ውሸት ሲደጋገም እውነት ይመስላል እንዲሉ፤ ሐሰትን በመደጋገም እና ሕብረተሰቡ ውስጥ እንዲሰርጽም እንዲራባም በማድረግ ኑሯቸውንና ሕልውናቸውን የገነቡ የአሸባሪው ሕወሓትና ግብራበሮቹ ከመቼውም በበለጠ አዲስ ስልትና ጥምረት ፈጥረው እንደ አዲስ መንቀሳቀስ ጀምረዋል። ይህ ሐሰትን የመደጋገምና ለእውነት የቀረበ አድርጎ ለማስረጽ የሚሞከር የተቀባ ሃሳብና የፈጠራ ወሬ ታዲያ፤ በወጉ ታይቶ እንዲገራ ካልተደረገ ውሎ ሲያድር በሕዝቡ ውስጥ ውዥንብር መፍጠሩ፤ በዓለም አቀፍ ማህበረሰቡም ዘንድ በድግግሞሹ ልክ ትኩረት መሳቡ አይቀሬ ነው።
ዛሬ ላይ አሸባሪው ሕወሓትና በውጭም፣ በውስጥም ያሉ መሰሎቹና ግብራበሮቹ ከእለት እለት እየተዳከመ የመጣውን ኃይላቻውን ለመጠገን፤ የሻከረ ግንኙነታቸውን ለማደስ፤ የተከዳ የጥፋት ጉዟቸውን የለዘበ በማስመሰል ወዳጅ ለማብዛት እንዲያስችላቸው የያዙት ይሄ የሃሰት መረጃና ፕሮፖጋንዳን በስፋት የማራገብ አካሄድ ነው። ይሄን ሲያደርጉ የጥፋት ዓላማቸውን ለማሳካት ያግዙኛል ያላቸውን ሁለት መንገዶችን በመያዝ ነው። አንደኛው በኢትዮጵያውያን መካከል ያልተገባ ጥርጣሬን በመፍጠር አንድነታቸውን ማላላት የሚያስችሉና የተጠኑ የፈጠራ ወሬዎችን ማባዛት ነው። ሁለተኛው፣ የዓለም አቀፉም ማህበረሰብ ትኩረት ይስቡልኛል ያሏቸውን የሰብዓዊና ሌሎች ጉዳዮች በራሳቸው መንገድ በሚያቀነባብሩት ሴራ አማካኝነት ከፍ አድርጎ ማስጮህ ላይ ያተኮሩ ናቸው።
በቅርቡም እነዚህን ሁለት ጉዳዮች በአንድ ላይ ሊያጣምርምኝ ይችላል፤ በተለይም የውጭውን ማህበረሰብ ትኩረት አገኝበታለሁ፤ ግንኙነቴንም አድስበታለሁ፤ እግረ መንገድም በውስጥ ለምሰራው ፕሮፖጋንዳና የጥፋት ዘመቻ የተሻለ ነገር ያስገኝልኛል ያለውን በ “ምርኮኛ” ስም በሺዎች የሚቆጠሩ ሲቪሎችን፣ የታገቱ የመከላከያ ሰራዊት ቤተሰቦችን፣ ሾፌሮችንና ሌሎችም የሕብረተሰብ ክፍሎች ለቅቄያለሁ የሚል አካሄድ ነው። ይሄንንም በቀይ መስቀል ኮሚቴ በኩል ያከናወነው መሆኑን የተናገረ ቢሆንም፤ የቀይ መስቀል ኮሚቴ ስለሚባለው ጉዳይ አላውቅም ማለቱ ግን የሕወሓትን የሽብር የቡድን የኖረና ያለ ውሸት ያጋለጠ ሆኗል።
ከሰሞኑ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት “በሃሰተኛ መረጃና ፕሮፖጋንዳ የዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ትኩረት ለመሳብ የሚደረግ ጥረት ቦታ የለውም!” ሲል ባወጣው መረጃ ይሄንኑ እውነት አረጋግጧል። በመግለጫው እንደተመላከተው፤ አሸባሪው የሕወሓት ቡድን ትክክለኛ ማንነቱን የዓለም ህዝብ እየተመለከተው መምጣቱንና በሃሰት ፕሮፖጋንዳ አሰልፎት የነበረው ድጋፍም መቀዛቀዙን ተከትሎ የዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ልብ እገዛበታለሁ ያለውን የ“ምርኮኞችን” ለቀቅሁ በማለት አጀንዳ ለማድረግ እየሞከረ ነው።
የወራሪነት፤ የአጥፊነትና የአገር አፍራሽ ትክክለኛ ገጽታውን ለመሸፈንና ሰላም ፈላጊ መስሎ ለመቅረብ የሚያደርገው መፍጨርጨር አንዱ መገለጫ ይህ ምርኮኞችን ለቀቅኩ የሚለው የሃሰት ትርክቱ ነው። የሽብር ቡድኑ የዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ለማደናገር ከዚህም በፊት የሃሰት መረጃዎችን በማቀነባበርና ተባባሪ ሃይሎችን እያሰለፈ የሴራው አካል ሲያደረግ መቆየቱ የሚታወስ ነው።
የሕወሓት የሽብር ቡድን የአማራና አፋር አካባቢዎችን በሃይል ወረራ ስር አድርጎ በቆየባቸው ወቅቶች በግዳጅ ይዞ ኢሰብዓዊ ተግባራትን ሲፈጽምባቸው የነበሩ ሰዎችንና ለራሱ ፕሮፖጋንዳ ፍጆታ ለማዋል ምርኮኛ በማለት የአገር ውስጥም ሆነ ዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ለማጭበርበር እየሞከረ ነው።
