እስክንድር ቦጎሲያን ከአርመንና ከኢትዮጵያ ወላጆቹ የተገኘ ኢትዮጵያዊ ሰዓሊ እና የስዕል መምህር ነበር። አብዛኛውን የሕይወቱን ክፍል በአሜሪካን ያሳለፈው ይኸው የስዕል ጥበበኛን የሚያስቃኘንን አጭር የሕይወቱን ታሪክ ከመማር ደጉ ገጸ ድር አግኝተናል፤ ለአንባቢ በሚመች መልኩ እንዲህ አቅርበነዋል።
የልጅነትና የወጣትነት ጊዜ
እስክንድር ቦጎሲያን እኤአ በሐምሌ 1937 አዲስ አበባ ውስጥ ተወለደ። በወቅቱ አዲስ አበባ በሙሶሎኒዋ ኢጣሊያ ለ1 ዓመት ከግማሽ ግድም ተይዛ የቆየችበት ዘመን ነበር። እናቱ ወ/ሮ ፀዳለ ወልዴ ተክሌ ኢትዮጵያዊ ሲሆኑ አባቱ ኮስሮፍ ጎርጎሪዎስ ቦጎሲያን ደግሞ አርመናዊ ነበሩ። ምንም እንኳን ዘራቸው ከአርመን ይመዘዝ እንጂ አባቱ በክቡር ዘበኛ የኮሎኔልነት ማዕረግ የነበራቸው ብርቱ ወታደር እንደነበሩ ይነገራል።
አያቱ ግሪጎሪዎስ ቦጎሲያን የታወቁ ነጋዴ የነበሩ ሲሆን በተለይም ከአፄ ምኒልክ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት የነበራቸውና ንጉሠ ነገስቱንም በመወከል የአውሮፓ ተወካያቸው በመሆን እንደ አምባሳደርነት ያገለገሉ ሰው ነበሩ። አባቱ በወቅቱ በነበረው የኢጣሊያ ወረራ ኢትዮጵያን ለመጠበቅ በነበረው ትንቅንቅ ትልቅ ተሳትፎ የነበራቸው ሲሆን በተለይም ልጅ በነበሩበት ወቅት አብዛኛውን ጊዜያቸውን በእስር ላይ ነበር ያሳለፉት። በዚህም ምክንያት ከእህቱ አስቴር ቦጎሲያን ጋር በመሆን አጎታቸው ካቲግ ቦጎሲያን ጋር ነበር አብዛኛውን የልጅነት ጊዜያቸውን ያሳለፉት። አጎታቸው ካቲንግ በወቅቱ የግብርና ምክትል ሚኒስትር የነበሩ ትልቅ ሰው እንደነበሩ ታሪካቸው ይገልፃል።
የግእዝ ትምህርቱን በቄስ ትምህርት ቤት የተማረው እስክንድር በአንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ቆይታው አማርኛን እንግሊዝኛን፣ አርመንኛን እና ፈረንሳይኛን ተምሮ አለፈ። ቀጥተኛ ባልሆነ እና በትርፍ ጊዜው ስዕልን በተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት መቅሰም የጀመረው እስክንድር በኋላ ላይ በእውቁ የኢትዮጵያ ስዕል ታሪክ አዋቂ ስታኒስላስ ቾጅናኪ አማካኝነት ሊቀረፅ ችሏል።
ሥራዎቹ
እስክንድር በ1954 በአፄ ኃይለሥላሴ የብር ኢዮቤልዩ በዓል ላይ ሽልማትን ማሸነፍ ሲችል፣ ይህንን ሽልማት ባሸነፈ በአመቱ ወደ አውሮፓ ተጉዞ እንዲማር የእስኮላርሺፕ ዕድል አገኘ። በዚህም በለንደን የቅዱስ ማርቲን ትምህርት ቤት እና ስሌድ ትምህርት ቤቶች ለሁለት ዓመታት ትምህርቱን ተከታተለ። ከዚህ በኋላም ለዘጠኝ አመታት ፓሪስ በሚገኘው የአካዳሚ ደ ላ ግራንዴ ቿሚየር ሲማር ከዚያም ሲያስተምር ቆየ። በ1966 ወደ አገሩ በመመለስ በኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ፋይን አርትስ ትምህርት ቤት እስከ 1969 መምህር ሆነ። በ1970 ወደ አሜሪካን አገር የተጓዘው እስክንድር ከ1972 እስከ 2001 ድረስ በሀዋርድ ዩኒቨርሲቲ ሲያስተምር ቆይቷል።
