‹‹ካያያዝ ይቀደዳል ካነጋገር ይፈረዳል›› ይላል የአገሬ ሰው። አንዳንድ ጊዜ እንዳመጣልን የምንናገረው፤ እንዳሻን የምንመነዝረው ነገር ከጊዜ በኋላ ሊያመጣ የሚችለውን ውጤት መገመት ይሳነናል።
ትዝ ይለኛል፤ የአሸባሪው ሕወሓት የስልጣን ዘመን እንዳበቃ በርካቶች በመገናኛ ብዙሃን እየወጡ ቡድኑን እየኮነኑ ራሳቸውን እንደፃድቅ መቁጥር ጀምረው ነበር። በሂደት ደግሞ የለውጥ ሃዋርያ ነን ሲሉም ተሰምተዋል፤ እኛም እስቲ ይሁን አልን። ታዲያ እነዚህ አካላት ከጥቂት ጊዜ በኋላ ለውጡ እኛ እንደፈለግነው አልሄደም ብለው በጥቂት ወራት ውስጥ ማኩረፍ ጀመሩ። እንደ ጨቅላ ህፃን አባብሉን፤ ዳይፐር በየደቂቃው ቀይሩልን ማለቱን ተያያዙት። ሕወሓት ጨቋኝ ነው ሲሉ ቆይተው ከእሱ በላይ ጨቋኝና አረመኔ መሆን ፈለጉ።
ነፃ እናወጣለን ብለው ጭራሽ ነፃነት ቃሉ ጠፋቸው። በየመንደሩ መተናኮልና ከመንግስት ጋር እሰጣ ገባ ጀመሩ። ትጥቅ ፍቱ ሲባሉ ‹‹ፈቺ ማነው አስፈቺውስ?›› ብለው ደረታቸውን ነፍተው የፀጥታ ችግር ሆኑ። ውል አልባ ፖለቲካቸውን መሰብሰብ አቅቷቸው ህዝብን ለከፋ ችግር መዳረግ ጀመሩ። ለዚህም ለአብነት ያህል ሸኔን፣ የቤንሻንጉል ነፃ አውጪ ግንባርን፣ የቅማንት ኮሚቴ የመሳሰሉትን መጥቀስ ይቻላል።
የጠራ ፖለቲካ ፍልስፍና እና አካሄድ ሳይኖራቸው አሸባሪውን ሕወሓት እየጠሉ ራሳቸው በሚፈጥሩት ሴራ እና ተንኮል ከሕወሓት በላይ የሚጠሉና አስነዋሪ ሆነው አረፉ። አገር ጭንቅ ላይ በሆነችበት ሰዓት መንግስትን ለመጣል ከሥር መገዝገዝ ከኋላ መውጋት ጀመሩ። ጭራሽ ሸኔ ከሕወሓት ጋር በመሆን ማዕከላዊ መንግስትን እየወጋ ስለመሆኑ የጃል መሮ የስልክ መረጃ ልውውጥ ይፋ ሆነ። ሌሎችም ጫካው ጥራኝ ብለው ለውጥ አመጣልን ያሉትን መንግስት ላይ ቃታ መሳብ ጀመሩ።
ቆመ ጠብቀኝ የጦር መሳሪያ እና ቆመህ ጠብቀኝ በሆነ የፖለቲካ አካሄድ በብዙ መንገድ የተጠናከረውን መንግስት እንገረስሳለን አሉ። ከዚህ መረዳት የሚቻለው ነገር ቢኖር ፍላጎታቸው ከባድ ነው። እነዚህ አካላት ለቀቅ ቢደረጉ እንኳን ህዝብን ከህዝብ እያጫረሱ ኢትዮጵያን በመበታተን ለግብፅ እና የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ተላላኪነታቸውን የሚመሰክሩ እንጂ ምንም የሚፈይዱ አይሆኑም።
ታዲያ የኢትዮጵያ ህዝብ እውነታውን በመረዳት በአሁኑ ወቅት አንቅሮ እየተፋቸው ነው። በተገኙበት እርምጃ እየወሰደባቸውም ይገኛል። ይህ የሚያሳየው ይህ ቆሞ ቀር የሆነ የፖለቲካ እሳቤያቸው የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በዚህ አገር ላይ ዋጋ አልባ ስለመሆኑ ነው።
