
ምክትል ፕሬዚደንቷ ይህንን ተማጽኗቸውን ያቀረቡት በአገሪቷ በርካቶች የተገደሉበት ሁለት የጅምላ ጥቃቶች መፈፀማቸውን ተከትሎ ነው።
ካማላ፣ ከአስራ አምስት ቀን በፊት በቡፋሎ በሚገኝ የገበያ ማዕከል የተገደሉት የ86 ዓመቷ ሩት ዋይት ፊልድ የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ ተገኝተው ነበር።
ይህ ጥቃት የተፈፀመው 19 ህጻናት እና ሁለት መምህራን ከተገደሉበትና በቴክሳስ ግዛት በሚገኝ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ከተፈፀመው ጥቃት አስር ቀናት በፊት ነው።
ካማላ ይህንን እና ሌሎች በአገሪቷ የተፈፀሙ ጥቃቶችን ጠቅሰው እየደረሰ ላለው የመሣሪያ ጥቃት “ይበቃል!” ለማለት ጊዜው አሁን ነው ብለዋል።
“ይህ በአገራችን መከሰት እንደሌለበትና አንድ ነገር ለማድረግ ጽናት ሊኖረን እንደሚገባ ሁሉም ሰው መስማማት እና በአንድ ላይ መቆም ይኖርበታል” ሲሉም በቀብር ሥነ ሥርዓቱ ላይ ለተገኙ ሰዎች ተናግረዋል።
ካማላ “መፍትሔው ግልጽ ነው። መፍትሔው የኋላ ታሪክን ማጥናትና የጥቃት መሣሪያዎችን ማገድን ያካትታል” ሲሉም አክለዋል።
“የጥቃት መሣሪያዎች ምን እንደሆነ ታውቃላችሁ?” ሲሉ በመጠየቅም “ እነዚህ መሣሪያዎች የተሰሩት ለውስን ዓላማ ነው። ይህም በፍጥነት በርካታ ሰዎችን ለመግደል። የጥቃት መሣሪያዎች የጦር መሣሪያ ናቸው። በመሆኑም ባልታጠቀ ሰላማዊ ማኅበረሰብ ዘንድ ቦታ የላቸውም” ሲሉም አብራርተዋል።
በአሜሪካዋ ቴክሳስ ግዛት፣ ኡቫልዴ ከተማ፣ ማክሰኞ ዕለት በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ በተፈፀመው ጥቃት ድርጊቱን የፈፀመው የ18 ዓመቱ ወጣት ሁለት ኤአር-15 በከፊል አውቶማቲክ የሆነ ጠመንጃ የነበረው ሲሆን አንደኛው ከልደቱ በኋላ እንደተገዛ ተዘግቧል።
ወጣቱ በጥይት ተመትቶ ከተገደለ በኋላ ፖሊስ እስከ 1 ሺህ 657 የሚደርሱ ጥይቶችን እና 60 መጽሔቶችን በእጁ አግኝቷል።
በኒው ዮርክ፣ ቡፋሎ ከተማ ጥቃት የፈፀመው ሌላኛው የ18 ዓመት ወጣት ቀደም ብሎ ከባለሥልጣናት ጋር ተገናኝቶ የነበረ ሲሆን የራሱን ኤአር-15 ዓይነት መሣሪያ በሕጋዊ መንገድ ሲገዛ ማንም አላስጠነቀቀውም ነበር።
“አንድ ሰው ቢያንስ ምንም ነገር ሳያውቅ እንዴት ነው ሌሎች ሰዎችን የሚገድል መሣሪያ ሊገዛ የሚችለው? ያ ሰው ከዚህ በፊት ሌላ ወንጀል ሰርቶ ያውቃል? ለራሳቸውም ሆነ ለሌሎች ሰዎች ስጋት ናቸው? ያ ምክንያታዊ ነው” ብለዋል ካማላ ሃሪስ ቅዳሜ ዕለት ባደረጉት ንግግር።
ሆኖም ሁለንተናዊ የሆነ የጀርባ ጥናት የማካሄድ እና የጥቃት መሣሪያዎች ላይ እገዳ የመጣል ሙከራው እንቅፋት አጋጥሞታል። ጉዳዩ በአሜሪካ ከፋፋይ ነው። ሁሉም ዲሞክራቶች በሚባል ደረጃ በዚህ ላይ ጥብቅ ቁጥጥር እንዲደረግ የሚደግፉ ሲሆን ይህንን ሃሳብ የሚጋሩት ሪፐብሊካኖች ግን 24 በመቶ ብቻ ናቸው።
ተፅዕኖ ፈጣሪው ብሔራዊው የጠመንጃ ማኅበር (ኤንአርኤ) በጠመንጃ ፖሊሲ ጉዳይ የምክር ቤት አባላቱ ላይ ተፅዕኖ ለማድረግ ከፍተኛ በጀቱን ይጠቀማል።
ዓርብ ዕለት የቀድሞ የሪፐብሊካን ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ የመሣሪያ ጥብቅ ቁጥጥር ሳይሆን ትምህርት ቤቶች የተሻለ ጥበቃ እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል።
በብሔራዊ የጠመንጃ ማኅበሩ ስብሰባ ላይ የተናገሩት የቀድሞ ፕሬዚደንቱ፣ ሰላማዊ አሜሪካውያን ራሳቸውን ከአደጋ ለመጠበቅ የጦር መሣሪያ ሊፈቀድላቸው ይገባልም ብለዋል።
በዚያው ዕለት ጥቃት በተፈፀመበት ቴክሳስ ግዛት ፣ ኡቫልዴ በሚገኘው ትምህርት ቤት ውስጥ ሌላ መሣሪያ የሚተኩስ ሰው በመኖሩ ፖሊስ ወደ መማሪያ ክፍል ውስጥ እንዳልገባ ታውቋል።
በምትኩ ህጻናት እርዳታ እንዲደረግላቸው የድንገተኛ ጊዜ አገልግሎትን ሲማጸኑ 40 ደቂቃዎችን ለመጠበቅ ተገደዋል።
ፖሊስ አሁን ወደ ክፍሎቹ ላለመግባት የወሰነው ውሳኔው ስህተት መሆኑን አምኗል።
የአሜሪካው ፕሬዚደንት ጆ ባይደን እሁድ ዕለት ኡቫልዴን በሚጎበኙበት ወቅት ጥብቅ የሆነ የመሣሪያ ቁጥጥር እንዲኖር ጥሪ ያቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ቅዳሜ ዕለት አሜሪካውያን በመሣሪያ ጥቃት ላይ ድምጻቸውን እንዲያሰሙ ፕሬዚደንቱ አሳስበው ነበር።
ምንጭ ቢቢሲ
አዲስ ዘመን ግንቦት 23/2014