ከዛሬ አራት ዓመት በፊት ግንቦት 20 ዜና ነበር። እነሆ ዛሬ ታሪክ ሆኗል። ታሪክ ደግሞ የዛሬ ሳይሆን የትናንት ክስተት ነውና ግንቦት 20 ታሪክ ሆኖ ‹‹እንዲህ ሆኖ ነበር›› ልንለው ነው።
ቀደም ባሉት ሳምንታት እንዳልነው ይህ የግንቦት ወር የደርግ እና የኢህአዴግ ወር መስሏል። የሚገርመው ግን ገና ወደፊትም አለን። ግንቦት 27 ራሱ የኢህአዴግና የደርግ ታሪክ ነው። እሱን ሳምንት ስንደርስ እናየዋለን። ለዛሬው የምናስታውሰው የግንቦት 20 ክስተቶችን ነው።
ከ31 ዓመታት በፊት ግንቦት 20 ቀን 1983 ዓ.ም ኢህአዴግ ወታደራዊውን የደርግ መንግሥት ገርስሶ አዲስ አበባን የተቆጣጠረበት ቀን ነው። የኢህአዴግ ከፍተኛ አመራር የነበሩ የጻፏቸው መጻሕፍት፣ በተለያዩ መድኮች የተናገሯቸው ንግግሮች፣ በመንግሥት መገናኛ ብዙኃን የተሠሩ ዘጋቢ ፊልሞች… እንደሚያሳዩት ኢህአዴግ ደርግን ያስወገደው በሕዝብ ትብብር ነው።
ምንም እንኳን ጦርነቱ የዓመታት ቢሆንም ኢህአዴግ ግንቦት ሃያን በተለየ ያከብረው የነበረው አዲስ አበባን የተቆጣጠረበትና ቤተ መንግሥት የገባበት ቀን ስለሆነ ነው።
የተለያዩ የታሪክ ድርሳናት እንደሚያሳዩት ኢህአዴግ ደርግን ለማስወገድ ሕዝባዊ ድጋፍ የሚያስገኙ ዘዴዎችን ተጠቅሟል። ከእነዚህም አንዱ የጦርነቱን ዘመቻዎች የአካባቢው ሰዎች በሚያከብሯቸውና በሚያደንቋቸው ሰዎች ይሰይም ነበር። የአካባቢው ሰዎች በሚናገሩት ቋንቋ ይሰይም ነበር።
ለምሳሌ፤ በወለጋ እና በሌሎች የምዕራብ ኢትዮጵያ አካባቢዎች የነበረውን ዘመቻ ‹‹ቢሊሱማ ወልቂጡማ›› ብሎ ነበር የሰየመው። የአፋን ኦሮሞ ቃል ሲሆን ነፃነትና እኩልነት ማለት እንደሆነ ሲነገር ቆይቷል። በዚህ ስም የሰየመውም የአካባቢው ሰው የአፋን ኦሮሞ ተናጋሪ ስለሆነ ነው።
በወሎ በኩል የነበረው ዘመቻ ደግሞ ዘመቻ ዋለልኝ ተብሎ ተሰይሟል። ዋለልኝ መኮንን የወሎ ተወላጅ ሲሆን የብሔር ፖለቲካ አቀንቃኝ ነበር። ኢህአዴግ ይህን የተጠቀመው ዋለልኝ መኮንን የወሎ ተወላጅ ስለሆነ ወሎዎች ይወዱታል ብሎ ሳይሆን ምናልባትም የብሔር ፖለቲካ ጀማሪና አቀንቃኝ ስለነበረለት ይሆናል።
በጎንደር በኩል የነበረው ዘመቻ ደግሞ እስከ ጎጃም ድረስ ‹‹ዘመቻ ቴዎድሮስ›› ይባል ነበር። በዚያ አካባቢ ያለው ማኅበረሰብ የአጼ ቴዎድሮስ ነገር ሲነሳ ወኔው ይቀሰቀሳል ብሎ ስላሰበ ይመስላል።
አራተኛውና አዲስ አበባን የተቆጣጠረበት የመጨረሻው ዘመቻ ደግሞ ‹‹ዘመቻ ወጋገን›› ይባላል። ‹‹የመጨረሻዋ ጥይት የተተኮሰችበት›› ይሉታል የኢህአዴግ ሰዎች።
በ2008 ዓ.ም ግንቦት 20 ሲከበር የኢህአዴግ ጽሕፈት ቤት ካቀረበው ጽሑፍ፤ የግንቦት 20 ቀን 1983 ዓ.ም ክስተት የሚከተለውን እናስታውስ።
