ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በዓለም ቅርሶች መዝገብ ከሰፈሩ አስራ አንድ የማይንቀሳቀሱ ቅርሶች አንዱ በሆነው የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ውስጥ ከሚገኘው ከራስ ዳሸን ተራራ ከፍታ እስከ ዳሎል ዲፕሬሽን ዝቅታ ድረስ በአስደናቂ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ እና የአየር ንብረት፣ የብርቅዬ የዱር እንስሳት መገኛ፣ የራሷ የዘመን አቆጣጠርና ፊደል፣ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶች ባለቤት ነች።
የበርካታ ታሪካዊ ባህላዊ እና ተፈጥራዊ ሀብቶች ባለቤት ብትሆንም ከዘርፉ እንደሌሎች አገራት በአግባቡ መጠቀም ግን አልቻለችም። ከዚህም ሌላ እነዚህን ሀብቶች በየጊዜው ከሚከሰት አደጋ ጠብቆ ከትውልድ ወደ ትውልድ ለማሸጋገር የሚደረገው ጥረትም እንዲሁ በርካታ ፈተናዎች የተደቀኑበት ነው። ዘርፉን የሚመሩት የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣንም ሆነ የቱሪዝም ሚኒስቴር እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ችግሮችን ነቅሰው በመለየት ለመፍታት የሚያደርጉት ጥረትም ተመሳሳይ ውስብስብ ችግሮች የሚያስተናግድ ነው። በዚህ የተነሳ አገሪቷ ከቱሪስቶች ልታገኘው የሚገባትን ጥቅም እስካሁን አላሳካችም ለማለት ያስደፍራል።
ነባር እና አዳዲስ የቱሪስት መስህቦችን ማልማት፣ የቱሪዝም የገበያ ልማትን እንዲሁም አገልግሎትን ማላቅ፣ ትብብር እና አጋርነትን ማጠናከር እንዲሁም የአቅም ግንባታ ሥራዎች መሥራት የዘርፉ የትኩረት አቅጣጫ ቢሆኑም፣ መሬት ላይ በተግባር የሚሠራው እና በትክክል እንዲሆን የሚፈለገው ክንዋኔ ግን ለየቅል ነው።
የዘርፉ ባለሙያዎች በጥናቶቻቸው እንደሚጠቁሙት፤ ለተጠቀሱት ችግሮች ዋንኛው መንስኤ ሳይንሳዊውን መንገድ ተከትሎ ዘርፉን በአግባቡ መምራት አለመቻል ነው፤ የክትትል እና ቁጥጥር ሥርዓቱ የላላ መሆን፣ የባለድርሻ አካላት ቅንጅት ማነስ ደግሞ ሌሎች የሚጠቀሱ ችግሮች ናቸው። የተጠቀሱት ችግሮች በተለይ የተፈጥሮ መስህብ በሆኑትና በፓርክና ጥብቅ ቦታዎች በተከለሉ አካባቢዎች ጎልተው ይታያሉ።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መንግሥት ለቱሪዝም ዘርፉና በኢትዮጵያ ለሚገኙ ፓርኮችና የመስህብ ስፍራዎች በሰጠው ልዩ ትኩረት ምክንያት ተስፋ ሰጪ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ። አዳዲስ መዳረሻዎችን ከመፍጠር ባሻገር የነበሩትን የማልማት፣ የመጠበቅና ለጎብኚዎች የማስተዋወቅ ሥራም እየተከናወነ መሆኑንና ሌሎች በርካታ ማሳያዎችን ለእዚህ ማንሳት ይቻላል። ለእዚህም በአዲስ አበባ የተገነቡት የአንድነት፣ የወዳጅነትና የእንጦጦ ፓርኮች እንዲሁም በተለይ የኮይሻ፣ ወንጪ ደንዲ እንዲሁም ጎርጎራ ታላላቅ ፕሮጀክቶች ይጠቀሳሉ።
