ተማሪዎች ነቃ፤ እናቶች እፎይ ያሉበት – የተማሪዎች ምገባ
ድህነት ከሚፈትናቸው የዓለም አገሮች ውስጥ ኢትዮጵያ አንዷ ናት። ብዙዎች መሰረታዊ ፍላጎታቸውን ማሟላት የማይችሉበት ሁኔታ አለ። በተለይም ከመሠረታዊ ፍላጎቶች መሟላት ጋር ተያይዞ የሚያጋጥመው ችግር በቀላሉ የሚታይና የሚፈታ አይደለም። በመሆኑም አሁንም ድረስ ብዙዎች ከመሰረታዊ ፍላጎት በተለይ ምግብ ሲቸገሩ ማስተዋል የተለመደ ሆኗል። በተለይ በአሁኑ ወቅት የኑሮ ውድነቱ ሁሉንም እየፈተነ ባለበት ጊዜ በዝቅተኛ የኢኮኖሚ ደረጃ ላይ የሚገኘው ዜጋ ምግብ ፈተና ሆኖበታል። በዚያው ልክ የተመጣጠነ ምግብ ማግኘት እጅግ ከባድ ነው። ከዚሁ ጋር ተያይዞ 40 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ የመቀንጨር ችግር እንደሚያጋጥመው ጥናቶች ያመላክታሉ። የምግብ እጥረት ለሰውነትና አእምሮ መቀንጨር ብቻ ሳይሆን ለትምህርት ማቋረጥም አንዱ ምክንያት ሆኖ ቆይቷል።
ይህንኑ ውስብስብ ችግር ለመፍታት በተለያዩ አካባቢዎች የትምህርት ቤት የተማሪዎች ምገባ እንዲጀመር አስገዳጅ ምክንያት ሆኗል። የምግባ ፕሮግራሙ ከተጀመረ ጀምሮም በተለይ በተማሪዎች ላይ በትምህርት አቀባበል እንዲሁም ከትምህርት ቤት መቅረት ላይ ለውጥ እንዲያመጣ አስችሎታል። ለዚህ ምስክሮቹ የምገባ ፕሮግራሙ ተጠቃሚ ተማሪዎች ናቸው። መምህራንና ወላጆችም ይሄንን ሀሳብ የሚያጠናክሩ ናቸው። በዳግማዊ ምኒልክ አፀደ ሕጻናትና የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ተገኝተን ካነጋገርናቸው ተማሪዎች መካከል የሰባተኛ ክፍል ተማሪ ዳዊት ፍጹም አንዱ ነው። የምገባ ፕሮግራሙ በትምህርቱ ላይ ትኩረት አድርጎ እንዲያጠና እንዳደረገው ይናገራል።
ተማሪ ዳዊት እስከ ስድስተኛ ክፍል ትምህርቱን ሲከታተል በብዙ ችግር እንደነበር ያስታውሳል። በተለይም እናቱን ላለማስቸገር ምሳ ሳይቋጠርለት የሚሄድበት ጊዜ ቀላል አልነበረም። እናቱም ቢሆኑ በሰው ቤት ልብስ አጥበውና ለውዝ ሸጠው ስለሚያስተዳድሩት ሁልጊዜ ሞልቶላቸው ምሳውን ላይቋጥሩለት ይችላሉ። ምግብ ሲኖር ጎርሶ ሲያጣም ረሀቡን ችሎ እንዲማር ተገዷል። ክፍል ውስጥ ቢገባም ትምህርቱን ለመከታተል ግን ይቸገር ነበር። ስለዚህ አብዛኛውን ጊዜ የትምህርቱን ሰዓት በእንቅልፍ እንደሚያሳልፍ ያስታውሳል። ይሄ ውጤቱ ዝቅ እንዲል አድርጎታል።
‹‹እስከ ስድስተኛ ክፍል ግንፍሌ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው የተማርኩት። በደረጃ ከ20 በላይ እንጂ ከዚያ በታች ወጥቼ አላውቅም›› የሚለው ተማሪ ዳዊት፤ በእናቱ ብርታትና ከእርሱ የባሱ ሰዎችን ሲያይ እንደሚጽናና ይናገራል። ምክንያቱም በረሃብ ምክንያት ራሳቸውን ስተው የሚወድቁ፣ የተማሪዎችን ፊት ላለማየት ከክፍል የሚቀሩ ጥቂቶች እንዳልነበሩ ያስታውሳል።