‹‹…. አዲስ አበባ በሦስት አቅጣጫ በኢህአዴግ ሰራዊት ተከባለች። ከየትኛውም የአገሪቱ ክፍል የሚወጣም ሆነ የሚገባ የለም። የቀለበቱ ማጥበብ ቀጥሏል። አምቦ የነበረው ሰራዊት ወደ ሆለታና ታጠቅ ተጠጋ። በጅማ በኩል የነበረው ግልገል ግቤን ተሻግሮ ወሊሶን አልፎ ወደ አለም ገና ተጠግቷል። ደብረብርሃን የነበረው ኃይል ገሚሱ ወደ ደቡብ ምሥራቅ በመጓዝ ደብረዘይትን ከበባት። ማንኛውም የጦር አውሮፕላን ወደ ሰማይ አልወጣም፤ አልወረደም።
….ግንቦት 19 ቀን 1983 ልክ ከቀኑ 10 ሰዓት ወታደራዊ ዘመቻውን በበላይነት የሚያስተባብረው ቡድን ለመጨረሻ የሰላም ውይይት ሎንደን ከነበረው የበላይ አመራር ‹‹ቀጥል›› የሚል አጭር መልዕክት ደረሰው። ቀድሞ በተደረገው ጥናት አዲስ አበባ በሦስት ግንባር ተከፍላለች።
በአምቦ ግንባር የነበረው በጎጃም በር በኩል ወደ ፒያሳ በመዝለቅ መርካቶን ተቆጣጥሮ ወደ ጅማ መንገድ ያመራል።
ሁለተኛው ግንባር በደብረዘይት የሚመጣ በአቃቂ ገብቶ ንፋስ ስልክ፣ ጎተራ፣ ቄራ፣ አራተኛ ክፍለጦር፣ ስታዲየም ጨምሮ እስከ ሜክሲኮ ያለውን ይይዛል።
ሦስተኛው በሰንዳፋ የሚመጣ በኮተቤ በመውረድ ብረታ ብረት ፋብሪካ ከደረሰ በኋላ ለሦስት ንዑስ ግንባር ይከፈላል። አንዱ በመገናኛ በኩል ወደ ኤርፖርት ያመራል። ሁለተኛ ክፍል በ22 ሰንጥቆ ወደ መስቀል አደባባይ በመሄድ ታችኛውን ቤተመንግሥት ይቆጣጠራል። ሦስተኛው ክፍል በእንግሊዝ ኤምባሲ አቅጣጫ በግንፍሌ አድርጎ ወደ አራት ኪሎ በመግባት ቤተመንግሥትን ይቆጣጠራል።
ኮማንደሮቹ ይህንን ድልድል በማድረግ ሌሊቱን በሙሉ ሲዘጋጁ አደሩ። እነ ሐየሎም በነበሩበት አቅጣጫ ታጠቅ አካባቢ የነበረው ኃይል ማታ ወደ ከተማ የመፍረስ ምልክት ስለታየ ይህ ኃይል ወደ መሃል ከተማ ከገባ አላስፈላጊ ዋጋ የሚያስከፍል ውጊያ ስለሚያስከትል አስቀድሞ መያዝ አለበት ተብሎ ስለ ተወሰነ በዋዜማው የተወሰነ ኃይል ቀድሞ ወደ ቦታው እንዲጠጋ በማድረግ በኮልፌ 18 ማዞሪያ በኩል ተዘጋ። ከከተማው ወደ ውጪ እንዲበተንም ተደረገ።
አስቀድሞ የወጣው ስትራቴጂ በሚገባ የሠራ መሆኑ እየተረጋገጠ መጣ። የመንግሥት አብዛኛው ወታደር ከአዲስ አበባ ከመግባቱ በፊት እንዲበታተን ተደረገ። ገሚሱ መሣሪያ የያዘ ገሚሱ መሣሪያ የሌለው እየተንቀረፈፈ ከሚገባ በስተቀር ተደራጅቶ ወደ ከተማዋ የሚያፈገፍግ ሰራዊት አልነበረም። ይህ ለኢህአዴግ ትልቅ ድልና ስኬት ነበር። በሕዝቡ ዘንድም ስጋትን የቀነሰ ነበር።
የወጋገን ዘመቻ ዋና አላማው የቀረውን ሰራዊት መደምሰስ ሳይሆን ከተማዋን በብልሃት መቆጣጠር ነበር…››
በሕወሓት ጀማሪነትና መሪነት የተደረገው የትጥቅ ትግል በዚህ መልኩ ኢህአዴግ አዲስ አበባን ተቆጣጥሮ ለ27 ዓመታት ያህል ኢትዮጵያን መራ። በ2010 ዓ.ም ለውጥ መጣ፤ ሕወሓትም ወደ ሽብር ቡድንነት ወረደ። ግንቦት 20ም ታሪክ ሆነ!
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ግንብት 21 ቀን 2014 ዓ.ም