የመስህብ ስፍራዎችን የመጠበቅ፣ ፓርኮችን የማልማትና ከአደጋ የመከላከል ሥራ በመንግሥት ብቻ የሚከናወን ተግባር አይደለም። ይህ ተግባር የማህበረሰቡን፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማትን፣ የመገናኛ ብዙኃንን ጨምሮ በርካታ የሚያገባቸው አካላትን ማሳተፍ ይኖርበታል። ከዚህ ጋር ተያይዞም አንዳንድ ግብረ ሰናይ ድርጅቶችና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት የቱሪዝም ዘርፉን ለማሳደግና በተለይ ፓርኮች የሚደርስባቸውን የተለያዩ ጉዳቶች ለመቀነስ እየሠሩ እንደሚገኙ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
ከእነዚህ ተቋማት መካከል በቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝና በባለቤታቸው የተመሠረተው «ኃይለማርያም እና ሮማን ፋውንዴሽን» ይገኝበታል። ይህ ድርጅት በተለይ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ፓርኮችን እና የቱሪዝም ሀብቶችን መሠረት አድርጎ ልዩ ልዩ ሥራዎችን እንደሚሠራ ይታወቃል።
ከሰሞኑም «የዓለም የብዝሃ ሕይወት ቀን» በተከበረበት ወቅት ድርጅቱ ከኢትዮጵያ የዱር እንስሳ ጥበቃ ባለሥልጣን ጋር በመሆን በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ፓርኮችና ጥብቅ ስፍራዎች ያሉባቸውን ችግሮች፣ የመልማት አቅምና የሚያስገኙትን ከፍተኛ ምጣኔ ሀብታዊ ጠቀሜታ በተመለከተ የምክክር መድረክ ተካሂዷል።
ይህን አስመልክቶ የባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ናቃቸው ብርሌው ለዝግጅት ክፍላችን ባደረሱት መረጃ ላይ እንደተመለከተው፤ በሃያት ሬጀንሲ ሆቴል የተሰናዳው ይህ የምክክር መድረክ ዋንኛ አላማ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ፓርኮች በተለይም የባሌ፣ ነጭ ሳር እና የጨበራ ጩርጩራ ብሔራዊ ፓርኮች ያላቸው ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታና እያጋጠሙት ያሉት ችግሮችን የሚዳስሱ ጽሑፎች ቀርበው በመፍትሄ ሃሳቦች ላይ ምክክር ማድረግን ያለመ ነበር።
በዕለቱ ጽሑፎችን ያቀረቡት ባለሙያዎችም ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ቱሪዝም እና የብዝሃ ሕይወት ጥበቃ ዙሪያ ያላትን ሀብት እንዲሁም የምጣኔ ሀብት አቅም ከመዳሰሳቸውም ባለፈ በፓርክነት የተከለሉ ስፍራዎች እያጋጠሟቸው ያሉትን ፈተናዎችና ስጋቶችን አመላክተዋል።
