እስከ ዛሬዋ እለት ድረስ በዓለማችን ብዙ የቫይረስ ዓይነቶች ተከስተው የብዙዎችን ሕይወት ነጥቀዋል። ዓለም ላይ አሉ የተባሉ ሳይንቲስቶች፣ የሕክምና ባለሙያዎችና ሌሎች ጠበብቶች ደግሞ ለእነዚህ ወረርሽኞች የሚሆኑ ክትባቶችንና መድኃኒቶችን ለማምረት ብዙ ሌሊቶችን እንቅልፍ አጥተው አሳልፈዋል። ብዙዎቹም ይህ ልፋታቸው ፍሬ አፍርቶ ለአንዳንዶቹ የመከላከያ ክትባት፤ ለሌሎቹ ደግሞ ፈዋሽ መድኃኒት እስከማግኘት የደረሰ ውጤትም አሳይተዋል።
የቅርብ ጊዜውን የኮቪድ-19 ወረርሽኝን እንኳን ብንመለከት ሳይታሰብ በአንዷ የቻይና ግዛት ላይ ተከስቶ በፍጥነት ዓለምን በማዳረስ እስከዛሬዋ እለት ድረስ ለብዙዎች መታመምና መሰቃየት፤ አለፍ ሲልም ውድ ሕይወትን መነጠቅ ምክንያት ሆኗል። ለዚህ አስከፊ ሕመም የዘርፉ ጠበብት ዝም ብለው አልተቀመጡም። በአጭር ጊዜ ውስጥ ውጤታማ የሆነ ክትባትን አግኝተው እነሆ አሁን ክትባቱ በመላው ዓለም ላይ ተሰራጭቶ ቫይረሱ ወረርሽኝ ከመሆን አስከፊ ደረጃው እንዲወርድም ሆኗል።
ዓለም ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ገና አላገገመችም፤ በየሀገሩ አሁንም ሰዎች በተህዋሱ እየተጎዱ ነው። በተህዋሱ የሚሞተው የሰው ቁጥርም እንዲሁ ቀላል አይደለም። በወረርሽኙ ሳቢያ በመላው ዓለም ከተከሰተው የኢኮኖሚ ድቀት ለማገገም ገና ዓመታትን መውሰዱ አይቀርም። ነገር ግን ይህችው ያልታደለች ዓለም ከኮሮና ወረርሽኝና የሩስያ ዩክሬን ጦርነት ከደቀኑት ስጋት ሳትላቀቅ ሌላ ፤ ምናልባትም አስፈሪ ስጋት ከፊት ለፊቷ ተደቅኖባታል። አዲስ የወረርሽኝ በሽታ ስጋት ፤ የዝንጀሮ ፈንጣጣ (መንኪ ፖክሰ)።
በብሪታኒያ ተከስቶ ወደ ሌሎች የዓለማችን ሀገራት እየተዛመተ ስለሚገኘው እና ምናልባትም በዓይነቱ አስፈሪ ስለሆነው የዝንጀሮ ፈንጣጣ በሽታ ወረርሽኝ ዓይነት እና ያሳደረውን ስጋት ስንመለከት በሽታው የሚከሰተው‹‹መንኪ ፖክስ›› በተባለ ቫይረስ ሲሆን ለፈንጣጣ (ስሞልፖክስ) ከሚያጋልጠው ቫይረስ ጋር ዝርያው ይቀራረባል። የዝንጀሮ ፈንጣጣ ቀድሞ ከነበረው ፈንጣጣ ጋር ሲነጻጸር ቫይረሱ የሚሰራጭበት ፍጥነት አናሳ ከመሆኑም በላይ ሕመሙም ያን ያህል የበረታ አይደለም።
የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያመለክተው የዝንጀሮ ፈንጣጣ ተህዋስ በዝንጀሮዎች ላይ መገኘቱ በምርመራ ለመጀመሪያ ጊዜ የተረጋገጠው እእአ በ1958 ዴንማርክ ውስጥ ሲሆን፤ መንኪ ፖክስ ወይም የዝንጀሮ ፈንጣጣ የሚለውን ስያሜ ያገኘውም ከዝንጀሮዎች በተወሰደ ናሙና ጋር ተያይዞ ነው። ቫይረሱ በሰዎች ላይ መኖሩ በምርመራ የተረጋገጠው ደግሞ እአአ በ1970፣ በኮንጎ ዲሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ በአንድ ሕጻን ላይ ነበር።