ይሁንና እነዚህን ፀረ-ሰላም ሃይሎችን እንቅስቃሴ ለመግታትና ሁኔታዎችን ለማስተካከል በሚደረገው ጥረት ብዙ ፈተናዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ ማሰብ ባይከብድም አሮጌ አስተሳሰባቸው ተቀብሮ አዲስ የፖለቲካ እሳቤ በኢትዮጵያ ሰማይ ስር መድመቁ አይቀሬ ነው።
በእርግጥ አዲስ የፖለቲካ እሳቤን አገራዊ መሰረት ማስያዝ በአንዲት ጀንበር የሚሆን አይደለም። ሂደት ይፈልጋል፤ የህዝብን ተሳትፎ ይፈልጋል፤ መስዋዕትነት ይፈልጋል። ለዚህ ደግሞ እራስን በተገቢው መንገድ ማዘጋጀት ወሳኝ ነው።
አሁነኛው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚያስፈልገው ነው። እንደቀደሙት ዘመናት የሽግግር ወቅቶች በኪሳራ እንዳይጠናቀቅ መጠንቀቅ ያስፈልጋል። በብዙ ጥቅም የተሳሰሩ የፖለቲካ ሐይሎች በአገራዊ ፖለቲካ መድረኩ ላይ አሉ አንዱ ሲነካ ሌላው ኡኡታውን ያስነካዋል። ከአገር ውስጥ እስከ ውጭ ድረስ በጥቅም የተሳሰሩ አካላት ለኢትዮጵያ ተቆርቋሪ መስለው ይጮኻሉ።
በአንድ ወቅት የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በፓርላማ መደበኛ ስብሰባ ላይ በጣም ያረጁ ተሽከርካሪዎች ለምን ከመንገድ ላይ በፍጥነት ዘወር አይደረጉም የሚል ይዘት ያለው ጥያቄ እንደቀረበላቸው አስታውሳለሁ። ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚመጡ ጎብኚዎችን በየመንገዱ እየተገተሩ የሚያስተናግዱ 30 እና 40 ዓመታትን ያሳለፉ ላዳ መኪናዎችን ከመንገድ ይወገዱልን ለሚለው የህዝብ እንደራሴዎች ጥያቄ እንዲህ የሚል ምላሽ ሰጥተው ነበር።
«ችግሩ አገባቡ ላይ አይደለም አወጣጡ ላይ ነው። በየዳገቱ እያረፈ የሚሄደውን መኪናም ቢሆን ከመንገድ ውጭ ማድረግ የሚያስችል አሠራር አለ። ነገር ግን አፈፃፀሙ አስቸጋሪ ይሆናል። ምክንያቱም በዚህች መኪና ላይ የተንጠለጠለ ህልውና ያለው ቤተሰብ አለ። እናም ይህችን መኪና ከሥራ ውጭ ስናደርግ አማራጭ የሥራ ዕድል እየፈጠርን ነው ወይ የሚለውን ማየት ይኖርብናል።
ከቅደም ተከተሉ ጋር እያያዝን ነው እንጂ ዋናው ጉዳይ ከጥቅም ውጭ መሆን የሚገባቸው መኪኖች አለመኖራቸው አይደለም። ሌላው ቀርቶ የቤተመንግስት መኪኖችም በንጉሱ ዘመነ መንግስት ለአፍሪካ አንድነት ድርጅት ተብለው የተገዙ መርቸዲስ መኪኖች ናቸው እስካሁን ድረስ ጥቅም ላይ የሚውሉት። አንዳንድ ጊዜም እንግዳ እንደያዙ ዳገት ላይ ያርፋሉ። በጣም ለብዙ ዓመታት በማገልገላቸው በቱሪስት መስህብነት ደረጃ የሚመረጡ መኪኖች ናቸው። ከአገልግሎት አንፃር ግን ችግር አለባቸው። በመሆኑም እነሱን ለመተካት ሙከራ እየተደረገ ይገኛል። ነገር ግን የሌላውን ህብረተሰብ መኪና መተካት የመንግስትን መኪና የመተካት ያክል ቀላል አይደለም» ብለዋል