እስክንድር ቦጎሲያን በፓሪሱ የሙሲ ዴ አርት ሞደርኔ ስዕሉ የተገዛለት የመጀመሪያ አፍሪካዊ የኮንቴምፖራሪ ሰዓሊ ሲሆን በ1966 ደግሞ በ1964 የሠራውን የጁጁ ሠርግ ተብሎ የተሰየመ ስዕሉ በኒውዮርኩ ሙዚየም ኦፍ ሞደርን አርት ተቀባይነት ሊያገኝ ችሏል።
በ1977 ለተባበሩት መንግሥታት የፈርስት ዴይ ከቨር ስታምፕ መሥራት የቻለ የመጀመሪያው አፍሪካዊም ነው። በዚህ ሥራውም በተባበሩት መንግሥታት የዓለም ፌዴሬሽን አማካኝነት ስፖንሰር ሊደረግ ችሏል። በዚህም ዘረኝነትን እንዋጋ በሚል ይኸው ሥራው በመስከረም 19/ 1977 እትም የሽፋን ገፅ ላይ ሊወጣ ችሏል።
በ2001 ከከበደች ተክለአብ ጋር በመሆን ዋሽንግተን ዲሲ ውስጥ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ የሠራው ሥራ እጅግ ከሚወደዱለት ሥራዎች አንዱ ነው። ሥራዎቹ ከላይ ከተገለፁት የሙዚየም ኦፍ ሞደርን አርት ኢን ኒውዮርክ እና ሙሲ ደ አርት ሞደርኔ በተጨማሪ በስቱዲዮ ሙዚየም ኢን ሀርለም እና ዋሽንግተን በሚገኘው በናሽናል ሙዚየም ኦፍ አፍሪካን አርት ይገኛሉ።
ግላዊ ሕይወት
እስክንድር ቦጎሲያን አይዳ ማሪያም እና ኤድዋርድ አዲሱ የተባሉ ሁለት ልጆችን አፍርቷል። እስክንድር ቦጎሲያን በሀዋርድ ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል ውስጥ ሕክምና እያደረገ በ65 ዓመቱ በፈረንጆቹ ግንቦት 4/2003 ከዚህ ዓለም በሞት ሊለይ ችሏል። ከሞቱ በኋላ የናሽናል ሙዚየም ኦፍ አፍሪካን አርትስ ሙዚየም ዳይሬክተር የሆነችው ሼረን ፓተን ፡ «እንደ አንድ የዘመናዊ የአፍሪካ ስዕል አርቲስትነቱ ለሌሎች ብዙኃን መንገዱን መክፈት የቻለ ሲሆን ትልቅ ማንነቱን ግን እንድናጣው አድርጎ ተለይቶናል» ስትል ገልፃዋለች።
ሽልማቶች
የኃይለሥላሴ የስዕል ሽልማት 1967፣ ኮንቴምፖራሪ አፍሪካን ፔንተርስ ሽልማት ጀርመን 1967፣ የ29ኛው አመታዊ የጥቁር አርቲስቶች ሽልማት ስፔልማን ኮሌጅ አትላንታ ጆርጂያ፡ 1970፣ የዲስትሪክት ኦፍ ኮሎምቢያ የማበረታቻ የምስክር ወረቀት ፣ በተባበሩት መንግሥታት አፓርታይድን ለመዋጋት ከተመሠረተው ልዩ ኮሚቴ የማበረታቻ የምስክር ወረቀት፣ 1984፣ ከሲቲ ኦፍ ሚያሚ ቢች የማበረታቻ የምስክር ወረቀት 1985 ተጠቃሾቹ ናቸው፡፡
(አቤል ገ/ኪዳን)
አዲስ ዘመን ግንብት 21 ቀን 2014 ዓ.ም