‹‹የድሃ ልጅ መሆን በትምህርት ቤት ውስጥ በብዙ መልኩ ያሸማቅቃል። ይዞ ከሚመጣው ምግብና መጠን አንጻርም ብዙ ፈተና ነው።›› ያለን ተማሪ ዳዊት፤ አንድ ቀን የገጠመውንና ዘላለም የማይረሳውን ነገር ያነሳል። ጊዜው እናቱ ምሳ ያልቋጠሩለት ነበር። ነገር ግን አብሮ መብላት የተለመደ ስለነበር ያ ጉጉት አድሮበታል። ስለዚህም ከእነርሱ ጋር እመገባለሁ ብሎ አስቦ ትምህርቱን በአግባቡ ተከታትሎ ወጣ። ሆኖም ያሰበው አልሆነም።
ጓደኞቼ ችግሬን ይሸከሙልኛል የሚላቸው ተማሪዎች ምሳ ስላልያዝክ አብረኸን መብላት አትችልም አሉት። በዚህም እጅግ አዘነ። ከእረፍት በኋላ የሆነውን እያሰበ የባሰ ረሃቡ ጠናበት። በዚህም እንቅልፍ ብቻ ሳይሆን እንባም ተናነቀው። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ከጓደኞቹ ጋር መብላቱን አቋረጠ። ከተቋጠረለት ይበላል ካልተቋጠረ ደግሞ ጦሙን ውሎ ወደቤቱ ይመለሳል። ያን ጊዜ የሆነውን መቼም ማሰብ እንደማይፈልግ አጫውቶናል።
አሁን ነገሮች በመቀየራቸው ደስተኛ ብቻ ሳይሆን በውጤትም የተሻለና የደረጃ ተማሪ እንደሆነ የሚናገረው ዳዊት፤ ይህንን ሥር የሰደደ ችግር በመጠኑም ቢሆን እንደሚቀርፍ ተስፋ የተጣለበት የትምህርት ቤት ምገባ ፕሮግራም እነርሱን ብቻ ሳይሆን ቤተሰቦቻቸውንና መምህራንን እፎይ እንዳስባላቸው ያምናል። በተለይም መንግሥት ወጥ በሆነ መንገድ መተግበሩ ዝቅ ያለ ስሜት ሳይሰማቸው ከእኩዮቻቸው እኩል እንዲማሩና ውጤታማ እንዲሆኑ እንዳስቻላቸውም ያነሳል።
የትምህርት ቤት የተማሪዎች ምገባ ሰፊ ፕሮግራም እንደሆነና በተለይም ለልዩ ፍላጎት ተማሪዎች ትልቅ ሸክምን ያቀለለ እንደሆነ የሚናገሩት ደግሞ በዚሁ ትምህርት ቤት የልዩ ፍላጎት መምህር ሳራ መብራቱ ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት፤ የተማሪዎች የምገባ ፕሮግራም ችግረኛ ተማሪዎችን ለመርዳት በትምህርት ቤት ማኅበረሰቡና በተለያዩ ተቋማት ለዓመታት ሲደረግ የነበረ ነው። መምህራንም ድጋፉ አርኪ ባይሆንም ከኪሳቸው እያዋጡ የአቅማቸውን ድጋፍ ያደርጉ ነበር። አሁን ግን በመንግስት ደረጃ ድጋፍ ተደርጎ በወጥነት የምገባ ፕሮግራሙ መጀመሩ ለሁሉም እፎይታን ሰጥቷል።
