የማህበራዊ ጤና እጅግ በጣም ሰፊ እና ትርጉሙም ከቦታ ቦታ፣ ከአመለካከት አመለካከት የሚለያይ ነው፡፡ ነገር ግን በአብዛኛው ማህበረሰብ እንዲሁም የማህበራዊ ጤና ባለሞያዎች ማህበራዊ ጤናን በዚህ ጠቅለል ባለ መልኩ ለመተርጎም ችለዋል፡፡ ማህበራዊ ጤና ማለት የሰዎች ወይም የማህበረሰብ ትርጉም ያለው የእርሰ በእርስ ጤናማ እና ምርታማ የሆነ ግንኙነት ወይም የግንኙነት መንገድ ማለት ነው፡፡ ሰዎች በዙሪያቸው ከሚገኙ ሰዎች ጋር የሚኖራቸው እራስን የማላመድ፣ እራስን ከማህበረሰብ ጋራ የማገናኘት አቅምን፣ የማህበረሰቡ አንድ አካል የመሆን ስሜትን ያካተተ ነው፡፡
የማህበራዊ ጤና ጥቅም
የማህበራዊ ጤና ለሰዎች ጤና ወሳኝ ከሚባሉ የጤና ዘርፎች ውስጥ አንዱ ነው፡ ፡ ለዚህም የዓለም የጤና ድርጅት (WHO) የጤናን ትርጉም ሲሰጥ ማህበራዊ ጤና እንደ አንድ ዋነኛ የጤና ግብዓት አድርጎ ነው የወሰደው ። ለትውስታ ያክል እ.አ.አ በ1948 (WHO) ጤናን በዚህ መልክ ተርጉሞ አስቀምጦታል፡፡ «ጤና ማለት የህመም አለመኖር ማለት ሳይሆ ን ሰዎች በአካላዊ፣ በአዕምሯዊ፣ እንዲሁም በማህበራዊ ግንኙነታቸው የሚኖራቸው የጤንነት ወይም የደህንነት ስሜት ማለት ነው» ከዚህም በመነሳት ሰዎች በማህበራዊ ጤና የሚኖራቸው ስሜት እራሳቸውን ከአካላዊውም ሀነ ከአዕምሯዊው ጤና እራሳቸውን ለመጠበቅ ይረዳቸዋል፡፡
አንዳንድ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ሰዎች የማህበራዊ ጤናቸው የታወከ እንደሆነ ከአዕምሯዊው ጤና ጋር በቀጥታ እንደሚገናኝ እና አልፎ ተርፎም ለአካላዊ ጤና መታወክ እንደሚዳረጉ ያሳያሉ። ለምሳሌ ያክል በማህበራዊ ጤና መጓደል የተነሳ ለአዕምሯዊው ጤና መታወክ እንደ (ድብርት፣የእንቅልፍ ማጣት፣ለጭንቀት፣)የመሳሰሉት አይነት የአዕምሯዊው ጤና እክሎች በስፋት ሲጠቁ ታይተዋል፡፡ በሌላ መልኩ ደግሞ ሰዎች በማህበራዊ ግንኙነታቸው ጤናማ ግንኙነት አላቸው ተብሎ የሚታሰቡ ሰዎች ለ (ስኳር ህመም፣ ለልብ ህመም፣ ለደም ግፊት የመጋለጥ እድላቸው እጅግ አነስተኛ ነው)
የማህበራዊ ጤና ከአዕምሯዊው ጤና በጣም ከፍተኛ የሚባል ግንኙነት ያለው ነው፡፡ በአዕምሯዊው ጤና መታወክ ያላቸው ሰዎች ከማህበረሰብ ጋር የሚኖራቸው ጤናማ ግንኙነት በቀላሉ የሚታወክ እና መልሰው ለማህበረሰባዊ ጤና መታወክ የመጋለጥ እድላቸውን በሰፊው ይጨምረዋል፡፡ ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነን ‹‹የድብርት ወይንም ድባቴ›› የምንለው የአዕምሮ ህመም ከዋና መግለጫዎች አንዱ ብቸኝነት እና ህይወትን አጨልሞ የማየት ሁኔታ ነው፡፡ የዚህ ህመም ያላቸው ሰዎች እራሳቸውን ከማንኛውም መሰረታዊ ግንኙነት የሚያርቁ ናቸው። በተጨማሪ የህይወትን ትርጉም ከማሳጣታቸው እና ከጨለምተኝነት ባህሪያቸው የተነሳ ከሰዎች ጋር ያላቸውን ግንኙነት በበጎ የሚያዩ አይደሉም ። በዚህም ምክንያት ከማህበረሰቡ የመገለል፣ማህበረሰቡም እነርሱን የማግለል ሁኔታ ይፈጥራል ።
ከላይ የተጠቀሱት የማህበራዊ ጤና እና የአዕምሯዊ ጤና ግንኙነት በጣም የጠነከረ ይሁን እንጂ ማህበራዊ ጤና ከአካላዊ ጤና ምንም አይነት ግንኙነት የላቸውም ማለት አይደለም፡፡ ለዚህም አንድ አንድ የአካላዊ ህመሞች የሰውነት ገፅታን ወይም አቋምን የሚያበላሹ ህመሞች (የቆዳ ችግር፣ የአካል ጉዳተኝነት) ወዘተ…በማህበራዊ ኑሮ ላይ የሚፈጥሩት አሉታዊ ተፅእኖ እጅግ ከባድ ነው፡፡
ለማጠቃለያ ያክል ማህበራዊ ጤና እጅግ አስፈላጊ እና ከሌሎች የጤና አይነቶች (አካላዊ እና አዕምሯዊ ጤና) ጋር ተናንሶ የማይታይ የጤና ዘርፍ በመሆኑ ሰዎች ለሁለቱ የጤና አይነቶች የሚሰጠውን ትኩረት ያህል ለማህበራዊ ጤና ያልተናነሰ ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ ሰዎች በማህበራዊ ጤና መታወክ ሲያጋጥማቸው ወደ ስነ አዕምሮ ሀኪም በመሄድ ችግራቸውን በመናገር መፍትሄ ሊያገኙ ይገባቸዋል፡፡ ማህበራዊ ጤና እንደማንኛውም የጤና አይነት መታከም የሚችል አንድ የጤና አይነት ነው፡፡
አዲስ ዘመን ቅዳሜ መጋቢት 14/2011