የአውሮፓ ሀገራት በኢራን ላይ ከባድ ማዕቀቦችን እንደሚጥሉ አስጠነቀቁ

ፈረንሳይ፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና ጀርመን በኢራን ላይ ከባድ ማዕቀቦችን ሊጥሉ እንደሚችሉ አስጠንቅቀዋል። የኢራን የኒውክሌር መርሃ ግብር ድርድር እስከ ነሐሴ ወር መጨረሻ ተጨባጭ ለውጥ ካላሳየ፣ ሀገራቱ በኢራን ላይ ከባድ ማዕቀቦችን እንደሚጥሉ ዲፕሎማቶች ተናግረዋል።

የፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዦ-ኖል ባሮ ‹‹ድርድሩ ግልጽ የሆነ ለውጥ ካልታየበት እኤአ በ2015 የኒውክሌር ስምምነት መሠረት ከኢራን ተነስተውላት የነበሩ ኢኮኖሚያዊ ማዕቀቦች በሚቀጥለው ወር በድጋሚ ወደ ቀድሞ ቦታቸው ሊመለሱ ይችላሉ›› ብለዋል።

ፈረንሳይና አጋሮቿ ከ10 ዓመታት በፊት ተነስተው የነበሩት የጦር መሳሪያ፣ የፋይናንስና የኒውክሌር ቁሳቁሶች ማዕቀቦች በድጋሚ እንዲጣሉ ማሰባቸው ተገቢ እንደሆነ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል። ባሮ ‹‹ኢራን ጠንካራ፣ ተጨባጭና የሚታመን ፍላጎትና ተግባር ከሌላት፣ በነሀሴ ወር መጨረሻ ላይ ማዕቀቦቹን በድጋሚ እንጥላለን›› ነው ያሉት።

ሀገራቱ የማስጠንቀቂያ ቀነ ገደብ ይፋ ያደረጉት ለኢራን የኒውክሌር መርሃ ግብር አዲስ መፍትሔ እንዲፈለግ የሚጠይቁ ድምፆች ከየአቅጣጫው እየተሰሙ ባሉበት እና እስራኤልና አሜሪካ በኢራን የኒውክሌር ተቋማት ላይ ጥቃት ፈጽመው ጉዳዩ ዓለም አቀፍ መነጋገሪያ በሆነበት ወቅት ነው።

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጀርመን፣ የዩናይትድ ኪንግደምና የፈረንሳይ አምባሳደሮች በኢራን ላይ ማዕቀቦቹን መልሶ ስለመጣል ተወያይተው እንደነበር ‹‹አሶሺየትድ ፕሬስ›› (The Associated Press) ዘግቧል። ከእዚህ በተጨማሪም የሦስቱ ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ከአሜሪካው አቻቸው ማርኮ ሩቢዮ ጋር ስለጉዳዩ በስልክ ተወያይተዋል።

የፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዦ-ኖል ባሮ ባለፈው መጋቢት ወር ለሀገሪቱ ፓርላማ ባደረጉት ንግግር፣ ሰላማዊ ድርድሮች ካልተሳኩ ወታደራዊ ርምጃዎች መታየታቸው እንደማይቀር ስጋታቸውን ገልጸው እንደነበር ይታወሳል።

‹‹ኢራን ፈጽሞ የኑክሌር ጦር መሣሪያ ባለቤት መሆን የለባትም፤ከኢራን ጋር የሚደረጉ የዲፕሎማሲ አማራጮች የመሳካታቸው እድል ጠባብ ሆኖ ቆይቷል›› ብለው ነበር።

በመንግሥታቱ ድርጅት የኢራን ተወካዮች እስካሁን ስለጉዳዩ ያሉት ነገር ባይኖርም፣ የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ ከቀናት በፊት በሰጡት ማብራሪያ፤ ማዕቀቦቹን ለመመለስ ማሰብ የአውሮፓ ኅብረት በኢራን የኒውክሌር መርሃ ግብር ድርድር ውስጥ ያለው ሚና እንዲያከትም እንደሚያደርገው አስጠንቅቀዋል።