በሽታው በሰዎች ላይ መረጋገጡ ግማሽ ክፍል ዘመን ተሻግሯል። በሽታው ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፈው ሰውነት ላይ በሚገኝ የቁስል ንክኪ፣ ሌሎች የሰውነት ፈሳሾች ንክኪ፣ ከመተንፈሻ አካላት የሚወጡ ፈሳሾች፤ እንዲሁ፣ በሕመምተኛው ሰው በተበከሉ አልባሳት ንክኪ አማካኝነት እንደሆነ መረጃው ያመለክታል። የዝንጀሮ ፈንጣጣ ተሐዋሲ ከሰው ወደ ሰው ከተላለፈ በኋላ ከ 6 እስከ 13 ቀናት የሕመም ምልክት ሊያሳይ ይችላል።
በመካከለኛውና ምዕራብ አፍሪካ አገራት በገጠራማ አካባቢዎች በብዛት የታየው ይህ ቫይረስ በተለይም ጥቅጥቅ ያለ ደን ባለባቸው አካባቢዎች ላይ ተደጋግሞ እንደሚያጋጥም እየተነገረም ይገኛል። ቫይረሱ ሁለት ዓይነት ዝርያ ያለው ሲሆን፣ አንደኛው የምዕራብ አፍሪካው ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የማዕከላዊ አፍሪካው ነው። ብሪታኒያ ውስጥ ቫይረሱ ከተገኘባቸው ሰዎች ሁለቱ ከናይጄሪያ የተጓዙ ሲሆን፤ የተገኘባቸውም የምዕራብ አፍሪካው ቫይረስ ሊሆን የሚችልበት ዕድል ሰፊ መሆኑ ነው እየተነገረ ያለው።
በሌላ በኩልም እነዚህ ብሪታኒያ ላይ ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ቢረጋገጥም ከሌሎች ሰዎች ጋር ግን ይህ ነው የሚባል ግንኙነት እንዳልነበራቸውም ። ምንም ዓይነት ወደ ሌላ አገር የሄዱበት የጉዞ ታሪክም የላቸውም። ምናልባት ሰዎቹ ብሪታንያ ውስጥ ቫይረሱ ከተሰራጨ በኋላ በበሽታው እንደተያዙ ይገመታል።
ይህ ቫይረስ ሲከሰት የተለያዩ ምልክቶችን የሚያሳይ ሲሆን ከምልክቶቹ መካከልም ሙቀት (ትኩሳት)፣ ራስ ምታት፣ የጀርባ ሕመም፣ የጡንቻ ሕመም፣ የሰውነት እዚህም እዚያም ማበጥ እና በማንኛውም ነገር ላይ ፍላጎት ማጣት ጥቂቶቹ ናቸው። በተጨማሪም ሙቀቱ (ትኩሳቱ) ጋብ ሲል ሰውነት ከፊት ጀምሮ ማሳከክ ይጀምራል። መላው ሰውነትን ቢያሳክክም ክንድና እግር አካባቢ የበለጠ እንደሚያሳክክ የዓለም ጤና ድርጅት፤ እንዲሁም የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ያወጣው መረጃ ያመለክታል። የሚከሰተው እከክ በጣም የሚያምና በተለያየ ደረጃ የሚያልፍ ነው። ቆዳ ላይ የሚከሰተው እብጠት ኋላ ላይ ቆዳ እንዲቆስልና እንዲረግፍም ያደርጋል። ጠባሳ ጥሎም ሊያልፍ ይችላል።
ይህ የዝንጀሮ ፈንጣጣ ከማሳከክና ከመቁሰል በኋላ በራሱ ጊዜ የሚጠፋ እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን ምናልባትን ከ14 እስከ 21 ቀናት ውስጥ ሙሉ በሙሉ እንደሚድንም መረጃዎች ያመለክታሉ። በሽታው የተለያዩ የመተላለፊያ መንገዶች ያሉት ሲሆን በተለይም በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር የቅርብ ንክኪ ያላቸው ሰዎች ይበልጥ ተጋላጭ ናቸው። በሌላ በኩልም በቆዳችን ክፍተቶች በኩል፣ በዓይን፣ በአፍንጫ ወይም በአፍ በኩል ቫይረሱ ወደ ሰውነታችን ሊገባ እንደሚችልም ተገልጿል። በወሲብ ወቅት ባለ ንክኪ ቫይረሱ ይተላለፋል። በልብስ ወይም በሌሎችም ንክኪ ባላቸው ጨርቆችም የመተላለፊያው መንገድ ነው። ዋናው ግን በቫይረሱ ከተያዙ ዝንጀሮዎች፣ አይጦች ወይም ሌሎች እንስሳት ጋር ንክኪ ከተደረገ ቫይረሱ በቀላሉ ወደ ሰውነት በመግባት ለሕመም የመዳረግ እድል እንደሚኖረው ተገልጿል።