መምህራኑን ከመዋጮ፤ ተማሪዎቹን ደግሞ ከመሳቀቅ አድኗቸዋል። በዚያ ላይ በትምህርት አቀባበላቸውና በውጤታቸው ጥሩ ደረጃ ላይ እንዲያርፉ እድል ፈጥሮላቸዋል። ከሁሉም በላይ እኩልነት እንዲሰማቸው አድርጓቸዋል። የተማሪዎች የምገባ ፕሮግራም ተማሪዎችን ብቻም ሳይሆን ስራ አጥ የነበሩ የተማሪዎች ወላጆችም የስራ ዕድል ተፈጥሮላቸዋል። ይሄ በብዙ መልኩ አስደሳች ስራ ነው።
‹‹የተማሪዎች ምገባ ፕሮግራም በመንግስት ደረጃ ሲጀመር ሁሉንም ተማሪ ያካተተ አልነበረም ››የሚሉት መምህርቷ፤ የፕሮግራሙ በጀት ውስን ስለነበረ እንዲመገቡ የሚደረጉት በጣም የተቸገሩትን በመለየት ነበር ። ይህ ደግሞ ተማሪዎች ላይ የሚፈጥረው ጫና ከአሁኑ አንጻር ሲነጻጸር ከባድ ነበር። ምክንያቱም ምሳ አልተቋጠረልኝም፤ አይቋጠርልኝም፤ የድሃ ድሃ ነኝ፤ ርቦኛል የሚል ልጅ ባለመኖሩ ችግረኞችን ለመለየት ይከብዳል። ሲወድቁ አለያም በተማሪዎች አማካኝነት ሲነገረን ብቻ ነው ምዝገባ የምናደርግላቸው። ይህ ደግሞ ችግራቸውን በውስጣቸው ይዘው ውጤታማ ላይሆኑ የሚችሉ ተማሪዎችን ያበራክታል። በዚያ ላይ ተለይተው መታገዛቸው የዝቅተኝነት ስሜት እንዲሰማቸው ያደርጋቸዋል። ስለሆነም የቀደመው እገዛ ጥሩ ጎን እንዳለው ሁሉ ድክመትም እንደነበረበት ያስረዳሉ።
አሁን እየተከናወነ ያለው ግን በብዙ መልኩ ተመራጭ መሆኑን ያነሳሉ። ብዙ እድሎችን ለተማሪዎች ያመቻቸ እንደሆነም ይናገራሉ። በተለይም የማርፈድ ምጣኔ መቀነስ ላይ ያሳዩት ለውጥ እጅጉን ያስገርማቸዋል። በእርግጥ ጠዋት ላይ ቁርስ ይቀርባል። ነገር ግን ብዙ ተማሪ አይመጣም ብዬ አምን ነበር። ሆኖም ያገኘሁት ተቃራኒ ነገር ነው ይላሉ።
በምግብ ምክንያት ትምህርቱን የሚያቋርጥና በክፍል ውስጥ የሚያዛጋ እንዲሁም የሚተኛ ተማሪ የለም። በዚህም የተረጋጋ የመማር ማስተማር ስርዓት ተዘርግቷል። የሁሉም ተማሪ ልዩ ትኩረት ትምህርቱ ላይ ብቻ ሆኗል። በውጤት ደረጃም ብዙ መሻሻሎች ታይተዋል። የመንግስት ትምህርት ቤት ከግሎች ጭምር የተሻለ እንዲሆን አድርጓል ።
በትምህርት ሚኒስቴር የትምህርት ቤት ምገባ መርሃ ግብር ዳይሬክተር አቶ ደሊል ከድር በበኩላቸው እንደሚሉት፤ ፍኖተ ካርታው የተማሪዎች የምገባ መርሃ ግብር አለመኖር በትምህርት ጥራት ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተጽዕኖ እንደሚያሳርፍ በጥናት ጭምር አረጋግጦ ያስቀምጣል። በመሆኑም የትግበራው መነሻ ይህ ሀሳብ እንዲሆን አስችሏል።
ከተለያዩ ጥናቶች መመልከት እንደተቻለውም ሕጻናት ምግብ ሳያገኙ መማር ስለማይችሉ እንዲያቋርጡ ይገደዳሉ። እናም መጠነ ማቋረጥን ለማስቀረት ምገባ ግድ እንደሆነ ታምኖበት ወደትግበራው ተገብቷል። መጀመሪያ አካባቢ መርሃ ግብሩን ለማስጀመር የተሟላ አሠራር አልነበረም። በዚህም አደረጃጀት በመፍጠር ወይም በዳይሬክተር ጄኔራል ደረጃ በማቋቋም ወደ ሥራ እንዲገባ ተደርጓል። የአሠራር ሥርዓት ያስፈልግ ስለነበርም ከፍኖተ ካርታውና ከትምህርት ፖሊሲው በመነሳት የማስፈጸሚያ ሥነ ሥርዓትን በማዘጋጀት ጸድቆ ክልል ድረስ እንዲወርድ ተደርጓል ብለዋል።
