በየቀኑ የተለያየ ጉዳይ እያነሱ ማብጠልጠል፤ አጀንዳ እየመዘዙ መኮነንና መንቀፍ እጅግ ቀሎናል። ላየነው ችግር መፍቻ ቁልፍ ከማመላከት ይልቅ ጉዳዩን መተቸትና ማነወር ልማድ አድርገናል። እርግጥ ነው የበዙ ስህተቶች መታረም ይገባቸዋል ማለታችን ትክክል ነው። ያልተገቡ ዝንፈቶች ቢቃኑ ማለታችን ቅንነት ነው። ነገር ግን እኛ ስህተቶችን ስናይ ለማረም የሚያስችሉ አስተያየቶችን ከመስጠት ይልቅ ስህተቱን ሠራ የምንለውን አካል ማብጠልጠል መሆኑ ነው ስህተታችን።
ከምስጋና ይልቅ ትችትና ነቀፌታ የሚቀናን ብዙዎች ነን። መልካም ነገር አይተን የማድነቅ አልያም ደግሞ የተግባሩ ባለቤትን ማመስገን ተራራ የመውጣት ያህል የሚከብደን እኛ አልፎ አልፎ የሚገጥመንና ለዚያውም በእኛ አተያይና አመለካከት ላይ ተመርኩዘን ልክ አይደለም ብለን ያመንበትን ነገር መተቸትና ማንኳሰስ እጅጉን ይቀለናል። እንዴት ይታረም የሚለው ጥያቄ ወደኛ አይቀርብም፣ እንዴት እንዘርጥጠው በምን ያህል ከባድ ቃል ላብጠልጥለው የሚለው ቀዳሚው እርምጃችን ይሆናል።
ለእኛ ስህተት ነው ብለን ላመንን የተዛነፈ ጉዳይ በምን መንገድ ይታረም የሚለው ዋንኛ ሀሳብ ጉዳያችን አይደለም። የጉዳዩ ልክ አለመሆን እንዴት አግዝፌ ለሌላው ልንገር፤ እንዴት አንኳስሼ የጉዳዩን መዛባት ላጉላና ላመላክት የሚለው ላይ ብዙ ሰዓት እንፈጃለን። ወገን ለእኛ ግን ተገቢ የነበረው ጉዳዩን ማብጠልጠልና ማንኳሰስ ሳይሆን በዚህ መንገድ ቢታረም የሚለው መፍትሔ አመላካች አቅጣጫ ጠቋሚ ሀሳብ ነበር። እሱ ነው የራቀብን። ያንን ነው መልመድ ያቃተን።
አብዛኞቻችን የተመለከትነው ስህተት አልያም ዝንፈት ልክ አለመሆኑን ብቻ እያነሳን ማብጠልጠል ማንኳሰስና መንቀፍ ትክክለኛ ተግባርም አድርገን ወስደንዋል። ወገን የምንፈልገው ስህተቱ እንዲታረምና መጥፎው ተግባር እንዳይደገም ማድረግ አልያም አሳዛኙ ድርጊት ማስቆም ከሆነ ትችትና ዘለፋ እንዴት መፍትሔ ሊሆን ይችላል። በፍፁም፤ ሊሆን አይችልም። ተግባር ግሳፄ አይገባም አይደለም ያልኩት፤ ስንገስፅ እንዳባቶች ወደፊት በምን መልክ መስተካከል እንዳለበትም እየጠቆምን መሆን አለበት ነው መነሻ ነጥቤ።
ምንኛ ከባድ ስህተት ነው ምነው ባላየሁት ያስባለን ተግባርም ቢሆን የሚስተካከልበትና ደግሞ እንዳይደረግ ወይም እንዳይደገም መፍትሔ ማመላከቱ፤ ከመዝለፍና የስህተት ፈፃሚው ከማነወር ከፍ ያለው ተግባር መፍትሔ ማመላከት ነው። ቀድሞም ዓላማችን ጉዳዩ እንዲታረም ከሆነ የያነውን ስህተት እዳይደገም ነው ወይስ ስህተት የሠራውን ሰው በማነወር ላይ ነው ትኩረት ማድረግ ያለብን? ዓላማችን ሁለተኛው ከሆነ ፍጹም ስህተት ውስጥ ነን። ነገር ግን መግራትን ዓላማችን ካደረግን አግሪ መፍትሔ ማቅረቡ ይመረጣል።
“አይ! ሳናውቅለት ለካስ እንዲህ ነው ጉዳዩ” ያስባለን ዛሬ ድረስ አልተረዳነውም እንጂ እውነት ላይ ነበር የቆመው ብንል ዘግይቶ ገብቶን እራሳቸውን በፈረድንበት ላይ የመሰከርንበት አጋጣሚ ብዙ ነው። እንዴት ሊሆን ቻለ? ምን አልባት የሆነ ምክንያት ቢኖረውስ አላልንም ነበር ያኔ። ዘግይቶ ጊዜ ካለፈ በኋላ ሲገለጥልን እህ እንዲህ ነው ለካ ብለናል ተባብለናል። ይህ የአንዱ ችኩል ፈራጅነታችን ማሳያ የምክንያት ሰጪነት አልያም ምን አልባት እኮ የሆነ ያልገባን ጉዳይ ሊኖር ይችላል የሚለው ምክንያታዊነት ከኛ ስለራቀ ነው።
