የኪነ ጥበብ ባለሙያው አምጦ የወለደውን ኪናዊ ሥራው ታዳሚ ጋር ሲደርስለት የመጀመሪያ ደስታው ይሆናል። ያ በብዙ ጥረቱ ከሽኖ ያቀረበውን የኪነት ውጤቱን በተደራሲው ተወዶለት መልካም የሆነ አስተያየት ሲሰጠው ብሎም ሥራህን ጥሩ አድርገህ ሰርተሀልና ምስጋናና ሸልማት እንካልህ ሲባል ፍስሀው ጥግ ይደርሳል። በእርግጥም በሠሩት ሥራ መሸለም በጥረት ልክ ምስጋናን ማግኘት የለውጥ ማቀጣጠያ አንዱ ምክንያት መሆኑን ብዙዎች ያምናሉ። በአገራችን የኪነ ጥበብ ባለሙያውን ለማበረታታት ታስቦ በየዓመቱ እየተካሄዱ ያሉ ሙያዊ ሽልማቶች ለኪነ ጥበቡ እድገት አዎንታዊ ሚና እየተጫወቱ መሆኑን ከሥራዎቹ ለውጥ እና እድገት መረዳት ይቻላል።
በአገር ውስጥ በኪነ ጥበቡ ዘርፍ በየዓመቱ ከሚዘጋጁ የሽልማት ዓይነቶች ውስጥ አንዱ ነው፤ ‹‹ጉማ ሽልማት›› ስያሜው በኢትዮጵያ የመጀመሪያ ከሆነው ባለ ቀለም ፊልም ‹‹ጉማ›› የወሰደው ጉማ ሽልማት(አዋርድ) ዘንድሮ ለ8 ጊዜ በደማቅ ሁኔታ የኪነጥበብ ሥራዎች በተለይም በፊልሙ ዘርፍ የዓመቱ ምርጥ ያላቸውን ሸልሟል። ጉማ ሽልማት ለስምንት ተከታታይ ዓመታት የፊልም ባለሙያዎችን ሲሸልም በሙያቸው ባሳዩት ትጋት ሲያበረታታ ቆይቷል። በዚህም በፊልም ሥራ ዘርፍ ጥሩ መነቃቃት መፍጠርም ችሏል።
ጉማ የኪነጥበብ ባለሙያዎች ሥራ በባለሙያዎች አስመርጦ አድማጭ ተመልካችን አሳትፎ ኪነ ጥበባዊ ፈጠራን የሚያበረታታና የሚሸልምበት ይህ ታላቅ ዝግጅቱ ዘንድሮ ከወትሮው በተሻለ ድምቀትና ከዚህ ቀደም ከነበሩት ሽልማቶች ከፍ ያለ ቁጥር ባላቸው ዘርፎች ጥበበኛው ከታዳሚው ምስጋና ያገኘበት ትልቅ መድረክ ነው። በመድረኮቹ ላይ ከተላለፉ መልዕክቶች በተጨማሪ ለሽልማቱ በክብር ተጠርተው የነበሩ እንግዶችና አርቲስቶች በተለያየ መልኩ ያንፀባረቁት ልዩ ልዩ መልዕክት መድረኩን አድምቆት አምሽቷል።
በእርግጥ ከሽልማት ሥነሥርዓቱ ጋር ተያይዞ የሚካሄዱ የፎቶና የልዩ ልዩ መርሀ ግብሮች ጉማ አዋርድን ወትሮም የተለየ ያደርጉታል። አርቲስቶች በፎቶ ግራፍ ሥነ ሥርዓትና በመድረክ ላይ እየቀረቡ የሚያስተላልፉት መልዕክት የመድረኩን አጓጊነት ከፍ አድርጎት ታይቷል። በዚህ ጥበብ ከብሮ ባለጥበቡ ነግሶ ባመሸበት የሽልማት መድረክ ላይ፤ አገራዊ ፍቅንና ሰላምን የሚሰብኩ አንድነትና መተባበርን የሚነግሩ ፆታዊ ጥቃትንና ትንኮሳን የሚኮንኑ መልዕክቶች ተንፀባርቀዋል።