እንደ አቶ ደሊል ገለፃ ፤ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የምገባ ምርሃ ግብሩ ሙሉ በሙሉ ተጀምሯል። በብዙ መልኩም ለውጦች ታይተዋል። ለምሳሌ፡- መጠነ ማቋረጥን፣ መድገምንና የትምህርት አቀባበልን በብዙ መልኩ አሻሽሏል። በተመሳሳይ ቁጥሩም ቢሆን በብዙ መልኩ ልዩነት ታይቶበታል። ለአብነት መርሃ ግብሩ እንደተጀመረ 25 ሺህ ልጆች የምገባው ተጠቃሚ ነበሩ። በ2014 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ደግሞ ተጠቃሚው 1 ሚሊየን 740 ሺህ 706 ደርሷል።
በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተከናወነ ያለ የምገባ ፕሮግራም በገንዘብ መጠንም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ሄዷል። ይህም በመንግስት/ክልሎች በራሳቸው በጀት ብር 2 ቢሊየን679 ሚሊየን 83ሺህ 640፤ በአጋር ድርጅቶች የሚከናወን (WFP, CHILD SFP, ECW & Koica) 415 ሚሊየን122ሺህ 73.32 በድምሩ 3 ቢሊየን 94 ሚሊየን 205 ሺህ 713.32 ብር መያዙንም አብራርተዋል።
በክልል ብዛት እንዲሁም በትምህርት ቤቶች መጠን እየጨመረ እንደሆነ የላኩልን መረጃ ያመላክታል። ይህም የክልል ብዛቱ (ሁለቱን ከተማ አስተዳደሮች ጨምሮ) 9፣ ወረዳ ብዛት 298፣ ትምህርት ቤቶች ብዛት 3,593፣) ናቸው። ያልጀመሩት ደግሞ ቤኒሻንጉል እና ትግራይ ሲሆኑ፤ አሁንም በሀገር ደረጃ ያለው የትምህርት ቤት የምገባ ሽፋን እጅግ ዝቅተኛ መሆኑንም አንስተዋል።
የትምህርት ቤት ምገባ ፕሮግራም 100 ሺህ ሕፃናትን ሲመገቡ በአማካይ 1ሺህ668 ሰራተኞች ሥራ ይፈጠራሉ ያሉት አቶ ደሊል፤ በአሁኑ ወቅት በ 51 አገሮች ውስጥ ወደ 65ነጥብ 4 ሚሊዮን የሚሆኑ ሕፃናት በአፍሪካ ውስጥ በትምህርት ቤት ምገባ ተጠቃሚ ናቸው። እ.ኤ.አ. በ 2013 ከነበረው 38ነጥብ4 ሚሊዮን ጋር ሲነፃፀር በጣም ከፍተኛ ነው። እናም ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ ኢትዮጵያ የምትገኝበት ምስራቅ አፍሪካ 11ነጥብ 4 ሚሊዮኑን እንደሚሸፍን በመረጃው አስቀምጠዋል።