በመድረኩ ላይ ጽሑፍ ያቀረቡት አቶ ሻሚል ከድር የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ቺፍ ዋርደን ናቸው። እሳቸው እንደሚሉት፤ የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ በ1960ዎቹ አካባቢ ለመጀመሪያ ጊዜ በአገራችን ከተቋቋሙት ሦስት ፓርኮች አንዱ ነው። ፓርኩ ከአዲስ አበባ በ400 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ሲገኝ ስፋቱ 2150 ስኩየር ኪሎ ሜትር ነው። ከሰሜን ወደ ደቡብ 74 ኪሎ ሜትር ከምዕራብ ወደ ምሥራቅ ደግሞ 53 ኪሎ ሜትር ይሰፋል።
ፓርኩ ከባህር ወለል በላይ ከ1500 እስከ 4377 ጫማ ባለ ልዩነት ውስጥ የሚገኙ አካባቢዎችን ያካትታል። 4377 ጫማ የሚረዝመውና ከኢትዮጵያ በከፍታው ሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው የቱሉ ዲምቱ ተራራን ጨምሮ የአፍሮ አልፓይን ከፍተኛ ቦታዎች በዚህ ፓርክ ውስጥ ይገኛሉ። የባሌ ተራሮች ከፍተኛ አካባቢ በተለያየ መንገድ የተፈጠሩ ሐይቆች፤ እርጥበት አዘል መሬቶች፣ የእሳተ ገሞራ ቅሪቶች መገኛ ነው።
ቺፍ ዋርደኑ እንደሚናገሩት፤ ፓርኩን ልዩ የሚያደርጉት የተፈጥሮ አቀማመጡ አፍሮ አልፓይታን (ቀዝቃዛና ውርጫማው) አካባቢ 1000 ኪሎ ሜትር ስኩየር ስፍራን የሚሸፍን በአፍሪካ የመጀመሪያው ፕላቶ መኖሩ፣ በኢትዮጵያ በከፍታው በ2ኛ ደረጃ የሚገኘው የቱሉ ዲምቱ ተራራ በመገኘቱ እና ስደተኛና በአካባቢው የሚቆዩ በርካታ አእዋፍ መኖራቸው፤ በኢትዮጵያ ትልቁና ወደ ሰባት ሺህ ኪሎ ሜትር ስኩዬር የሚሸፍነው የሀረና ደን በውስጡ በመገኘቱ ተጠቃሾች ናቸው።
ከዚህም ሌላ ከ1600 በላይ የሚሆኑ ልዩ ልዩ ዓይነት ዕፅዋቶች፣ 78 ዓይነት አጥቢ የዱር እንስሳት፤ 280 የአእዋፍ ዝርያዎች በፓርኩ ተጠልለው ይገኛሉ። ከነዚህም መካከል 32 ዓይነት ዕፅዋት፣ 31 የሚጠጉ ብርቅዬና ድንቅዬ የዱር እንስሳትና ወደ ስድስት የሚጠጉ ዕፅዋት ይገኙበታል፤ እነዚህም በብሔራዊ ፓርኩ ካልሆነ በስተቀር በሌላው ዓለም ፈጽሞ የማይገኙ እንደሆኑ አቶ ሻሚል ይገልፃሉ። በባሌ ተራሮች ፓርክ ከሚገኙት 78 አጥቢ የዱር እንስሳት 17 የሚሆኑት በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ ሲሆን ሦስቱ ደግሞ በዚህ ፓርክ ውስጥ የሚገኙ ብርቅዬ እንስሳት መሆናቸውን ያስረዳሉ።
«ፓርኩ ለብዝሃ ሕይወት መጠበቅ እና ከቱሪዝም ለሚገኝ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ከፍተኛ ድርሻ ቢኖረውም የተለያዩ ፈተናዎች ተጋርጠውበታል» የሚሉት ቺፍ ዋርደን አቶ ሻሚል፤ በተለይ አርሶ አደሩ ከብቶችን ለግጦሽ በሚል በተከለለው ስፍራ የማስገባት፣ ደንንና የተለያዩ እፅዋቶችን መንጥሮ ለማገዶና ለእርሻ የማዋል አደገኛ ዝንባሌ እንደሚስተዋል ይናገራሉ።
