በአፍሪካ አህጉር ዋነኛ ገብስ አምራች ከሆኑ አገራት መካከል ከቀዳሚዎቹ ተርታ የምትመደበው ኢትዮጵያ፣ ይህን ምርት በግብዓትነት የሚጠቀሙት የቢራ ፋብሪካዎቿ አብዛኛውን የብቅል ፍላጎታቸውን የሚያሟሉት ከውጭ አገራት በሚገባ ምርት መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ። በአገሪቱ የሚፈለገውን ያህል ምርት የሚያቀርቡ የብቅል ፋብሪካዎች ካለመኖራቸው ባሻገር ዘመናዊ የአስተራረስ ዘዴን ያለመከተልና አርሶ አደሮች ለፋብሪካዎች የሚያቀርቡት የብቅል ገብስ በሕገ-ወጥ ነጋዴዎች መወሰድ ለብቅል አቅርቦቱ ዝቅተኛ መሆን የሚጠቀሱ ሌሎች ምክንያቶች ናቸው። በዚህም የተነሳ የአገሪቱ የቢራ ፋብሪካዎች አብዛኛውን የብቅል ገብስ ፍላጎታቸውን የሚያሟሉት በውጭ ምንዛሬ ከውጭ አገራት ገዝተው በማስገባት ነው።
አገሪቱ አብዛኛውን ብቅል ከውጭ ማስገባቷ ተደራቢ በሆነ የውጭ ምንዛሬ እጥረት እንድትቸገር ከማድረጉም ባሻገር አርሶ አደሮች ለፍተው ካመረቱት ገብስ የሚገባቸውን ያህል ተጠቃሚ እንዳይሆኑም ያደርጋል። ከዚህ በተጨማሪም ይህ በብቅል አቅርቦት ሰንሰለት ላይ የሚታየው ችግር ለቢራ ዋጋ መናርም የራሱን ሚና መጫወቱ አይቀርም። ይህ በብቅል አቅርቦትና ፍላጎት መካከል ያለው አለመመጣጠን አገሪቱ ግዙፉን የምርት አቅሟን ተጠቅማ ለዘርፉ አዳጊ ፍላጎት በቂ ምላሽ እንዳትሰጥ መሰናክል ሆኖባታል። ስለሆነም በቢራ ብቅል አቅርቦት ላይ ላሉ ችግሮች መፍትሄ መፈለግ ከውጭ ምንዛሬ እጥረት፣ ከአርሶ አደሮች ተጠቃሚነትና ከዋጋ ንረት አንፃር ለሚፈጠሩ ችግሮችም መፍትሄ መፈለግ ተደርጎ ይቆጠራል።
ብቅልን በአገር ውስጥ በማምረት ከላይ የተጠቀሱትን ችግሮች ያቃልላል የተባለ የብቅል ፋብሪካ በኢትዮጵያ ተገንብቶ በቅርቡ ሙሉ በሙሉ ወደ ማምረት ተሸጋግሯል። ኢንቪቮ ግሩፕ (InVivo Group) የተባለው ግዙፍ የፈረንሳይ የግብርና ዘርፍ ድርጅት በባለቤትነት ከያዛቸው ተቋማት መካከል አንዱ የሆነው ሱፍሌ ማልት ግሩፕ (Malteries Soufflet) ያስገነባው ይህ ሱፍሌ ማልት ኢትዮጵያ ፋብሪካ (Soufflet Malt Ethiopia) ከሁለት ሳምንታት በፊት ተመርቆ ለአገልግሎት በቅቷል።
ሱፍሌ ማልት ኢትዮጵያ ማምረት የጀመረው ባለፈው ዓመት ሲሆን፣ ሱፍሌ ማልት ግሩፕ በአፍሪካ ምድር የገነባው የመጀመሪያው የብቅል ፋብሪካም ሆኗል። ፋብሪካው በቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ በ10 ሄክታር መሬት ላይ የተገነባ ሲሆን፣ በዓመት 60ሺ ቶን ብቅል የማምረት አቅም አለው። ከዚህ በተጨማሪም ፋብሪካው ይህን አቅሙን ወደ 110ሺ ቶን የማሳደግ እቅድ ይዟል።
75 በመቶ የሚሆነውን ግብዓት ከኢትዮጵያውያን አርሶ አደሮች እየተቀበለ የሚገኘው ይህ ፋብሪካ፣ ለቢራ ምርት የሚያስፈልገውን ብቅል ከማምረት በተጨማሪ ገብስ ከአርሶ አደሮች እየተቀበለ ለአርሶ አደሮቹ የንግድ ትስስር እንዲፈጠርላቸው አድርጓል። ፋብሪካው ከ50ሺ የገብስ አምራች አርሶ አደሮች ጋር የገበያ ትስስር በመፍጠር በአመት 80ሺ ቶን ገብስ ለፋብሪካው እንዲያቀርቡም የገበያ ዕድልን መፍጠር ችሏል። ወቅቱ የደረሰበትን ቴክኖሎጂ ይጠቀማል የተባለው ፋብሪካው፣ በውሃ ኃይል ከሚሠሩ የኤሌክትሪክ ማመንጫዎች የሚገኝ ኃይል ስለሚጠቀም ከካርበን ልቀት ነፃ እንደሆነም ተነግሯል።
