የተወለደችው እዚሁ አዲስ አበባ ነው። የጠቢባን መፍለቂያ ከሆነው ፈረንሳይ ለጋሲዮን አካባቢ፤ በተለምዶ 41 ኢየሱስ የሚባለው ሰፈር። ቤታቸው ከሌላኛው የዚያ አካባቢ ተወላጅ አርቲስት ንብረት ገላው ቤት ወረድ ብሎ ነው። የተወለደችበት ቤተሰብ ትልቅ ቤተሰብ ነው። አባት እና እናቷ ባለ ብዙ ልጅ የተከበሩ ባለትዳር ናቸው። እንደ ማንኛውም የትልቅ ሰው ቤት ቤቱ ሥነ ምግባር በጥብቅ የሚከበርበት እና ሁሉ ነገር በሥርዓት የሚከወንበት ቤት ነው። በዚህ ቤተሰብ ውስጥ ግን አንድ ቅልጥፍጥፍ ያለች እና ደፋር የሆነች ልጅ ተወለደች። ያቺ ልጅም የጥበብ ሰው ሆና የአቶ ኃይሌን ቤተሰብ አስጠራች። ስሟም ንጹህ ነው።
በልጅነቷ ጎበዝ ተማሪ ነበረች። የምትኖርበት ቤተሰብም ለትምህርት ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጥ ቤተሰብ ነው። ስለዚህም ለጥበብ የሚሆን ትኩረት አልነበራትም። እንዲያም ቢሆን ግን ቤታቸው እና ሰፈራቸው የሚመጡት ሰዎች የሚያወሩበት ዘዬ ይማርካት ነበር። ስለዚህም ንግግራቸውን ጆሮዋን ጥላ ታዳምጣለች፤ እሷም ትለምደዋለች። የሆነ ሆኖ እስከ 11ኛ ክፍል ንጹህ እና ኪነ ጥበብ ፊት ለፊት አልተገናኙም። 11ኛ ክፍል ስትደርስ ግን አንድ ቀን ትምህርት ቤታቸው ውስጥ ፍጻሜው የሚል ተውኔት ሲሠራ ተመለከተች። በጣም ተደነቀች። በተለይ አንደኛዋን ተዋናይ በጣም ወደደቻት። ስለዚህም የዚያን ቀን ተዋናይ መሆን እንዳለባት ወሰነች። ወዳስደነቀቻት ልጅ ሄዳ እንዴት እንደሷ ተዋናይ መሆን እንደምትችል ትጠይቃታለች። ልጅቷም ወደ ድራማ ክበብ መግባት እንዳለባት ትነግራታለች። እንደተባለችው ትገባለች። ትወናው ይሳካላታል። ያንኑ ተውኔት እሷም በግሩም ሁኔታ ትተውነዋለች። ከዚያ በኋላ የትወና ሕይወቷ በይፋ ይጀመራል።
ትወና ውስጥ ስትገባ ያ እየሰማች ያደገችው የገጠር ዘዬ ዋነኛ መገለጫዋ ይሆን ዘንድ ብቅ አለ። በመጀመሪያ ሥራዋ በታዋቂው ተዋናይ በምናቡ ከበደ ጥቆማ ብራ በሚል ፊልም ተሳተፈች። ትወናዋ ተደናቂነት አተረፈ። በተለይም የዘዬው ነገር ተወዳጅ አደረጋት። ውሎዋም በገጠር ዘዬ ብቃታቸው በጣም ተደናቂ ከሆኑት አብርሀም አስመላሽ እና በምናቡ ከበደ ጋር መሆኑ በምትሠራው ነገር ላይ የበለጠ ብስለት እንዲኖራት አደረገ። ከገጠር ዘዬ ባለፈ በሌሎች ገጸ ባህርያትም ብቁ ትወና ያሳየችው ንጹህ ሕዝብ ግን ለይቶ የወደዳት በገጠር ዘዬዋ ነው።
ከዚያ ደግሞ ታዋቂዎቹ ጥላሁን ጉግሳ እና አለምነህ ዋሴ ማስታወቂያዎች ላይ እንድትሠራ ዕድል ሰጧት። ከዚያም ዕድሎቿን ማባከን የማታውቀው ንጹህ ጥላሁን ዘውገ እና አለልኝ መኳንንት ታዋቂ በሆኑበት ስንቅ ድራማ ላይ የመሳተፍ ዕድል ሲሰጣት በአግባቡ ተጠቀመችበት። በተለይ ግን በሬድዮ ፋና በሚተላለፉ ድራማዎች ላይ ያሳየችው ብቃት በጣም ተደናቂ ነበር።