በሌላ በኩል በስፍራው በሚኖሩ የቤት ውስጥ ውሾች አማካኝነት በሚተላለፍ ተዛማች በሽታ አማካኝነት በፓርክ ውስጥ የሚገኙ የዱር እንስሳትና አእዋፋት ተጋላጭ እንደሚሆኑ ይጠቁማሉ። በሌላ በኩል መነሻው የማይታወቅ የሰደድ እሳት በየጊዜው በፓርኩ ላይ አደጋ እየፈጠረ መሆኑን ገልፀው፣ እነዚህን ችግሮች በአፋጣኝ መፍታት ያስፈልጋል ሲሉ ምክረ ሃሳባቸውን ይሰጣሉ። ችግሮቹን ነቅሶ መፍታትና ማኅበረሰቡ ለሀብቱ እንዲቆረቆር ግንዛቤ መፍጠር ከፓርኩ የሚገኘውን ጥቅም ለማሳደግ እንደሚረዳ ነው የሚናገሩት። ከኢኮኖሚያዊ ጥቅም ባሻገር በስፍራው ለመድኃኒትነት የሚውሉ በርካታ እፅዋት መገኘታቸው ተጨማሪ እሴት እንደሚሆን ያስረዳሉ።
የብዝሃ ሕይወት ቀን መከበርን አስመልክቶ ስለ ባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ አጭር ጽሑፍ ያቀረቡት ቺፍ ዋርደኑ መንግሥትም ሆነ የሚመለከታቸው አካላት ለሀብቱ መጠበቅ በትኩረት እንዲሠሩ አሳስበዋል።
በምክክር መድረኩ ላይ ሌላው ጽሑፋቸውን ያቀረቡት የነጭ ሳር ብሔራዊ ፓርክ ቺፍ ዋርደን አቶ ሽመልስ ዘነበ ናቸው። እንደ እርሳቸው ገለፃ የነጭ ሳር ብሔራዊ ፓርክ 514 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ላይ ያረፈ ነው፤ ከአዲስ አበባ 507 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ በውስጡ 351 የአእዋፍ 16 የዓሣ እንዲሁም ከ91 በላይ አጥቢ እንስሳትን የያዘ እና ጫሞ ሐይቅም ናይል ክሮኮዳይል የተባለ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኝ የአዞ ዝርያን በውስጡ ይዟል። ፓርኩ በአመት ከ 41 ሺህ በላይ ጎብኚዎችን በማስተናገድ በሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
«ከስምንት በላይ ደረጃቸውን የጠበቁ ሎጆችና ሪዞርቶች መገኛ ነው። በዓሣ ምርት 100 ሚሊዮን ብር የሚያስገኝ ነው» የሚሉት ቺፍ ዋርደኑ፣ 250 ሺህ ለሚሆኑ ለአርባምንጭ ነዋሪዎች የውሃ አቅርቦት መዳረስ ዋንኛ ምክንያት መሆኑን ይናገራሉ። በዚህ ምክንያት ከፓርክና ከመስህብነት ባሻገር ለአገሪቱና በዙሪያው ለሚኖሩ የማኅበረሰብ ክፍሎች አያሌ ኢኮኖሚያዊ በረከቶችን የሚያስገኝ እንደሆነ ይገልፃሉ።
ይሁን እንጂ አርሶ አደሮች የተከለለውን ፓርክ በመጣስ በመስፋፋታቸው፣ ከብቶችን በፓርኩ ውስጥ የማሰማራት አዝማሚያ፣ በአባያና ጫሞ የደለል መሙላትና መድረቅ፣ ፓርኩን ለማስተዳደር በቂ በጀት አለመኖሩ፣ የሰው ኃይል ፍሰት እና ሌሎችም ተደማምረው ከፍተኛ አደጋ ውስጥ እንደሚገኝ ይገልፃሉ። በደለሉ ምክንያት የዓሣ ምርት መቀነሱን አመልክተውም፣ የአካባቢው ማኅበረሰብ የገቢ ምንጭ ማሽቆልቆሉ እንደማይቀር ያስረዳሉ። የመሠረተ ልማት ግንባታ ክፍተት በመኖሩ ምክንያትም በጎብኚዎች ላይ ጫና ከማሳደሩም በላይ ለቁጥጥርና ጥበቃ እንቅፋት እንደሆነ ነው ስጋታቸውን የሚገልፁት።