ባለፈው ዓመት በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ሳይካሄድ የቀረው የጉማ ሽልማት ዘንድሮው ስምንተኛ የሽልማት መርሀ ግብሩን ባሳለፍነው ሐሙስ ሲያከናውን የተመረጡ አገርኛ ፊልሞች ለውድድር ቀርበው ለመሸለም በቅተዋል። ጉማ ሽልማቱ ከሚሰጥበት ዓመት ቀድሞ ተሠርተው በተለያዩ ሲኒማ ቤቶች ለሕዝብ እይታ የበቁ ፊልሞችን ነው የሚሸልመው። በዚህ በየአመቱ በሚካሄደው የፊልም ሽልማት ባለፈው ዓመት ማለትም በ2013 ዓ.ም ተሠርተው በአገራችን የተለያዩ ሲኒማ ቤቶች ላይ ለሕዝብ እይታ የበቁ ፊልሞች አወዳድሮ ሸልሟል።
በዚህ ሂደት ባለፉት 7 ዙሮች ፊልሞችን በባለሙያዎች አወዳድሮ ሥራቸውን መርጦና ለፊልም ባለሙያው ሽልማት ሲሰጥ በቆየው ጉማ አዋርድ ዘንደሮም ለስምንተኛ ጊዜ 22 የተመረጡ ፊልሞችን አወዳድሮ በ14 የተለያየ የፊልም ጥበብና ዘውግ ዕጩ አድርጎ በማቅረብ እውቅናና ሽልማት አበርክቷል።
ቀደም ባሉት ዓመታት ይሰጡ ከነበሩት የሽልማት ዘርፎች ውሰጥ ያልነበረውና በብዙዎች ለምን ይህ ዘርፍ ሳይካተት ቀረ በሚል የሚነሳው ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ ዘርፍ አንዱ ነበር። ከዚህ በተጨማሪም የሄርሜላ ልዬ ዕጣ የተሰኘ ሽልማትም ባልተለመደ መልኩ የተካሄደ ሽልማት ሆኖ አልፏል። ጉማ ሽልማቱ በሥራው እጅጉን አድካሚና ጥረት የሚጠይቀውን ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ ዘርፍ ከወትሮው በተለየ መልክ የሽልማት ዘርፍ አድርጎ ማካተቱ በባለሙያዎች ከፍተኛ አድናቆት አግኝቷል።
በጉማ ሽልማት ታጭተው የቀረቡ ፊልሞች በተለያየ ዘርፍ ብርቱ ፉክክር አድርገው የነበረ ሲሆን በተለይም አንድ ሆነው በልዩ ልዩ ዘርፎች ዕጩ ሆነው የቀረቡም ፊልሞች ነበሩ። በአንድ ዘርፍ የታጩ ገናዡ፣ስለመናና ሲሳይ ነው የተሰኙ 3 ፊልሞች ሲሆኑ፣ በሁለት ዘርፍ ታጭቶ የነበረው ደግሞ እንደዚህ እንደዚያ የተሰኘ ፊልም ነው። በአራት ዘርፍ የታጩት ሚስት ጨርሰናል 2 እና ሊያት ሲሆኑ በአምስት ዘርፍ የታጩት 4 ፊልሞች ተካተዋል። የፍቅር ጥግ የሚል ርእስ የተሰጠው ፊልም ደግሞ በአስራ አንድ ዘርፍ በመታጨት በመድረኩ ላይ ደምቆ አምሽቷል።
8ኛው ጉማ ሽልማት አሸናፊዎች
የዚህ ደማቅ መድረክ የክብር ሙሽሮች የሆኑት የዕለቱ አሸናፊዎች መድረክ ላይ አጓጊ በሆነ ትዕይንት ታጅበው ሽልማታቸውን ተቀብለዋል። የሕይወት ዘመን ተሸላሚ ፕሮፌሰር ሰሌማ መኩሪያ ሆነዋል። የተማሪዎች አጭር ፊልም ተሸላሚ (መባ) አብርሃም ከበረ ሲሆን በምርጥ አጭር ፊልም ዘርፍ (አይቀር) አሸናፊ መስፍን በመሆን ሽልማቱን ወስደዋል። በምርጥ ዶክመንተሪ ፊልም በኢቢሲ የተሠራው የውበት ሻማ የተሰኘው የፍቃዱ ከምባታ ሥራ አሸናፊ ሆኗል።
ተከታታይ ድራማ ዘርፍ