በፋብሪካው የምርቃ ሥነ ሥርዓት ላይ የተገኙት የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ፣ ሱፍሌ ማልት ተጨባጭ አቅም ያላቸው እንዲሁም ባስቀመጡት የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ሥራቸውን መፈፀም የሚችሉ የፈረንሳይ ድርጅቶች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው በኢንቨስትመንት እንዲሰማሩ በቀረበው ጥሪና በተገባው ቃል መሠረት ወደ አገር ውስጥ ከገቡት ኩባንያዎች መካከል አንዱ መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ከአብዛኛዎቹ የአፍሪካ አገራት በተሻለ ለኢንቨስትመንት በእጅጉ ምቹ መሆኗን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ‹‹በብዙ የአፍሪካ አገራት ለኢንቨስትመንት የሚውል መሬት ከመንግሥት ጋር ተዋውሎ ማግኘት አስቸጋሪ ነው። በአንጻሩ በኢትዮጵያ ይህን የመሬት ዕድል ማግኘት ይቻላል። በኢትዮጵያ አምራቾች የሚያስፈልጋቸውን የኤሌክትሪክ ኃይል በጣም በረከሰ ዋጋና በቀላሉ ማግኘት ይችላሉ። ኢትዮጵያ የተማሩና በፍጥነት መማር የሚችሉ እንዲሁም ፋብሪካን ማሠራትና ኢንዱስትሪውን ማገዝ የሚችሉ በርካታ ወጣቶች አሏት። አገሪቱ ትልቅ ገበያ መሆኗም ለኢንቨስትመንት ምቹ ያደርጋታል›› ብለዋል። ስለሆነም ኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ የሚፈልጉ ቁርጠኛ ባለሀብቶችን ለመቀበልና ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር ዝግጁ እንደሆነች ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ ገልፀዋል።
አምራቾች በአገር ውስጥ የተዘጋጀን ምርት እንደሌሎች አገራት ወደ ውጭ መላክ ብቻ ሳይሆን ምርታቸውን በአገር ውስጥ ገበያ የማቅረብም ሰፊ ዕድል እንዳላቸውም ተናግረዋል። ‹‹ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡት ኢንቨስተሮችም መጠቀም ብቻ ሳይሆን አገራችንንም መጥቀም የሚችሉ መሆን አለባቸው፤ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ስንገነባ ብዙ ሀብት ስላፈሰስንባቸው ውጤቱን ማየት እንፈልጋለን›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ መንግሥት በበኩሉ ወጪ አውጥቶ ለኢንቨስተሮች የሚሆን መሠረተ ልማት እንደሚያሟላ ገልፀዋል።
‹‹ለፋብሪካው የሚያስፈልገውን የገብስ ግብዓት ሙሉ በሙሉ ከአገር ውስጥ ማዘጋጀት ስለሚቻል አንድም ኪሎ ገብስ ከውጭ እንዲገባ አናደርግም›› ብለዋል። ‹‹ለግብዓቱ የሚሆን በቂ ውሃና መሬት አለን፤ የግብርና ማሽኖችንም እያስገባን ነው፤ ለአዲሱ ፋብሪካ ብቻ ሳይሆን ለሁሉም የብቅል ፋብሪካዎች የሚሆን ግብዓት ከአገር ውስጥ እንዲጠቀሙ እናደርጋለን፤ መንግሥትም አስፈላጊውን ክትትልና ድጋፍ ያደርጋል›› ሲሉ ቃል ገብተዋል።
የኢንቪቮ ግሩፕ ሊቀ መንበር ፊሊፕ ማዢን ኢትዮጵያ በገብስ ምርት ከፍተኛ አቅም ያላት አገር መሆኗን ጠቅሰው፣ ይህን አቅም ተጠቅሞ ምርት ማሳደግ እንደሚያስፈልግ ይገልጻሉ። ፋብሪካው በ60 ሚሊዮን ዩሮ እንደተገነባ የጠቆሙት ሊቀ መንበሩ፣ በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ውስጥ በብቅል ምርት ራስን ለመቻል የሚደረገውን ጥረት የማገዝና የማሳካት እቅድ እንዳለውም ተናግረዋል።