በበርካታ የሬድዮ ድራማ፤ ፊልሞች እና ተውኔቶች ዝናን ያተረፈችው ንጹህ ኃይሌ የታዋቂነት ተወዳጅነት ማማ ላይ የደረሰችው ግን አሁን 9ኛ አመቱ ላይ በደረሰው ቤቶች በተሰኘው ድራማ ነው። በዚህ ሲትኮም ላይ ተወዳጅ የሆነችበትን የገጠር ዘዬ በሚገባ የተጠመችበት ሲሆን የተሰጣት ገጸ ባህሪ ለዛ ያላት መሆኗ እና እሷም ገጸ ባህሪዋን በሚገባ መወጣቷ ሻሼ የሚለው ስም የገጸ ባህርዩአ ስም ብቻ ሳይሆን የንጹህ ሁለተኛ ስም እስኪመስል ድረስ ንጹህ እንድትታወቅ አድርጓታል። እሷ በቴሌቪዥን ሲትኮሙ ትታወቅ እንጂ የሁልጊዜም ምርጫዋ ግን ቴአትር ነው። ገንዘብ የለውም ግን ቴአትር ከሁሉም ይበልጣል፤ ከዚያ ቀጥሎ ከባድ ሥራ የሬድዮ ድራማ ነው። የሬድዮ ድራማ የማይታይ ነገርን ማሳየት መቻል ስለሆነ ከባድ ነው በማለት ከፊልም እና የቴሌቪዥን ድራማ ይልቅ ለቴአትር እና ብዙ ለሠራችበት ለቴሌቪዥን ድራማ ቅድሚያ እንደምትሰጥ ትናገራለች። ንጹህ በሬድዮ ድራማ ዘርፍ ብዙ የሠራች ሲሆን በቴሌቪዥን ድራማም የታወቀችባቸውን ቤቶች እና ስንቅ ተውናለች። በፊልም በኩል ደግሞ ሰምና ወርቅ፤ ፈንጂ ወረዳ፤ ቤኒኦን እና ሌሎችን ሠርታለች።
ንጹህ ባለትዳር እና የሁለት ልጆች እናት ናት። ባለቤቷን አቶ በላይ መኩሪያን ያገኘችው የኩዊንስ ኮሌጅ ተማሪ ሆነው ሳለ ነው። አንድ ቀን እሱ የሚማርበት እና እሷ የምትማርበት ክፍሎች ወደ አንድ ክፍል እንዲጠቃለሉ ሲደረግ የዛሬውን የልጆቿን አባት አየችው። ወደደችው። እሱም የፍቅር ምላሽ ሰጠ። ፍቅሩ አየጦፈ ሄደ። ትምህርታቸውን ሲጨርሱ ሁለቱም የአካውንቲንግ ዲፕሎማ እና ትዳር ይዘው ወጡ። በዚህ መልኩ 1993 መጋቢት 22 ቀን የተጀመረው ፍቅር በ1997ቱ ብጥብጥ ለሁለት ሳምንታት ካልተገናኙበት ጊዜ በቀር ቀን በቀን እየተገናኙ እና እየተመካከሩ አሳድገውት በ2003 ሚያዝያ 29 ቀን በትዳር ተቋጨ።
ትዳር ከተያዘ በኋላ ቀጣዩ እርምጃ ልጅ መውለድ ነበር። ነገር ግን እሱም ቀላል አልሆነም። የባል እና የሚስቱን ትእግስት እና እምነት የሚፈታተኑ ነገሮች ተከሰቱ። ከአንዴም ሁለት ጊዜ ነፍሰ ጡር መሆኗ ከተረጋገጠ በኋላ ጽንሱ ጠፋ። በኋላ ላይ እንዲያውም ልጅ መውለድ እንደማትችል ተነገራት። ነገር ግን ሁሌም ቢሆን ከጎኗ የማይጠፋው ባለቤቷ በዚህ አልተስማማም። ንጹህን እያበረታ ቀጠለ። የማለቅስበት ቦታ እስካጣ ድረስ አጠገቤ ነበር ትላለች ያደርግ የነበረውን እንክብካቤ ስትገልጽ።
ከብዙ ትእግስት በኋላ ግን የተጠበቀው ፍሬ ደረሰ። ልጅ ወለደች። ደገመችም። አሁን ላይ ንጹህ እና በላይ የአብላካት በላይ እና መክሊት በላይ እናትና አባት ሆነዋል። የተረጋጋ ሕይወት እየኖርኩ ነው የምትለው ንጹህ ለትዳር ያላት ምልከታም ከፍተኛ እንደሆነ ትናገራለች። ለዚህም ምክንያቷ እናትና አባቷ ናቸው። ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ አብረው የኖሩት እናት እና አባቷ እጅግ እንደሚዋደዱ እና እንደሚከባበሩ ትናገራለች። እናቴ አባቴን ስታከብር አባቴ የእናቴን ፊት ሲያይ እያየሁ ነው ያደግኩት ትላለች።
ንጹህ ከሥራ ውጪ ባለው ጊዜ ብዙም ደጅ የምትታይ ዓይነት ሰው አይደለችም። ብዙ ጊዜዋን ቤት ማሳለፍ እንደምትፈልግ የምትወደው አርቲስቷ ምግብ ማብሰል ላይ ጎበዝ እንደሆነች በብዙ ወዳጆቿ ይነገራል። እሷም ታምናለች። መሥራት የምትወደው ምግብ ዓሣ ሲሆን ከምግብ ሁሉ ፍቅር የሌላት ደግሞ ለዱባ እንደሆነ ትገልጻለች። ንጹህ ጥበብን ለዝና ብቻ የሚጠቀሙት ሰዎች የሌሎችን በር መዝጋት ትተው የሚሳካላቸውን ነገር እንዲፈልጉ ጥሪ እያቀረበች የጥበብ ተሰጥኦው ያላቸው ሰዎች ሳይታክቱ እንዲሠሩ እና ተሰጥኦቸውን በጥበብ እንዲደግፉ ትመክራለች።
(አቤል ገ/ኪዳን)
አዲስ ዘመን ግንብት 21 ቀን 2014 ዓ.ም