ለችግር እየተጋለጡ መሆኑን የተረዳው መንግሥትም፤ በመንግሥት ሆስፒታሎች ይሰጥ የነበረውን የኩላሊት እጥበት አገልግሎት በአምስት እጥፍ የሚያሳድግና ለታካሚዎች ትልቅ እፎይታን የሚሰጥ ”የኩላሊት እጥበት ማዕከል” በዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል አሰርቶ፤ ባሳለፍነው ሳምንት አስመርቋል።
ማዕከሉ በተመረቀበት ጊዜም የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ እንዳሉት የአዲስ አበባ ከተማ ካቢኔ አባላት እንደ አዲስ ሲዋቀሩ ከተሰጣቸው ኃላፊነቶች መካከል አንዱ፤ በተለይም ተላላፊ ባልሆኑ እንደ ኩላሊት ባሉ ህመሞች የሚሰቃዩ፣ ገቢያቸው አነስተኛ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተደራሽ የሚያደርጉ ሥራዎችን መስራት ነው።
የኩላሊት በሽታ ከእለት እለት ቁጥሩ እየጨመረ መምጣቱን የተናገሩት ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ የኩላሊት እጥበት ህክምናውም በተለይም ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው ሰዎች ላይ የሚያደርሰውን ጫና ለመቀነስ የከተማ አስተዳደሩ ባለፉት ሁለት ዓመታት ድጎማ ሲያደርግ መቆየቱን ተናግረዋል።
አገልግሎቱ በሶስት የመንግሥት ተቋማትና የግል ሆስፒታሎች እየተሰጠ ያለ ቢሆንም፤ አገልግሎቱ በቂ ባለመሆኑ የዚህ ማዕከል መከፈት በከተማዋ ሲሰጥ የቆየውን የኩላሊት እጥበት ህክምና በአምስት እጥፍ የሚያሳድገው መሆኑን ተናግረዋል።
ከተማ አስተዳደሩ የችግሩን አሳሳቢነት ተረድቶ ማዕከሉን የገነባ ሲሆን፤ ተቀማጭነቱን አሜሪካን አገር ያደረገው የአብ ሜዲካል ሴንተር ደግሞ 30 የኩላሊት ማጠቢያ ማሽኖችን ከነአስፈላጊ ግብዓቶቻቸው አምጥቶ በመግጠም አገልግሎቱ በፊት ከነበረበት ወደ ላቀ ደረጃ እንዲደርስ አድርጓል ነበር ያሉት። በቀጣይም ህንጻው የኩላሊት ንቅለ ተከላን በሚያሟላ መልኩ እንደሚዘጋጅም ጨምረው ተናግረዋል።
ይህ ይበል የሚያሰኝ የታማሚዎችን ብቻ ሳይሆን የቤተሰባቸውንም ተስፋ የሚያለመልም ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት። ቃል በተገባው መሰረትም ማዕከሉ ከእጥበት ባሻገር ንቅለ ተከላውንም እንዲያከናውን ይደረጋል የሚል እምነትም አለን።
እፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን ግንቦት 27/2014