
አዲስ አበባ፡– በመዲናዋ የመንገድ ግንባታ ሥራ ላይ የወሰን ማስከበር ተፅእኖ እያሳደረበት መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መንገዶች ባለስልጣን አስታወቀ።
የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ እያሱ ሰለሞን ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደተናገሩት፣ በመዲናዋ ውስጥ ከ100 በላይ የመንገድ ግንባታ ሥራዎች ሲኖሩ በአብዛኞቹ ላይ በወሰን ማስከበር ችግር ምክንያት ግንባታውን በወቅቱ ማጠናቀቅ አልተቻለም።
የተፅዕኖ ሰለባ ከሆኑትም መንገዶች መካከል ከአውቶብስ ተራ – መሳለሚያ እስከ ኮልፌ ቀለበት፤ የቂርቆስ ማርገጃ – ቡልጋርያ፤ ከሲ.ኤም.ሲ ተነስቶ – ሰሚት መድኃኒዓለምና ሌሎችም የመንገድ ፕሮጀክቶች የወሰን ማስከበር ችግር ከፍተኛ ፈተና የሆነባቸው ናቸው።
ወሰን ማስከበር ያጓተተው እንደመኖሩ መጠንም በታለመለት የጊዜ ገደብ እየተከናወነ ያለም እንዳለ የገለጹ አቶ እያሱ፣ የፑሽኪን አደባባይ-ጎተራ ማሳለጫ 90 በመቶ በመጠናቀቁ በቅርብ ሙሉ በሙሉ ተጠናቅቆ ለትራፊክ ክፍት ይሆናል።
ባለስልጣኑ ችግሮቹን ለመፈታት ያላሰለሰ ጥረቶች እያደረገ ቢሆንም በመንገዶች ላይ የሚስተዋል የህገ ወጥ ንግድ፣ በመንገዶች ላይ የሚከማች የግንባታ እቃዎች፣ ሥራውን አጓትቶታል ሲሉ አቶ እያሱ ተናግረዋል።
በመንገድ ግንባታ ሂደት ላይ ትልቅ ማነቆ የሆነው የወሰን ማስከበር ችግር ለመፍታት ከወትሮው በተለየ መልኩ በቅርብ ክትትልና በልዩ ትኩረት በምክር ቤት ደረጀ እየተሰራ እንደሆነም አመላክተዋል።
መንገድ ተጀምሮ በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ማከናወን ካልተቻለ በኢኮኖሚ ላይ ከሚያሳድረው ጫና በዘለለ ነዋሪዎችን ለምሬትና ለእንግልት ይዳርጋል ያሉት አቶ እያሱ ፣ የተጓተቱት መንገዶችም በነዋሪዎች የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ላይ ጫና እያስከተሉ ነው ብለዋል።
በተመሳሳይም በግንባታ ላይ ያሉና የተጓተተ አፈጻጸም ካለባቸው መካከልም ከቃሊቲ- ቡልቡላ- ቂሊንጦ፤ ከአውቶብስ ተራ መሳለሚያ፤ ከቦሌ ኤርፖርት ጎሮ፤ ቦሌ ሚካኤል መሻገሪያ ድልድይ፤ ከአውግስታ ወይራ፤ ከአራራት ሆቴል ኮተቤ- ካራ፤ በኮዬ ፈቼ፤ በቦሌ አራብሳና በበሻሌ የሚገኙ የጋራ መኖሪያ መንገዶች እንደሚገኙበት ተናግረዋል።
ዳይሬክተሩ በሂደቱ የሚገጥም ችግርን ለመፍታት ሁሉም ባለድርሻ አካላት በቅንጅት እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበው፣ ተቋራጮቹም በሙሉ አቅማቸውን ሥራ ላይ ማዋል እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።
ፕሮጀክቶቹ በተያዘላቸው ጊዜ ተጠናቀው ለታለመላቸው ዓላማ እንዲውሉ በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ሥራ እየተሰራ መሆኑን ያነሱት አቶ እያሱ፣ በቀጣይም ችግሩን ለማቃለል ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር የሚያካሂደው ቅንጅታዊ አሰራር ይበልጥ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
በመንገድ ሀብት ላይ ጉዳት የሚያደርሱ ተቋማትና ግለሰቦች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ በቃልና በፅሁፍ ማስጠንቀቂያ እየተሰጠ ነው። ከድርጊታቸው ያልታረሙ ተቋማትና ግለሰቦች ላይ ህግን መሰረት ባደረገ መልኩ እርምጃ በቀጣይም ይወሰዳሉ ብለዋል አቶ እያሱ።
አቶ እያሱ በመንገድ መሠረተ ልማት ላይ የሚፈፀሙ ህገ-ወጥ ተግባራትን ለመከላከል የሚወሰደው ህጋዊ እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።
የፕሮጀክቶቹ ግንባታ ሲጠናቀቅ የትራፊክ ችግር ለማቃለልና የከተማዋን ገፅታ ለማሻሻል ከፍተኛ ፋይዳ አለው ሲሉ አቶ እያሱ ተናግረዋል ።
በሌላ በኩል በአሁኑ ወቅት በበርካታ አካባቢዎች የመንገድ ጥገና ሥራ እየተከናወነ ነው። ለአብነትም ከኢትዮ ጠቢብ ሆስፒታል – መድኃኒዓለም፤ ከኮካ – አማኑኤል፤ ከአማኑኤል – መሳለሚያ፤ ከታይዋን ዊንጌት፤ ከፖሊስ ሆስፒታል – ልደታ ወረዳ 10 ፤ ከሩዋንዳ አደባባይ – ቀለበት መንገድና ሩዋንዳ ኤምባሲ የሚወስዱ መንገዶች የሚጠቀሱ እንደሆኑ አመላክተዋል።
ሙሳ ሙሐመድ
አዲስ ዘመን ግንቦት 23/2014