የእስራኤልና የአሜሪካ ጥቃት ለጉዳዩ መፍትሔ ለማግኘት የሚደረገውን ጥረት በእጅጉ አስቸጋሪ እንዳደረገው የጠቆሙት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፤ አሜሪካ በኢራን ላይ በድጋሚ ጥቃት እንደማይሰነዘር አስተማማኝ ዋስትና መስጠት ከቻለች፣ ቴህራን ከዋሺንግተን ጋር የምታደርገውን የኒውክሌር ድርድር ለመቀጠል ዝግጁ እንደሆነችም ተናግረዋል።

የኢራን ፓርላም ቅድመ ሁኔታዎች እስኪሟሉ ድረስ ኢራን ከአሜሪካ ጋር የምታደርገውን ድርድር መቀጠል እንደሌለባት አሳስቧል። ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕና የመካከለኛው ምሥራቅ መልዕክተኛቸው ስቲቭ ዊትኮፍ ደግሞ ከኢራን ጋር የሚደረገው ንግግር በቅርቡ እንደሚጀመር ገልጸዋል።

ቻይና በበኩሏ፣ ኢራን ሉዓላዊነቷንና ብሔራዊ ክብሯን ለማስጠበቅ ለምታደርገው ትግል የምትሰጠውን ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥል ገልጻለች። የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ ለኢራኑ አቻቸው አባስ አራግቺ ‹‹ቻይና ኢራን የያዘቸውን የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ያለማምረት እንዲሁም የኒውክሌር ኃይልን ለሰላማዊ የኃይል ማመንጫ የመጠቀም ዓላማና ቁርጠኛነት ያለውን ፋይዳ ትገነዘባለች›› ብለው እንደነገሯቸው የመሥሪያ ቤታቸው መግለጫ አመልክቷል።

በ2015 ስምምነት መሠረት ኢራን የኒውክሌር ፕሮግራሟ ክትትል እንዲደረግበት እና ዩራኒየም ማበልጸጓን ለመገደብ በመስማማቷ፣ ተጥለውባት ከነበሩ የምጣኔ ሀብት ማዕቀቦች መካከል አንዳንዶቹ ተነስተውላታል። በስምምነቱ ላይ እንደተጠቀሰው፣ ቴህራን የሚጠበቅባትን ካልፈጸመች፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከተጣሉባት በኋላ በስምምነቱ መሠረት ተነስተውላት የነበሩ ማዕቀቦች በድጋመ ሊጣሉባት ይችላሉ።

ኢራን እ.አ.አ በ2015 ከስድስት ኃያላን ሀገራት (አሜሪካ፣ ቻይና፣ ሩሲያ፣ ጀርመን፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና ፈረንሳይ) ጋር የኒውክሌር ስምምነት (Joint Comprehensive Plan of Action) መፈራረሟ ይታወሳል።

ስምምነቱ ኢራን የኑክሌር ጦር መሳሪያ ግንባታዋን እንድታቆምና በምላሹም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ በአውሮፓ ኅብረትና በአሜሪካ የተጣሉባት ማዕቀቦች እንዲነሱላት ይደነግጋል።

ኢራን ስምምነቱን የማታከብር ከሆነም ቀደም ባሉት ጊዜያት ከተጣሉባት ማዕቀቦች የከፉ ፖለቲካዊና ምጣኔ ሀብታዊ ተፅዕኖ ያላቸው ማዕቀቦች እንደሚጣሉባት፤ ከእዚያም አልፎ ጉዳዩ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት እንደሚቀርብ በስምምነቱ ድንጋጌዎች ውስጥ ተጠቅሷል።

ከስምምነቱ መፈረም በኋላም ኢራን የስምምነቱን ድንጋጌዎች ተቀብላ አንዳንድ ርምጃዎችን ወስዳ ነበር። ከእነዚህም መካከል በናታንዝ እና ፎርዶው ጣቢያዎች የሚገኙ ግብዓቶች እንዲወገዱ መደረጉ፤ በብዙ ቶን የሚቆጠር ዩራኒየም ወደ ሩሲያ መወሰዱ እና የዓለም አቀፉ አቶሚክ ኃይል ኤጀንሲ ባለሙያዎች የኢራንን የኑክሌር መሳሪያ ግንባታ በየጣቢያዎቹ ተገኝተው መመልከታቸው ይጠቀሳሉ።