እንደርሳቸው ማብራሪያ፣ ፋብሪካው በአቅርቦት ሰንሰለቱ ውስጥ ያሉትን ከውጭ የሚገቡ ግብዓቶችን በአገር ውስጥ ለማምረትና አገር በቀል ምርቶችን ለመጠቀም የሚያስችል ፕሮጀክት እየተገበረ ነው። በዚህም በአካባቢው አርሶ አደሮች የሚመረት ገብስ በመጠቀም ምርቱን ለቢራ ፋብሪካዎች እያቀረበ ይገኛል። ይህም በአሁኑ ወቅት እስከ 70 በመቶ የሚሸፍነውንና ከውጭ የሚገባውን የግብዓት ግዢ ለማስቀረት ያስችላል።
ድርጅቱ ከሁለት ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ በማድረግ የአርሶ አደሮችን ምርታማነት ለማሳደግ የሚያግዙ ተግባራትን አከናውኗል። በዚህ ተግባሩም የእርሻና የንግድ ባለሙያዎችን በመመደብ ከ50ሺ በላይ ለሚሆኑ አርሶ አደሮች ልዩ ልዩ ድጋፎችን አድርጓል። የምርቱንና የግብዓቱን ጥራት ለመጠበቅ እንዲያስችለውም የአምራቾችን አቅም የመገንባትና በምርት ሂደቱ ቀጥተኛ ተሳትፎ እንዲኖራቸው የማድረግ ሥራ ሠርቷል። አርሶ አደሮቹን ከፋብሪካው ጋር በማስተሳሰር የተከናወነው ተግባር ለምርቱም ሆነ ለአርሶ አደሮቹ ሕይወት መሻሻል በጎ አስተዋፅኦ አበርክቷል ሲሉ ያብራራሉ።
የፋብሪካውን ግንባታ በንቃት ሲከታተሉ እንደነበር የጠቆሙት በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር ሬሚ ማሪሹ በበኩላቸው፣ ፋብሪካው ከአራት ዓመታት በፊት የኢትዮጵያ እና የፈረንሳይ መሪዎች በአገራቱ ያደረጓቸው ስኬታማ ጉብኝቶች ውጤት አካል እንደሆነና ፕሮጀክቱ የኢትዮጵያና የፈረንሳይ መልካም ግንኙነት ማሳያ መሆኑንም ተናግረዋል።
‹‹ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ የፈረንሳይ ባለሀብቶች በአገሪቱ ያሉ ዕድሎችን ለመመልከት ብቻ ሳይሆን ትክክለኛ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክት ሃሳብና አቅም ይዘው እንዲመጡ በጠየቁት መሠረት እውን የሆነ ኢንቨስትመንት ነው። ሱፍሌ ማልት ኢትዮጵያ ፋብሪካ የምርት ግብዓቶችን ከውጭ ከማስገባት ይልቅ ግብአቶችን ከአርሶ አደሮች የሚቀበል በመሆኑ ይህ የፋብሪካው ተግባር የኢትዮጵያ መንግሥት ከያዘው የገቢ ዕቃዎችን በአገር ውስጥ ምርት የመተካት (Import Substitution) እቅድ ጋር የሚጣጣም ነው›› ብለዋል።
አምባሳደሩ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያና ፈረንሳይ 125 ዓመታትን ያስቆጠረ የዲፕሎማሲ ግንኙነት አላቸው። በተለይ ካለፉት አራት ዓመታት ወዲህ ፈረንሳይ የኢትዮጵያን የምጣኔ ሀብት ሪፎርሞች እየደገፈች ትገኛለች። የፈረንሳይ ኩባንያዎች ለኢንቨስትመንት በሚሰማሩባቸው አገራት ውስጥ ለሚገኙ የአገር ውስጥ ግብዓቶች ትኩረት የሚሰጡ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ባላቸው የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴም ይህንኑ ተግባራቸውን አጠናክረው ይቀጥላሉ። ፈረንሳይ በኢትዮጵያ በእርሻ ኢንቨስትመንት ዘርፎች የመሰማራት ፍላጎት አላት።
መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤በኢትዮጵያ የተገነቡት የኢንዱስትሪ ፓርኮች መሰል ፋብሪካዎችን በማስተናገድ በምርት አቅርቦት፣ በውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት፣ በሥራ ዕድል ፈጠራ፣ በውጭ ምንዛሬ ግኝት፣ በገበያ ትስስርና ተዛማጅ ዘርፎች ለአገራዊ ምጣኔ ሀብት እድገት ትልቅ አስተዋፅኦ እያበረከቱ ይገኛሉ። ሱፍሌ ማልት ኢትዮጵያ የሚገኝበትና ከእነዚህ የፋብሪካ መናኸሪያዎች መካከል አንዱ የሆነው የቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ በ353 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ ሲሆን በመጀመሪያው የግንባታ ምዕራፍ ብቻ 13 የውጭ ባለሀብቶችን በማስተናገድ ከ23ሺ በላይ ለሆኑ ሰዎች የሥራ ዕድል ፈጥሯል። ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ ከ240 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ያስገኘና ከ34 ነጥብ አምስት ሚሊዮን ዶላር በላይ የሚያወጡ ተኪ ምርቶችን ለአገር ውስጥ ገበያ ያቀረበ ኢንዱስትሪ ፓርክ ነው።
የቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ በውስጡ ለያዘው የሱፍሌ ማልት ኢትዮጵያ ፋብሪካ የብቅል ምርት ግብዓት የሆነው ገብስ በሚመረትበት አካባቢ ላይ ይገኛል። የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሳንዶካን ደበበ እንደሚናገሩት፣ ፋብሪካው በተኪ ምርት ላይ ያለው ድርሻ የላቀ ነው። ኩባንያው በምርጥ ዘር ምርምር፣ በአቅርቦት ሰንሰለት እንዲሁም በዘር ብዜትና ሰብል አያያዝ ከግብርና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች፣ ከኅብረት ሥራ ማኅበራት እና ከአርሶ አደሮች ጋር በመሥራት በምርት ማሻሻያ ሂደት ላይ ትልቅ አዎንታዊ ሚና እየተጫወተ ይገኛል። ፋብሪካው በተኪ ምርት ላይ የተሰማራ በመሆኑ ብቅልን ከውጭ ለማስመጣት በየዓመቱ የሚወጣውን ከ50 ሚሊዮን ዶላር በላይ ማትረፍ ተችሏል።
በቀጣይ ዓመታት የኢንዱስትሪ ፓርኮችን የበለጠ ውጤታማ ለማድረግ አዳዲስ አሠራሮችን በመዘርጋት በጥናት ላይ የተመሠረቱ ማሻሻያዎችን በመንደፍ የአገር ውስጥ ባለሀብቶችን ከውጭ ባለሀብቶች ጋር በማቀናጀት ፓርኮቹ በጥቂት ዘርፎች ላይ ብቻ እንዲወሰኑ ከማድረግ ይልቅ አገራዊ ፋይዳ ያላቸውን የምርትና የገበያ አማራጮችን ለመፍጠር በትኩረት እንደሚሠራም የኢንዱስትሪ ፓርኮች ኮርፖሬሽን ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሳንዱካን ደበበ ጠቁመዋል።
ከዚህ ባሻገርም የኢንዱስትሪ ፓርኮች መሠረታዊ ዓላማ አምራች ኢንዱስትሪዎች የሚያጋጥሟቸውን የአገልግሎትና የመሠረተ ልማት ፈተናዎች በማቃለልና ልዩ የፖሊሲ ድጋፎችን በማቅረብ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ማድረግ መሆኑን ጠቅሰው፣ ለፓርኮቹ የመሠረተ ልማት አቅርቦት ልዩ ትኩረት መስጠት እንደሚገባም ሥራ አስፈጻሚው አስገንዝበዋል።
በኢትዮጵያ የቢራ ፍላጎት በየዓመቱ እየጨመረ መጥቷል። ይህንንም አንድም በአገሪቱ በየጊዜው እየተከፈቱ ካሉት የቢራ ፋብሪካዎች ብዛት መረዳት ይቻላል። ለዚህ አዳጊ ፍላጎት አስተማማኝ አቅርቦት ለመፍጠር ደግሞ ዋነኛው ግብዓት ለሆነው የብቅል ምርት ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል። የግብዓቱ ዋነኛ አምራች የሆነችው ኢትዮጵያ በዚሁ ግብዓት እጥረት ምክንያት ፈፅሞ መቸገር እንደሌለባት ቁርጠኛ አቋም መያዝና ለትግበራውም ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ ለነገ የማይባል ተግባር ሊሆን ይገባል።
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ግንቦት 18 ቀን 2014 ዓ.ም