ውድ አንባቢያን፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰጡት ምላሻ አሮጌ መኪኖችን ስለመቀየር ለተጠየቁት ጥያቄ ነው፤ እኛ ግን አሁን እየተነጋገርን ያለነው አሮጊ የፖለቲካ አስተሳሰብን ስለመቀየር ነው። ይህ ነገሮች የቱን ያህል ውስብስብ እንደሆኑ ለማሳየት እድል የሚሰጥ ይመስለኛል። ነገሮችን በቀላሉ ማድረግና መከወን ቢቻል መንግስትም እስካሁን ባልዘገየ ነበር የሚል እምነት አለኝ።
አንዲት ተሽከርካሪ በተነካች ቁጥር የበርካቶችን ሕይወት እንደሚዳስስ ሁሉ በሽግግር ወቅት በተለይም አገር በአሁን ወቅት ባለችበት አስቸጋሪ ወቅት አንድ በወንጀል የተጠረጠረ ግለሰብ ሲታሰርም የታሳሪውን መታሰረ የፖለቲካ መቆመሪያ ለማድረግ የሚጮሁ ድምጾችን ብዛትና የጩኸቱን ከፍታ መገመት አያዳግትም።
መንግስት ይህን እውነታ ታሳቢ በማድረግ አንዳንዶችን በሆደ ሰፊነት ለማለፍ እየተገደደ ይመስለኛል። አንዳንዶቹን ደግሞ በሂደት ከጥፋታቸው ይማራሉ አሊያም ሕይወት ያስተምራቸዋል ከሚል እሳቤ በዝምታ ሊያልፋቸው እንደወሰነ ይሰማኛል።
በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ እንደተናገሩት፤ በመታሰር መጀገን የሚፈልጉ በርካታ አካላት እና ግለሰቦች እንዳሉ መታዘብ ጀምረናል። በወንጀል ተጠርጥረው የነበሩ አካላት በዋስ ከተለቀቁበት ወንጀል እንኳን ነፃ ሳይባሉ በወራት ልዩነት ደግመው ወደለመዱት ቤታቸው ወይንም ማረሚያ ቤት ሲመለሱ እያየን ነው።
ይህ የሚያሳየው ጥፋትን ሆን ብሎ በመደጋገም መንግስትን እየተፈታተኑ በእስር የመጀገን የተዛነፈ የስነ ልቦና ቀውስ እየተፈጠረ መሆኑን አመላካች ነው። እንደዚህም ሆኖ ግን መንግስት ብዙ ነገሮችን በዝምታ እያለፈ ነው። በዚህ ውስጥ በግልጽ መረዳት የሚቻለው መንግስት በሂደት ይስተካከላሉ ብሎ የሚያምናቸው በርካታ ነገሮች እንዳሉ ነው።
ኢትዮጵያን ለመታደግ ሲባል ብዙ መሰዋዕትነት እየተከፈለ ባለበት ታሪካዊ ወቅት ይህ ትዕግስት ለጊዜው መንግስትን ቸልተኛ ያስብለው፤ ያስተቸው ይሆናል እንጂ ለኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ማበብ ግን የራሱ የሆነ አዎንታዊ ሚና ይኖረዋል ብዬ አምናለሁ። ከዚህም በተጨማሪ ነገሮች በሂደት እንደሚስተካከሉና ጊዜ የማይመልሰው ነገር አለመኖሩን ከመረዳት የሚመነጭ አስተዋይነት እንደሆነም እረዳለሁ።
ዶክተር ጀኔኑስ
አዲስ ዘመን ግንቦት 26/2014