ስምምነቱ ሲፈረም አሜሪካንን ሲያስተዳድሩ የነበሩት የወቅቱ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ስምምነቱ እንደትልቅ ዲፕሎማሲያዊ ድል ተቆጥሮላቸዋል። ኦባማን ተክተው ወደ ነጩ ቤት የመጡት ቢሊየነሩ ዶናልድ ትራምፕ ግን ስምምነቱን መቀበል ይቅርና ስለስምምነቱ መስማት አይፈልጉም።

ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ‹‹የምንጊዜውም መጥፎው ስምምነት›› እያሉ የሚያብጠለጥሉትን ይህን ስምምነት እንደሚሰርዙት ያስታወቁት ገና በፕሬዚዳንታዊ የምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት ነበር። ሥልጣን እንደያዙም አሜሪካንን ከስምምነቱ አስወጥተዋታል።

ትራምፕ ስምምነቱ ኢራንን ለተወሰኑ ጊዜያት ብቻ ከኒውክሌር ማበልጸግ ተግባሯ የሚገታ እንጂ ረጅም ርቀት ተወንጫፊ ባሊስቲክ ሚሳይሎችን ከማምረት የሚያግዳት አይደለም ብለው ያምናሉ። እንዲያውም ስምምነቱ ኢራን በውጭ ሀገራት ባንኮች ያላትንና እንዳይንቀሳቀስ ታግዶባት የነበረውን በመቶ ቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር ገንዘብ እንዲለቀቅላት ስላደረገ ኢራን ገንዘቡን ሽብርተኞችን ለመደገፍ፣ የጦር መሣሪያ ለመግዛት እንዲሁም አክራሪነትን ለማስፋፋት ተጠቅማበታለች ሲሉ ይከራከራሉ።

ፕሬዚዳንት ትራምፕ የኢራን የኑክሌር ስምምነትን የማይቀበሉባቸው ምክንያቶች ብዙ እንደሆኑ በተንታኞች ዘንድ ይገለጻል። ሰውየው የአሜሪካ ጠንካራ አጋርና ወዳጅ የሆነችውን እስራኤልን ለማጥፋት እቅድ አላት የምትባለው ኢራን የኑክሌር መሣሪያ ታጥቃ ማየት አይፈልጉም።

በመጀመሪያው የሥልጣን ዘመናቸው የልጃቸው ኢቫንካ ትራምፕ ባለቤት የሆኑት አይሁዳዊው ጃሬድ ኩሽነር የፕሬዚዳንቱ ከፍተኛ አማካሪ መሆን ደግሞ ሰውየው ለኢራን ያላቸውን ጥላቻ አባብሶታል ብለው የሚናገሩም አሉ።

ፕሬዚዳንት ትራምፕ እስላማዊቷን ሪፐብሊክ አጥብቀው በመኮነን ይታወቃሉ። በመጀመሪያው የሥልጣን ዘመናቸው የኢኮኖሚ ማዕቀቦችን ጨምሮ በኢራን ላይ የተለያዩ ርምጃዎችን ወስደዋል። ለአብነት ያህል ሀገራትና ትልልቅ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ከኢራን ነዳጅ እንዳይገዙ አስጠንቅቀዋል፤የኢራንን አብዮታዊ ዘብ ከአሸባሪዎች መዝገብ አስፍረውታል፤ከባድ የጦር መሣሪያዎችን ኢራን ወደምትገኝበት ቀጣና ልከው አሠማርተዋል።

የስምምነቱ ፈራሚ የሆኑ የአውሮፓ ሀገራት (ዩናይትድ ኪንግደም፣ ጀርመንና ፈረንሳይ) ግን ኢራን የኑክሌር ጦር መሣሪያ ባለቤት እንዳትሆን ለማድረግ ስምምነቱን አክብሮ ከመቀጠል የተሻለ ሌላ አማራጭ እንደሌለ ደጋግመው ገልጸዋል። የአሁኑ የሀገራቱ የማዕቀብ ማስፈራሪያ ደግሞ ስምምነቱ አደጋ ውስጥ እንደገባ ማሳያ ተደርጎ መቅረቡ አይቀርም።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ሐሙስ ሐምሌ 10 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You