ቫይረሶች ምን ጊዜም ሰዎችን ለከፋ የጤና ጉዳት ከመዳረግ ጀምሮ ለሞት የማብቃትም ኃይል ያላቸው ናቸው። ነገር ግን የዝንጀሮ ፈንጣጣም ከሌሎች ቫይረሶች አንጻር የአስጊነት መጠኑ አናሳ ሲሆን አብዛኞቹ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ለከፋ ሕመም አይዳረጉም ይላሉ የዓለም ጤና ድርጅትና የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ያወጧቸው መረጃዎች።
ልክ እንደ ፈንጣጣ በተወሰኑ ሳምንታት ውስጥ ይረግፋል። ሆኖም ግን በሽታው ከፍተኛ ደረጃ ሊደርስም ይችላል። በምዕራብ አፍሪካ በበሽታው ሳቢያ የሞቱ ሰዎች አሉ። በቫይረሱ ከተያዘ ሰው ጋር ወሲብን ጨምሮ ማንኛውም ዓይነት ንክኪ ሲኖር የበሽታው የመተላለፍ ዕድል ያለው ሲሆን፣ በተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪ ወንዶች ዘንድ ለበሽታው የመጋለጥ ዕድልም ታይቷል።
ቫይረሱ ለመጀመሪያ ጊዜ የታየው በማቆያ ውስጥ ባለ ዝንጀሮ ላይ ነበር ያለው የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ እ.ኤ.አ ከ1970 ወዲህ በ10 የአፍሪካ አገራት በሽታው ተከስቷል። በ2003 በአሜሪካ ሲከሰት ከአፍሪካ ውጪ የመጀመሪያ ጊዜው ነበር። ወደ አገሪቱ ከገቡ እንስሳት ላይ አንድ ውሻ በቫይረሱ ተይዞ ነበር ሕመሙ የተነሳው። 81 ሰዎች በቫይረሱ ቢያዙም የሞተ ሰው አልነበረም።
አአአ በ2017 በናይጄሪያ ቫይረሱ በከፍተኛ ደረጃ ተሰራጭቶ 172 ሰዎች መያዛቸው ይታወሳል። 75 በመቶ ታማሚዎች ከ21 እስከ 40 ዓመት የሆናቸው ወንዶች ናቸው። ሕክምናውን በተመለከተም ሁለቱ ተቋማት ያወጧቸው የተለያዩ መረጃዎች ለበሽታው ምንም ዓይነት ሕክምና እንደሌለውም ይገልፃሉ። ነገር ግን ስርጭቱን ለመቆጣጠር ክትባቱ በሽታውን በመከላከል ረገድ 85 በመቶ ውጤታማ ሆኖ ተገኝቷል። ከብሪታኒያ የጤና ደኅንነት ተቋም የሚወጡ መረጃዎች እንደሚያሳዩትም በሀገሪቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ቫይረሱ ከተገኘበት ሰው ጋር ግንኙነት ከነበራቸው 50 ሰዎች መካከል አንዱ ብቻ በቫይረሱ ስለመያዙ ገልጿል፤ ይህ ደግሞ የቫይረሱ የስርጭት መጠን ውስን መሆኑን ያሳያልም ብለዋል።
የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እንዳስታወቀው፤ በአንዳንድ የዓለም አገራት የተከሰተውን የዝንጀሮ ፈንጣጣ በሽታ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገባ ለመከላከል የሚያስችሉ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥራዎች እየተሠሩ ነው። መንኪ ፖክስ በተሰኘው ቫይረስ የሚከሰተው የዝንጀሮ ፈንጣጣ ለመጀመሪያ ጊዜ የተከሰተው በምዕራብ አፍሪካ ሲሆን አሁን ላይ በሽታው ከ50 ዓመት በኋላ በምዕራቡ ዓለም ዳግም ብቅ ብሏል።
እስከ አሁን ስፔን፣ ፖርቹጋል፣ ጀርመን፣ ቤልጂየም፣ ፈረንሳይ፣ ኔዘርላንድስ፣ ጣሊያን፣ ስዊዘርላንድ፣ ስዊድን፣ ካናዳ፣ አሜሪካና አውስትራሊያ ቫይረሱ የተገኘባቸው ሀገራት ሆነዋል። በእነዚህ ሀገራት በቫይረሱ የተጠቁ ሰዎች 92 የደረሱ ሲሆን ሌሎች አገራት ለዝንጀሮ ፈንጣጣ ተጋላጭ እንዳይሆኑ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ የዓለም ጤና ድርጅት ማሳሰቡ ተገልጿል። የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩትም ይህንኑ ይደግመዋል፡፡
ይህንንም ተከትሎ ቫይረሱን ለመከላከል የሚያስችሉ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን ነው የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የገለጸው። ኢንስቲትዩቱ ኢትዮጵያ የበሽታውን ሥጋት ለመቀነስ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እያከናወነች መሆኑን ይገልጻል። በተለይም ኅብረተሰቡ ስለ ቫይረሱ በማስተማር በሽታውን አስቀድሞ ለመከላከል የሚያስችሉ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች መጀመራቸውም ተገልጿል። በዚህም ዜጎች ወደ ተለያዩ ሀገራት ጉዞ ሲያደርጉ ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ለተጓዦችና ለባለድርሻ አካላት ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ እየተሠራ መሆኑንም እንደዛው።
ቫይረሱ ቢከሰት እንኳን በቀላሉ ለመቆጣጠር ለትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎችና ተጠቃሚዎች፤ እንዲሁም ለሕክምና ባለሙያዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራው እየተሠራ ስለመሆኑም ኢንስቲትዩቱ አሳውቋል። ጎን ለጎንም አገሪቱን ከሌሎች አገራት ጋር በሚያገናኙ ድንበሮች ላይ ተገቢው ጥንቃቄ እንዲደረግ የቅኝት ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን አሳውቋል ።
ኅብረተሰቡ የበሽታውን ምልክቶች በሚያይበት ጊዜ በቅርብ ላለ ጤና ተቋም፤ እንዲሁም በነጻ የስልክ መስመር በ8335 እንዲያሳውቅ ኢንስቲትዩቱ አሳስቧል።
እፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን ግንቦት 20/2014