የጨበራ ጩርጩራ ቺፍ ዋርደን አቶ ተስፋዬ አይመታ በምክክር መድረኩ ላይ ስለ ፓርኩ ጽሑፍ ካቀረቡት መካከል ናቸው። እሳቸው እንደሚሉት፤ ጨበራ ጩርጩራ ብሔራዊ ፓርክ በመካከለኛው ኦሞ ሸለቆ ውስጥ ይገኛል። አጠቃላይ የቆዳ ስፋቱ 1400 ካሬ ኪሎ ሜትር ነው። በስፋቱም ግዙፍ ከሚባሉ ብሔራዊ ፓርኮቻችን አንዱ እንዲሆን ያደርገዋል።
ፓርኩ የአፍሪካ ዝሆን መኖሪያ ነው። በቁጥር 500 የሚደርሱ ዝሆኖች የሚገኙበት መሆኑ ልዩ ያደርጉታል። በዓይነት 39 የሚደርሱ ትላልቅና መካከለኛ የዱር እንስሳት እንዲሁም 18 የሚሆኑ የትናንሽ የዱር እንስሳት መኖሪያም ነው። እስከ አሁን በተደረገው ጥናት በአጠቃላይ 57 የሚሆኑ አጥቢ የዱር እንስሳት መኖሪያ እንደሆነ ተረጋግጧል።
እንደ ባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክና የነጭ ሳር ብሔራዊ ፓርክ ይህ ፓርክም በርካታ አደጋዎች የተጋረጡበት ነው። በተለይ ለእርሻና ለማገዶ በሚል የደኖች ምንጣሮ በሕገወጦች በስፋት እንደሚካሄድ ቺፍ ዋርደኑ ይናገራሉ። ዝሆኖቹ ክልሎችን እየጣሱ በሰዎች ላይ ጉዳት ማድረሳቸውና እስካሁን ድረስ 32 የሚጠጉ ሰዎች መሞታቸው ሌላኛው ችግር መሆኑን ጠቅሰዋል።
የፓርኩ ሠራተኞች እነዚህን ችግሮች ለማስቀረት አቅደው እየሠሩ ቢሆንም፣ የበጀት እጥረት እክል እንደሆነባቸውም ያስረዳሉ። በአሁኑ ሰዓት የጨበራ ጩርጩራ ብሔራዊ ፓርክ በዓመት 600 ሺህ የኢትዮጵያ ብር ብቻ እንደሚመደብለት ነው የሚናገሩት። ይህ ማለት ከሚፈለገው አጠቃላይ በጀት ከ10 በመቶ በታች እንደሆነ ያስረዳሉ።
እንደ መውጫ
አገራችን 27 ብሔራዊ ፓርኮች እንዳሏት መረጃዎች ያመለክታሉ፤ ከእነዚህ ፓርኮች መካከል 13 ያህሉ በፌዴራል ደረጃ የሚተዳደሩ ናቸው። 14ቱን ደግሞ ክልሎች በኃላፊነት ተረክበው ይቆጣጠሯቸዋል። የኢትዮጵያ ዱር እንስሳ ጥበቃ ባለሥልጣን ፓርኮችን የመቆጣጠር የማልማትና በጎብኚዎች ተመራጭ እንዲሆኑ የማስተዋወቅ ኃላፊነትን ወስዶ ይሠራል።
ከሰሞኑም ከኃይለማርያምና ሮማን ፋውንዴሽን ጋር በመተባበር ለብዝሃ ሕይወት መጠበቅ፣ ለቱሪዝም እድገትና ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ብሎም ለአገር ገፅታ ግንባታ ከፍተኛ አበርክቶ ያላቸውን ሦስቱን ብሔራዊ ፓርኮች አስመልክቶ ያካሄደው መፍትሄ አመላካች ምክክርም አንዱ ነው። በውይይቱ የመንግሥትም ሆነ የግል ተቋማት ፓርኮቹ ከልዩ ልዩ ችግሮች የሚላቀቁበትን፣ በተሻለ ደረጃ የሚለሙበትንና ከስጋት ነፃ የሚሆኑበትን መንገድ ለመፈለግ እንደሚሠሩ ይፋ አድርገውበታል።
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ግንብት 21 ቀን 2014 ዓ.ም