አሁን አሁንማ የተላመደን ነገር ፤ በጅምላ አንድን ጉዳይ ተነስቶ ውርጅብኝ ማዝነብ ማብጠልጠልና መዝለፍ ሆኗል። ስህተቱ ትክክል ይሁን አይሁን ማረጋገጥ ሰከን ብሎ መመርመር ፈፅሞ አንወድም።
በእርግጥ እኛ ጋር አስተያየት ማለት የሰማነውና ያየነውን ጉዳይ ሳንመረምር እንዲሁ ፈርጀን ማለፍ ነቅፈን መተው ከእኛ ጋር ስለቆየና ስለተላመድነው ያንን ማድረግ ብርቃችን አይደለም። ብርቅ የሚሆንብን ከተቺዎች ነጠቅ ብለን ይሄ ጉዳይ ግን በዚህ መንገድ ቢታረም ብሎ የመፍትሔ ሀሳብ ማቅረብ ነው። ይሄ ነው የተለየም የገዘፈም ሀሳብ።
እሺ ስህተት አልያም ዝንፈት አይተን እንንቀፍ እንተች፤ ነገር ግን በዚያው ከምንዘጋው ስለምን እንዲህ ቢደረግ ብለንስ ስድብ ነቀፌታና ዝልፊያችን በመፍትሄ አናጅበውም? ወገን ትችትና ነቀፌታችን ከመፍትሔ ሀሳብ ጋር ቢሆን መግባባታችን ከፍ ይላል። ጉዳዩ የምንመለከትበት አተያይ ይለያያልና የነቀፍነው ጉዳይ ባለቤት በተሳሳተ መልኩ አይቶት ለእርሱ ትክክል የመሰለውን አድርጎ ከሆነ ያደረከው ትክክል አይደለም፤ ይሄንን እኮ በዚህ መልክ ማድረግ ትችል ነበር ብንል ምንኛ ያማረ ነው።
ባየነው ነገር ቅሬታችንን ለሚመለከተው ማሰማታችን፤ እንዲስተካከል የምንፈልገው ነገር ተበላሽቶ ስናይ ለምን ማለታችን መልካም ነው። መልካም ያልነው ተገቢ ያልሆነና ለማረም የማይመች ለማስተካከል የማያነሳሳ ትችትና ነቀፌታ እንጂ። ጉዳዮች እንዲቀኑ አስተያየታችን በጉዳዩ ላይ መፍትሔ አመላክቶ ቢያልፍ መልካም ነው። እኛም የምንፈልገውና እንዲሆንም የምንመኘው “ስህተት ነው” ያልነው ያን ስህተት መልሰን እንዳናይ፤ መጥፎ ያልነው ደግሞ እንዳይገጥመን ነውና ወደ መፍትሔው ብናነጣጥር።
በዚህ ወቅት ከስህተታችን ታርመን ወደ ትክክለኛው መንገድ መመለስ አገርና ሕዝብ ወደሚያቀናው ጎዳና ማምራት ከሁላችንም ይጠበቃል። የሰዎች ስህተት ለእኛ የሚገዝፍብን እኛ ንፁህ ነን ብለን ስለምናስብ ነው። ነገር ግን በአንድ መንገድ እኛም ስህተት ውስጥ ልንሆን እንችላለን።
የእኛ ስህተት ሰዎች ሲያመለክቱንም ሆነ እኛ ስህተት ነው ብለን የምናስበውን ጉዳይ የሚታረምበትን መንገድ ማመላከትና እንዲህ ቢታይም ማለትና መባል ቢለመድ ለመቅናታችን ቀላል መንገድ ይሆናል።
ፍጹምነት ላይ የቆመ እኔ ከምንም አይነት ስህተት ንፁሕ ነኝ የሚል ካለ ደግም የንፅሕናን ጥግ በወጉ ያልተገነዘበ ኃላፊነቱንና የሚጠበቅበትን በትክክል ያልተረዳ ይመስለኛል። ለሆነው፣ እየሆነ ላለውና ወደፊትም ለሚሆነው ሁሉ እኔ አንተና እነሱ በአንድም በሌላም መልኩ አስተዋፅዖ አለን። እናም ስህተቶችን ለማረም እንዲረዳን የስህተቶቹን ምንነት ተገንዝቦ ያንን ስህተት ለማረም የሚረዱ መፍትሔዎች መጠቆሙ ላይ ትኩረት እናድርግ። ያኔ ሕመማችን ሁሉ ይሽራል፤ስህተታችንም ይቀንሳል። አበቃሁ ቸር ይግጠመን።
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን ግንቦት 20/2014