ምርጥ የተከታታይ ድራማ ጽሑፍ (እረኛዬ) ቤዛ፣ አዜብ እና ቅድስት በመሆን የአሸናፊነት ክብሩን ሲቀዳጁ፣ በምርጥ ተከታታይ ድራማ ተዋናይት ዘርፍ ሳያት ደምሴ ከእረኛዬ ድራማ በመሆን ተመርጠዋል። የዚህ ዘርፍ አሸናፊዋ ሳያት ደምሴ ሽልማቱን በራሷ ምክንያት እንደማትቀበል በመግለጿም የጉማ አዋርድ ልዩ ገጠመኝም ሆኖ አልፏል።
ምርጥ ተከታታይ ድራማ ተዋናይ ብርሃኑ ድጋፌ ከእግር እሳት ድራማ ሽልማት የተቀበለ ሲሆን፣ ምርጥ ሲትኮም 9ኛው ሺ ሆነው ተመርጠዋል። እንዲሁም ምርጥ ተከታታይ ድራማ ዳይሬክተር አብርሃም ገዛኸኝ ከእግር እሳት ድራማ ሲመረጥ ምርጥ ተከታታይ ድራማ እረኛዬ በመሆን አሸናፊ ሆነዋል።
በፊልም ዘርፍ
በዚህ ዘርፍ ብርቱ የሆነ ፉክክር የተደረገበት ሲሆን በመጨረሻም መድረኩ ላይ የተመረጡ የዘርፉ የዓመቱ አሸናፊዎች በክብር ሽልማታቸውን ተቀዳጅተዋል። በዚህም በምርጥ ፊልም ማን ያዘዋል፣ በምርጥ ዳይሬክተር ኑር አክመል በራሱ በማን ያዘዋል ፊልም የተመረጡ ሲሆን የዓመቱ ምርጥ ተዋናይ በመሆን ሽልማት የተቀዳጀው እንግዳሰው ሀብቴ (ቴዲ) በግዛት ፊልም ነበር።
የዚሁ ዘርፍ የዓመቱ ምርት ሴት ተዋናይት አምለሰት ሙጬ በምን አለሽ ፊልም አሸናፊ በመሆን የተመረጠች ሲሆን፣ በምርጥ የፊልም ጽሑፍ አንተነህ ኃይሌ ስንብት በተሰኘው ተወዳጅ ፊልም አሸናፊ ሆኗል። በየአመቱ በጉማ ሽልማት የሚካሄደው አንድ ምርጥ በተመልካች ምርጫ መሠረት የፍቅር ጥግ ፊልም ማሸነፍ ችሏል።
ምርጥ ድምፅ አብርሃም ዳንኤል በከርቤ ፊልም የተመረጠ ሲሆን፣ በምርጥ ኤዲተር ዳንኤል ግርማ በምን አለሽ ፊልም አሸናፊ ሆነዋል። ምርጥ የፊልም (ስኮር) ጆርካ መስፍን በምን አለሽ ፊልም የተመረጠ ሲሆን በምርጥ ማጀቢያ ሙዚቃ ደግሞ እሱባለው ይታየው የፍቅር ጥግ በተሰኘ ፊልም የዓመቱ ምርጥ በመሰኘት ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
በምርጥ ሲኒማቶግራፈር ዳንኤል ግርማ በስንብት ፊልም ሲመረጥ፣ በምርጥ ሜክአፕ ዳግማዊ አለማየሁ በምን አለሽ ፊልም የዓመቱን ክብር ተቀዳጅተዋል። እንዲሁም ተስፋ የተጣለባት ተዋናይት ሕፃን መቅደላዊት አስተርይ በየፍቅር ጥግ ፊልም፣ ተስፋ የተጣለበት ተዋናይ ሕፃን ሳሙኤል ወንድይፍራው በስንብት ፊልም አሸናፊ ሆነዋል። ምርጥ ረዳት ተዋናይት እታፈራሁ መብራቴ በማንያዘዋል ፊልም አሸናፊ ስትሆን ምርጥ ረዳት ተዋናይ ሽመልስ አበራ በየፍቅር ጥግ ፊልም አሸናፊ መሆን ችለዋል። በዚሁ አመት የተጀመረው ሴት ፊልም ሰሪዎችን ለማበረታት የሚሰጠው ሽልማት የመጀመሪያ ተሻለሚ አለምፀሐይ በቀለ በመሆን ከመድረኩ ሽልማቷን ተቀብላለች።