መንግስት ጉዳዩን አስመልክቶ እያደረገ ባለው ማጣራት በሽብር ቡድኑ ምርኮኞች ናቸው ተብለው የተለቀቁት አብዛኞቹ ዜጎች የመከላከያ ሰራዊት ከትግራይ ክልል ለቆ በወጣበት ወቅት በሽብር ቡድኑ ታግተው የቀሩ የሰራዊቱ ቤተሰብ አባላት መሆናቸው ታውቋል። በሌላ በኩል ከልዩ ልዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ለስራ ትግራይ ክልል ውስጥ ይኖሩ የነበሩ ሲቪል ነዋሪዎችን አግቶ የቆየው የሽብር ቡድኑ፤ አሁን የፖለቲካ ትርፍ አገኝበታለሁ ባለው የፕሮፖጋንዳ ድራማ የመከላከያንና የተለያዩ ጸጥታ ሃይሎችን መለዮ በማልበስ በምርኮኛ ስም አሰልፏቸዋል።
የሕወሓት ሽብር ቡድን ከሰሞኑ የጦርነት ክተት እያወጀና በይፋም እየተዘጋጀ መሆኑን ማስታወቁን ተከትሎ ያለችውን እንጥፍጣፊ ስንቅ ወደ ጦርነት ለማዞርና ለዳግም ጥፋት ራሱን እያዘጋጀ ለመሆኑ የአሁኑ ድርጊቱ ሁነኛ ማሳያ ነው። የዚህ እኩይ ሽብር ቡድን ተባባሪ የሆኑና በተለያዩ አካባቢዎች የሚንቀሳቀሱ እንደ ሸኔና ሌሎችም ታጣቂ ጽንፈኛ ቡድኖች የዚህ ፕሮፖጋንዳ ተባባሪዎች ናቸው።
ጉዳዩን አስመልክቶም የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን በመግለጫው እንዳለው፤ የሕወሓት የሽብር ቡድን ከእነዚህ ጽንፈኛ ቡድኖች አባላትን በመመልመልና በማሰባሰብ ከሸኔ የሽብር ቡድን ጋር በጋራ ሲያሰለጥናቸው የነበሩ ሰርጎ ገብ ሃይሎችንም በምርኮኛ ስም አደራጅቶ የእኩይ ተልእኮው ማስፈጸሚያና መረጃ መቀበያ ለማድረግ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን በመንግስት በኩል የተደረገው ማጣራት አመልክቷል። በመሆኑም መላው ህዝብም ከዚህ ቀደም በሽብር ቡድኑ የሚነዙትን ሃሰተኛ ወሬዎች አላማና የሕወሓትን የአጥፊነት ተልዕኮ በማስታወስ አሁንም የሚያሰራጫቸው ወሬዎች የጥፋት ተልእኮውን ለማስፈጸም የሚጠቀምባቸው መሆኑን ሊገነዘብ ይገባል።
ከመንግስት ኮሙዩኒኬሽን መግለጫም ሆነ ከሕወሓት የሽብር ቡድን እና መሰሎቹ አሁናዊ እንቅስቃሴ መረዳት የሚቻለው፤ ቡድኑ አሁን ላይ ክፉኛ እየተገፋና በሕዝቡ ውስጥም በሚፈጽማቸው አፈናና በሚፈጥራቸው የከፉ ሰብዓዊ ቀውሶች ምክንያት ቅቡልነቱ እየከሰመ፤ በውስጥም በውጭም ጫና እየበረታበት በመጣ ጊዜ፤ ሌላ የማደናገሪያና ትኩረት መሳቢያ የሃሰት ፕሮፖጋንዳ ዘመቻዎችን መፍጠር ላይ መጠመዱን ነው። ይህ ደግሞ የቡድኑ የኖረ ባሕሪ፤ ዛሬም በዛው መንገድ ተጉዞ ሕዝቦችን ለመከፋፈልና ዓለም አቀፍ ድጋፍ በማግኘት በኢትዮጵያ ላይ ዳግም ጫና እንዲያሳድሩ ለማድረግ የወጠነው ሴራ ነው።
ምንም እንኳን ይሄን መሰል አካሄዱ የኖረና የተለመደ ቢሆንም፤ በወጉ ተገንዝቦ ትክክለኛውን መረጃ ማውጣትና ለሕዝቡም ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብም ማስረዳት ካልተቻለ የራሱ የሆነ ተጽዕኖ መፍጠሩ አይቀርም። በተለይ ሕዝቡ በዚህ ተደጋግሞ የሚነገርና የሚራባ ሃሰተኛ ወሬና ፕሮፖጋንዳ እንዳይደናገር ተገቢውን መረጃ መስጠት፤ ሃሰቱን በእውነት አስደግፎ ማጋለጥና ማስረዳት ተገቢ ነው። ይህ ሲሆን ደግሞ ሕዝብ በራሱም ከመደናገር ይወጣል፤ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብም የማስረዳትና የማሳወቅ ሚናውን በመወጣት ከሚፈጠረው ጫና፤ ከሚመጣው አደጋ ራሱንም አገሩንም መታደግ የሚችልበትን አቅም ይፈጥራል። ይህ እንዲሆን ደግሞ በሽብር ቡድኖች የሃሰት ፕሮፖጋንዳዎች ከመደናገር ወጥተን በእውነት ላይ የተመሰረተ መረጃን መቀባበል፤ በአንድ ቆመንም መታገል የሁሉም ኃላፊነት መሆኑን መገንዘብ ይገባል።
በየኔነው ስሻው
አዲስ ዘመን ግንቦት 24/2014