በኢትዮጵያ 16 በመቶ የሚሆነው የተማሪዎች መጠነ መድገም ደግሞ ከተመጣጠነ ምግብ ችግር ጋር የተያያዘ እንደሆነ የሚጠቅሰው መረጃው፤ ይህንን ችግር ለመፍታት ታስቦ የትምህርት ቤት ምገባ መርሃ-ግብር በሀገር ደረጃ ከ1987 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ እንዲሆን ተደርጓል ይላሉ።
የተማሪዎች ምገባ አፈጻጸም የተማሪዎች ምገባ መርሃግብር ወደ ተግባር ሲቀየር የክልል ቢሮዎች በራሳቸው በጀትና ከልማት አጋሮች ጋር በተገኘው የገንዘብ ድጋፍ ከቅድመ መደበኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ፤ በ2013 ስኬታማ ከነበሩ እቅዶች መካከል የትምህርት ምገባ መርሃ ግብሩ አንዱ እንደነበር አስታውሰዋል። ምንም እንኳን በአንዳንድ ክልሎች የምገባ መርሃግብሩ አስቀድሞ የነበረ ቢሆንም፤ መርሃግብሩ በ2013 በክልሎች ደረጃ የነበረ አፈጻጸም ጥሩ የሚባል እንደነበረም አብራርተዋል።
በተለይም በኦሮሚያ ክልል፣ የደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል (በትምህርት ቤት ምገባ በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀስ እና በአንድ ወቅት ተሞክሮውን ማቅረብ የቻለ) እንዲሁም አማራ ክልል በጀት በመመደብ መርሃግበሩን ሲያካሂዱ እንደነበር ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል።
የመርሃ ግብሩ መልካም አጋጣሚዎቹ ይህን የምገባ መርሃ ግብር ከተማሪዎች በተጓዳኝ ያመጣው መልካም አጋጣሚ እንዳለ የገለጹት ዳይሬክተሩ፤ ከዚህ ቀደም ልጆቻቸውን ለመመገብ አቅማቸው ይፈተን የነበሩ ወላጆች በዚህ መርሃግብር መጀመር ኢኮኖሚያቸው ከፍ እንዳለላቸው ያስረዳሉ። ምክንያቱም ለቤታቸው ወጪ የሚሆን የልጆቻቸው ወጪ ተቀንሶላቸዋል። እናም በምገባው ብዙ የማህበረሰብ ክፍል እፎይ እንዳለም ይናገራሉ።
በየአካባቢው ከሚገኙ የህብረት ስራ ማህበራት ጋርም የሥራ ትስስር መፈጠሩ የአገሪቱን ኢኮኖሚ ከፍ ያደርገዋልም ብለዋል። እናም የተማሪዎች ምገባ ትኩረት ተሰጥቶ ከተሰራበት የተሻለ እድል ይዞ እንደሚመጣም ያምናሉ። ነገር ግን መንግስት በሰጠው ትኩረት ልክ ማህበረሰቡም ሆነ አጋር አካላት እንዲሁም ተማሪዎች እድሉን በአግባቡ መጠቀምና የተሻለውን ማሳየት ይኖርባቸዋል። ነገሮች መስመር የሚይዙትና የትምህርት ጥራቱ የሚረጋገጠው ሁሉም ክልሎች ለዚህ ሥራ ትኩረት ሰጥተው ሲሰሩ በመሆኑ የትምህርት ቤት ምገባ መርሃግብሩን በአግባቡ ሊመሩት እንደሚገባም ያሳስባሉ።
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ግንቦት 22/2014