የሽልማቱ ፋይዳ በአርቲስቶች አንደበት
በአሁኑ ወቅት በአገር ደረጃ በተለይም በፊልም መስክ እየተበራከቱ ያሉ ሽልማቶች ለፊልም ሥራው እድገት ያለው ሚና ላቅ ያለ እንደሆነ አያጠያይቅም። በጉማና መሰል ሽልማት ለኪነጥበቡ እድገት ከፍተኛ መሆኑ በሽልማት መድረኩ ላይ ተገኝተው አስተያየታቸውን የሰጡ የፊልም ባለሙያዎችም ነበሩ።
የጉማ ሽልማት ላይ ተገኝተው አስተያየት ከሰጡት መካከል ደራሲና ዳይሬክተር ቢኒያም ወርቁ፣ የኪነጥበብ ባለሙያው በመሸለሙ ብርታትን ያገኛል በማለት ሃሳቡን ገልጿል። ሽልማቱ የፊልም ባለሙያው ለሌላ የተሻለ ሥራ እራሱን የማዘጋጃ መንገድ ይሆነዋል፤ በማለት ጠቀሜታውን አስረድቷል። በኮቪድ-19 ምክንያት ቀዝቅዞ የነበረውን የፊልም ዘርፍ ለማነቃቃትና ወደፊት ዘርፉ የሚፈለገውን ያህል ጠቀሜታ ያበረክት ዘንድ መሰል ሽልማቶችና ማበረታቻዎች ሊቀጥሉ እንደሚገባም አስተያየቱን ሰጥቷል።
በዚሁ መድረክ ላይ ከተገኙት የፊልም ባለሙያዎች መካከል አንዱ አርቲስት ሰራዊት ፍቅሬ፣ ጉማ የኪነጥበብ ባለሙያዎች የሚገናኙበት መድረክ ከመሆኑ በተጨማሪ ፊልም ሰሪው የሥራውን ውጤት የሚያይበትና ለጥረቱ ሽልማት የሚያገኝበት መሆኑን ተናግሯል። መሰል የፊልም ሥራ ሽልማቶች ለዘርፉ ዕድገት ያላቸው ጠቀሜታ የጎላ መሆኑና በተለያዩ ምክንያቶች ተቀዛቅዞ የነበረውን የፊልም መስክ የማነቃቃት አቅም እንዳላቸውም ጠቅሷል።
በሽልማቱ ላይ ዕጩ የነበረችው ተዋናይት ሀና መርሀፅድቅ በበኩሏ፣ መሰል የሽልማት መድረኮች መከናወናቸው በሙያው ላይ የሚሳተፉ የፊልም ባለሙያዎችና ተዋንያን እጅጉን የሚያበረታና በሥራዎቻቸው ጠንካራ እንዲሆኑ መነሳሳትን የሚፈጥር መሆኑ ገልፃለች። በተለይም ባለሙያው በሥራው ተግቶ እንዲሠራና ሙያዊ ክህሎቱን ለማሳደግ ብሎም የተሻሉ ሥራዎችን ሕዝብ ጋር ለማድረስ እንዲተጋ ያደርገዋል ስትል ተዋናይት ሀና ተናግራለች።
እጅጉን አበረታች ሂደት ላይ የነበረው የፊልም ዘርፍ ባለፉት ጥቂት አመታት በተለያዩ ምክንያች መቀዛቀዝ ገጥሞት እንደነበረ የሚናገሩት ባለሙያዎቹ፤ በኪነ ጥበቡ ዘንድ የሚዘጋጁ መሰል ሽልማቶችና ማበረታቻዎች ለዘርፉ መነቃቃት ያላቸው ሚና የጎላ መሆኑን ያስረዳሉ። ትኩረት ተሰጥቶ ከተሠራበት ማህበረሰብ ብሎም አገርን በአስተሳሰብና በኢኮኖሚ የላቀ ለውጥ ማምጣት የሚያስችለው የፊልም መስክ ለማበረታታትና ለማሳደግ መሰል ማበረታቻዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ይታመናል።
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን ግንቦት 18 ቀን 2014 ዓ.ም