
-በኢትዮጵያ በዓመት ከ17 ሺ በላይ ዜጐች በትምባሆ ጭስ ህይወታቸውን ያጣሉ
አዲስ አበባ:- አዲስ አበባ ከተማን ከትምባሆ ጭስ ነጻ ለማድረግ የሚያስችል የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሐግብር ተጀመረ። በኢትዮጵያ በዓመት ከ17 ሺ በላይ ዜጐች በትምባሆ ጭስ ህይወታቸውን እንደሚያጡ ተገለጸ።
በዓለም ለ35ኛ በኢትዮጵያ ለ30ኛ ጊዜ “የጸረ ትምባሆ ቀን ለእኛና ለምድራችን ስጋት ነው” በሚል መሪ ቃል በአዲስ አበባ ትናንት ተከብሯል።
በአዲስ አበባ ሁሉም ክፍለ ከተሞች የተሳተፉበት አዲስ አበባን ከትምባሆ ነጻ የማድረግ የግንዛቤ ማስጨበጫ የንቅናቄ ሥራ ተጀምሯል።
የጸረ ትምባሆ ቀን ትናንት በተከበረበት ወቅት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የምግብ፣ የመድሃኒት፣ የጤና እንክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ትግስት በዳዳ ቀኑን አስመልክቶ እንደገለጹት፤ የትምባሆ ጭስ በሰው ሕይወት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ነው።
ትምባሆ በሰው ልጆች ላይ እያደረሰ ያለው የጤና ጉዳት አሳሳቢ በመሆኑ ለህብረተሰቡ የግንዛቤ ማስጨበጫ ለመስጠት አላማ ያደረገ ነው ያሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሯ፣ የትምባሆ ጭስ ከሌሎች በሽታዎች በበለጠ በሰው ጤና ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያስከተለ ነው። በዓለም በዓመት ስምንት ሚሊዮን ገደማ ሰዎች በትምባሆ ጭስና በእነሱ ምክንያት በተዘዋዋሪ ስምንት ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች ህይወታቸው ያልፋል ብለዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የምግብ፣ የመድኃኒት፣ የጤና እንክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 1112/2011 በወጣው አዋጅ መሰረት የትምባሆ ምርት የጤና ማስጠንቀቂያና ገላጭ ፅሁፍ ቁጥር 45/2012 ህገ ወጥ የትምባሆ ንግድ ቁጥጥር ማስወገድ ፕሮቶኮል ለመፈረምና ለማጽደቅ ሂደት ላይ ነው። ህብረተሰቡ ራሱን ከትምባሆ ጭስ መጠበቅ አለበት፣ እኔ አላጨስም ብሎ በዝምታ መመልከት ብቻ ሳይሆን በያገባኛል ስሜት መካከል ያስፈልጋል ብለዋል።
የትምባሆን ጭስ ለመከላከል ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ምክትል ዳይሬክተሯ፤ በሕዝብ መዝናኛዎች፣ ሆቴሎች ላይ በሚያጨሱ አካላት ላይ እርምጃ እየተወሰደ ነው። ሁሉም ህብረተሰብ የትምባሆን ጭስ ለማስቆም 9864 ነጻ የስልክ መስመር በመደወል ጥቆማ ማድረስ መቻል እንዳለበት አሳስበዋል።
እንደ ወይዘሮ ትግስት ገለጻ፤ ባለስልጣኑ ከሚሰራቸው ተግባራት መካከል አንዱ የትምባሆንና አደንዛዥ ዕጽን ከመከላከልና ከመቆጣጠር አንጻር አዲስ አበባ ከተማን ከትምባሆ ጭስ ነጻ የማድረግ ሥራ ተቀርጾ እየተሰራ ነው። የዓለም አቀፍ የጸረ ትምባሆ ቀንን ምክንያት በማድረግ ትምህርታዊ የቅስቀሳ ሥራ ከተለያዩ አጋር አካላት ጋር በመተባበር በከተማዋ አምስት የሚደርሱ ክላስተሮችን መሰረት ያደረገ የሶስት ቀን የጸረ ትምባሆና ሱስ ትምህርታዊ ቅስቀሳና የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርታዊ ቅስቀሳ መካሄድ ጀምሯል።
ሞገስ ተስፋ
አዲስ ዘመን ግንቦት 24/2014